Saturday, 08 August 2020 11:56

ኢትዮጵያና ኬንያ የረጅም ርቀት ሩጫን ማዳን አለባቸው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 የዓለም አትሌቲክስ ማሕበር በትራክ ላይ እንደረጅም ርቀት ከ3ሺ ሜትር በላይ የማወዳደር ፍላጎት የለውም፡፡
        3ሺ ሜትር መሰናክልና 5ሺ ሜትር ከዳይመንድ ሊግ ተሰርዘዋል፤ ለቲቪ ስርጭት አይመቹም በሚል የማያሳምን ሰበብ ነው፡፡ የ ዓለም አ ትሌቲክስ ማሕበር ታሪካዊ ቅ ሌት ቢ ሖንም…

              ከ70 ዓመታት በፊት በእንግሊዝና በአሜሪካ አትሌቶች በመላው ዓለም የተስፋፋው የረጅም ርቀት ሩጫ፤ ዛሬ ላይ  ሕልውናው በምስራቅ አፍሪካ አገራት ኢትዮጵያና ኬንያ ስር ወድቋል፡፡ በግሪክ የኦሎምፒክ መሰረት  የተጣለበት የማራቶን ውድድር  ጨምሮ የትራክ ምርጥ ውድድሮች የሚባሉት 10ሺ ሜትርና 5ሺ ሜትር በሚያሳስብ ሁኔታዎች ውስጥ ገብተዋል፡፡ በተለይ በትራክ ላይ የሚካሄዱት የረጅም ርቀት ሩጫዎች ከዋና ውድድሮች ተርታ ከመውጣታቸው በላይ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ውድድሮች በመቋረጣቸው ነው፡፡ ከረጅም ርቀት ሩጫዎች ከባድ የሚባለው 10ሺ ሜትር ሲሆን በዚህ የውድድር አይነት ስኬታማ የሆኑ ሯጮች ከፕሮፌሽናል አትሌቶች በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ 5ሺ ሜትር ወደ ሩጫው ስፖርት ለመግባት የመጀመርያው ምርጫ የሆነና  በትራክ ላይ ማራኪ ውድድር የሚታይበት ነው፡፡ ሁለቱ የረጅም ርቀት የውድድር አይነቶች ፕሮፌሽናል አትሌቶች ከ10 እና ከ15 ዓመታት በላይ የሩጫ ዘመን እንዲኖራቸው ያዘጋጃሉ:: አትሌቶች በትራክ ላይ ሲወዳደሩ ቆይተው  በአገር አቋራጭ፤ በማራቶንና በጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች ውጤታማ እንዲሆኑ ያመቻቻሉ፡፡ በኦሎምፒክ፤ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች የበርካታ አገራት አትሌቶችን በማሳተፍም የተለዩ ናቸው 10ሺ እና 5ሺ፡፡  የአትሌቲክስ ብቃት መገለጫ፤ የአትሌቶች  ፅናት መለኪያ እና በአስደናቂ ፉክክራቸው የሚታወቁ ነበሩ፡፡ በአጠቃላይ በትራክ ላይ የሚካሄዱ የረጅም ርቀት ውድድሮች በዓለም የአትሌቲክስ ስፖርት ታሪክ ላይ አበይት ሚና ነበራቸው፡፡
በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በየዓመቱ በትራክ ላይ ይካሄዱ የነበሩ የረጅም ርቀት ውድድሮች አሁን እየተመናመኑ መጥተዋል፡፡ በኦሎምፒክና በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ እየተወሰኑ ነው፡፡ የ10ሺ ሜትር የትራክ ውድድር  ከቀድሞው የጎልደን ሊግና ሌሎች የውድድር መርሐግብሮች የወጣው ከ10 ዓመታት በፊት ነበው፡፡ ዛሬ ላይ 10ሺ ከትራክ ወጥቶ በ10ኪሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ መለወጡ ያሳዝናል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ባሳለፋቸው ውሳኔዎች  በ3ሺ ሜትር መሰናክልና በ5ሺ ሜትር ላይም ተመሳሳይ አደጋዎችን መጋረጡ ያሰጋል:: ስፖርት አድማስ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት የረጅም ርቀት ሩጫን ለማዳን የሚያስፈልገውን ትኩረት ለማመልከት ይህን ፅሁፍ አዘጋጅቷል፡፡
