Sunday, 16 August 2020 00:00

የጥበብ ሰማይ ሊታረቅ ሲፈልግ ምልክቱን ያሳያል

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(4 votes)

 እስክሪብቶዬን ያነሳሁት በሁለት እጄ ነው፡፡ ላንስሎት በድንጋይ ውስጥ ተሽጦ የኖረውን ምትሃታዊ ሰይፍ በሁለት እጁ መዞ እንዳወጣው፡፡ እያካበድኩ ሳይሆን የእውነት ብዕር ማንሳት እየከበደኝ መጥቶ ነበር፡፡ ዲጂኖ እንደ ማንሳት ወይም ብቅል ለመውቀጥ ሙቀጫ እንደ ማንሳት ተራ ጉዳይ እየመሰለኝ አሰልችቶኝ ነበር፡፡ በብዕር አካፋ ፊደል እንደ ማፈስ ዝም ብሎ እጅ መላጥና እጅ ተልጦ የሚፃፈውም ነገር የአንባቢውን ጨጓራ ከመላጥ የማይዘል እየሆነብኝ ስለመጣ ብዕር መሰንዘር እየከበደኝ መጥቶ ነበር፡፡
ዛሬ ግን ግፊቱ ከእውነት የመነጨ ሳይሆን አይቀርም መሰለኝ፣ እንደ ምንም ሳነሳው እየቀለለኝ መጣ፡፡ ለነገሩ ምንም የምጨምረው ነገር የለም፡፡ “ትዝታሽን ለኔ፣ ትዝታዬን ላንቺ; ስለተባለው ድርሰት ለማለት የተነሳሁት ሁሉ ሳይባልም ቢተው ያን ያህል የሚለውጠው ነገር የለም፡፡ ውበትን ባታደንቀው ውበት መሆኑ አይካድም፡፡ የእሱባለው አበራ ንጉሴ መጽሐፍ ጥንቅቅ ያለ ውበት ነው፡፡ እውነት ባይኖረው ውበት አይሆንም፡፡ ተገርሜ ለመፃፍ ተነሳሁኝ፡፡
በመሰረቱ መጽሐፉን መጀመሪያ የገዛሁት በጥርጣሬ ነበር፡፡ ብዙ የተጮኸላቸው መጽሐፍት የጩኸቱ ገደል ማሚቶ ተምታቶ ሲጨርስ ዋጋ የተፃፈባቸው የሉክ ክምር ሆነው ሲቀሩ ነበር የታዘብኩት፡፡ የጥበብን የአካሄድ አቅጣጫ ፊትና ጀርባ መለየት ተስኖኝ፣ ህልውናዋ በጭብጨባ ውስጥ የሚፈጠርና የሚጠፋ ነው ብዬም ስቼ ነበር::
የውበት አማልዕክት  ለመታረቅ ፊቷን ስትመልስ ምልክቶች በማሳየት ነው:: “ትዝታሽን ለኔ፣ ትዝታዬን ላንቺ” አንድ ምልክት አድርጌ ወስጄዋለሁኝ፡፡ ውበት አሁንም እንዳለ የሚያሳይ ምልክት:: ትውልድ መክኖ እንዳልቀረ የሚያሳይ ምልክት፡፡
የተሟላ ውበት በመጽሐፍ ተመስላ በገበያ መሀል ስታልፍ በዝምታ ማድነቅ እንጂ በፉጨት መልከፍ አልፈልግም፡፡ ተደንቄ ከአይን ያውጣሽ እያልኩ መንገድ መልቀቅ ነው የምፈልገው፡፡ በቡዳ እንዳትበላ እንትፍ እያልኩ ነው የምሸኛት፡፡ መድረስ የሚቻልበት ከፍታ ላይ እንድትወጣ እመኛለሁ እንጂ አላስደነግጣትም፡፡
ግን መጀመሪያ መጽሐፉን ስገዛ በንቀት ነበር፡፡ “ትዝታሽን ለእኔ፣ ትዝታሽን ላንቺ” የሚለው መጠሪያ ራሱ የተቀላወጠ በመሆኑ ሌላ ፋሽን ተከታይ #ውበት ነኝ; ብላ ልትጨማለቅ የመጣች ነበር የመሰለኝ፡፡ ግን አገላብጬ ልተዋት ያልቻልኩት መታረቂያ ስለሆነኝ ነው፡፡ ጥበብ እንደ መብረቅ ብረት ስትወድቅ ብዙ ጊዜ ነጐድጓድ አሰምታ አይደለም፡፡ ዝም ብላ ነው የዘመንን ያረጀ ግድግዳ የምታፈርሰው ወይም መታደስ ያለበትን በአዲስ ትንፋሽ የምታድሰው፡፡
