Saturday, 08 August 2020 13:34

የአርሶአደሩ ሚሊየነር የስኬት ምስጢር

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

   "ሰው ስራን አክብሮ መስራት ከቻለ ይለወጣል ይከበራል"


               በሰሜን ጐንደር ዞን ደባርቅ ወረዳ ቦዛ በሚባል ቦታ በ1953 ዓ.ም የተወለዱት አቶ አንዳርጌ ታከለ ጥሩ መልካም፤ ፊደል የመቁጠር ዕድል ሳያገኙ ነው ያደጉት፡፡ ገና በታዳጊነታቸው ጠብመንጃ አንግተው ወደ እርሻ ሥራ መግባታቸውንም ይናገራሉ፡፡
ትዳር ይዘው ልጆች ከወለዱ በኋላ ልጆቻቸውም የእሳቸው ዕጣ ፈንታ እንዳይደርሳቸውና ሳይማሩ እንዳይቀሩ በሚል ከቀዬአቸው ወጥተው ወደ ከተማ ገቡ፡፡ ወደ ከተማ መግባታቸው ግን ለሳቸውም አዲስ የስኬት በር ከፍቶላቸዋል፤ ወደ ንግድ ሥራ ገብተው የአርሶአደር ባለሃብት ሊሆኑ በቅተዋል፡፡ ባለፈው ሰሞን ለሥራ ወደ ሰሜን ጐንደር የተጓዘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በእኚህ አርሶአደር ባለሃብት መኖሪያ ቤት ተገኝታ ስለ ህይወት ጉዟቸውና የስኬት ምስጢራቸው ጠይቃቸዋለች፡፡
አቶ አንዳርጌም ሁሉንም በጣፋጭ አንደበታቸው አውግተዋታል፡፡ ወጋቸውን እንደወረደ አቅርበነዋል፡፡ እነሆ፡-


            ጋሽ አንዳርጌ፤ እስቲ ጨዋታችንን ከአስተዳደግዎ እንጀምር---
ያው እኛ አገር ከፍ ስትይ ት/ቤት አትላኪም:: በዛን ወቅት አካባቢያችን ላይ ትምህርት አልተስፋፋም ነበር፡፡ እድሜዬ ከፍ ሲል በ16 ዓመቴ መሳሪያ ገዝተው ሰጡኝ፤ ጠብመንጃዬን አንግቼ ሳርስ እውላለሁ፡፡ ውጭ ብቻ አልነበረም የምሰራው፤ እናታችን የወንዶች እናት በመሆኗ እቤት ውስጥ ያለውን ሥራ የሚያግዛት የለምና ሌሊት ተነስቼ ለእናቴ እህል እፈጫለሁ፤ ልክ እንደ ሴትም እንጀራ እንጋግራለን፡፡ ሥራ የተባለ የሚቀረን የለም፤ በዚህ አይነት ነው ያደግነው፡፡
ከዚያ በስንት ዓመትዎ ትዳር ያዙ?
በ1974 ዓ.ም የካቲት 12 ቀን ነው የተዳርኩት:: ለትዳር ስንወስን እንደ አሁኑ አይደለም:: ባለቤቴ የ10 ዓመት ህፃን፣ እኔ የ21 ዓመት ወጣት ሆኜ ነው የተጋባነው፡፡ ያኔ ሚስት መርጦ የሚያጭልሽን ቤተሰብሽን መቀበል እንጂ ማንገራገር የለም፡፡ እኔም ሚስት ታጭቶልሃል ተብሎ ነው የተነገረኝ እንጂ ጥቁር ትሁን ቀይ እማውቀው የለኝም:: የሰርጉ እለት ካልሆነ በስተቀር አትተያይም:: ሚስት ታጨልህ ስትባይ ታፍሪያለሽ፤ በቃ:: በሁሉ ይሄው ነው፡፡ ከዚያ ባልኩሽ ቀን ተጋባን፣ ልጅ ወለድን እልሻለሁ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ከ18 ዓመት በታች የሆነች ልጅ ማግባት በህግ አይፈቀድም፤ ያኔ የ10 ዓመት ልጅ ማግባት ይፈቀድ ነበር ማለት ነው?
በእርግጥ በባህሉ በ10 ዓመት ማግባት አይከለከልም፤ ግና አብሮ መተኛት አይፈቀድም፤ እንደየ እድሜዋ መጠን ሶስትም ይሁን አራት ዓመት ከባልየው ቤተሰብ ጋር እንደ ልጅ ሆና አብራ ታድጋለች:: ባሏ ዞር ብሎ አያያትም:: ለምን ብትይኝ፤ ለአቅመ ሄዋን እስትትደርሱ ምንም አይነት ግንኙነት እንዳትፈጽሙ ተብሎ በአባቶች ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፡፡ በዚህ ምክንያት እድሜዋ ለአቅመ ሄዋን እስተምትደርስ እንደ እህትና እንደ ወንድም ነው አብረን የኖርነው፡፡ ልጅቷ በህፃንነቷ የምትታጨው ወይም የምትዳረው የባልየው ቤተሰብ ሌላ እንዳይወስድባቸው ሲሉ ነው፡፡  
ከተማ ለመግባት ምን አነሳሳዎትና  ወደ ደባርቅ መጡ?
ዝም ብዬ ሳስበው እኔ ባለመማሬ የጦር መሳሪያ ተሸክሜ ለመኖር ተገድጃለሁ:: ከዚያ በኋላ ልጆቼ ሳይማሩ የእኔን እጣ ፈንታ መያዝ የለባቸውም፡፡ ልጆቼን ከተማ ወስጄ ማስተማር አለብኝ ብዬ ከባለቤቴ ጋር ተነጋገርን፡፡ እኛ ከብቶችና እህል እንጂ ብር የለንም፤ እንዴት ብለን ከተማ እንገባለን አለች፡፡ እና ምን ይሻላል ብዬ ብል አንተ ህድና አንድ ሁለት ዓመት ሰርተህ ትወስደናለህ የሚል ሃሳብ አመጣች፡፡ የለም አይደረግም፤ እንደዚህ አይሆንም አልኩኝ፡፡
ለምን?