በ2020ው ዳይመንድ ሊግ በትራክ ላይ ረጅም ርቀት የሖነው 3ሺ ሜትር ነው፡፡ ከ10ሺ መጥፋት በኋላ በ3ሺ መሰናክልና በ5ሺ ውድድሮች ላይ የተቃጣ የዓለም አትሌቲክስ ታሪካዊ ቅሌት ነው፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር የ3ሺ ሜትር መሰናክል እና 5ሺ ሜትር ውድድሮችን ከዳይመንድ ሊግ ውጭ እንዲሖኑ አወዛጋቢ ውሳኔ ያሳለፈው ከዓመት በፊት ነበር፡፡ 200 ሜትር ሩጫ፤ ዲስከስ እና የስሉስ ዝላይም የተሰረዙት ሌሎች የውድድሩ መርሐግብሮች ናቸው፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ማሕበር ታሪካዊ ቅሌት ፈፅሟል በሚል ከፍተኛ ተቃውሞች ተሰምተዋል፡፡ ያለፉትን 5  ወራት የዓለምን ስፖርት ያመሰው የኮሮና ወረርሽኝ ሁኔታውን ያድበሰበሰው መስሏል፡፡ የረጅም ርቀት ሩጫ በኮሮና ሳቢያ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የገባ የውድድር አይነትም ሆኗል:: በጎልደን ሊግ ዘመን የዓለምን አትሌቲክስ የሚመራው ተቋም የ10ሺ ሜትር ሩጫን  በማያሳምን ውሳኔ መሰረዙ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ለውሳኔው በተሰጠው ምክንያት 10ሺ ሜትር በስፖንሰርሺፕ ለመደገፍ ኩባንያዎች አይፈልጉም ተብሎ ነበር፡፡ ኢትዮጵያና ኬንያን 25 ዙር ማየት ተመልካቹን እንደሰለቸውም ተወስቷል፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ባለድርሻ አካላት የነበረው ተቃውሞ ከዚህ የማያልፍ ስለነበር፤ ታላቁን የትራክ ውድድር ከስታድዬም አስውጥቶ የጎዳና ሩጫ አድርጎታል፡፡ የረጅም ዘመን ታሪክ ያላቸውን ስፖርቶች ጠብቆ በማቆየት መስራት ያለበት   የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ወደ ሌላ ስህተት የመጣውም በዚህ ሳቢያ ነው፡፡ በዳይመንድ ሊግ ላይ 3ሺ ሜትርን ከፍተኛው የረጅም ርቀት ውድድር ለማድረግ ሲወስን ባለታሪኮችን እንደዘነጋቸው ያመለክታል፡፡ ውድድሮቹን ከዳይመንድ ሊግ ለማስወጣት ከአሁን ዘመን የቴሌቭዥን የስርጭት ሽፋን ጋር አለመጣጣማቸውን ምክንያት ማድረጉ ደግሞ በጣም ያሳፍራል፡፡ ከውሳኔው አንፃር የዓለም አትሌቲክስ ስፖርት ማህበር World Athletics በቀድሞ የረጅም ርቀት ሯጭ እንግሊዛዊው ሴባስቲያን ኮው ፕሬዝዳንት መመራቱና አዲሱ ሎጎውንም የትራክ ምስል ማድረጉ ብዙዎችን ግራ አጋብቷቸዋል::   የረጅም ርቀት ሩጫን በ3ሺ ሜትር መወሰኑ፤ ከፍተኛ እድገት እያሳዩ የነበሩትን 3ሺ ሜትር መሰናክልና 5ሺ ሜትርን ከዳይመንድ ሊግ ውጭ ሲያደርጋቸው ረጅም ርቀትን ሆን ብሎ የሚያጠፋበት ርምጃ  አስመስሎበታል፡፡ በአትሌቲክስ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገቡትን የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ከስፖርቱ የአመራር አቅጣጫ ማግለሉንም አረጋግጧል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ በዳይመንድ ሊግ የ3ሺ ሜትርና 5ሺ ሜትር ውድድሮችን የሰረዝበትን ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ የኬንያና የኢትዮጵያ አትሌቲክስን የሚያስተዳድሩ አካላት በይፋ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡ የኬንያ አትሌቲክስ ፕሬዝዳንት ጃክሰን ቱዌ የረጅም ርቀት ውድድር ከዳይመንድ ሊግ መሰረዙ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶችን የስኬት ምዕራፍ ያሰናከለ እና ጉሮሯቸውን የዘጋ በሚል አጣጥለውታል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ባሳለፈው ውሳኔ አባል ፌደሬሽኖችን በተሟላ መንገድ አለማማከሩን