Saturday, 08 August 2020 15:16

ቀታሪ ግጥም

Written by  ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ
Rate this item
(2 votes)

የሰው መሰል መንጋ ክምር ተበተነ፡፡
            (ሒሳዊ አስተያየት፤ በቢኒያም ፍቃዱ “ነጋልሽ መሰለኝ እና ሌሎች ግጥሞች”)


          ግጥም የወቅቱን መንፈስ (ድባብ) መቋጠሪያና አፈፍ ማድረጊያ መዳፍ ናት -- ለሰው፡፡ የህመሙን ልክ መስፈሪያ ናት:: አረረም መረረም የባይተዋርነት ስሜት ያጠላባታል፤ የተዝረከረከውን የህልውና ጥገግ ማንፀሪያ፣ መፍተያ በመሆኑዋ የደደረ ስሜት አዛይ ናት፡፡
በርግጥ ሁሌም ብርሐን አሳዳጅ ፣ ህልም ሰናቂ ናት፡፡ ይህ ግን በተቃራኒ የህይወት መልኮች መካከል የተሰነቀረች ጩኸት ያደርጋታል፡፡ ታዛቢ፣ ነቃሽ በመሆኗ ብርቱ ነች፡፡ ስለቷ ይቆርጣል፡፡ የተበተነን ትሰበስባለች፤ የተሰበሰበን ትበትናለች፡፡ ዞሮ ዞሮ እጣዋ ህልውናን መትከል ፣ ማፅደቅ በመሆኑ ጩኸቷ እንደ ፍንዳታ ይቆጠራል ፤ ያናጋል፡፡ ያንገራግጫል፡፡
ማንገራገጩ ከልማድ ጋር የሚደረግ ግብግብ ነው፡፡ የህመሙ ምንጭ የነባር ልማድ መንገራገጭ ይመስለኛል፡፡ መንገራገጭ ... መንገራገጭ...
በርግጥ በህይወት ውስጥ ሁሉም ልማዶች በግጥም ለመባል ወይም ለመፃፍ ተራ የሚጠባበቁ አላፊም፣ጠፊም  ወይም ደግሞ ቋሚ ነገሮች ናቸው፡፡ ያም ሆኖ ያገላለፅ ትባቱ (ዘይቤው) ያፀድቀዋል፡፡ ብርታቱ የህልውና ስዕል ሆኖ እንዲቀጥል ምክንያት ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው መጥፎም፣ ጥሩም የሆኑ ጉዳዮች ግጥምን “ግድ” የሚሉት፡፡
ማገዶ
  መሆን ሲችል ፍሬ
  ከ’ንክርዳድ ተሽሎ፣
  ተራ ጥቅም ግዞት
  ህሊናውን ጥሎ፡፡
        ጭራሮ’ና ቅጠል
        መጠቀሚያ ምጋጅ፣
       ብዙሐን የጠሉት
       የሹመኞች ወዳጅ፡፡
                  ኬት መጣ ባላልነው
                  ባውሎ በፈጠነ፣
                  የሰው መሰል መንጋ
                   ክምር ተበተነ፡፡
(በቢኒያም ፍቃዱ ፣ "ነጋልሽ መሰለኝ እና ሌሎች ግጥሞች"፤ 2011 ዓ.ም፣ ገፅ 23)
ግጥሙ  የዘመንን ህመም ጠቋሚ በሆነ መንገድ የፖለቲካችንን አጨዋወት ያሳያል:: በወጪና በወራጁ መካከል ያለውን የአሰላለፍ ምግባራዊነት ወይም ረብነት ያጠይቃል፤ በማሽሟጠጥ፡፡ ሽሙጡ፦
  "የሰው መሰል መንጋ
  ክምር ተበተነ፡፡”