የለም የለም፤ ይሄ ጥሩ አይደለም፡፡ ምን መሰለሽ፤ እኔ ከተማ ሄጄ ሌላ እለምድና ወይም ደግሞ እኔ እግሬ መውጣቱን አይቶ አንዱ ወደሷ ዘሎ ይገባና ነገር ይበላሻል:: አየሽ ከዚያ በኋላ ትዳር መፍረስ፣ ልጅ መበተን ይመጣል፤ ስለዚህ ተያይዘን አንድ ላይ መሄድ አለብን ብዬ ተያይዘን ልጆቻችንን ይዘን መጣን፡፡
ምን ይዛችሁ ከተማ ገባችሁ?
ቀደም ሲል ገጠር እያለን እዚህ ከተማ ላይ 250 ካሬ ሜትር ቦታ በ1ሺህ 800 ብር ገዝተን ነበር፡፡ እዛ ቦታ ላይ ትንሽ ቤት ሰርተን 40 ብር አከራይተናት ነበር፤ እኛ ግን በሚቀንስ ገንዘብ ትንሽዬ ቤት ተከራይተን ልጆቻችንን አስገባን፡፡ ከዚያ በኋላ እኔ አጣና ንግድ ጀመርኩ፤ ባለቤቴ ደግሞ ብድርና ቁጠባ ከሚባል ጥሩ ተቋም ትንሽ ብር ተበድራ ትንሽዬ ሱቅ ከፈተች፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልን እያገገምን መጣን፡፡ እኔም በአጣና ንግዱ ሰበብ ከኮንስትራክሽን ድርጅቶች ጋር መቀራረብና መገናኘት ጀመርኩኝ፡፡ የአጣና ንግዱም አትራፊ ሥራ ነበር፡፡ እኔም ጫካ ሄጄ እንጨት እቆርጣለሁ፤ ከገበሬውም እገዛለሁ:: ለፕሮጀክቶች አስረክባለሁ:: በዚህ ሁኔታ አከራይተናት የነበረችውን ቤት በተሻለ መልኩ ሰርተን እቤታችን ገባን፡፡ እዛ እየኖርን ምን ገጠመን መሰለሽ? ጐረቤቶቻችን ቴሌቪዥን ነበራቸው፡፡ የዛን ጊዜ እንዳሁኑ እሞላው ቤት አልነበረም:: ከዚያ ልጆቼ ጐረቤት ቴሌቪዥን ሊያዩ ሲሄዱ "ሂዱ ሂዱ ባላገር ሁላ--ቤት ታቆሽሻላችሁ፤ በር ላይ ሁኑ" ተብለው ደጅ ላይ ቆመው ነበር የሚያዩት፡፡ ይሄን ሁሉ ተቋቁመን ቴሌቪዥንም ገዛን፤ በራሳችን መብራትም አስገባን፡፡ ቤታችን አሲይዘን ባንክ አበደረንና ንግዳችንን ማስፋፋት ጀመርነ:: እኔና ባለቤቴ ቀን የሰራነውን ማታ ኦዲት እናደርጋለን፤ ይገርምሻል ምን እንዳተረፍን ምን እንዳጠፋን እንገማገማለን፤ ብቻ እንዲህ እንዲህ እያልን----በዛን ጊዜ ብዙ የሚባል ወደ 500 ሺህ ብር መሰብሰብ ቻልን፡፡ ታዲያ በዛን ጊዜ አይሱዙ መኪና 200 ሺህ ነበር የሚገዛ፤ አይሱዙ ገዝተህ ነግድ ይሉኛል ብዙ ሰዎች፡፡ እኔ ደግሞ መኪና ተገዛሁ አንዱ ልጄ ሹፌር ሌላው እረዳት ልሁን ብለው ከእጄ ይወጡና ሳይማሩ ይቀራሉ ብዬ ፈራሁና ከባለቤቴ ጋር ተመካከርንበት፤ ልጆቻችን ትምህርታቸውን እስኪጨርሱ ድረስ ቤት ነው መግዛት ያለብን ብለን ይህን አሁን ያለንበትን ቦታ ገዛን፡፡ ይገርምሻል---ይህ ቦታ አሁን ከተማ መሆኑን አትይ ገጠር ነበር፤ እልም ያለ ገጠር፡፡ ያን ጊዜ ታዲያ ቦታም እርካሽ ነበር፤ ለምን? ገጠር ስለሆነ:: 200 ካሬውን በ7 ሺህ፣ ሌላውን 200 ካሬ በ9 ሺህ ብር ገዛንና ያንን ብር እዚህ ቤት ላይ አዋልነው፡፡ እኛ የበፊቱ ቤታችን ሆነን ይህንን ሰርተን 8 ሺህ ብር አከራየነው:: በከተማው ትልቁ የቤት ኪራይ ተብሎ ተወርቶ፣ ለፕሮጀክት አከራይተን፣ ለሁለት አመት የኪራዩን ብር አጠራቀምን፡፡ ከዚያ እዚህ ደባርቅም ጐንደርም ሰው እያወቅሁ መጣሁ፡፡ መቼም ሃብት ለታደለ እንጂ ላልታደለ ሰው ከንቱ ነው፡፡ እናም ጐንደር የፍሎሪዳን ሆቴል ባለቤት አስተዋወቁኝ፤ የሱቅ እቃ ሸጠህ ትመልሳለህ እያለ ይልክልኝ ነበር፡፡ እኔም ቃሌን ጠብቄ እልካለሁ፤ ብቻ እንዲህ እያልን ነው የተጓዝነው፡፡
እኛ በእንግድነት ያረፍንበት አፄ ቴዎድሮስ ሎጅ የእርስዎ ነው፤ ሎጁን ሙሉ በሙሉ የገነቡትም እርስዎ እንደሆኑና በዚህ የተነሳም "አርሶአደሩ መሃንዲስ" እንደሚባሉ ሰምቻለሁ:: እስኪ ስለሱ ያጫውቱኝ--?