የወቀሱት ጃክሰን፤ በትራክ የአፍሪካውያን ጥንካሬ በረጅም ርቀት ሩጫ መሆኑን፤ በርካታ አዳዲስ አትሌቶች መውጣት መቀጠላቸውን ከግምት ውስጥ ያላስገባ ግብታዊ ርምጃ ብለውታል፡፡ የኬንያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት  ፖል ቴርጋት ደግሞ የረጅም ርቀት አትሌቲክስ ላይ የተላለፈው ውሳኔ ሃላፊነት የጎደለው መሆኑን ተናግሯል፡፡ በኬንያ በረጅም ርቀት ሩጫ ወጣቶች ከትምህርት ቤት አንስቶ በከፍተኛ ሁኔታ መሳባቸውን  በርቀቱ ያላገናዘበ ጥናት በዓለም አትሌቲክስ መደረጉንም አውግዞታል፡፡ መጭው ትውልድ በአትሌቲክስ የትራክ ውድድሮች የሚኖሩትን ምርጫዎች አጥብበውታል በሚልም ቅሬታውን አሰምቷል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክሰ ፌደሬሽን  በበኩሉ የዓለም አትሌቲክስ ድምፁን አጥፍቶ ረጅም ርቀትን ለመግደል መሞከሩን ነው በተለያየ መንገድ ያሳወቀው፡፡ በዳይመንድ ሊግ ላይ ላይ ለረጅም ርቀት ትኩረት አለመሰጠቱን ዝም ማለት ወደፊት በዓለም ሻምፒዮናም ላይ የሁለቱን ርቀቶች ህልውና አደጋ ውስጥ የሚከት ነው ብሏል፡፡ ታላቁ የረጅም ርቀት አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በበኩሉ  የዓለም አትሌቲክስ ረጅም ርቀትን ከውድድሮች ተርታ ማጥፋቱ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶችን  ያገለለ፤ በውድድሮቹ የሚታዩትን እድገቶች የሚያጓትት በሚል ተችቶታል፡፡
እውነት የረጅም ርቀት ውድድሮች ለቲቪ ስርጭት አይመቹም?  የማይረባ ሰበብ
የረጅም ርቀት ሩጫዎች በ90 ደቂቃዎች ለተወሰነው ዓለም አቀፍ የብሮድካስት ሰዓት አይመቹም የሚለው የዓለም አትሌቲክስ ምክንያት ነባራዊ ሁኔታውን ከግምት ውስጥ ያስገባ አይመስልም፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ዓለም አቀፍ የብሮድካስት ኩባንያዎች ለረጅም ርቀት በሚሰጡት ሽፋን የ10ሺሜትር እና የ5ሺ ሜትር ውድድሮችን ሙሉ ስርጭት በቀጥታ እንደማይስተላለፉ ይታወቃል፡፡ በሁለቱ የውድድር አይነቶች በሚኖረው ስርጭት  የመነሻው  ዙርና እንዲሁም የመጨረሻዎቹ ሁለት ዙሮች ናቸው፡፡ ብዙውን ጊዜ የረጅም ርቀት ሩጫዎች እየተካሄዱ በቲቪ የሚሰራጩት በመሃል በሜዳ ላይ የሚካሄዱ የአትሌቲክስ ውድድሮች ናቸው:: ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓለም አትሌቲክስ አመራሮች በአሁኑ ዘመን የሩጫ ስፖርት አድናቂዎች ከ5 ደቂቃዎች በላይ ግዜ የሚወስድ ውድድር ለመታደም ትእግስት የላቸውም በሚል ምክንያት ለመከራከር መሞከራቸውም ያስገርማል፡፡ በዓለም ስፖርት ኢንዱስትሪ የሚስተዋለው ሁኔታ  ከዚሁ የማያሳምን ሰበብ ጋር የሚቃረን ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን በጠበቁ የረጅም ርቀት ውድድሮች በትራክ ላይ 10ሺ ሜትር እና 5ሺ ሜትር   በ400 ሜትር ትራክ ላይ  25 ዙር እና 12 ዙር እንደሚሮጡ ይታወቃል:: 5ሺ ሜትር  እስከ 13 ደቂቃ እንዲሁም እስከ 10ሺ ሜትር እስከ 30 ደቂቃዎች ይወስዳሉ፡፡ በማራቶን እና በጎዳና ላይ ሩጫዎች ከ2 ሰዓት ተኩል እና ከ1 ሰዓት ያነሰ ጊዜ ይወስዳሉ፡፡ የእግር ኳስ ጨዋታ ከ90 እስከ 120 ደቂቃዎች ይወስዳል፤ ክሪኬት ለበርካታ ሰዓታት የሚካሄድ ነው:: በቴኒስ በራግቢ እና በጎልፍ የሚካሄዱ ውድድሮች  ከረጅም ርቀት የላቀ ግዜ የሚወስዱ ናቸው፡፡ እናም የረጅም ርቀት ውድድሮች በስታድዬም ለሚታደማቸው እና በቲቪ ለሚመለከታቸው ሁሉ ቆይታቸው ያሰለቻል የሚለው ምክንያት እንዴት ሊያሳምን ይችላል፡፡
