Saturday, 15 August 2020 15:29

የአስተያየት አፈጣጠር/ምሥረታ (formation)

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  --የሕዝብ አስተያየት አፈጣጠር ሰዎች በአካባቢያቸው ካለው ዓለም ጋር ዘወትር በሚያደርጉት ግንኙነት ወቅት ይከሰታል፡፡ ዘወትር ከመገናኛ ብዙኃን፣ ኢንተርኔት፣ ሶሻል ሚዲያ፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ ጓደኞችና የቤተሰብ አባላት አሳማኝ መልዕክቶች ይጐርፋሉ:: እንዲሁም የሕዝብ ጉዳዮችን በተመለከተ ከትምህርት ቤቶች፣ ከመንግሥትና የፖለቲካ ድርጅቶች ሰዎች መረጃዎችን ያገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ከፖለቲካ የምርጫ ዘመቻም ስለ ተወዳዳሪዎቹና አቋማቸው እንዲሁም ስለ ወቅቱ ጉዳዮች ይማራሉ፡፡ እንግዲህ እነዚህ ተከታታይ መረጃዎች ናቸው ሰዎች ስለተለያዩ የፖለቲካ ኩነቶች፣ ተዋናዮችና ፖሊሲዎች የሚኖራቸውን አስተያየት የሚቀርጹት፡፡
የአስተያየቶችና የጠባዮች መሠረት የሆኑት ልማዶችና (norms) የተወሰኑ ባሕርያት ወይም የማይለወጡ ሐሳቦች (stereotypes) በሕዝብ አስተያየት ምሥረታና ለውጥ ወይም አለመለወጥ ላይ ከባድ ተጽእኖ አላቸው፡፡ እነዚህም ፅንሰ ሐሳቦች ሰዎች ለመለወጥ፣ አንድ ድርጊት ለመፈፀም፣ እንዲሁም አስተያየታቸውን በምርጫ፣ በሰላማዊ ሰልፍ፣ በብጥብጥና አድማ ለማሳየት ለምን እንደሚገፋፉ ለማወቅ ጠቃሚ መሆናቸውን የሕዝብ አስተያየት ምሁራን ይረዳሉ፡፡ ለዚህም ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ዎል ስትሪትን ተቆጣጠሩ “Occupy Wall Street” ብሎ ለተነሳው ንቅናቄ፣ በመነሻው ወቅት የአሜሪካን ሕዝብ ያሳየው የነበረው የጋለ ስሜትና ድጋፍ ቆይቶ ንቅናቄው ምንም የጠራ መልእክት እንደሌለውና ተቃዋሚዎቹም በደንብ ያልተደራጁና ችሎታ የሌላቸው መሆናቸው ግልጽ ሲሆን ማጣጣሉ ነው፡፡
በግለሰብ ጠባይ ዙሪያ የሕዝብ አስተያየትን ካጠኑት መካከል የሶሲዮሎጂስቱ የደብሊው ፊልፕስ ዴቪሰን (W.Phillips Davison)  ሞዴል ለሕዝብ አስተያየት ምሥረታ ጉዳዮች (issues) ያላቸውን ሚና አጥብቆ ይናገራል:: እንደ ዴቪሰን አስተያየት፤ “…የምሥረታው ሂደት የሚጀምረው ጉዳዩ በቀረበ ወቅትና ሰዎች ሐሳቦችን በተለዋወጡ ጊዜ ነው፡፡ ጉዳዩ ወደ ሦስተኛ፣ አራተኛ፣ አምስተኛ ሰው በተላለፈ ጊዜ ሥር እየሰደደ ነው ይባላል፡፡ ብዙዎች ጉዳዮች ይህ የሰዎች ሰንሰለት ረጅም ርቀት እንኳን ሳይሄዱ ይጠፋሉ፤ ይሁንና የሚቀሩት ጥቂቶቹ የሕዝብ አስተያየት መነሻ ይሆናሉ:: የቅርብ ጊዜ ተምሳሌት የሚሆነን የዩቲዩብ ቪዲዮ መልዕክቱን በተጋሩት ሰዎች መጠን ወይ ገንኖ ይቆያል (“go viral”) አለበለዚያም ይደበዝዛል”::