እውነት ነው፡፡ ያው የቤት ኪራዩንም አጠራቅመን ሌላም ተጨማሪ ስራዎች እየሰራን፣ እጃችን ላይ ገንዘብ ጠርቀም ሲል አሁን ሎጁ ያረፈበትን ቦታ በኢንቨስትመንት እንድናገኝ ጠየቅን፡፡ በዛን ጊዜ "አንተ አርሶ አደር ነህ፤ ይህን ቦታ የምትጠይቀው ልትሰራ ነው ልታበላሽ" እስከመባል ደርሰን ነበር፡፡ ግን እግዜር ፈቅዶ ሰርተን ተወዳዳሪ ለመሆን በቅተናል፡፡ እናንተም ስትመጡ እዚህ ሎጅ ነው ያረፋችሁት፤ በጥራቱና በአገልግሎቱ ላይ አስተያየት ልትሰጡበት ትችላላችሁ፡፡ እንደምታዩት ግንባታውንም የቤቶቹን ዲዛይንም ራሴ ነኝ የሰራሁት፡፡ በአጠቃላይ ልስራ ብሎ ሰው ከተነሳ መስራት የሚያቅተው ነገር የለም፡፡ የስራ ባህል በራሴ በግሌ አዳብሬያለሁ ብዬ አምናለሁ፤ ከጅምሩ ጀምሮ ስራ አክብሬ በመስራቴ ነው ለውጥ ያመጣሁት፡፡ ገጠርም ቢሆን፣ በአሁኑ ወቅት የእርሻ መሬት አለኝ፤ በደንብ አመርታለሁ፤ ከብቶችም አሉኝ፡፡ ፈጣሪም ቢሆን ጣሩ እመስልላችኋለሁ፤ አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤ ተመኙ ይሳካላችኋል ነው ያለው፤ ላልጣረ፣ ላላንኳኳ ላልሰራና ላልተመኘ አይሳካለትም፡፡ ስለዚህ እየጣርን ነው የአምላክን እገዛ መጠየቅ ያለብን፡፡ በሌላ በኩል አንቺ እየሰራሽ ነው ሰውን ማሰራት ያለብሽ፤ ስትሰሪ የሰው አትመኚም፤ ስትሰሪ ጥሩ ነገር ታገኛለሽ፡፡ ስትሰሪ አንቺን እያየ ሌላው ለስራ ይነሳሳል፡፡ በሌላ በኩል፤ ለእኔ የሰጠ አምላክ ለሌላው ሊሰጠው ስለሚችል አካባቢውን መስሎ መስራት ግድ ይላል፡፡
እኛ ወደ ሎጁ ገና ስንገባ እርስዎ የስራ ቱታዎን ለብሰው ከቀን ሰራተኞቹ ጋር ሲሰሩ ባለቤት አልመሰሉንም ነበር ---
ትክክል ነው፤ ሰርተሽ ማሳየት እንጂ ቆሞ መመልከት ምን ይፈይዳል? ስትሰሪ ጤነኛም ትሆኛለሽ እኮ፤ ትረኪያለሽም፡፡ ያገኘ ያጣል ያጣም ያገኛል፣ ጤነኛ ይታመማል የታመመም ይድናል፤ ሁኔታዎች ተቀያያሪ ናቸው፡፡ “አለኝ ብለህ አትኩራ አጣሁ ብለህ አትፍራ” ነው’ኮ እግዚአብሔር የሚለው፡፡ እየሰራሽ ማስተማር ምሳሌ መሆን አለብሽ፤ እኔ እግዚያብሔርን የምለምነው እየሰራሁ ልለፍ ብዬ ነው:: መስራት አሁንም መለወጥ እፈልጋለሁ፡፡ ልንገርሽ፤ ድሮ 10ሺህ 20ሺህ ሲባል እንዳው ተቆጥሮ ያልቅ ይሆን እምለው ሰውዬ፤ አሁን ስለሰራሁ ተለውጫለሁ፤ ሌላው ቀርቶ መሬት ተከራይቼ ባህር ዛፍ ተክለን 5 ሚ. 41 ሺህ ብር ነው ከሽያጩ የተከፈለን፡፡ ይሄ ከመስራት ነው የሚገኘው፡፡ ሰው በማንኛውም ሁኔታና ጊዜ ስራን አክብሮ መስራት ከቻለ ይለወጣል ይከበራል፡፡
ቀድሞ የልጆችዎ መምህር የነበሩ ሰው አግኝቼ፣ የልጅ አስተዳደግ ላይ ያለዎትን ቁርጠኝነት ሲያጫውቱኝ ነበር፡፡ እስኪ ልጅ አስተዳደግ ላይ ያለዎትን አቋም ይንገሩኝ?