የረጅም ርቀት ተወዳጅነት የቀነሱ ሌሎች ምክንያቶችና ቀጣይ ተፅእኖዎች
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር የረጅም ርቀት ውድድርን ለብሮድካስተሮች አይመችም በሚል የማያሳምን ምክንያት ከዳይመንድ ሊግ ቢሰርዝም ለስፖርቱ የሚያስፈልግው ትኩረት እንዲቀንስ ሌሎች ሁኔታዎችም አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ እንደኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን መግለጫ ዓለም አቀፉ ማህበር ባስተላለፈው ውሳኔ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ተጎጂ የሆኑት አህጉራዊው የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌደሬሽን በሙስና ብልሹ አሰራር በመዘፈቁ ነው፡፡ የአፍሪካ አትሌቶች በተለይ በረጅም ርቀት ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገቡ የኢትዮጵያ እና የኬንያ የቀድሞ አትሌቶች በዓለም አትሌቲክስ ማህበር እና ምክርቤት ውክልናቸው ማነሱም ሌላው ችግር ነው፡፡ ዓለም አቀፉን የአትሌቲክስ የበላይ ተቋም በረጅም ርቀት ውስጥ ያለፉ የቀድሞ አትሌቶች እየመሩት ቢሆንም ከፍተኛ የውጤት ክብረወሰን ያላቸው ኢትዮጵያ እና ኬንያ በታዋቂ አትሌቶቻቸው በቂ ውክልና አለማግኘታቸው እንዳይሟገቱ አድርጓቸዋል፡፡ የውድድር አይነቱን ተወዳጅነት ለመጨመር እንዳይሰሩም ገድቧቸዋል::  የምስራቅ አፍሪካ አገራት አትሌቶች የረጅም ርቀት ሩጫን በስኬታቸው የላቀ ደረጃ እንደማድረሳቸው በውድድሮቹ እጣ ፋንታ ላይ የመወሰን መብት ነበራቸው፡፡ የስፖርት ትጥቅ አምራቾችና ሌሎች ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የውድድር አይነቱን  በምቹና የተጣጣመ ስምምነት በስፖንሰርሺፕ እንዲደግፉ የተጣረበት ሁኔታ የለም፡፡ ይህ ደግሞ ውድድሮችን የሚያዘጋጁ ከተሞችን ቀስ በቀስ አጥፍቷቸዋል፡፡  ለዓለም አቀፍ ውድድሮች በሚሰጠው የቲቪ ስርጭት ላይ በረጅም ርቀት ሩጫዎች ላይ የሚሰጡ የቀጥታ ዘገባዎችና፤ የኮሜንታተር ስራዎች ላይ ድክምትም ነበር፡፡ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በረጅም ርቀት ላይ ስኬታማ ሲሆኑና የሜዳልያ ሰንጠረዡን ሲቆጣጠሩ ለሌላው ዓለም የሚነግሩት ሃሳብ ያነሰ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከኢትዮጵያና ኬንያ አትሌቶች በሚሰሩ ቃለምምልሶች የቋንቋ ክፍተት መስተዋሉ ይህን ለማረምም ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማህበር አለመስራቱ ከሌላው ዓለም ለስፖርቱ ሊገኝ የሚችለውን ድጋፍ አስቀርቷል፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ፕሬዝዳንት ሴባስቲያን ኮው ቦርድ ሰብሳቢነት የሚመራው ዳይመንድ ሊግ በአሁኑ ወቅት በዓለም የትራክ ሩጫ ዋና ውድድር እንደመሆኑ ቀደምቶቹን የረጅም ርቀት ሩጫዎች የመርሃግብሮቹ አካል በማድረግ መስራት የሚጠበቅበት ሃላፊነት ቢሆንም  አላደረገውም፡፡ የረጅም ርቀት ሩጫዎች በየዓመቱ ሲካሄዱ ፈጣንና የተሻሻሉ ሰዓቶች የማስመዝገቡ ሂደት ይቀላጠፍ ነበር፡፡ በምርጥ አትሌቶች የሚደረጉ ፉክክሮች እየበዙ በመምጣት  የውድድሮቹን ተወዳጅነት ለማስጠበቅ እድሎች ይፈጠሩ ነበር፡፡ የዓለም አትሌቲክስ በምን መስፈርት ይህን የስፖርት እድገት እንዳልፈለገው ለማስረዳት ይከብዳል፡፡ የረጅም ርቀት ሩጫ በየሁለት ዓመቱ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በየአራት አመቱ በኦሎምፒክ መድረክ መወሰናቸው የስፖርቱን እድገት ያቀጭጨዋል፡፡ የረጅም ርቀት ሩጫዎች መመናመን የኦሎምፒክና የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ድምቀትንም የሚፈታተን ነው፡፡ አትሌቶች በውድድር መድረኮቹ ለመሳተፍ  ሚኒማ የሚያሟሉበትን እድል  ያወሳስበዋል፡፡ ይህም ምርጥ ኦሎምፒያኖችና የዓለም ሻምፒዮን አትሌቶች በየጊዜው የሚወጡበትን እድል ይቀንሰዋል፡፡  በሌሎች የአትሌቲክስ የውድድር መደቦች ላይም አሉታዊ ሁኔታዎችን መፍጠሩ አይቀርም፡፡ የትራክ ውድድሮች እየጠፉ ሲሄዱ አትሌቶች ተገቢውን የእድሜ እርከን ጠብቀው የውድድር መደቦቹን ሂደት በአግባቡ እንዳይከተሉ እንቅፋት ይሆንባቸዋል፡፡  በጐዳና ላይ ሩጫዎች ፤ በግማሽ ማራቶንና በማራቶን ውድድሮች መሳተፍ ብቸኛ አማራጭ ይሆንና በከባድ ውድድሮች የሩጫ ዘመናቸውን ያሳጥርባቸዋል፡፡
የ3ሺ ሜትር መሰናክልና የ5ሺ ሜትር ውድድሮችን ከዳይመንድ ሊግ ውድድር ውጭ በመሆናቸው የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በላቀ ብቃታቸው የሚያገኙትን የሽልማት ገንዘብ አስቀርቶባቸዋል፡፡ ዳይመንድ ሊግ ላይ በየከተማው በሚካሄዱ ውድድሮች እስከ 6ኛ የገንዘብ ሽልማት ያለ ሲሆን ለ1ኛ 10ሺ ዶላር፤ ለ2ኛ 6ሺ ዶላር እንዲሁም ለ4ሺ ዶላር ይበረከታል:: በፍፃሜው ውድድር ደግሞ ለ1ኛ 50ሺ ዶላር፤ ለ2ኛ 20ሺ ዶላር እንዲሁም ለ10ሺ ዶላር ይሰጣል፡፡ ስለሆነም የረጅም ርቀት ውድድሮች ከዳይመንድ ሊግ ውጭ ሲደረጉ ከፍተኛው ጉዳት በምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ላይ ደርሷል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የኢትዮጰያ አትሌቶች በ5ሺ ሜትር በ2018 እኤአ ላይ ከ1 እስከ 5 እንዲሁም በ2017 እኤአ ላይ ከ1 እስከ 4 ደረጃ በዳይመንድ ሊጉ በማግኘት  ተሳክቶላቸው እንደነበር ማውሳት ይቻላል፡፡
የረጅም ርቀትን ለማዳን ከተቃውሞ ያለፈ ስራ ከምስራቅ አፍሪካ….
በዓለም አትሌቲክስ   የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላቸውን የረጅም ርቀት ውድድሮች ከምድር ገፅ የሚያጠፉ ውሳኔዎች እየበዙ መጥተዋል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ተቃውሟቸውን በተለያዩ ሚዲያዎች በማሰማት እና ደብዳቤ በመፃፍ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በሌሎች አማራጮችም ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የዓለም አትሌቲከስ የበላይ አካልና ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ የረጅም ርቀት ውድድሮችን ለመታደግ ምንም አይነት ጥረት እያደረጉ አይደለም፡፡ የረጅም ርቀት ሩጫ ህልውናን ለመታደግ ኢትዮጵያና ኬንያ መነሳት አለባቸው፡፡ የዓለምን አትሌቲክስ የተሳሳቱ አቅጣጫዎች  በከፍተኛ ደረጃ መሞገት የሚጠበቅባቸው ከእነዚህ የምስራቅ አፍሪካ የወጡ ታላላቅ የረጅም ርቀት አትሌቶች ናቸው፡፡ በድህረ ኮቪድ ይህን ሁኔታ ለመቀየር በምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ከፍተኛ ዘመቻ መካሄድ ይኖርበታል፡፡ በዳይመንድ ሊግ የተጀመረው ስረዛ በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ መድረክ ሊቀጥል ስለሚችል ይህን ሁኔታ በጥብቅ ትኩረት መከታተል አስፈላጊ ነው፡፡  የዓለም አትሌቲክስ ለምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ተገቢውን