Tuesday, 18 August 2020 17:30

የፍቅራችን ሻማ

Written by  ደበ
Rate this item
(3 votes)

 ከምሽቱ አንድ ሰዓት እስከ ሁለት ሰዓት ያህል በስልክ እናወራለን፡፡ አንዳንዴም ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት እስከ አንድ ተኩል ልናወራ እንችላለን፡፡ ሁኔታው የሚወሰነው በዕለቱ በሚኖረን የወሬ መጠንና የውስጥ ፍላጐታችን ሃይል ነው፡፡ እኔ በበኩሌ አንዳንዴ ባናወራ የምልበትም ቀን አለ፡፡ ሥራ ሲበላሽብኝ ወይም የሀገሪቱ ሁኔታ ሲያስጠላኝ ጥቅልል ብዬ በጊዜ ብተኛ ደስ ይለኛል፡፡
ችግሩ እኔ ባስጠላኝ ቀን እሷ እንደ ሲካካ ዶሮ የተፍለቀለቀች እንደሆነ ነው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ሁለታችንም ካስጠላን፣ “በቃ ቻው” ተባብለን በአጭሩ እንለያያለን፡፡  
መስኪ የምትወደድ ናት፡፡ ፀባይዋ ደስ ይላል፡፡ ለማንም ሰው ጥሩ ነገር የምታስብ፣ ሰው ሲሳካለት ተደስታ የማትጠግብ ናት፡፡ ጥርጣሬ የሚባል ነገርማ አልፈጠረባትም፡፡ መንገድ ላይ ስትሄድም የወደቀ ሰው ካየች፣ እንቅፋት የመታው ሰው ከገጠማት “እኔን!...እኔን ይምታኝ!..እኔን ይድፋኝ!.; ስትል ትውላለች፡፡
አንዳንዴ ታስቀኛለች፡፡ ;ለስንቱ አዝነሽ ትችያለሽ?; እላታለሁ፡፡ እሷ ደግሞ #መቼም የሰው ልጅ ወገኑ ሲጐዳ ካልተሰማው፣; ትልና ዐይኖችዋ እንባ እንዳቀረሩ እንደ ማልጐምጐም ትላለች፡፡
“አንተ ግን አረመኔ ነህ!...በማን ወጥተህ ነው? እናትህ ሠፍሳፋ ናቸው፤ አባትህም ጥሩ ሰው እንደነበሩ ሰምቻለሁ; ትለኛለች፡፡
“በሞሶሎኒ ወጥቼ ነው!” ስላት ጀርባዬን ድቁስ ታደርገኝና ደስ ይላታል፡፡
“እኔ አሁን አንተን ነው የማገባው? ልጃችን ብቻ ባንተ እንዳይወጣ!...መልኩ እንደኔ ቀይ እንዳይሆን፣ ልቡ እንዳንተ እንዳይጨክን…”
“ታዲያ ጨካኝ ለምን ታገቢያለሽ?”
“ምን አውቄ? ግራ ይገባኛል--”
“ፍቅር ሒሳብ የለውም የሚባለው ደርሶብሽ ነው!”