በሚል ተወክሏል፡፡ የመጀመሪያው መስመር ሰው በመንጋ ተመስሏል፡፡ ይህ ደግሞ መንጋነት ለእንስሳት እንጂ ለሰው የተገባ እንዳልሆነ ይጠቁማል፡፡ ምናልባትም መንጋነት ለአውዳሚ ተግባር እንጂ ለልማት፣ ለእድገት የዋለ ማህበራዊ አሰላለፍ አለመሆኑ የተጠቆመበት ስንኝ ይመስለኛል:: በእርግጥ ከሰው ይልቅ “የአንበጣ መንጋ” ስንባል በይበልጥ እንግባባለን፤ መቼስ አንበጣ ለመልካም በመንጋ አይጓዝ፡፡ ይህም እውነት የሚሆነው በእኛው አሰላለፍ (በሰውኛ) ከተመለከትነው እንጂ በአንበጣ ቦታ ሆነን ካየነው የህልውናው መሰረቱም አይደል!? ሰው መሆን ደግሞ የተፈጥሮን ህፀፅ መንቀስም፣ ማረቅም ነው፡፡
ሰውነት ከመንጋነቱ ባሻገር የአንበጣን ሚና ለመጫወት ሲሰለፍ ግን ትርፉ ያው እንደምናየው ነው፡፡ ለአብነት የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት ምክንያት በማድረግ፣ ሀገር ለማውደም የወጣውን የሰው መንጋ በአንበጣ ወይም በግሪሳ ውክልና በአቻነት ሊታይ ይችላል፡፡
በእርግጥ የመንጋው ክምር መበተኑን የሚገልፀው ቀጣዩ ስንኝ የስሜቱ ማርገቢያ ነው፤ ለግጥሙ፡፡ ስለሆነም “ክምር ተበተነ::” በሚል መስፈሩ አንድም ያ ሁሉ የመንጋ ክምር የሹመኞችን ተልዕኮ ይዞ መሰማራቱን፣ ሀገር መውረሩን እንረዳለን፡፡ ወረራውም ለማህበረሰቡ ዱብዳ ፣ ያልታሰበ ማዕት መሆኑን
  «ኬት መጣ ባላልነው
 ካውሎ በፈጠነ ፣” በሚል ተገልጿል፡፡ ይህ የመንጋ ፖለቲካዊ ተግባር ሀገሪቱ ላይ በተደጋጋሚ የተከሰተ (የተፈፀመ) ታሪክ የመዘገበው ሒደት ነው፡፡
ይህ “ካውሎ የፈጠነ” የሰው መሰል መንጋ ከየት መጣ? ማን ላከው? ምን ተልዕኮ አለው? የሚሉትን ጥያቄዎች በሚመልስ መልኩ እንደሚከተለው ተሰናኝቷል፡፡
ጭራሮ’ና ቅጠል
መጠቀሚያ ምጋጅ፣
ብዙሐን የጠሉት
የሹመኞች ወዳጅ፡፡
እዚህ ላይ ሁሉም ነገር ግልፅ ነው:: የመንጋው አሰላለፍ ከፖለቲከኞች ጎራ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በእርግጥ ፖለቲከኞች እነማን ናቸው? ብለን ስንጠይቅ አንድም ከስልጣን መንበር የተገለሉ አካላት፣ ሁለትም ፅንፈኛ አቋም ያላቸው  ግለሰቦችና ቡድኖች መሆናቸውን እንረዳለን፡፡ “ብዙሐን የጠሉት” የሚለው ስንኝ የህዝብ ጠላት የሆነውን አካል መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ለዚህ “ህውኃትን ከነጭፍሮቿ «እንደ ምሳሌ መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ የእነዚህ ቡድኖችም ሆነ የሌሎቹ  መንጋነት  መሰረቱ በዋናነት “በዘር” እና በጥቅማጥቅም ላይ እንደሆነ  የሚታወቅ ሐቅ ነው፤ ዘላቂ ህልውናን ያንቋሸሸ፡፡