ዋጋ አለመስጠቱ ተረጋግጧል:: ከረጅም ርቀት ውድድሮች በታዋቂው 10ሺ ሜትር ከደረሰው ጥፋት ወዲህ በ3ሺ ሜትር መሰናክልና በ5ሺ ሜትር ተመሳሳይ አደጋ መጋረጡ አፍሪካን በአንድ አቋም እንድትሟገት ማነሳሳት ይኖርበታል፡፡ ከረጅም ርቀት ሩጫዎቹ በፊት የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የበላይነት በዝቶበታል በሚል የውድድር ታሪክ የደበዘዘውን የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ታሪክ እንዲደገምም መፈቀድ የለበትም፡፡
ኢትዮጵያና ኬንያ በዓለም አትሌቲክስ ያገኙትን የላቀ ክብርና ስኬት ለመጠበቅ የተለያዩ አማራጮችን በማፈላለግ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡
የኬንያ አትሌቲክስን የሚመራው ተቋም ከኢትዮጵያ አቻው በተለየ የተሻሉ ተግበራትን ማከናወኑ ይስተዋላል:: የኮሮና ወረርሽኝ ሁኔታዎችን ባያስተጓጉላቸው ኖሮ በያዝነው የ2020 የውድድር ዘመን በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በሚገኘው ኪሳራኒ ስታድዬም አፍሪካዊ ዳይመንድ ሊግ ለማካሄድ እቅድ ነበረው፡፡ ታዋቂው የስፖርት ፀሃፊ ኤልያስ ማኩሪ በዴይሊ ኔሽን ላይ በፃፈው ልዩ ትንታኔ 3ሺ ሜትር መሰናክልና 5ሺ ሜትር ውድድሮች ከዳይመንድ ሊግ ውጭ እንዲሆኑ በማድረግ እንዲሁም 10ሺ ሜትር በማስረሳት ከዓለም የቴሌቭዥ ራዳር ውጭ መደረጋቸውን አሳዛኝ ብሎታል፡፡ በአውሮፓ ስታድዬሞች የሚካሄዱ የአትሌቲክስ ውድድሮች በአሟካይ እስከ 50ሺ ተመልካች ማስተናገዳቸውን የጠቀሰው ኤልያስ ማኩሪ በኢትዮጵያ እና በኬንያ ተመሳሳይ ዓመታዊ ውድድሮችን በዋና ከተሞች በማካሄድ የረጅም ርቀትም ማዳን እንደሚቻል መክሯል፡፡ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር መለስ አለም ተካ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ያከናወኑትን ተግባር በተምሳሌትነት ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡ አምባሳደር መለስ ባለፈው 1 ዓመት ያሳለፉት ተመክሮ በዚሁ ጉዳይ ላይ ከተለያዩ የኬንያ አትሌቲክስ አመራሮች እና አትሌቶች እና ሚዲያዎች ጋር እንዲመክሩ እድሉን ፈጥሮላቸዋል፤  በአግባቡም ተጠቅመውበታል፡፡  አምባሳደሩ በኬንያ ጋዜጣ ላይ ባቀረቡት ፅሁፍ ኢትዮጵያ እና ኬንያ በረጅም ርቀት በዓለም አትሌቲክስ ያስመዘገቡት የላቀ ስኬት የጥረትና የብርታት ምሳሌ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በስፖርት ቱሪዝም ላይ በጋራ እና በልዩ ትኩረት መስራት አለባቸውም ብለዋል፡፡ የኬንያዋን የአትሌቶች መገኛ  ኤሎዶሬት በመጎብኘት የመጀመርያውን የኬንያ ዓመታዊ የአትሌቲክስ ኮንፍረንስ የተካፈሉት አምባሳደር መለስ፤ ሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ምርጥ አትሌቶቻቸውን በሚያሳትፉባቸው አህጉራዊ ውድድሮች ላይ መስራት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በእንግሊዝ ለንደን ከተማ የሚካሄደው የለንደን ማራቶን ከ128 ሚሊዮን ፓውንድ መዋፅለንዋይ ያንቀሳቅሳል ያሉት አምባሳደሩ፤ በመላው ዓለም ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገቡ ታላላቅ አትሌቶች፤ ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጮች እና ማራቶኖን ተወዳዳሪዎችን በማስተባበበር እንደለንደን ማራቶን ሁሉ የናይሮቢ ማራቶን እና የአዲስ አበባ ማራቶንን