በእኔ እምነት መውለድ በጣም ቀላል ነው፤ ማሳደጉ ነው ከባድ፡፡ እኔ ደግሞ መጀመሪያም ከትውልድ ቀዬዬ ስወጣ ዓላማዬ ልጅ ማሳደግና ማስተማር ስለነበር በዚህ በኩል ቸል ብዬ አላውቅም፡፡ ልጆች ከመምህራን ጋር የሚቆዩበት ጊዜ በጣም ትንሽ ነው፡፡ ከወላጆች ጋር ብዙ ጊዜ ያሳልፋሉ፡፡ እናም ልጅ ካልተከታተሉት አልባሌ ቦታ ይውላል:: ያልሆነ ሱስ ይለምዳል፤ በአጠቃላይ መስመሩን ይስታል፡፡ ስለዚህ በሳምንቱ ቀናት የተማሩትን በሳምንት አንዴ ት/ቤት እሄድና አቴንዳንስ አስወጥቼ አያለሁ:: ያልተገኙባት ቀን ካለችም ለምን እላለሁ፤ የጐደለችው ነገር ካለም እጠይቃለሁ፡፡ ሌላው ለመምህራን ጥያቄ እጠይቃለሁ፣ ስነምግባራቸው እንዴት ነው? ይረብሻሉ? ክፉ ይናገራሉ? እንዴት ነው እላለሁ:: ምክንያቱም አንዳንድ ልጆች እቤት ጥሩ መስለው ውጭ ሌላ ሌላ  ያልተገቡ ባህሪያት ያሳያሉ፡፡ ዩኒቨርስቲ እስከሚሄዱበት ጊዜ ድረስ ቤቴ ውስጥ ሰሌዳ ሰቅዬ መምህር ቀጥሬ እየከፈልኩ  አስተምራቸዋለሁ፡፡ ለምን ካልሽኝ፤ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እፈልጋለሁ:: አሁን ያለንበት ዘመን ሆቴል ለመምራት እንኳን የግድ ትምህርት ያስፈልጋል፡፡ አሁን በእኔ ደረጃ እንኳን መማር እየፈለግሁ ነው፡፡
ወደፊት ያልተማረ ሰው ንግድ ፈቃድ አይሰጠውም ሊባል ይችላል እያልኩ እሰጋለሁ እጠረጥራለሁ፡፡ በፊት በፊት ብዙ ነገር ባልተማረ ሰው ነበር ሲመራ የማየው፤ አሁን ያ ነገር እየተቀየረ አብዛኛው ጉዳይ በተማረ ሃይል ነው እየተመራ ያለው:: በዚህ ምክንያት ልጆቼን በአግባቡ ነው እከታተል የነበረው፡፡ አንድ ጊዜ ምን አጋጠመኝ መሰለሽ --- ልጄ ታመመችና ሶስት ቀን ቀረች፤ በአራተኛው ቀን ሄዳ ተምራ ስትመጣ "ወላጅ አምጪ አላሉሽም?" አልኳት:: “አንተ ነህ ዝም ብለህ የምታካብደው እንጂ ምንም አይሉም፤ ሌላው ወላጅም ልጁን አይከታተልም፤ አንድ ወር ሁለት ሳምንት ቆይቶ ቢመጣ የት ቆየህ አይባልም" ስትለኝ በጣም ነደድኩ፤ እሰማይ ልሁን እመሬት አላውቅም፤ በጣም ነው የተሰማኝ፡፡ በነጋታው ት/ቤት ሄድኩና "ልጆቼ ትምህርት ቤት በአግባቡ ይመጣሉ አይመጡም?" ብዬ ስጠይቅ “የአንተ ልጆች መች ቀርተው ያውቃሉ” አሉኝ፡፡ "እስኪ ዝም ብለህ አቴንዳንሱን አሳየኝ" ስለው አመጣልኝ፡፡ ሶስቱም ቀን ላይ መጥታለች ተብሎ ምልክት ምልክት ተደርጐበታል፡፡ እንደገባች ተደርጐ ነው የተሞላው፡፡ በጣም አዘንኩ ተናደድኩ:: ተጣላሁ፡፡ ከዚያ ከርዕሰ መምህሩ ጋር ተገናኘሁና ቁጭ አልን፡፡ ስም ጠሪው ተጠራና መጣ "መጥታለች በቃ! መጥታለች" ብሎ ገጠመኝ፡፡
ከዚያስ እርስዎ ምን አሉ?
አልመጣችም፤ ልጄ ታምማ ቤት ውስጥ ነው የቆየችው፤ አልኩ፡፡ እሱም ድርቅ ብሎ መጥታለች አለ፤ ጠብ ገጠምን፤ በዚህ መልኩ ተጣልቼ ወጣሁ፡፡ በነጋታው ዳይሬክተሩ ደውሎ ጠራኝ:: መምህሩ (ስም ጠሪው) መልቀቂያ አስገብቷል:: "የመጣችውን ተማሪ አባትየው አልመጣችም ብሎ እኔን ውሸታም ለማስመሰል ሞክሯል እናም ሞራሌ ተነክቷል ስላለ ይቅርታ እንድትጠይቀው ነው" አለኝ፡፡ እኔም "እሺ አስቤበት ልምጣ" ብዬ ወጣሁ፡፡ ከዚያ የታከመችበት ሀኪም ቤት ሄጄ ሶስት ቀን ህክምና ላይ እንደነበረች የሚያሳይ ማስረጃ አጽፌ ይዤ ሄድኩኝ:: ያንን ማስረጃ ይዤ ስቀርብ ስም ጠሪው ደነገጠ፤ ይቅርታም ጠየቀ፡፡ ዳይሬክተሩ ታዲያ እንደመጣች ተደርጐ ምልክት የተደረገው ለምንድን ነው ሲሉኝ "መምህሩ ራሱ ስም መጥራት ሲገባው በተማሪ ነው ስም የምታስጠሩት" አልኳቸው:: "ያ ተማሪ የሚወደው ተማሪ ከቀረ እንደመጣ አድርጐ ምልክት ያስቀምጣል፤ የጠላው ተማሪ ቢመጣ እንኳን የቀሪ ምልክት ያደርግበታል፤ እንዲህ እያደረጋችሁ ነው አገሪቷን የምትጐዷት" አልኳቸው፡፡ "ልጄ ሳትመጣ ነው መጣች ያስባልካት፤ ይህን በማድረግህ ልጄን አትጠቅማትም ትጐዳታለህ እንጂ፤ ይሄ ነገር መታረም አለበት" ብዬ አስጠንቅቄ ወጣሁ፡፡
በዚህ ተግባርዎም ት/ቤቱ ሸልሞታል አይደል?