እንደ ሶሲዮሎጂስቱ ኸርበርት ብሉመር፤ የሕዝብ አስተያየት አፈጣጠር የሚከሰተው በውይይት ጊዜ ባለው መመላለስ ሲሆን፤ ቅርጽ የሚይዘው ግን በእሰጥ አገባው ወቅት ነው:: የሕዝብ አስተያየት ተፈጠረ ማለት ሰዎች የየራሳቸውን ልምድ በመጋራት ለአስታራቂ ሐሳብና ከእኔ ይቅር ለማለት ዝግጁ ናቸው ማለት ነው፡፡ እንደዚህም በማድረግ ነው የተከፋፈለው ሕዝብ አንድ ሆኖ ተግባር ላይ የሚሰማራው:: እንደዚሁም የቪንሰንት ፕራይስና ዶናልድ ኤፍ ሮበርትስ (Vincent Price and Donald F. Roberts) ሞዴል፤ የሕዝብ አስተያየትን የማኅበራዊ ሂደት መሆኑን ገልጾ ሲያብራራ፤ “የሕዝብ አስተያየት አፈጣጠርና አለዋወጥ ሂደት የተወሳሰበና የፖለቲካ ተዋንያኑን፤ ሚዲያንና ፍላጐት ያለውን ሕዝብ የሚያቅፍ ሆኖ፣ እነዚህ ሁሉ በማኅበራዊ ጉዳዮች አስተያየት ላይ ተጽእኖ ለማሳደር ይጥራሉ፤ ስለሆነም የሕዝብ አስተያየት ሂደት የማኅበራዊ ስምምነት ውጤት ነው” ይላል፡፡
ሰዎች በህይወት ዘመናቸው ከአካባቢያቸው ካሉት ሰዎች የሚማሩት ማኅበራዊ ልማድ፣ እምነትና ጠባይ አስተያየታቸውን ይቀርጻል:: በዚህም ሂደት ውስጥ ቤተሰብ፣ የሃይማኖት ተቋሞች (ቤተ ክርስቲያንና መስጊድን የመሰሉ)፣ ትምህርት ቤቶች የሕዝብ አስተያየትን በመቅረፅ ሂደት ውስጥ ያላቸው ሚና ቀላል አይደለም፡፡ የእነዚህ ተቋሞች ተጽእኖ የሚጀምረው ማልዶ ቢሆንም፣ በሰው ልጅ የዕድሜ ዘመን ውስጥም ቆይቶ ይታያል:: “የፖለቲካ ባህሉ ተመሳሳይ በሆነበት አገር፣ ይህ የሆነበት ምክንያቱን ለማወቅ በመጀመሪያ መታየት ያለባቸው ቦታዎች የሕፃናት ማሳደጊያ፣ ትምህርት ቤት፣ ቤተ ክርስቲያን…” ናቸው ይላል ዋልተር ሊፕማን:: የፖለቲካ አስተሳሰብን በመቅረጽ ረገድ ቤተሰብ ዋነኛው ነው፡፡ ቤተሰብ ሕፃናትን በተለያዩ የማኅበራዊ ልማዶችና እሴቶች ይቀርጻቸዋል፤ ይህም ወደፊት ለሚኖረው የፖለቲካ ሥርዓት ባሕርይ አስፈላጊነት አለው፡፡ ቤተሰብ የፖለቲካ መሪዎችን፣ አክቲቪስቶችን፣ እንዲሁም ፖለቲከኞችን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ የፖለቲካ ሥራዎች ያከናውናል፡፡ የኬኔዲና የቡሽ ቤተሰቦች በአሜሪካ፣ የኬንያታ ቤተሰብ በኬንያ፣ የኔህሩ ቤተሰብ በሕንድ ለዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው፡፡
ቤተሰብ በአባላቱ አስተሳሰብና አስተያየት ምሥረታና አፈጣጠር ላይ ስለሚኖረው ተጽዕኖ ሀርውድ ኤል ቻይልድስ፣ “የሕዝብ አስተያየት ባሕርይ፣ አፈጣጠር እና ሚና” ብሎ በሰየመው በ1965 እ.ኤ.አ በወጣው መጽሐፉ እንዲህ ብሏል፡-
