Wednesday, 05 August 2020 00:00

መፈተሽ ያለበት የጽንፈኛ ፖለቲከኞች አስተሳሰብ!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

  የዚህ ጽሑፍ መነሻ ‹‹የትምህርት ሥርዓታችን መፈተሽ አለበት›› ሲሉ አንድ የአጋርፋ ነዋሪ የሰጡት አስተያየት ነው:: እሳቸውን እንዲህ እንዲሉ ያስገደዳቸው የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ መገደልን ተከትሎ፣ በሚኖሩበት አጋርፋ ከተማ የሰውን ሕይወት በማጥፋት፣ የግልና የመንግሥት ንብረት በማውደም የተፈጸመው ድርጊት ከግምታቸው በላይ መሆንና የድርጊቱ ፈጻሚዎችም ወጣቶች መሆናቸው ነው፡፡
‹‹የትምህርት ሥርዓታችን ይፈተሽ›› የሚለው አባባላቸው የሚጠቁመው መሠረታዊ እውነት፣ አጥፊዎቹ ተራና መሐይም ሰዎች ሳይሆኑ የትምህርት ቤትን ደጃፍ የረገጡ መሆናቸውን ነው:: በየአካባቢው የተካሔደውን ግድያ፣ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ቃጠሎ እንዲሁም ፋብሪካ የማውደም ሥራ የመሩትና ያስፈጸሙት ቢያንስ መንበብና መጻፍ የሚችሉ ናቸው፡፡ አጥፊዎቹ  ሲገድሉና ንብረት ሲያወድሙ የነበሩት የስም ዝርዝር ይዘው በስም እየጠሩ እንደነበር በደሉ ከደረሰባቸው ግለሰቦች አንደበት ሰምተናል፡፡
ከየአካበቢው የሚመጡ መረጃዎች፤ የድርጊቱ ዋና ፈጻሚዎች ወጣቶች መሆናቸውን ቢያመለክቱም፣ እንደእሳቸው  ጣቴን በመምህራንና በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ለመቀሰር ይከብደኛል፡፡ ‹‹አንተ የዚህ አካባቢ ባለቤት ነህ ፤እሱ መጤ ነው›› የሚል ሥርዓት ከተዘረጋ ወደ ሰላሳ ዓመት ገደማ እየተጠጋ ቢሆንም፣ ተማሪዎቻቸው እርስ በእርስ ተጣልተው ወደ እነሱ በቀረቡ ጊዜ ‹‹ጓደኛህ አይደለም፤ እንዴት እንዲህ ታደርጋለህ?›› ብለው የሚገስጹና የሚመክሩ መምህራን፤ ‹‹ከአንተ ዘር ውጭ ያለን ሰው ካላጠፋህ ሰላም አይኖርህም›› ብለው ያስተምራሉ ብሎ ማሰብ ይከብደኛል፡፡ አጀንዳውን ወደ ትምህርት መዋቅሩ መውሰድ ዋናውን ወንጀለኛ፣ ፖለቲከኛውንና የፖለቲካ መስመሩን ነጻ እንደማድረግም ይቆጠራል፡፡
ከ200 ያላነሱ ሰዎች የተገደሉበትንና ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች ለአካል ጉዳት የተዳረጉበትን፣ 1022 መኖሪያ በቶችና 227 ሆቴሎች እንዲሁም ስድስት ፋብካዎች ዶግ አመድ የተደረጉበትን  አልፎም ግምቱ ያልተገለጠ ንብረት የተዘረፈበትን ይህን የጥፋት ዘመቻ ያቀደው፣ ያደራጀውና የመራው ማን ነው? ተብሎ መጠየቅ አለበት:: እያንዳንዱ ነፍሰ ገዳይ፣ ቤት አቃጣይ፣ ንብረት ዘረፊ ወዘተ  በሠራው ወንጀል ልክ  የሕግ ተጠያቂ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣  የትኛው የፖለቲካ ድርጅት ወይም ቡድን ነገሩን እንዳቀደና እንደመራ ፍርጥርጥ ተደርጎ መውጣት ይኖርበታል፡፡ ከመንግሥት ወገን እነማ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ጥፋቱን ሲደግፉ ነበር? እነማንስ በምን ምክንያት ኃላፊነታቸውን መወጣት ሳይሆንላቸው ቀረ? ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡
ሰዎችን ለመግደል፣ የግለሰቦችንና የመንግሥትን ንብረት ለማውደም አስቦና አቅዶ የተነሳው የፖለቲካ ኃይል፣ ሃጫሉን የገደለው እንደ ተኩስ ማስጀመሪያ ለመጠቀም ነው ብል አልተሳሳትኩም:: ግድያውን ተከትሎ የተከፈተው የጥፋት ዘመቻ፤ እቅዱን ወደ ተግባር የማሻገሪያ መደበኛ እንቅስቃሴ እንጂ ፍትሕ የመጠየቂያ የተቃወሞ  መግለጫ  ሆኖ ሊቆጠርም አይገባም፡፡