በማዘጋጀት መስራት አለብን ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በምስራቅ አፍሪካ የሚካሄዱት የአትሌቲክስ ውድድሮች  በማራቶን ብቻ ሳይሆን በረጅም ርቀት የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር የትራክ ውድድሮች ላይ እንዲያተኩሩ ይገባል፡፡ ረጅም ርቀትም መታደግ የሚችሉ፤ ዋንኛ ተሳተፊዎቻቸውን ከኬንያ እና ከኢትዮጵያ አድርገው ከሌላው ዓለም አትሌቶች መጋበዝ የሚችሉ ውድድሮችን በመስራቅ አፍሪካ ማዘጋጀት የረጅም ርቀት ሩጫን ከመጥፋት ያድነዋል፡፡
በረጅም ርቀት 5ሺ እና 10ሺ ሜትር ከ12 የዓለም ሪከርዶች እና ክብረወሰኖች
9 በኢትዮጵያውያን 3 በኬንያ
በረጅም ርቀት የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶችን የበላይነት ባለፉት 30 ዓመታት መመዝገቡ ይታወቃል:: በተለይ በ10ሺ ሜትር እና በ5ሺ ሜትር የዓለም ሪከርዶች፤ የዓለም ሻምፒዮና እና የኦሎምፒክ ክብረወሰኖች እንዲሁም የምንግዜም ምርጥ ፈጣን ሰዓቶች በኢትዮጵያና ኬንያ አትሌቶች የተያዙ ናቸው፡፡
በ10ሺ ሜትር  በሁለቱም ፆታዎች ዋናው የዓለም ሪከርድ፤ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና የኦሎምፒክ ክብረወሰኖች ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያውያን ተይዘዋል:: በወንዶች የ10ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድ ከ15 ዓመታት በፊት በሆላንድ ሄንግሎ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ 26፡17.53 በሆነ ጊዜ ያስመዘገበው ነው፡፡ በሴቶች ደግሞ የዓለም እና የኦሎምፒክ ሪከርድ ከ4 ዓመታት በፊት በብራዚል ሪዮዲጄኔሮ በተካሄደው ኦሎምፒያድ አትሌት አልማዝ አያና በ29፡17.45 በሆነ ሰዓት ተቆጣጥራዋለች፡፡
በ5ሺ ሜትር  በሁለቱም ፆታዎች የዓለም ሪከርዶች በኢትዮጵያውያን ሲያዙ የኬንያ አትሌቶች ደግሞ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ ያሉትን ክብረወሰኖች አስመዝግበዋል፡፡ በወንዶች 5ሺ ሜትር የዓለም ሪከርዱ ከ16 ዓመታት በፊት በሆላንድ ሄንግሎ 12፡37.35 በሆነ ጊዜ ያስመዘገበው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ  ነው፡፡ በሴቶች ደግሞ ከ12 ዓመታት በፊት በኖርዌይ ኦስሎ 14፡11.15 በሆነ ጊዜ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ይዘዋለች፡፡
በ5ሺ ሜትር የኦሎምፒክን ክብረወሰን ያስመዘገበው በ2008 እኤአ ቤጂንግ ላይ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ 12:57.82 በሆነ ሰዓት ሲሆን በሴቶች ደግሞየኬንያዋ አትሌት ሄለን ኦቡሪ በሪዮ ኦሎምፒክ 14፡ 26 .17 በሆነ ጊዜ አስመዝግባለች፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በሁለቱም ፆታዎች የሻምፒዮናውን ክብረወሰኖች ኬንያውያን ይዘዋቸዋል፡፡ በወንዶች የሻምፒዮናውን ክብረወሰን 12 ፡52 39 በሆነ ጊዜ በ2003 እኤአ ላይ የጨበጠው አትሌት ኤሊውድ ኪፕቾጌ ሲሆን የሴቶቹን ክብረወሰን ደግሞ ሌላዋ ኬንያዊት ሄለን ኦቡሪ በ2019 እኤአ ላይ በኳታር ዶሃ 14 ፡26. 22 በሆነ ጊዜ አስመዝግበዋለች፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ
80 በመቶ የሜዳልያዎች ስብስብ  የኢትዮጵያ እና የኬንያ
