Saturday, 21 July 2012 10:46

ዲኬቲ በየወሩ ሁለት ሚሊዮን ኮንዶሞች ያሰራጫል

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

ዲኬቲ ኢትዮጵያ፤ አዲስ አበባን ጨምሮ በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በሚገኙ 150 ከተሞች ውስጥ ባሉት 185 ክበባት አማካይነት በኮንዶም ስርጭቱ ላይ በስፋት እየሠራ እንደሚገኝና በአሁኑ ወቅትም ወርሃዊ የኮንዶም ሽያጩ ሁለት ሚሊዮን መድረሱን አስታወቀ፡፡

ድርጅቱ ከ500 በላይ ለሚሆኑ የኮሚሽን ሽያጭ ሠራተኞች በቢሾፍቱ ከተማ ባዘጋጀው የአቅም ግንባታ ሥልጠና መክፈቻ ፕሮግራም ላይ የዲኬቲ ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ሚስተር አንድሪው ቢፒለር እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ በሽያጭ ሰራተኞቹ በመጠቀም የኮንዶም ስርጭቱን በማስፋፋት በገጠራማው የአገሪቱ ክልሎች ሣይቀር ኮንዶም እንደልብ እንዲገኝ እየሰራ ይገኛል፡፡

ህብረተሰቡ ኮንደምን በቀላሉና በቅርብ የሚያገኝበትን ሁኔታ ማመቻቸት ዋንኛ ተግባራቸው እንደሆነ የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ ለዚህ ዓላማ ተግባራዊነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ለሚገኙት የኮሚሽን የሽያጭ ሠራተኞች በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በስራቸው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡትንና ለድርጅቱ ከፍተኛ እገዛ በማድረግ ላይ ከሚገኙት የሽያጭ ሠራተኞች ውስጥ የተወሰኑት ተመርጠው ታይላንድ የሚገኘውን የኮንዶም ፋብሪካ ለማስጐብኘት እቅድ እንደተያዘ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሽያጭ ሥራ ላይ የተሰማሩት በሙሉ ገቢያቸውን ማሳደግ እንዲችሉ ድርጅቱ እየሠራ መሆኑንም አክለው ገልፀዋል፡፡

ዲኬቲ ኢትዮጵያ በወጣት የኮሚሽን የሽያጭ ሠራተኞች ኮንዶም የማከፋፈል ሥራውን ከጀመረ እ.ኤ.አ ከግንቦት 2007 ዓ.ም ጀምሮ ከ81 ሚሊዮን በላይ ኮንደሞች መሸጡን የተናገሩት የአገር ውስጥ ሽያጭ አስተባባሪው አቶ ፋሲል ጉተማ፤ ከዚህ ሽያጭም የኮሚሽን ሠራተኞቹ ከ5.1 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማግኘታቸውንና ይህም በርካታ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የቻለ ፕሮግራም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በድርጅቱ ለስምንት አመታት በሽያጭ ሠራተኛነት መሥራቱን የገለፀው አስፋቸው በሪሁን፤ አንዱን ፓኬት ሰንሴሽን ኮንዶም ከድርጅቱ በ55ብር ተረክበው በ72ብር፣ ህይወት ትረስት ኮንዶምን ደግሞ በ22 ብር ተረክበው በ30 ብር እየሸጡ የሚገኘውን ትርፍ በድርጅታቸው አማካይነት 75% ለእነሱ፣ 25% ደግሞ ለድርጅታቸው ማጠናከሪያ እንደሚያውሉት ተናግሯል፡፡ ከስምንት ዓመታት የኮሚሽን የሽያጭ ሠራተኛነት በኋላ ድርጅቱ ዘንድሮ በቋሚ ተቀጣሪነት ከወሰዳቸው 16 ወጣቶች መካከል አንዱ የመሆን እድል ማግኘቱንም ተናግሯል፡፡ በኮንዶም ሽያጭ ወቅት የተለያዩ ችግሮች እንደሚያጋጥማቸው የገለፀችውና ከአሰበ ተፈሪ እንደመጣች የተናገረችው ወጣት የሽያጭ ሠራተኛ ቅድስት ፀጋዬ፤ የኮንዶም ሽያጭ እንደጊዜውና እንደ ሁኔታው የሚቀያየር መሆኑን ጠቅሳ፤ በፆም ወቅት ሽያጩ እንደሚያሽቆለቁልና በበዓላትና በፆም ፍቺዎች ወቅት ግን ሽያጩ በከፍተኛ መጠን እንደሚጨምር ተናግራለች፡፡ በኮሚሽን የሽያጭ ሠራተኛነቷም በወር ከ1ሺህ እስከ 1500 ብር የሚደርስ ገቢ እንደምታገኝ ቅድስት ተናግራለች፡፡

 

 

Read 4029 times Last modified on Saturday, 21 July 2012 11:01