አዎ ተሸልሜበታለሁ፤ ት/ቤቱ በክብር ሸልሞኛል፡፡ የሚገርምሽ መጽሐፍ ለልጆቼ እገዛለሁ፤ እንዲያነቡና እንዲያጠኑ አብሬያቸው እሆናለሁ፤ ፈተና ሳምንት ሲቀረው ጥናት እንዲያቆሙ አደርጋለሁ:: ከዚህ በኋላ አታንብቡ ተረጋጉ ነው የምላቸው፡፡ የምትችሉትን ያህል ስሩ፤ ነገር ግን ከሰው እንዳትቀስሙ (እንዳትኮርጁ ማለታቸው ነው) ነው የምላቸው:: ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜ ስንመለከት በጣም ጐበዝ የተባለው ተማሪ ይወድቃል፡፡ አሁን ያለንበት ጊዜ ጥሩ አይደለም፤ ተንኮል ብቻ የሞላበት ስለሆነ መልሱ “D” ን ሰርዞ “C”ን ይቀባል፤ ያ ጐበዝ ተማሪ ያኛውን ለመሸወድ ያልሆነውን መልስ ቀብቶ ይቆይና ረስቶት በዚያው ያስረክባል፤ ከኮራጁ ጋር አብሮ ይረፈረፋል፡፡ አንቺዬ ተንኮል’ኮ ግም ነው፡፡ ስለዚህ ልጆቼን የምትችሉትን ያህል ስሩ እንጂ እንዳትቀስሙ ነው የምላቸው፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን፤ ትልቁ ልጄ ፊት ለፊትሽ የምታይው የመጀመሪያ ልጄ ነው፤ ወንድሜ ነው የሚመስለኝ፤ ሰርካለም አንዳርጌ ይባላል፡፡ እኛም ተቀጥተን እንዳደግን፣ እሱም በጨዋነት ነው ያደገው፡፡ ሰው ቀና ብሎ አያይም፤ በት/ቤትም በመጥፎ አስጠርቶኝ አያውቅም፤ በምህንድስና ተመርቆ አውራ ጐዳና ተቀጥሮ በሲቪል መሃንዲስነት ለሁለት ዓመት ሰርቶ #አባቴ ካንተ ጋር ብሰራ ይሻለኛል; ብሎ አሁን ከእኔ ጋር ይሰራል፡፡ ድሬው አያት አድርጐኛል፤ እላይ ከከተማው መሃል አንድ ግሮሰሪ አለኝ፤ በእሱ ሰርተህ አገግምና ለታናናሾችህ ታስረክባለህ፤ መንግስትም ኮንቴይነር ሱቅ ሲሰጥ ለ5 ዓመት ነው ብዬ ሰጠሁት፤ እየሰራ ነው፤ በሹፍርናም በኩል ይሰራል፤ ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለው:: ሁለተኛው ልጄ ሸጋው አንዳርጌ ይባል ነበር:: በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከእኔና ከወንድሞቼ ጋር ዘምቶ፣ ከአንድ ወንድሜ ጋር ለአገሩ ተሰውቷል፡፡
ሦስተኛዋ ልጄ የሺሀረግ አንዳርጌ ትባላለች:: ለስሙ ሴት ናት እንጂ እንደኔው በረሃ ወርዳ፣ ተንገላትታ አብራኝ ነው የተለወጠችው፡፡ ስለሷ ስናገር እንባዬ ይመጣል፤ ስጠቁር ትጠቁራለች፤ ብቻ ደሜ ናት፤ እሷ ለየት ያለች ናት፡፡ ትምህርቷን እንደጨረሰች አንተን ማገዝና አብሬህ መስራት ነው የምፈልገው አለች፡፡ በትዳር እንድትወሰን አድርጌ አይሱዙ ገዝቼ ሰጥቻታለሁ፤ ቤትም ሰርቼላታለሁ፤ የተሟላ ህይወት ነው ያላት፤ ጐረቤቴም ናት፡፡ ሁለት ልጆች ወልዳለች፤ አሁንም የሎጁ ማንኛውም ግዢ በእሷ ነው የሚከናወነው:: አራተኛው ልጄ ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጂ ተመርቆ ሲወጣ ወጪ መጋራቱን 21 ሺህ ብር ከፍዬ ዋናውን ዲግሪውን ይዞ መጣ፡፡ ማስተርስህን ቀጥል ብለው ታናሹ ኢንጂነሪንግ ስለሚማር እሱ እስኪጨርስ እኔ ሆቴሉን ልምራ አለ፡፡ አሁን ብትቀጠር መንግስት በትንሹ ስንት ይከፍልሃል አልኩት 3ሺህ ብር አለኝ፤ እኔ 6ሺህ ብር እየከፈልኩህ በአካውንትህ ይቀመጥ፤ ቤቱ የራስህ የአባትህ ቤት ነው፤ የምትፈልገውን እየፈረምክ ውሰድ፤ ደሞዝህ ከተቀጠርክበት ቀን ጀምሮ ተቀማጭ ነው ብዬ በዚህ ተስማምተን እየሰራ ነው፤ የሎጁ ማናጀር ነው፡፡ ጥሩ ልጅ ነው፤ ቻይንኛ እንግሊዝኛ በደንብ ይችላል፤ በዚህ አይነት ቀጥሏል፡፡ ቸርነት አንዳርጌ ይባላል:: ለሆቴሉ ሙሉ ውክልና በፍ/ቤት ሰጥቼው በጣም ስለማምነው እየሰራ ነው፡፡ ትዳር እንዲይዝ እፈልጋለሁ፤ እሱ ደግሞ ቆይቼ አገባለሁ ይላል፤ እንግዲህ ሁሉም በጊዜው ይሆናል፡፡ የሱ ታናሽ አለም አንተ አንዳርጌ በኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ተመርቆ መጥቷል፡፡ ወደ መንግስት ሥራ እንዲገባ አልፈለኩም ነበር፡፡ ነገር ግን እሱ በመንግስት ሰራተኝነት ላይ ነው ያለው:: አይቶት ይመጣና የግል ስራውን አጥብቆ ይይዛል፡፡ የመጨረሻዋ ነፃነት ትባላለች፤ ጐንደር ዩኒቨርስቲ ለመግባት ከሴቶች አንደኛ ውጤት ይዛ ነው የሄደችው፤ ነርስ ናት፤ ዘንድሮ ወረርሽኙ ባይመጣ ትመረቅ ነበር፡፡ ይህን ሁሉ የምልሽ ት/ቤት ላይ የነበራቸውን መስመር በመጠበቄ በመከታተሌና አስተዳደግ ላይ ባሳየሁት ትግል ነው ሁሉም ለውጤት የበቁት ለማለት ነው፡፡
እስቲ ስለ ባለቤትዎ ደሞ ያጫውቱኝ --- ለስኬትዎ የባለቤትዎ ድርሻ ምን ያህል ነው?