የሽፋን መሽቀርቀር የጥልቀት ማነስን የሚወክል ስለሚመስለኝ ለመቀበል ከብዶኝ ነበር፡፡ ዘመናዊ ዱርዬነት ነበር የመሰለኝ መሽቀርቀሩ፡፡ በፈረሰ ጭቃ ቤት ጠባብ መስኮት የቫንጐን ክዋክብታማ ሰማይ ለማየት መድፈሩ፡፡ የመጀመሪያዎቹ ገፆች ላይ ያሉት የትዝታ ቁርጥራጮች፣ እንደተቦዳደሰ ዘመናዊ ጂንስ የትውልድ ጭርንቁስ ጥፈትን የሚወክሉ መስሎኝ ነበር፡፡ ትንሽ የከረመ ፔሲሚዝም አለብኝ፡፡
በቫንጐ “Starry night” ተመስረኩዞ የመጣ ሌላ አጭበርባሪ ነበር የመሰለኝ፡፡ ምንም አዲስ ትርጉም ሲጠፋ፣ የምንምን ፍቺ ጥልቅ ለማስመሰል ከሚታሹት መሀል ነበር ይሄም መጽሐፍ መጀመሪያ የመሰለኝ፡፡ ትዝታ ቅንጭብጫቢ ስለሆነ፣ በቅንጭብጫቢ ድረታ ደረቴን ሊረግጠኝ መስሎኝ ነበር፡፡ ደግሞም፣ የመጀመሪያዎቹ አንቀፆች ላይ በነጠላ ሰረዝ አንድን ነገር ለመግለጽ የሚጨነቅባቸው ገፆች እውነትም ግልጽ አልነበሩም፡፡ ጭቶ እያከኩ አንድ ስፍራ ላይ ቆመው ወደፊት መራመድ አቅቷቸው ከሚብሰለሰሉት መሃል ግን አይደለም እሱባለው፡፡ እሱባለው እና እሱ እንዳለው የተፃፈው መጽሐፉ፡፡
ቀስ እያለ ነው ውበት የሚገለፀው፡፡ እንደ ኪዩቢዝም የተጣፉ የሚመስሉት ትዝታዎች በኋላ ላይ እየተሳሰሩ መምጣት ይጀምራሉ:: ልክ እንደ ተፈጥሮ፡፡ ልክ እንደ "Butterfly effect” የቀደመው የድርሰቱ ገፆች ላይ የአተበው ትዝታ ውጤቱ  በሂደት ነው የሚታወቀው፡፡ ነጣጥሎ ትዝታዎቹን ባያሳይ ለካ ሲገጣጠሙ ወጥ ምስል ባልፈጠሩ ነበር! እውነታ ከቁርጥራጭ “ከፒክስሎፕ” እንጂ ከወጥ ሽመና ተመዞ የሚዘረጋ አይደለም ለካ!
ሞተሩ የሚሞቀው ከመሀል ጀምሮ ነው፡፡ በተለይ “ዲ” እና ቤተሰቧ መገለጽ ሲጀምሩ:: ሁሉም በየአንፃራቸው ነው የሚገለፁት:: ከአንብሮ እና አስተጻምሮ ለእያንዳንዱ እውነታ በሌላ እውነታ ነፀብራቅ ሲታይ ነው ከአንድ አንጻር ውገናና ሀሜት ነፃ የሚወጣው፡፡ ተቃርኖው ነው ወደ አንድነት የሚያወጣው፡፡  ሁለቱንም አንፃር በሚመለከተው አንባቢ አይን፡፡ ድርሰቱ ከሁሉም ነገር የተውጣጣ ይመስላል:: አልፎ ካላለፈው የቅርብ አመታት የዞረ ድምር የተቀመረ ነው፡፡ ነባራዊ እና ሀገራዊ ተሞክሮ፡፡ መጽሐፉን አያይዤ ሳነብ ግን የተውጣጣውን ትዝታ ረስቼ በአእምሮዬ ላይ የሚቀረው ወጡ ድርሰት ነው፡፡ የድርሰቱ ሙዚቃዊ ስሜት እንደ “Collage” የተለጣጠፈው የትዝታ ክምችትም ተዋህዶ አንድ ምስል ይሆናል፡፡ ምስሉ ነው እንጂ ጥፈቶቹ ይረሳሉ፡፡ ማን ከማን እንደወረሰ ይዘነጋል፡፡ የቀድሞ ጥበብን የሚያስታውሱ የምዕራፍ መግቢያዎች፣ መውጫ ላይ የእሱባለው ድርሰት አካል ይሆናሉ፡፡