በዓለም አትሌቲክስ ከፍተኛ ደረጃ ባላቸው የኦሎምፒክ እና የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና  የውድድር መድረኮች ሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ እና ኬንያ ከፍተኛ ውጤት እና የሜዳልያ ስብስቦችን አግኝተዋል፡፡
በኦሎምፒክ 10ሺ ሜትር በሁለቱም ፆታዎች ከፍተኛውን የሜዳልያ ስብስብ በማስመዝገብ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ናት፡፡ በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ተሳትፎ ታሪክ ከተመዘገቡ 24 ሜዳልያዎች መካከል  በ10ሺ ሜትር የተመዘገቡ ሲሆን 6 የወርቅ ሜዳልያዎች ናቸው፡፡ በኦሎምፒክ ላይ በ10ሺ ሜትር ወንዶች ኢትዮጵያ 5 የወርቅ፤ 3 የብርና እና 6 የነሐስ በአጠቃላይ 14 ሜዳልያዎች በመሰብሰብ ከዓለም አንደኛ ደረጃ ስትይዝ ኬንያ 1 የወርቅ፤ 4 የብርና እና 3 የነሐስ በአጠቃላይ 8 ሜዳልያዎች አሏት፡፡ በ10ሺ ሜትር ሴቶች አሁንም ኢትዮጵያ 5 የወርቅ፤ 2 የብርና እና 3 የነሐስ በአጠቃላይ 10 ሜዳልያዎች በመውሰድ ከዓለም መሪነቱን ስትይዝ ኬንያ ያስመዘገበችው 2 የብርና እና 1 የነሐስ በአጠቃላይ 3 ሜዳልያዎች ብቻ ነው፡፡ በኦሎምፒክ ላይ በ5ሺ ሜትር በሰበሰበችው የሜዳልያ ብዛት ኢትዮጵያ በሁለቱም ፆታዎች አንደኝነቱን እንደያዘች ነው፡፡ በ5ሺ ሜትር ወንዶች ኢትዮጰያ 3 የወርቅ፤ 2 የብርና እና 2 የነሐስ በአጠቃላይ 7 ሜዳልያዎች ስትሰበስብ ኬንያ 1 የወርቅ፤ 4 የብርና እና 4 የነሐስ በአጠቃላይ 9 ሜዳልያዎች አሏት:: በ5ሺ ሜትር ሴቶች አሁንም ኢትዮጵያ 3 የወርቅና 5  የነሐስ በአጠቃላይ 8 ሜዳልያዎች ስትወስድ ኬንያ ያስመዘገበችው 1 የወርቅና 4 የብር የነሐስ በአጠቃላይ 5 ሜዳልያዎች ብቻ ነው፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በረጅም ርቀት በተለይ በ10ሺ ሜትር የኢትዮጵያ የበላይነት የላቀ ነው:: በሻምፒዮናው ታሪክ በሁለቱም ፆታዎች ኢትዮጵያ በ10ሺ  የሰበሰበቻቸው 38 ሜዳልያዎች ሲሆኑ 16 የወርቅ ሜዳልያዎች ናቸው፡፡ በሁለቱም ፆታዎች ከፍተኛውን የሜዳልያ ስብስብ በማስመዝገብም ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ናት፡፡  
በ10ሺ ሜትር ወንዶች ኢትዮጵያ 9 የወርቅ፤ 6 የብርና እና 4 የነሐስ በአጠቃላይ 19 ሜዳልያዎች በመሰብሰብ ከዓለም አንደኛ ደረጃ ይዛለች፡፡ ኬንያ 3 የወርቅ፤ 5 የብርና 9 የነሐስ በአጠቃላይ 17 ሜዳልያዎች አሏት፡፡ በ10ሺ ሜትር ሴቶች አሁንም ኢትዮጵያ 7 የወርቅ፤ 8 የብርና እና 4 የነሐስ በአጠቃላይ 19 ሜዳልያዎች በመውሰድ ከዓለም መሪነቱን ስትይዝ ኬንያ ያስመዘገበችው 4 የወርቅ፤ 2 የብርና 6 የነሐስ በአጠቃላይ 12 ሜዳልያዎች ብቻ ነው፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5ሺ ሜትር በሰበሰበችው የሜዳልያ ብዛት ኬንያ በሁለቱም ፆታዎች 21 ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ ከኢትዮጵያ ብልጫ አላት፡፡
በ5ሺ ሜትር ወንዶች ኬንያ 7 የወርቅ፤ 3 የብርና 4 የነሐስ በአጠቃላይ 14 ሜዳልያዎች ስትሰበስብ ኢትዮጵያ 2 የወርቅ፤ 5 የብርና  4 የነሐስ በአጠቃላይ 11 ሜዳልያዎች አሏት፡፡ በ5ሺ ሜትር ሴቶች ደግሞ አሁንም ኬንያ 4 የወርቅና 2 የብርና 6  የነሐስ በአጠቃላይ 12 ሜዳልያዎች ስትወስድ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው 3 የወርቅና 4 የብር 2 የነሐስ በአጠቃላይ 9 ሜዳልያዎች ብቻ ነው፡፡


Read 704 times