በእውነቱ ባለቤቴ ጥጋብ ካሳዬ መልካም ሴት ናት፤ ክፉም አትናገር ሃሳቤንም አትቃወም፡፡ በል በርታ ብቻ ነው የምትለው፤ እየተመካከርን እየተደማመጥን እዚህ ደርሰናል፡፡ አሁን ሰው ሁሉ "አንዳርጌ ጐበዝ ነው፤ አንዳርጌ ብርቱ ነው" ይላል፤ ኧረ ተውኝ እናንተ፣ ባለቤቴ ባትኖር እኔ ብቻዬን ከምኑ ነበር የምገባ እላለሁ፡፡ ቤትሽ ሰላምና ፍቅር ካለ በውጭ ያለው ስራሽ ይሳካል:: አባቶቻችን ምን ይላሉ “ከቤት ዶሮ ሲታረድ ከውጭ ቆቅ ይያዛል” ይላሉ፤ መልካም ሴት ለባሏ ዘውድ ናት አይደል መጽሐፉ የሚል፤ በጣም ታማኝ ናት - ታዛዥ ናት:: ብቻ አሉታዊና አስጨናቂ ነገር ስለሌላት በጣም አከብራታለሁ፤ በስሟ አይሱዙ መኪና የቱር መኪና ሁሉ አላት፤ በጣም ደስ እንዲላት እፈልጋለሁ፡፡ እሷ ለእኔ እጣ ክፍሌ ናት፤ እንደሌላው ሴት አይደለችም:: ስለሷ መግለጽ ይቸግረኛል፤ ባንክ ውስጥ መቶ ሚሊዮን ይኑረኝ መቶ ሺህ ብር  ጠይቃኝ አታውቅም፡፡ ታማኝ ስለሆነች ታምነኛለች፤ በሷ ሰላማዊነት ነው እዚህ የደረስነው፡፡ አሁን ለምሳሌ የሎጁን ዲዛይን ስሰራ በራሴ ፈጠራ ነው የሰራሁት፤ ሌላ መሃንዲስ አላስፈለገኝም፤ አንድ ነገር አንድ ጊዜ ካየሁ ኮፒ ነው የማደርገው፤ ራሴ ነኝ የሰራሁት፡፡
ለዚህ ነው አርሶ አደሩ መሃንዲስ የሚባሉት?
አዎ ቅድም ነግሬሻለሁ፤ ለኢንቨስትመንት ፈትለፊት አስፓልት ዳር ቦታ ብጠይቅ "አርሶ አደር ነህ ታበላሻለህ ፊት ለፊት አትወስድም" ብለው እዚህ ጫካ ውስጥ በፊት ሲሰጡኝ "እብድና ከተማ ወደፊት ነው የሚሮጠው" ብዬ ተቀብልኩኝ፤ አሁን ቦታው የከተማ መሀል እየሆነ ነው፤ በአቅራቢያዬ ደባርቅ ዩኒቨርስቲም ተገነባ፡፡ ብቻ ብዙ ነገር አሳልፌያለሁ፡፡
ትምህርት ባይማሩም ሥራዎና ንግግርዎ ሁሉ ከተማረ ሰው ያልተናነሰ ነው፡፡ ይሄ እንዴት ሆነ?
በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜማ እስከ ዘጠኝ ተምሬያለሁ፤ ኧረ ተይኝ ይቺ ምን አላት! ታዲያ አሁንም የርቀት ትምህርት እየተማርኩ ነው፤ የርቀት ትምህርትና የርቀት ትዳር ዋጋ የለውም የውሸት ነው እንጂ፡፡ ትምህርትና ትዳር ፊት ለፊት ነው መገጠም ያለባቸው፡፡ ያው በርቀትም ቢሆን የምማረው ተወዳዳሪ ለመሆን ነው፡፡ ያኔ ይህንን ሎጅ ስመራ ብዙ ፈተና ገጥሞኛል፤ ባለመማሬ ነው ብዬ እናደዳለሁ:: አንደኛ ገበሬ ነህ ከተማ ታበላሻለህ ፊትለፊት አትወስድም ብለው ጫካ ውስጥ ሰጡኝ፤ በህይወቴ ስለማልረሳው ነው ይህንን ቃል የምደጋግምብሽ፡፡ ሁለተኛ ስሰራ አንድ ቀን እንኳን የከተማው ሃላፊዎች መጥተው ሳያዩኝ ሳያለሙ መሬት አጥረው ካስቀመጡት እኩል “ቦታውን የተነጠቅክ መሆኑን እናሳውቃለን" የሚል ደብዳቤ አመጡብኝ፤ ስራው መጀመሩን ምን ያህል ደረጃ እንደደረሰና እንደተገነባ ሳያዩት ነው የምልሽ፤ በዛን ጊዜ የነበሩት ሃላፊዎችን ነው የምልሽ፤ የአሁኖቹ አይደሉም፡፡ ከዚያ በኋላ የክልልና የዞን የኢንቨስትመንት ኮሚቴ በከተማው ላይ ያለውን ልማት ለመጐብኘት ሲመጣ ገብተው ሲያዩት 60 የሚሆኑ ሰራተኞቼ ግንባታ ላይ ሆነው ስራው በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ተመለከቱና ከሌላው የተሻለ ግንባታ ሆኖ ሲገኝ እነሱ አፈሩ፡፡ ኮሚቴዎቹ ለምንድነው ካላለሙት ውስጥ ስሙን የከተታችሁት ሲባሉ “ስላላየነው ነው” ብለው አረፉ፡፡ ሳታዩ እንዴት ተነጥቀሃል ብላችሁ ትፅፋላችሁ ብለው ሲያፋጥጧቸው መልስ አልነበራቸውም፡፡ ይሄን ሁሉ ተፅዕኖ ተቋቁሜ ፈጣሪ ይመስገን ሰራሁት፡፡ ደም የምርቃቱን ልንገርሽ ጉድ---
እሺ ያጫውቱኝ ---
እኔ በሎጁ ምርቃት ዕለት አርሶ አደር ስለሆንኩኝ በራሴ መሃንዲሲነት ሰርቼ ለዚህ በመብቃቴ እበረታታለሁ እመሰገናለሁ ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ እሸለማለሁ የሚል ሁሉ እምነት ነበረኝ፤ ነገር ግን በተቃራኒው በሩ ላይ ስትገቢ ያየሽው የአፄ ቴዎድሮስ ሀውልት አለ፤ እሱን ሀውልት እንዴት እዚህ ላይ ሰራኸው? ፊቱንስ እንዴት ወደ ትግራይ አዞርከው? ቴዎድሮስ በእጁ የያዘው ባንዲራ መሃል ላይ ለምን ኮከብ አላደረግህም? እያሉ አቃቂር በአቃቂር አደረጉት፡፡
እርስዎ ምን ምላሽ ሰጡ?
