Saturday, 08 August 2020 12:47

ቅጥ አምባሩ የጠፋው የዳያስፖራ ፖለቲካ አዲሱ የጽንፈኞች አድማ - "እንጀራ አትብሉ!" ሆኗል

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(14 votes)

 
                  "ጠ/ሚኒስትሩ የተበረከተላቸውን መኪና ይመልሱ!"

                ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የዓለም አገራት በስደት ላይ ከሚገኙ አንዳንድ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች "ዊርድ" የሆኑ የተቃውሞ መፈክሮችን እየሰማን ነው:: “ዳውን ዳውን ዐቢይ!…ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ!…ዳውን ዳውን ለማ!…ዳውን ዳውን ነፍጠኛ!” ሲሉ በተደጋጋሚ ሰምተናል - በአውሮፓ አደባባዮችና አውራ መንገዶች፡፡ የሚገርመው ደሞ በዚህ የ“ዳውን ዳውን” የፖለቲካ ፋሽን፤ እነ ቴዲ አፍሮና አስቴር አወቀ ሳይቀሩ ሰለባ ሆነዋል፡፡ "ዳውን ዳውን አስቴር! ዳውን ዳውን ቴዲ!" ተብለዋል፡፡ ፖለቲካውና ሙዚቃው ተደበላልቆባቸዋል፡፡ እናም ወዳጆቼ፤ ብታምኑም ባታምኑም፣ የዳያስፖራ ፖለቲካ ቅጥ አምባሩ ጠፍቷል::
ቅጥ አምባሩ ባይጠፋማ "እንጀራ እንዳትበሉ!" የሚል አስገራሚ ተቃዋሞ ወይም አድማ ከባህር ማዶ ጽንፈኞች አንሰማም ነበር፡፡ (እኛም በስደት አገር የምንኖር መሰላቸው እንዴ?) ሌላ የዳያስፖራ ቅጥአምባሩ የጠፋ ፖለቲካ ልንገራችሁ፡፡ በዚያን ሰሞን በአሜሪካ "ዳውን ዳውን" ለማለት አደባባይ የወጡ ጽንፈኛ ዳያስፖራዎች፤ በአንድ አሜሪካዊ ላይ ድብደባ ፈጽመዋል የተባለ ሲሆን "አንተም ነፍጠኛ ነህ!" እያሉ ሲደበድቡት እንደነበር ምንጮች ጠቁመዋል:: (አሜሪካዊውን በገዛ አገሩ ነፍጠኛ ብሎ መደብደብ የጤና አይመስለኝም!)
 በነገራችን ላይ በአገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ "ዘፋኞች ይውደሙ!" ተብሎ ስልፍ ሲወጣባቸው የአሁኑ  ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ለነገሩ የራሳቸውን አገር ትውደም ብሎ ሰልፍ በመውጣትም የዳያስፖራ ፖለቲከኞች በዓለም የመጀመሪያዎቹ ይመስሉኛል፡፡ “ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ!” - ታሪካዊ መፈክር ነው፡፡ (ግብጾች እንኳን ያልደፈሩት መፈክር!)
የዚያን ሰሞን በዱባይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አደባባይ ወጥተው “ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ!” ሲሉ የሰማ የአገሪቱ ፖሊስ ተገርሞ ወደ አንደኛዋ ሰልፈኛ ጠጋ ይልና፡- “Where are you from?” (አገራችሁ የት ነው?) ብሎ ይጠይቃታል፡፡ “Ethiopia!” (ከኢትዮጵያ ነኝ) ብላው አረፈች፡፡ (ፖሊሱ ግራ ሳይገባው አልቀረም!) ከዚያስ? ከዚያማ-- የኮቪድ-19 ክልከላን ጥሰው "ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ!" ለማለት አደባባይ የወጡትን ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ሥር አዋላቸው - እያንዳንዳቸውም እስከ 30ሺ ብር ቅጣት ይጠብቃቸው እንደነበር ተነግሯል፡፡ (ሲያንሳቸው ነው!)
በነገራችን ላይ "ኢትዮጵያ ትውደም" ወደሚል መፈክር የተገባው በአንድ ጀንበር አይደለም፡፡ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በብሔር ብሔረሰቦች ስም የአገር ፍቅር ስሜትን የመናድ ዘመቻ ነው ሲካሄድ የከረመው፡፡ (ራስን የመናድ ዘመቻ በሉት!) አገሪቱን በስሟ ለመጥራት እንኳን የሚደብራቸው የመንግስት አመራሮች እንደነበሩን እንዳትዘነጉ፡፡ (የሚመሩትን አገር መጥላት እርግማን ነው!) ፈጣሪም ይህንን በደል ቆጥሮ ነው መሰለኝ "ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው" የሚሉ አመራሮችን አመጣና አገሪቱንም ህዝቡንም ካሰው፡፡
ባለፈው ሳምንት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ባደረጉት ውይይትም ይኸው ጉዳይ ተነስቶ ነበር፡፡ በዚህ ውይይት ላይ ከተሳተፉት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች አንዱ የሆኑት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፤ በአሁኑ ወቅት ትግራይን በውዝግብ እያስተዳደሩ ያሉት የህወኃት አመራሮች ላይ የተለያዩ ክሶችን ሰንዝረዋል፡፡ ከእነዚህም አንዱ፣ አመራሮቹ ዛሬም፣ አገሪቱን ኢትዮጵያ ብሎ ለመጥራት የሚጠሉ ወይም የሚጸየፉ ናቸው የሚል ነው፡፡ በነገራችን ላይ ተመሳሳይ ውንጀላ በሌላም የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ተሰንዝሯል - በዚያው የውይይት መድረክ፡፡ ለተሰነዘሩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ የሰጡት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ግን ብዙ ትንተና ውስጥ ለመግባት አልፈለጉም፡፡ በአጭሩ፤ “ስሟን መጥራት የሚጠሉ ወገኖች ይጠፋሉ፤ እሷ ግን ትቀጥላለች!” ብለዋል፡፡ (በእርግጥም ኢትዮጵያ ትቀጥላለች!)
ዶ/ር አረጋዊ ኢትዮጵያን በስሟ ለመጥራት ይጸየፋሉ በሚል የወነጀሏቸውን ወገኖች በተመለከተ ሃሳባቸውን የገለፁት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለሁ የማስታውሰው ባሉት መዝሙር ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡-
“መቆየት ጥሩ ነው
አየን ብዙ መላ
እንጀራ ባቋራጭ
በምላጭ ሲበላ” …የሚለውን መዝሙር ያስታውሰኛል - ብለዋል ዶ/ር አረጋዊ፡፡
ወደ ዘመኑ ፅንፈኛ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ልመልሳችሁ፡፡ እነዚህ የ"ዳውን ዳውን" ፖለቲከኞች በቅርቡ ደግሞ ጠ/ሚኒስትሩ በበጎ ሥራቸው ያገኙትን የሰላም ኖቤል ሽልማት የማስነጠቅ ዘመቻ ጀምረዋል አሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ዘመቻ ተጀምሮ የኖቤል ሽልማት ኮሚቴው የማያዳግም ምላሽ መስጠቱ አይዘነጋም፡፡ “ከዚህ ቀደም የሰጠነውን ሽልማት ነጥቀን አናውቅም፤ ዶ/ር ዐቢይን የሸለምናቸው ይገባቸዋል በሚል ሙሉ እምነት ነው፤ አሁንም ያ እምነታችን አልተለወጠም! ወደፊትም አይለወጥም” የሚል መንፈስ ያለው ምላሽ ነው የሰጠው፤ የኖቤል ሽልማት ኮሚቴው፡፡
የዳያስፖራ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች ግን አልተዋጠላቸውም፡፡ የሽልማት ኮሚቴው ለ100 ዓመታት የተዳደረበትን ህግና መመሪያ በግድ ለማስቀየር ያሰቡ ይመስላሉ፡፡ (እንዴት ተጃጅለዋል!?) እናም በስደት የሚኖሩ ዳያስፖራ የሕግ ባለሙያዎች ተሰባስበው በዘመቻው ገፍተውበታል አሉ፡፡ አስገራሚው ነገር ምን መሰላችሁ? እነሱ እዚያ የጠ/ሚኒስትሩ የሰላም ኖቤል ሽልማት እንዲወሰድባቸው ሲታገሉ፣ ሌላ ታዋቂ ዓለም አቀፍ የሽልማት ተቋም ጠ/ሚኒስትሩን መሸለሙ ነው፡፡ ከምሬ ነው ባለፈው ሳምንት---- "የሰላም ኖቤል ሽልማቱ ለእኛ ጠ/ሚኒስትር ሳይሆን ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ነው የሚገባው!” የሚል አሳፋሪ ዘመቻ ላይ ሳሉ “ሬፒዩቴሽን ፖል ኢንተርናሽናል” የተባለ ሌላ ትልቅ ተቋም ዶ/ር ዐቢይን ከ100 ስመ ጥር አፍሪካውያን መሪዎች አንዱ አድርጐ መረጣቸው፡፡ (ለፅንፈኞቹ ኪሳራ ነው!)
