Saturday, 29 August 2020 10:48

ነገሩ አልሆን ብሎ ሁኔታው ሲጠጥር ጠጣሩ እንዲላላ የላላውን ወጥር ገጣሚ ሐይሉ ገ/ ዮሐንስ

Written by 
Rate this item
(10 votes)

      ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጨዋታ አዋቂ ሰው፣ ማእከላዊ ምርመራ ድርጅት እስር ቤት ይታሰራሉ። በእስረኞቹ ዘንድ የተለመደ የሻማ በመባል የሚታወቅ  አንድ ደንብ አለ፡፡ አዲስ የገባ እስረኛ ያለውን ገንዘብ ይሰጣል፤ የሚያውቀውን ቀልድ ያቀርባል፡፡ እኝህ ሽማግሌም ይሄንኑ ተጠየቁ፡፡ እሳቸው ጨዋታ አዋቂ ናችውና የሚሰጡት ቤተሰብ  ወይ ጓደኛ  ካመጣላቸው ገንዘብ መሆኑን ገልጠው፤ "ለጨዋታው ግን አንዴ ደብረማርቆስ ውስጥ የሆነውን ላጫውታችሁ"፤ ብለው ጀመሩ፡፡  
"ቅዳሜ ምሽት ሁለት ሴቶች ደጅ ውሃ ይወጡና ይመለሳሉ፡፡
አንደኛዋ፡- "በይ እንግዲህ ነገ እሁድ ጠዋት ቤተ ስኪያን እንገናኝ፤ አንቺ ከቀደምሽ አንቺ፣ እኔ ከቀደምኩ እኔ እዚያች ዘወትር  የምንቆምባት የሴቶች መቆምያ ጥግ ቆመን እናስቀድሳለን አደራ" ትላታለች፡፡ ሁለተኛዋም ጨመት ባለ ንግግር፤ "እስኪ እንግዲህ ወንዶቹ እንዴት እንዳሳደሩን አይተን ነዋ" አለች አሉ፡፡ ሽማግሌውም ቀጠሉና፤ "እንግዲህ እኛም እነዚህ አሳሪዎቻችን አንዴት አንዳሳደሩን እንይና የደነገጠ ዘመድም ሆነ ጓደኛ ነገ ከነገ ወዲያ ሲመጣልን፣ የሰጡኝን እሰጣችኋለሁ፤ ወፍራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል እንደሚባለው፣ እንዲሁ ስታዩኝ ወፍራምና ደልዳላ በመሆኔ ያለኝ መስያችሁ ነው እንጂ አሁን ገንዘብ አልያዝኩም" አሉ፡፡
እስረኞቹም፤ "ለመሆኑ በምን ታሰሩ አባባ?" ሲሉ ጠየቁዋቸው፡፡
 አዛውንቱም፤ "አንድ አለቃዬ ከመንግስት መስሪያ ቤታችን ገንዘብ ዘርፎ ጠፋ፤ አንተም ተመሳጥረህ አስጠፍተኸው ይሆናል፤ሚስጥረኛው ልትሆን ትችላለህ ብለው አሰሩኝ እንጂ እስረኛ አይደለሁም"
"ታዲያ ምንድን ነዎት? ምንድን ነኝ ይላሉ?" አሉና እስረኞቹ ቢጠይቁዋቸው፣ ሽማግሌውም "እንዲያው ቀብድ ነኝ፤ እኔ ቀብድ ነኝ፤ እስረኛ አይደለሁም" አሉ ይባላል፡፡
*   *  *
እንግዲህ አያሌ  የመከራ ዘመን  ታልፏል፡፡ በሰው እጅ ያለ ሰው አበሳው ብዙ ነው፡፡ በራሱ አያዝም፡፡ አስተማማኝ የሆነ የራሱ ሕይወትም የለውም፡፡ ጥፋቱም ሆነ ልማቱ በሌሎች ፍቃደ ልቦና ላይ የተንተራሰ ነው፡፡ የሕዝብም ዕጣ ፈንታ ደግ  መንግስትንና ክፉ መንግስትን የተንተራሰ ነው፡፡ የመንግስትን ፍቃደ ልቦና ይፈልጋል፡፡ አንድ በሕዝብ የተመረጠ መንግስት ሃላፊነት፣ የዚህን እውነታ መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ይህ አሌ የማይባል ሃቅ፣ በየዘመኑ አጋጥሞናል፤በሕዝብ ያልተመረጠ መንግስት ደግሞ በየጊዜው ጥርጣሬ የማየለየው፣ እምቢታና ለህዝብ አልታዘዝም ባይነት ነው ምሱ፡፡ ከትንኮሳ ከአሻጥር፣ ከተንኮል፣ ከሴራ፣ ከቅልበሳ፣ ከሽረባ፣ በጅምላ  መልኩ ከማያባራ አመጻ የማይለይ መንግስት ይሆናል አንደማለት ነው።  
ሌት ተቀን መልካም አስተዳደርንና ዲሞክራሲን አስተሳስረን መጓዝ፣ ለህዝባዊ ደህንነትና ለሃገር እድገት በብቃት መስራትን ይከስታል፡፡ በዚህ ላይ የጎረቤቶቻችንን አያያዝ በቅጡ ካወቅንበት፣ ከአነጋገር ይፈረዳል  ከአያያዝ ይቀደዳል የሚለውን ብሂል፣ እዳር አደረስነው ማለት ነው፡፡  እስከ ዛሬ ከንግግር ያላለፉ፣ የመጣ መንግስት ሁሉ አበክሮና ደጋግሞ አሸብርቆ የሚያወሳቸው፣ በወርቅ አልጋና በእርግብ ላባ የሚያስተኙን የሚመስሉ አያሌ ውብ ምኞቶች፣ ዕቅዶችና ሕልሞች አሉን፤ሆኖም ጉዳዩ የተግባራዊነት ጥያቄ ይሆንና በአብዛኛው መሬት የረገጠና ወሃ የቋጠረ  ፍሬ ነገር ሆኖ አናየውም፡፡ ረዥምና መራራ፣ ትእግስትን ፈታኝ የሆነን ለውጥ ማምጣት የሚቻለው አዎንታዊ ኃይልን እንዲያይል በማድረግና አሉታዊ ኃይል እንዲቀንስ በማድረግ ነው፡፡ ረብ ያለው ለውጥንና እድገትን ለመጎናፀፍ፣ የወጣቶችን ትጋት ማዳበር፣ የሴቶችን ተሳትፎ በስፋት ማበረታት፤ ተገቢውን ሰው በተገቢው ቦታ ላይ መመደብ፤ የሙያተኝነት ከበብ እንዲሉ፡፡  ክህሎትን መቀዳጀትንና ማቀዳጀት ዋናው ጉዳዮች ናቸው፡፡ ድህነትን ለመዋጋት ዋናው መሳርያ ከሚሆኑን ዕሴቶች አንዱ፤ ለሙያተኝነት ጥርጊያ ማመቻቸትና የሰው ኃይል አጠቃቀምን ስራዬ ብሎ ትኩረት መቸር ነው፡፡ ከመላላት ወደ መጠንከር በመጓዝ ነው ዕድገት ሊመጣ የሚችለው፡፡ በዲፕሎማሲ የታጀበ ዲሞክራሲ በማለምለምም ነው ዕድገት ሊመጣ የሚችለው፡፡
ገጣሚ ሐይሉ ገ/ ዮሐንስ፡-
"ነገሩ አልሆን ብሎ ሁኔታው ሲጠጥር
 ጠጣሩ እንዲላላ  የላላውን ወጥር " -- እንዲሉ፡፡

Read 15586 times