ሁለታችንም ያደግነው የድሮ ሲዳሞ ክፍለ ሀገር፣ አለታ ወንዶ ከተማ ነው፡፡ ሠፈራችን አንድ ስለነበር ሁሉን ነገር እንተዋወቃለን፡፡ ማርያም ሠፈር ያለን ልጆች የአንድ ቤተሰብ ያህል ነን፡፡
ይሄ አሥሬ “እኔን ይድፋኝ! እኔን ይምታኝ!” የሚለውንም ይዛ የመጣችው ከዚያ ነው፡፡ የሲዳማ ሰው አጠገቡ ሰው ሲወድቅ “አኔ ኪራ!” ይላል፡፡ “እኔን” ለማለት ነው፡፡ ምግብ ሲጋብዝህ “ቡሻ ኢቶ ኦኒ” ይላል፡፡ “እኔ አፈር ልብላልህ” ማለቱ ነው፤ "ብላልኝ--ጠጣልኝ”፡፡ ያሁኑ ዘመን ፖለቲካ ቢሸራርፈውም፣ አሁንም ቅሪቱ አለ፡፡ መስኪም ያ አልለቅ ብሏት ነው፡፡
በዚያ ላይ የትውልድ ሀገሯን ስትናፍቅ ልክ የላትም፡፡ መስከረም ሲጠባና እንቁጣጣሽ ሲደርስ በትዝታ ጨርቋን ጥላ ታብዳለች፡፡ የጓደኞችዋን ስም እየጠራች እንባዋ ዱብ - ዱብ ይላል፡፡ ለብዙዎቹ ትደውልላቸዋለች፡፡ በሕይወት የሌሉትን ስታስታውስ እኔ እሸሻለሁ፤ፊቷ ሚጥሚጣ እስኪመስል ይቀላል፡፡
አሁን ግን የምታለቅሰው በስልክ ነው፡፡
“ፈረንጅ ሀገር ሆነሽም ፈረንጁን “እኔን ይድፋኝ"! ትያለሽ?" ስላት፣
አንዳንዴ - ትሥቃለች፡፡ አንዳንዴ “ፈረንጅ ሰው አይደለም?” ትለኛለች፡፡
“አይ መስኪ አሁን’ኮ የሠፈርሽንም ልጅ በዘር ትመርጫለሽ!” ስላት
“በኢየሱስ ስም” ትለኛለች፡፡
“ምን ትያለሽ!...ሰው ተጨካክኗል”
“የሀገሬን ጥፋትማ አያሳየኝ!”
“ከዘረኝነት በላይ ምን ጥፋት አለ?...የኔና ያንቺን አኗኗርና አስተዳደግ አስበሽ መለስ ስትዪ ያስቅሻል…የሰለሞን አባት ትግራይ፣ የትርንጐ አባት ሰላሌ፣ ያንቺ አባት ጐጃሜ፣ የእኔ ጉራጌ አልነበሩ? ግን ዘራቸውን ማን ያውቅ ነበር?”
“ኧረ በስመአብ ወልድ!”
“በቃ - ተበላሽቷል!”
“አይዞህ ፀልይ! ይመልሰዋል፤ ያስተካክለዋል"
ባወራን ቁጥር ስለ ድሮ ሰዎች፣ ስለ ሠፈራችን፣ ስለ ቀበሌያችን መተረኳን አትተውም፡፡ አዲስ አበባ ከመጣች በኋላ ያለውን ነገር ብዙ ትኩረት አትሰጠውም፡፡ ዞራ ወደ ልጅነቷ ነው፡፡ አዲስ አበባ የኖረችው ዘመድ ቤት ስለሆነ ብዙም ደስተኛ የነበረች አትመስለኝም፡፡ ያጐቷ ሚስት በሥራ ብዛት ያሰቃየቻት ይመስለኛል፡፡ አንዳንዴ ከአፏ ሲያመልጣት ታወራልኛለች፡፡
“እትዬ ሃይለኛ ነበረች፤ በጥፊ ታጮለኝ ነበር” ብላ ነግራኛለች፡፡ ፊቷ ላይ የበለዘውን ቆዳ አንስቼ ባልጠይቃት እሱንም አትነግረኝም ነበር፡፡
ሰሞኑን ስንደዋወል እንደበፊቱ ደስ የማይለኝ ለምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ ይቺ ገነት የምትባል የመሥሪያ ቤታችን ሴት ያስለመደችኝ ጨዋታ አናቴ ላይ ሳይወጣ አይቀርም፡፡
ገነት፤ ሮማን ከመሠሉ ጉንጮችዋ መካከል በጠባቡ ፍንድቅ ካሉት ለምለም ከንፈሮችዋ መሀል ልብ በሚሰርቅ ጨዋታዋ ሳታባብለኝ አልቀረችም፡፡ በዚያ ላይ የማታውቀው ነገር የለም፡፡ የፈረንጁን የሀበሻውን ፊልም፣ የሬዲዮ ፕሮግራሙን፣ የመጽሐፉን ታሪክ ስትፈተፍትልኝ ቀልቤ ሁሉ ተጠቅልሎ እሷን ማሰብ ጀምሯል፡፡ ቢሆንም የልጅነቴ ናት ብዬ ሁሌ እሷን ከማጫወት አልቦዝንም፡፡ ነገር ግን እንደ ገነት አትጥመኝም፤ እንደ ገነት አታስደንቀኝም፤ ብቻ በገርነቷና በንፁህ ልቧ መደነቄ አይቀርም፡፡
“ባሪች”
“አቤት”
“ጨዋታ እየቀነስክ ነው?”