ግጥሙ በህዝቡ ዘንድ የተጠሉና የተገፉ ፖለቲከኞችን (ፓርቲዎችን) ተልዕኮ የሚያስፈፅሙ አካላትን “ጭራሮ’ና ቅጠል መጠቀሚያ ምጋጅ፣” በማለት ይገልፃቸዋል:: ስልብ መሆናቸውን ይጠቁማል፤ ህልም ያልቋጠሩ፣ በተዘረጋላቸው ቱቦ የሚፈሱ ተሰባሪና ረጋፊ አድርጎ ስሏቸዋል፡፡ ጭፍራ ከሌለ መሪ የለም እንደ ማለትም ነው፡፡
ግጥሙ ከላይ ለተገለፁ መንጋዊ ሰብዕናዎች መልስ አለው፡፡ የምርጫቸውን መደዴነት፣ መንጋነት ለማሳየት በንፅፅር ያቀረበው ዘይቤያዊ አገላለፅ በመጀመሪያው የግጥሙ አንጓ ላይ ሰፍሯል፡፡ እነሆ፦
መሆን ሲችል ፍሬ
ከ’ንክርዳድ ተሽሎ፣
ተራ ጥቅም ግዞት
ህሊናውን ጥሎ፡፡
በግጥሙ “ፍሬ” ለተሻለ ሰዋዊ ተግባር የህልውና ስዕል ሆኖ ተወክሏል፡፡ በህይወት ውስጥ እራስን ለላቀ ተግባር ማጨትን፣ ለሰው ልጅ ደህንነት፣ ለሞራል ግንባታና ለዘላቂ ህልውና ዘብ መቆምን ያነፅራል:: ፍሬ፤ ከእንክርዳድ ጋር የተወዳደረበት ምክንያት ይኸው ነው፡፡
ሌላው ወቅታዊ የፖለቲካ ክንውን በመጨረሻው አንጓ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ስንኞች የተገለፀውና በመጨረሻዎቹ ሁለት ስንኞች ደግሞ ያስከተለው ውጤት በግልፅ ተቀምጧል፤
"ኬት መጣ ባላልነው
 ካውሎ በፈጠነ፣” ይህ የአንድን ነገር ድንገተኛ ክስተት የሚወክለው “የሹመኞችን ጭፍራ” አደብ ያስገዛን አካል (በሀገራችን በመጋቢት ወር  በ2010 ዓ.ም  የተከሰተውን የስልጣን ለውጥ ወይም የለውጡን ሀይል ፈጣን ክስተት የሚወክል) ነው፡፡ ይህ ሀይል “ሹመኞችን ከነጭፍሮቻቸው” አደብ ማስገዛቱና መበተኑ “የሰው መሰል መንጋ / ክምር ተበተነ፡፡”  በሚል ተገልፇል፡፡
በመጨረሻው የግጥሙ አንጓ ላይ ሁለት ተቃራኒ ተግዳሮቶች (ሁነቶች) ተሰናስለው ቀርበውበታል፡፡ እዚህ ላይ የግጥሙ  ሐይል ይበረታል፡፡ ለሰው የወረወሩት ቀስት ራስን ይቀስት --- እንዲሉ
(ብዙሐኑ የጠሉት
የሹመኞች ወዳጅ ፡፡)
[ቀታሪ÷ስሩ ቀተረ ነው፡፡ ቀተረ÷እኩል ለመሆን ተከታተለ÷ተቀታተረ÷ተመለካከተ÷ተወዳደረ÷ተተካከለ÷ተመዛዘነ÷ተፈካከረ÷ተፈላለገ (አስ) ከባለ ቀትር አትቀታተር:: (ከሣቴ ብርሃን ተሠማ÷የዐማርኛ መዝገበ ቃላት÷ገፅ ፫ ፻ ፹ ፬÷ 2008 ዓ.ም) ግጥም ምንጬ ህይወት ነውና (ቋንቋው (መንገዱ) አዕምሮን፣ ስሜቱ ልብን እና መልዕክቱ ልቦናን ይቀትራል::) አዕምሮን፣ ልቦናንና ልብን የቀተረ ከምናብ የሚፈለቀቅ የፀነነ የጥበብ ውጤት ነው፡፡መቀተሩ ከልማድ ጋር የሚደረግ ግብግብ ነው፡፡ ፈጠራ ደግሞ ልማድን መሻገር ይጠይቃል፡፡ከልማድ ያልተሻገረ ግጥም ነፃ አያወጣም፡፡አይታኘክም-የተመጠጠ ነውና፡፡]Read 922 times