ብዙውን ጊዜ በቤተሰብ ውስጥ ነው የሕፃናት የመጀመሪያው ቀረጻ የሚካሄደው፣ ልማዶች እንዲሁም ጥላቻዎች፣ የሚሰረፁት፣ የሚወደድና የሚጠላ፣ የሚፈቀድና፣ እንዲሁም ግቦች የሚዳብሩት:: በተጨማሪም ወላጆችና ቤተሰቦች በሕፃናቱ የመጀመሪያ ዓመታት ወቅት በሚገፋፏቸው ጉዳዮች ላይ ሙሉ ቁጥጥር አላቸው፡፡ በዚህን ወቅትም ነው የቤተሰባዊ ሕይወት የቅርብ ግንኙነት፣ የቅጂ፣ ድግግሞሽና ሐሳብ ማቅረብ የሚጧጧፈው፡፡ የአበላል፣ የመኝታ፣ የጨዋታ ልማዶች፣ ቀደም ብለው ይዳብሩና፣ ልምምዶቹም አድገውና ጐልብተው የአስተሳሰብ ቅርጽ ይይዛሉ፡፡ በእነዚህ የቀደሙ ዓመታትም ነው ሕፃናት የሥልጣንን ተፈጥሮ የሚያውቁት፣ ቢያንስ በቤታቸው ውስጥ የሚገኘውን የሥልጣን ዐይነት፡፡ እንዲሁም በቤት ውስጥ ነው ልምዶችና ተጽእኖዎች ስሜትን የሚነኩ አንዳንዶቹም እጅግ አሰቃቂ የሆኑ የተለያዩ መልኮች የሚኖራቸው፡፡ ምንም እንኳ ቤተሰብ ስለቀደሙ ዓመታት አስተማሪ ባይሆንም ቅሉ፣ ችሎታን፣ ስሜትን፣ ምኞትን ወይም ተስፋን በማሳደግ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ ቤተሰብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በልጅነት ጓደኞች ምርጫ፣ በትምህርት ቤት አመራረጥና ሌሎች በዛ ያለ ጉዳዮች ላይ ተጽእኖ አለው፡፡ በርግጥም ለባህል መተላለፍ ተግባር፣ ለአጠቃላይና መካከለኛ አስተሳሰቦችና የተለዩ አስተያየቶች መዳበር ዋና ወኪል ነው፡፡
ትምህርት ቤቶችም እንዲሁ በሕዝብ አስተያየት አፈጣጠርና ምሥረታ ላይ ታላቅ ተጽእኖ ካላቸው ተቋማት መካከል የሚገኙ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ባሁኑ ጊዜ በሥልጣን ላይ የሚገኙት ሰዎች መሠረታዊ አስተያየት ወይም ዕይታ በአብዛኛው የተቀረፀው ከሃያና ሠላሳ ዓመታት በፊት ነበር፡፡ የአንደኛ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሕፃናትን ትናንሽ ኢትዮጵያዊያን፣ ኬንያዊያን፣ ናይጀሪያኖች፣ አሜሪካኖች፣ ጀርመኖች፣ ቻይናዊያን፣ የመኖች፣ ወዘተ አድርገው ይሠሯቸዋል፡፡ በሕፃናቱ አዕምሮ ውስጥ የሕዝቦችን ታሪክና ትውፊት፣ እምነትና ርዕዮተ ዓለም ይቀርፃሉ፡፡ ይህንንም ሲያደርጉ በሂደቱ የፖለቲካ ቅስቀሳን ተግባር ይደግፋሉ፡፡ የትምህርት ሥርዓቱም እሴቶችንና ርዕዮተ ዓለሞችን ከመቅረጽ ባለፈ ከትምህርት ቤት በተመረቀው ጐልማሳ የፖለቲካ ልምድና አስተያየት ላይ የሚንፀባረቅ ምሁራዊ ሙያዎችንና መሠረታዊ አስተሳሰብንም ያስፋፋል:: የትምህርት ሥርዓት በዜጐች ቀረጻ ላይ ተጽእኖ ከሚያሳርፉት መካከል አንደኛው ነው፡፡     
(ሰሞኑን ከወጣው የዶ/ር አድማሱ ጣሰው " የሕዝብ አስተያየት" እና ተዛማች ጽንሰ ሐሳቦች  መጽሐፍ የተቀነጨበ)


Read 2583 times