እኔ አባትሽ የምፈራቸው መሰለሽ፤ አፄ ቴዎድሮስ ሀውልት ላይ ያለው ባንዲራ በዛን ወቅት አንዲት አገር አንዲት ባንዲራ እሷም በእመቤታችን ማሪያም መቀነት የተሳለች ብቻ ነው የነበረችው፡፡ መሃሉ ላይ ምንም ነገር አልነበረውም፡፡ ሁለተኛ አፄ ቴዎድሮስ ፊታቸውን ወደዚህ ያዞሩበት ምክንያት፤ የነገሱትም ልጅ የወለዱትም ሰሜን ነው፤ የተሰውትም መቅደላ ነው፡፡ መጀመሪያ ታሪክ አጥኑ፤ ያለ እውቀት አትጠይቁ፤ ስለዚህ አቅጣጫው ትክክል ነው፡፡ ሌላው ነገር እዚህ አገርስ ወንድ እንዳለ ቢመለከት ምን ችግር ኖሮት ነው ወደዛ ዞረ ወደህ ዞረ የምትሉት ብዬ በብስጭት መለስኩላቸው:: ይሄ ፈተና አለፈና በሌላ ፈተና ፊቴ ላይ ተጋረጡ፡፡ በፊት አስፋልት ፊትለፊት አታለማም ታበላሻለህ ብለው ከኔ ቀጥሎ ወደ አስፋልት ያለውን 1ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ለአንዲት ከውጭ ለመጣች ሴት ሰጡ:: እሷም አጥራ አስቀምጣ ባለማልማቷ ተነጠቀች፡፡ ከዚያ እኔ ወደዛ እንዳልጠጋ በሬ ላይ አምጥተው የመብራት ትራንስፎርመር ተከሉበት፡፡ ለምንድነው ይህን አምጥታችሁ በሬ ላይ የተከላችሁት ብላቸው፤ ሴትየዋ ስለተነጠቀች ለሌላ ሰው ልንሰጠው ነው አሉ፡፡ እኔ ቦታው በማስፋፊያነት እንዲሰጠኝ አመልክቼ እስከ ክልል ድረስ ወጣሁ ወረድኩ፡፡ እስከ ክልል ስሄድ እዚህ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ወደ ክልል እየደወሉ እንዳይሳካልኝ እንቅፋት ይፈጥሩብኝ ነበር:: ነገር ግን ክልሉ በአካል መጥቼ ቦታውን ካየሁ በኋላ ውሳኔ እሰጣለሁ አለና የክልሉ ከተማ ልማቶች መጥተው አጥንተው ይገባዋል ብለው ሄዱ፡፡ ክልሉ ምን አለ? በአካባቢው የሊዝ ዋጋ መሰረት ከፍተኛውን ከፍሎ መሬቱን ይውሰድ ብሎ ወሰነ፡፡
የአንዱ ካሬ ሜትር ከፍተኛው የሊዝ ዋጋ በወቅቱ ስንት ነበር?
የአካባቢው ከፍተኛው የሊዝ ዋጋ እስካሁንም 900 ብር ነው፡፡ ነገር ግን ሰው የሚሰራውም የማይሰራውም ተጫርቶ ደባርቅ ላይ 6ሺህ 15 ብር ከፍተኛው ነው ተባለ፡፡ እኔን ወደኋላ ለመጐተት የሚሰራውም የማይሰራውም ነው ዋጋውን ያናረው፡፡ አይሰራውም አርሶ አደር ነው፤ በዚህን ያህል ብር አይወስደውም ብለው ነው 6ሺህ 15 ብር ያደረሱት፡፡ እንደዛ አድርገው ከለከሉኝ፤ ይገባዋል ተብሎ ግንቦት ወር 2011 ዓ.ም የተወሰነ በዓመቱ ግንቦት 27 ቀን 2012 ለእነሱ ጥቅማ ጥቅም ከፍዬ ከማስቀነስ በሚል በካሬ 6ሺህ 15 ብር ከፍዬ ከቤተሰቤ ጋር ተመካክሬ ካርታ አሰርቻለሁ፡፡
በቦታው ላይ የተተከለው ትራንስፎርመርስ ጉዳይ ምን ሊሆን ነው?