“በፍፁም!”
“ተራርቆ ፍቅር ሰለቸህ መሠለኝ!...አይዞህ …አንድ ላይ የምንኖርበት ቀን ቅርብ ነው:: መጥቼ እንጋባና አብረን እንኖራለን፣ ብቻ ፀልይ!”
“እሺ”
“የርቀት ትምህርት፣ የርቀት ፍቅር" ስቃይ ስለሆነ ብዙም አልወደውም፡፡ ግን መስከረም ድንቅ ሰው ናት፡፡ ሆድ የሚያባባ፣ ስሜት የሚያሳሳ ነገር አላት፡፡ ወደ ፍቅር የገባነውም ሳናውቀው ነው፡፡ አዲስ አበባ፣ ጦር ሃይሎች አካባቢ፣ አንድ ቀን ከተገናኘን በኋላ በተደጋጋሚ መደዋወል ጀመርን፡፡ ዋቢ ሸበሌ ጋርደን ተቀምጠን ብዙ ማውራት፣ የልብን መካፈል ቀጠልን፡፡ በኋላ አሜሪካ ለመሄድ የተወሰኑ ጊዜያት ሲቀሩ ፍቅረኛሞች ሆንን፡፡ አሁንም ባገባት ደስ ይለኛል፡፡ ግን ፍቅረኛ ኖሮኝ ሲከፋኝ አግኝቻት ሃሳቤን ካላጋራኋት፣ ሆዴ ሲባባ እጄን ትከሻዋ ላይ ጣል አድርጌ ካልተጽናናሁ በስልክ ብቻ ማውራት ምን ይረባኛል? ልቤ ሁለት ሆኗል፡፡ የገነት አንደበትና ጥበብ!...የመስኪ ቅንነትና የዋህነት....አንዳንዴ ልብ በሁለት ይንጠለጠላል፡፡ አሜሪካ መሄድ እንኳን ያን ያህል አያጓጓኝም!
አንድ ቀን ገነት እኔና መስኪ የምንገናኝበት ዋቢ ሸበሌ ጋርደን ቀጠረችኝ፡፡ እየገረመኝ፣ ትዝታዬ ፊቴ ላይ እንደ ነበልባል እየነደደ ሄጄ ተቀመጥኩ፤ ድምጽዋ፣ ቀይ ፊቷ፣ ዐይኔ ላይ ድቅን አለ፡፡
ገነት ያ መከረኛ የሙዚቃ ትንታኔዋን፣ የፊልም ትረካዋን ከስማርት ፎንዋ ልትጐለጉል መጣች፡፡ ዐይኖችዋ ግን ያሠክራሉ! ዐይን እንኳ እኛ ቤት ብርቅ አይደለም፡፡ አባቴ፣ እህቴ፣ እኔም ተመሳሳይ ዐይኖች አሉን፡፡ የገኒ ግን ዐለም አብሯቸው የሚዞር ይመስላሉ፡፡
ወተት በቡናዋን አዘዘች፡፡
እኔ ሳነመታ ቆየሁና “ስፔሻል ሻይ!” አልኩ፡፡
በዚህ መሀል የገነት ስልክ ጮኸና "ሄለው! ሄለው!" አለች፡፡
ዐይኖችዋ ሣቅ የቋጠሩ ይመስላል፡፡
“ባሪች!” አለችና አቀበለችኝ፡፡
ስልኩን ተቀብዬ ሳናግር “ለኔ ትዝታ ነው ወይስ ለአዲስ ፍቅር?” ሰውነቴ ሁሉ በውሃ ተነከረ፡፡
ተነስቼ እንደ ወፈፌ ቁልቁል ወደ ልደታ ጉዞ ጀመርኩ፡፡
በምን ተዓምር መስኪና ገነት ተገናኙ?...ሰላይ ልካብኝ ነበር?...ሰው ማመን ቀብሮ ነው…ህልም እየመሰለኝ …ብቻዬን እያወራሁ…ወደ ሠፈሬ!


Read 2534 times