ከአዳም ረታ ካልተነሳን ወደ እሱባለው አበራ ንጉሴ መድረስ የሚቻል አልመሰለኝም ነበር፡፡ መጽሐፉን አንብቤ ስጨርስ ግን በማን አቅጣጫ ወደ ማን መሄድ እንደሚቻል የሚያሳየው “የተጽእኖ ፈጣሪ ማነው?” ጠቋሚ ቀስት፣ ሁለት ነጥቦችን የሚያገናኝ ቀጥተኛ መስመር፣ ክብ ብቻ እንደሆነ በማመን እንዳጠናቅቅ አስገድዶኛል፡፡
ከመጽሐፉ ቀንጭቤ መጥቀስ አልፈልግም፡፡ መርጦ መጥቀስ አዳልቶ መቀነስ ነው፡፡ የተቀነሰው ወይም የተጠቀሰው ብቻውን ምንም አይደለም:: ስለ መጽሐፉ በመሰረቱ ምንም ተጨማሪ ነገር ማለት አይቻልም፡፡ በቃ ተሟልቶ በፈጣሪና ተሞክሮ የተገኘ ልጅ እንደማለት:: ውበት ነው፤ እውነት ነው፡፡ ሰው የሆነ እና ቋንቋውን ማንበብ የሚችል ሁሉ የነፍሱን ጡዘት ቀንሶ፣ ቀልቡን ሰብስቦ ቢያነበው፣ እውነትም ውበትም እንደሆነ ይረዳዋል:: ውበትን ከፋፍሎ ማድነቅ አይቻልም፡፡ ስለ አፍንጫዋ ስታደንቅ ከሙሉነቷ ቀንሰህ በማሞካሸት ነው፡፡
እቺ መጽሐፍ ውበት ናት፡፡ ደራሲውን አላውቀውም፤ ላውቀውም አልፈልግም:: ውበት በማን በኩል መጣ የሚለው አይደለም ነጥቡ፡፡ ውበት እንደ መብረቅ እመሀከላችን ወድቋል፡፡ ጥሩ ሙዚቃ ስሰማ እንደማደርገው፣ የሰማሁትን በትዝታዬ ይዤ ዞር እላለሁኝ፡፡ ደጋግሜ በመስማት ላረክሰው አልፈልግም፡፡ ለአንባቢም የመጀመሪያ የንባብ ትዝታ ውድ ነው፡፡ ሳይሰለች እንዲቆይ የተገኘውን ይዞ ማለፍ ያስፈልጋል፡፡
“ትዝታሽን ለእኔ፣ ትዝታሽን ላንቺ” ምርጥ ሙዚቃ ነው፡፡ ፔንታቶኒክ መስሎ ዳያቶኒክ የሚሆን፡፡ በየትኛውም ቲዎሪ ብትመትረው ውበት መሆኑን አይለውጠውም፡፡ በሊበራሊዝም መነጽር ወይም ዶ/ር ዮናስ እንደተነተነው ብቻ ውበትነቱ የሚፀድቅ አሊያም የሚወድቅ አይደለም፡፡ እኔ ውበት መሆኑን መስክሬ ሌላው አስቀያሚ ነው ሊለው አይችልም፡፡ ኢንተርቴክስቹዋሊዝም” ብትለው ወይም ሌላ ጥያቄው #ተሳክቷል ወይስ ተሞክሯል?” የሚል ነው፡፡ ለእኔ ይሄኛው ሙዚቃ ተሳክቷል፡፡ ጢም ብሎ ከሞላ የብርሐን ጉድጓድ ውስጥ መጥለፍ በሚችል የደራሲ ነፍስ፣ በሻይ ማንኪያ ተቀንሶ የተሰጠን ነው፡፡ የጥበብ ሰማይ ሊታረቀን ሲል የሚያሳያቸው ምልክቶች አሉ፣ ብዬ አምናለሁኝ፡፡ እርቁ ሂደት ነው፡፡ ከማን ጀምሮ ምን አይነት የውበት ገፀበረከት ተከናውኖ እንደሚጠናቀቅ እኔ መገመት አልችልም፡፡