ትራንስፎርመሩ ይነሳልኝ ብዬ አመልክቻለሁ:: ሁለተኛው በዚህ ቦታ ላይ ወደ ከተማው የሚገባ ትልቅ በጣም ትልቅ የውሃ መስመር አለ፡፡ ቀደም ሲል የውሃ መስመሩን በራስህ የምታስነሳ ከሆነ ማስፋፊያው ይፈቀድልህ ብለው ውል አስገብተውኝ ነበር፡፡ ከሶስተኛ ወገን ፀድቶ ሊሰጠኝ ሲገባ ነው ራስህ አንሳ የሚሉኝ:: እግዚሃር ያሳይሽ፡፡ ክልሉ ግን የውሃ መስመሩን ማስነሻና ማስዘርጊያ ግለሰቡ ሳይሆን መክፈል ያለበት መንግስት በሊዝ ዋጋው ያስነሳ ብሎ ወሰነልኝ:: አሁን የውሃውም መስመር ትራንስፎርመሩም ሲነሳልኝ በ2013 ዓ.ም ቦታው ግራውንድ ስላለው አርሼ በደባርቅ ውስጥ በጣም የተሻለ የሚባል ህንፃ ለመገንባት በዝግጅት ላይ ነኝ፡፡ ሌላው እኔ የምሰራውና ልጆቼ የሚያስቀጥሉት እቅድ ነድፌ አስቀምጫለሁ፤ ጊዜው ሲደርስ የምታዩት ይሆናል፡፡
የሎጁ ኢንቨስትመንት ምን ያህል ፈጅቷል? ለስንት ሰው የስራ እድል ፈጥሯል? በኮሮና ምክንያት የቀነሱትስ ሰራተኛ አለ?
ሎጁ ቀደም ብሎ በነበረው የዋጋ ሁኔታ በ6.5 ሚሊዮን ብር ነው የተሰራው፡፡ አሁን እድሳትና ማስፋፊያ እየተደረገለት ነው፤ ገና ወጪውን አስልቼ አልሰራሁትም፡፡ ወደ 26 ያህል ሰራተኞች አሉኝ፡፡ ወረርሽኙን በተመለከተ እዚህ ከተማ ላይ ከተከሰተና ከተስፋፋ ሙሉ ለሙሉ ሎጁን የአካባቢው ሰዎች እንዲጠቀሙበት እንዲጠለሉበት፣ ታማሚዎች እንዲታከሙበት ለከተማ አስተዳደሩ ፈርሜ አስረክቤያለሁ:: አያድርገውና ነገም ችግሩ ተፈጠረ ቢባል፣ ቁልፉን ላስረክብ ለህብረተሰቡ ቃል ገብቻለሁ:: ለምን ብትይ፤ ህዝብ ከሌለ ቤቱ ምን ያደርጋል? አንዱ የሚያስደስተኝ ይሄ ነው:: ሌላው የተቀነሱ ሰራተኞች እስካሁን ደሞዝ እየተከፈላቸው ነው፡፡ ምክንያቱም ወረርሽኙ በህይወት ከጐዳው በኢኮኖሚ ያደቀቀው ነው የበዛው፡፡ አሁን በጣም አጣብቂኝ ሰዓት ነው፤ ግንባታ እንዳይገነባ ሲሚንቶ 640 ብር ገብቶ ዛሬ ገዝቻለሁ፡፡ በግንባታ የቀን ስራ ሰርቶ ድሃው እንዳይበላ ማለቴ ነው፡፡ ሥራ አጡ በዝቷል:: በዚህ ምክንያት በአሁኑ ወቅት ሎጁ ሥራ ሰርቶ የሚገኘው ገንዘብ ወደ ኪሴ እንዲገባ አልፈልግም፡፡ እግዚአብሔር ምስክሬ ነው:: የሰራተኞቹን ደሞዝ እንዲሸፍን ነው የምፈልገው:: ቤቱን ስሩበት እኔንም ቤቱንም ተጠቀሙብን፤ ሰርታችሁ ደሞዝ አግኙ፤ ካልሰራችሁ ግን ቤቱም እኛም እናንተም የለንም አልኳቸው:: እንደምታዩአቸው ደፋ ቀና ብለው የሚሰሩ ጥሩ ጥሩ ልጆች ናቸው ያሉት፤ በዚህ አይነት ቀጥለዋል፡፡ ሁሉም አስቦ ነው የሚሰራው:: ደሞዝ ሲቀበሉ እቁብ ይጥላሉ፡፡ ይህም ሆኖ አያረካኝም፤ በቀጣይ ሁለትና ሶስት መቶ ሰው ሰርቶ የሚገባበት የስራ እድል መፍጠር ነው እቅዴ፡፡ ምክንያቱም እድሉን ለአንድ ሰው ብቻ የሰጠው ማን ነው? አጥፊም ከሆነ ሰው ጨምሮ እንዲጠፋ ነው እድሉ የተፈጠረው:: እርጥብና እድለኛም ከሆነ፣ ሌላ ሰው ጨምሮ እንዲያድግ ነው እድሉ የተፈጠረ፤ ስለዚህ የእኔ እድል ለእኔ ብቻ ሳይሆን የተፈጠረው ለሌሎችም ዜጐች ጭምር ነው፡፡
አሁንም ድረስ ጠብመንጃ ማንገት አላቆሙም አይደል?
እሯ እንዴት ብዬ እናት አለም----ያደገብኝን:: ራሴንም አካባቢዬንም አሁንም እጠብቃለሁ:: ፀጥታና ሰላምን ማስከበር የመንግስት ሥራ ብቻ ነው ብሎ መደምደም ትክክል አይደለም፤ ህብረተሰቡ ሰላሙን በመጠበቅ ላይ መሳተፍ የግድ አለበት:: ለምሳሌ እኔ በሳምንት አንድ ቀን ሀሙስ ሀሙስ መሳሪያዬን ታጥቄ ከሌሎች መሰሎቼ ጋር ከተማ ስጠብቅ ሮንድ ስዞር አድራለሁ፤ ይሄ ግዴታዬ ነው፡፡  

Read 2614 times