መንግሥት የሃጫሉን ግድያ የፖለቲካ ግድያ አድርጎ ተረድቶታል፡፡ ‹‹ ለመስከረም የነበራቸውን እቅድ ወደ ሰኔ ያመጡት ጌቶቻቸው ሰላዘዟቸው ነው፡፡ የሕዳሴውን ግድብ የመጀመሪያ ዙር ሙሌት ለማደናቀፍ ታስቦ የተሠራ ነው›› በማለት የሰጠው መግለጫ የሚያረጋግጠው ይህን አቋሙን ነው፡፡ ሃጫሉ የተገደለበት ምሽት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት፣ በግብጽ ጥያቄ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሙሌት ላይ እየመከረ፣ ሶስቱ አገሮች በየግላቸው የሰጡትን መግለጫ እያዳመጠ ከነበረበት ጊዜ ጋር መገጣጠሙ ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡
ሃጫሉን ገድሎ ወይም አስገድሎ፣ ሞቱን ሰበብ በማድረግ ወደ ማጥቃት የተራመደው የፖለቲካ ኃይል፤ ሁለት ነገሮችን እያለዋወጠ መጠቀሙን ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የሰጧቸው ምስክርነቶች  ያመለክታሉ፡፡ አንድ አካባቢ ዘርን መሠረት አድርጎ ጥቃቱን ከፈጸመ፣ ሌላው አካባቢ የሚጠቃው በሃይማኖቱ ምክንያት ይሆናል:: ዘር ላይ ባተኮረ ጊዜ ተጠቂዎች አማራና ጉራጌ ሲሆኑ በሃይማኖቱ ጊዜ ኦሮሞዎችም ጥቃት ይፈጸምባቸዋል፡፡  መንግሥት ይህን እውነት ሊደብቀውና ሊሸፋፍነው አይገባም፡፡ የአጭርና የረዥም ጊዜ መፍትሔ ሊፈልግለት የሚገባ አገራዊ ችግር መሆኑን መቀበል አለበት፡፡
ከጎናቸው ዘመዶቻቸው ባሰቃቂ ሁኔታ ተገድለው፣ ቤት ንብረታቸው ፈርሶና ተቃጥሎ፣ ባዶ እጃቸውን ቀርተው እውር አሞራ ሆነው ባሉበት ሰዓት እንኳ ዛሬም ‹‹ተወልደን ያደግነው እዚህ ነው፤  ሌላ የምናውቀው አገር የለንም፤ ብንሞት የምንቀበረው እዚህ ነው›› እያሉ የሚጮሁ ሰዎችን ድምጽ እየሰማን ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ለነዚህ ወገኖች ጠበቃና ከለላ በመሆን፣ አቃፊነቱን ማስመስከር አለበት፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ የጥፋት መልዕክተኛ የሆኑ የኦሮሞ ወጣቶችን ከጥፋት ድርጊታቸው ሊያስቆማቸው ይገባል፡፡
የአጋርፋው ነዋሪ፤ የትምህርት ሥርዓቱ መፈተሽ አለበት ቢሉም፣ ለእኔ ቀድሞ የሚታየኝና ቀድሞ መፈተሽ ያለበት የትምህርት ሥርዓቱን የቀረጸው የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች አስተሳሰብና የትግል ሥልታቸው ነው፡፡ ይህ ግድያ ለዘመናት ‹‹ምኒልክ ጡት ቆራጭ ነው፤ ምኒልክ ጨፍጫፊ ነው፤ ጠላትህ ነፍጠኛ ነው›› እያሉ ሲቀሰቅሱ የኖሩ የፖለቲካ ድርጅቶች  የሥራ ውጤት መሆኑ ሊድበሰበስ አይገባውም፡፡ የበሽታው መድኃኒትም ያለው በእነሱ እጅ መሆኑን ጠበቅ አድርጌ ከመናገር ወደ ኋላ አልልም፡፡
ከኦነግ ከፍተኛ መሪዎች አንዱ የነበሩትአቶ ሌንጮ ባቲ፤ ‹‹ኢትዮጵያ እኛን ገድላናለች፤ እንደ ኦሮሞ ብሔርተኛ ኢትዮጵያን መግደል (ዲኮንስትራክት) ነበረብን፤ አሁን ደግሞ ኢትዮጵያን ማንሳት (ኮንስትራክት) አለብን›› ማለታቸውን በቅርቡ አንብቤአለሁ፡፡ ስንቶቹ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ራሳቸውን እንደ አቶ ሌንጮ እየመረመሩ ነው?  የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡
ላለፈ ክረምት ቤት አይሠራም ቢባልም፣ ስህተትን ለማረም የሚረፍድ ጊዜ የለም:: በዝዋይ፣ በሻሸመኔ፣ በአርሲ ነገሌ፣ በአዳሜ ቱሉ፣ በአጋርፋ፣ በጅማ፣ በሐረርና በሌሎችም አካባቢዎች የተፈጸመው እልቂት፣ የወደመው ንብረት የመጨረሻ እንዲሆን ለማድረግ፣ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሌሎችም ለአገር ሰላምና እድገት  አሳቢ ወገኖች፣ ታች ገበሬው መንደር ድረስ ወርደውና ወጣቱ መሐል ገብተው ዘረኝነትን መታገል፣ ስለ ሰላምና አብሮነት መስበክ አለባቸው፡፡ የተጎዳውን የሕዝብ ስሜት ማከምና ለአገር እድገት በጋራ የሚሠራ ሕዝብ መፍጠር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው እላለሁ፡፡
ቸር ያሰማን!!!    

Read 6510 times