አንድን ትዝታ በብዙ ቃላት በመደረት፣ ቁም ስቅሉን አብልቶ ውበቱን እንዳይገለው ነበር ፍርሃቴ፡፡ ግን ደራሲው የሚጽፈው እንደ ግጥም ነው፡፡ ብዙውን ጥሎ ነው መሰረታዊውን ብቻ የሚያነሳው፡፡ የሚጽፈው እንደ ግጥም ነው፡፡ የሆነ ሙዚቃ ሁሌ አረፍተ ነገሮቹን ይዳበላቸዋል፡፡ ዘመናዊ ምት ያለው ግን እንደ ጥንቱ የሰውን መልካም ጐን ለማሳየት የሚጥር ሙዚቃ፡፡ በሳር ክምር ውስጥ መርፌን በመፈለግ ቃላት በዱላ ሲወቃ አይውልም፡፡ በዘለለው መጠን እንዲያውም ወደፊት የበለጠ ይራመዳል:: አይኑን ዘግቶ የእንጀራ አይን በሚሊዮን የቃላት ቀዳዳ ቢከፍት ለኔ ምን ያደርግልኛል:: ማጠሩ ተመችቶኛል፡፡ ሙዚቃን ከእውነታ መለየት የምፈልግ ነኝ፡፡ በሙዚቃ ውስጥ እውነታን መኖር አልሻም፡፡ ግጥምን አንብቤ ማስታወስ እንጂ፣ በግጥሙ ውስጥ እውነታን መርሳት አልፈልግም፡፡
“እስከ አለም ዳርቻ” እከተልሻለሁ የሚል ግጥም አነባለሁ እንጂ፣ ግጥሙን እድሜ ልኬን ሳነብ መኖር አልፈልግም፤ ወይም በተጨባጭ የወደድኳትን ሴት እስከ አለም ዳርቻ ስከተል መኖር፡፡ በ154 ገጽ ማለቁ ተገቢ ነው፡፡ አንዴም ሳያሰለቸኝ ነው ያለቀው፡፡
የቫንጐን starry night በሁለት ጽንፍ የሚረዱ ሃሳባዊያን አሉ፡፡ አንዳንዶች አስተማማኝነት የሌለው፣ እንደ አዙሪት እይታን የሚያጥወለውል እይታ ነው ይላሉ:: ሌሎች ደግሞ በጨለማ የተዜመ፣ ልብን የሚያሳዝን ግን መንፈስን የሚያክም ውበት ነው ይላሉ፡፡ አሉም አላሉም ነጥቡ ወዲህ ነው፡፡ ውበት ያከራክር ይሆናል እንጂ መካድ አይቻልም፡፡      
እሱባለው አበራ አንድ ውብ መጽሐፍ ሰርቷል፡፡ የአፃፃፍ ቴክኒኩን ለመበየን የተለያዩ ሃያሲያን ወይም ርዕዮተ አለማዊ ንድፈ ሃሳቦች ሊሰለፉ ይችላሉ:: በመጽሐፍ የጀርባ ገጽ ላይ ዶ/ር ዮናስ ጥሩነህ ያቀረበው የድህረ ዘመናዊ ትንታኔ አንዱ የማስረጃ መንገድ ነው፡፡ አንባቢው የተመለከተውን ለመረዳት የጽንሰ ሀሳብ መነጽር ሊያስፈልገው ይችል ይሆናል:: ውበት መሆኑን ለማወቅና ለመደነቅ ግን ሰው መሆን ነው የሚያስፈልገው፡፡ የአማርኛ ሆሄያት የቆጠረ ሰው፡፡ ይሄንን ነው ለጊዜው ማለት የምችለው፡፡ ባልልም የሚፈጠር ነገር የለም፡፡ ድርሰቱ እንደሆነ ተፈጥሯል፡፡
ጠቢባኑ ተስማሙም አልተስማሙም፣ የሆነ ነገር ብልጭ ብሏል፡፡ ከብልጭታው ውስጥ የመብረቅ ብረት መፈለግ ወይም አደገኛ ሞገድ ነው ብሎ በሽቦ ወደ መሬት ማሳ አድርገው መቅበር የእነሱ ምርጫ ነው:: ማክበርም መድፈርም ይችላሉ፡፡
አፈጣጠሯ የሚገርም አንድ ለየት ያለች ውበት ግን ከየት እንደመጣች፣ በምን ግፊት እንደመጣች ሳትታወቅ በአደባባይ እያለፈች ነው፡፡ እንደ ዶሮ እንቁላል፣ በተፈጥሮ ችሮታ ድንገት  የተጣለች ሳይሆን፣ ተሰጥኦና ማስተዋል ታክሎባት የተገኘች መሆኑን ሳስብ፣ በአክብሮት አንገቴን ዝቅ አደርጋለሁ:: መጽሐፉን ማንበብ ለሚፈልግ አሳልፌ እሰጣትና እኔ ግን በልቦናዬ አስቀምጣታለሁ፡፡  

Read 2034 times