በነገራችን ላይ እነዚህ የ"ዳውን ዳውን" ፖለቲከኞች ትንሽ ቆይተው ደግሞ ዓለም አቀፉ የሃዩንዳይ ኩባንያ ከሰሞኑ ለጠ/ሚኒስትሩ በስጦታ ያበረከተላቸውን በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን በኤሌክትሪክ የምትሰራ አውቶሞቢል መልሶ እንዲወስድባቸው የሚጠይቅ ዘመቻ መጀመራቸው እንደማይቀር እወራረዳለሁ:: (ፈጣጦች እኮ ናቸው!) ፈጣጦች ብቻ ሳይሆኑ ምቀኞችም ይመስሉኛል፡፡
እነዚህ ቅጥ አምባሩ የጠፋባቸው የዳያስፖራ ፖለቲከኞች፤ "ዶ/ር ዐቢይ የሰላም የኖቤል ሽልማትን መነጠቅ አለባቸው - በኤሌክትሪክ የሚሰራ የሃዩንዳይ መኪና ሊበረከትላቸውም አይገባም፡፡ በአረንጓዴ አሻራ  5 ቢሊዮን ችግኝ የመትከል ዕቅድ አሳክተዋል በሚል ዕውቅና እንዳይሰጣቸው ከወዲሁ እንቃወማለን- ወዘተ" እያሉ ብቻ የሚቀጥሉ ቢሆን ኖሮ እንዳልሰማን ልናልፋቸው እንችል ነበር፡፡ በነገራችሁ ላይ የአረንጓዴው አሻራ ዕውቅና የተባለው ገና ላልተሰጣቸው ዕውቅና ነው ዳያስፖራዎቼ የሚቃወሙት፡፡  
ወደ ቁምነገሩ ስንመጣ፤ ጽንፈኛ ዳይስፖራዎች ሞኛሞኝ በሚመስሉ ተቃውሞዎችና መፈክሮች ብቻ የሚወሰኑ እንዳልሆኑ ታዝበናል፡፡ “መንገድ ዝጋ…የመኪና ጐማ በምስማር እያስተነፈስክ እንቅስቃሴ አስተጓጉል …ሆቴልና ፋብሪካ አቃጥል…ከተማ አውድም …በነፍጠኞች ላይ እርምጃ ውሰድ” የሚሉ አደገኛና አጥፊ ድርጊቶችም ሲያዙ ሰምተናል፡፡ (ያውም በሰው አገር ተቀምጠው) በነገራችን ላይ አዕምሮአቸውን ነካ የሚያደርጋቸው የሚመስሉ አንዳንድ የዳያስፖራ ጽንፈኞች፤ የታዋቂ ግለሰቦችን ስም ሳይቀር  እየጠቀሱ የግድያ  ትዕዛዝ በሚዲያ ሲያስተላልፉ እየሰማን ነው (የዕልቂት ጥሪ በሉት!)፡፡
እናላችሁ… በዳያስፖራ ፅንፈኛ ፖለቲከኞች የተቃውሞ እንቅስቃሴ እየቀለድንና እያፌዝን መጓዝ አንችልም፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ፅንፈኛ የኦሮሞ ፖለቲከኞች እንደዘበት ሲያደርጉት የነበረው የነፍጠኛ ትርክት ፍሬውን በተደጋጋሚ ቅመናል፡፡ በተለይ ደግሞ በቅርቡ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተፈጠረው ሁከትና ነውጥ፤ በአገራችን ታሪክ ሰምተነው የማናውቀው አሰቃቂ ግድያና ዕልቂት ተፈጽሟል፡፡ ጠባሳው መቼም የማይሽር በቂምና በጥላቻ ላይ ተመስርቶ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈፀመው ዘግናኝ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት፤ የአገር የሞት ወይም የመፍረስ ጉዞ ጅማሬን በግልጽ የሚያሳይ ነው:: (ፅንፈኛ የዘር ፖለቲከኞች ህልማቸውን አሳክተዋል!)
እናላችሁ መንግስትም ሆነ ሌሎች አካላት ፅንፈኛ የዳያስፖራ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ከባህርማዶ ሆነው የሚረጩትን የዘረኝነት መርዝ ሳያናንቁ በልዩ ትኩረት ሊከታተሉት ይገባል፡፡ መርዘኛ መልዕክታቸው ዳግም ፍሬ አፍርቶ እንደ ሰሞኑ ዜጐችን ሰለባ ከማድረጉ በፊት መከላከልና መቀልበስ ለነገ የማይባል አገርን የማዳን አጣዳፊ ሥራ ነው፡፡ ካልሆነ ግን እኛም አገርም መፍረሱ አይቀርም፡፡  
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!


Read 4320 times