Saturday, 29 August 2020 10:54

በ5ሺ ሜትር

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 • የቀነኒሳ የዓለም ሪከርድ ከ16 ዓመታት በኋላ በ2 ሰከንዶች ተሻሽሏል፡፡
          • የናይክ ዘመናዊ የመሮጫ ጫማና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች እያወዛገቡ ናቸው፡፡
          • ‹‹በሩጫ ህይወቴ ቀነኒሳ የምንግዜም ምርጥ ተምሳሌቴ ነው፡፡ ›› ጆሽዋ ቼፕቴጊ
          • ‹‹የዓለምን ሪከርድ ማስመዝገብ ቀላል አይደለም ፤ ቼፕቴጊ እንኳን ደስ ያለህ ›› ቀነኒሳ በቀለ
          • የጥሩነሽ ሪከርድ ሳይሰበር 13 ዓመታት ሆኖታል


            ከሁለት ሳምንት በፊት በፈረንሳይ ሞናኮ ውስጥ በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በ5ሺ ሜትር ትራክ ላይ አዲስ የዓለም ሪከርድ መመዝገቡ ይታወቃል፡፡ የ23 ዓመቱ  ኡጋንዳዊ አትሌት ጆሽዋ ቼፕቴጊ የዓለም ሪከርዱን ያስመዘገበው በ12 ደቂቃ ከ35.36 ሰከንዶች ሲሆን በኢትዮጵያዊው ቀነኒሳ ለ16 ዓመታት (በ12 ደቂቃ ከ37.35 ሰከንዶች) ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን በ2 ሰከንዶች አሻሽሎታል፡፡
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የዓለምን አትሌቲክስ በከፍተኛ ደረጃ ባናጋበት የውድድር ዘመን ላይ ኡጋንዳዊው አትሌት የዓለምን ሪከርድ ለማስመዝገብ መብቃቱ በከፍተኛ ደረጃ ተደንቋል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ሮከርዱን እስኪያፀድቀው ግን በውድድር ላይ የሮጠበት የናይክ ዘመናዊ የመሮጫ ጫማ፤ የተመደቡት አሯሯጮች አሰራር እና ተጨማሪ የኤሌክትሮኒክ ድጋፎች ሲያወዛግቡ ይቆያሉ፡፡ በብዙዎቹ ውይይቶች ላይ ጆሽዋ ጄፕቴጊ ከ16 ዓመታት በኋላ የቀነኒሳን ክብረወሰን ለመስበር የቻለው በከፍተኛ ምርምር የተሰራው የናይኪ መሮጫ ጫማ እና የሪከርድን ሂደት የሚያቀላጥፍ ቴክኖሎጂን በመጠቀሙ ነው ተብሏል፡፡ ጆሽዋ ጄፕቴጊ ሞናኮ ከተማ ላይ የዓለም ሪከርዱን ካስመዘገበ በኋላ  በሰጠው አስተያየት ‹‹ የዓለም ሪከርድ ማስመዝገብ ከኦሎምፒክና ከዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያ ክብር ጋር የሚመጣጠን ነው፡፡ ስለዚህም በውጤቴ ተደስቻለሁ:: በሩጫ ህይወቴ ቀነኒሳ የምንግዜም ምርጥ ተምሳሌት ነው፡፡ ከእሱ የሩጫ ዘመን ብዙ ትምህርቶችን አግኝቻለሁ፡፡›› ብሎ ተናግሯል፡፡  ኢትዮጵያዊው ቀነኒሳ በበኩሉ በኢንስታግራም ገፁ ባሰፈረው መልዕክት በሄንግሎ ያስመዘገበውን የዓለም ሪከርድ መቼም እንደማይረሳው ገልፆ፤ በምንም አይነት ሁኔታ የዓለም ሪከርድን ማስመዝገብ ቀላል እንደማይሆን በመጥቀስ በኒውዮርክ ራኒንግ ቲም እና በግሎባል ኮምኒኬሽን ስር አብሮት የሚወዳደረውን ጆሽዋ ጄፕቴጊ ‹‹የቡድን አጋሬ እንኳን ደስ ያለህ›› ብሎታል፡፡
በታዋቂዎቹ የአትሌቲክስ ዘጋቢ ድረገፆች ራነርስዎርልድ፤ ሌትስራን እና ሌሎችም ሚዲያዎች ላይ በቼፕቴጊ የዓለም ሪከርድ ዙርያ ውዝግቦች ተፈጥረዋል፡፡ በሞናኮው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ላይ በኮቪድ 19 ሳቢያ በተፈጠሩ የጉዞ መጉላላቶች ምርጥ አትሌቶች አለመሳተፋቸውን የጠቀሱ ትችቶች አሉ፡፡ በተለይ ግን በ5ሺ ሜትር ውድድሩ ላይ በዘመናዊ አሯሯጭነት የተመደቡት ሶስት ፕሮፌሽናል አትሌቶች፤ በመሮጫው ትራክ ላይ የሪከርድ ፍጥነትን የሚያመለክተው የወቭላይት ቴክኖሎጂ እንዲሁም የመሮጫ ታኬታ የሆነው Nike ZOOMX Dragonfly ላይ የዓለም ሪከርድን ለመስበር ልዩ እገዛ አድርገዋል የሚሉ ነቀፋዎች በብዛት ተሰራጭተዋል፡፡ የቀነኒሳን የዓለም ሪከርድ በሁለት ሰከንዶች ያሻሻለው ኡጋንዳዊ ቼፕቴጊ ለቀረቡት ትችቶች ምላሾችን ሰጥቷል፡፡ ‹‹ባስመዘገብኩት ሪከርድ ከእነ ቀነኒሳ፤ ኃይሌና ኪፕቾጌ ተርታ መሰለፌ አስደስቶኛል፡፡ በውድድሩ ላይ የቴክኖሎጂ ድጋፍ ምንም ልዩነት የሚፈጥር አልነበረም:: ወደ ሪከርድ የሚመራውን የዌቭላይት ቴክኖሎጂ ውድድሩ ከተጋመሰ በኋላ ዞር ብዬ አላየሁትም፤ የመሮጫ ጫማውም ሊያወዛግብ አይገባም፡፡ አሁን ያለንበት ግዜ 2020  ነው፡፡ 1970ዎቹ፣ 1980ዎቹ ወይንም 1970ዎቹ ላይ አይደለንም፡፡ ስፖርቱ ደግሞ በየጊዜው እድገት እያስመዘገበ ይቀጥላል:: እነኃይሌ፤ እነቀነኒሳ በሩጫ ዘመናቸው ከእነሱ በፊት ከነበሩት ታላላቅ ሯጮች በቴክኖሎጂ ተሻሽለው የተሰሩላቸውን ጫማ ተጠቅመዋል፡፡ እኔ ያረግኩትን የናይክ መሮጫ ምን ልዩ የሚያደርገው ሁኔታ የለም፡፡›› በሚል ሰፊ ማብራርያ ሰጥቷል፡፡ ከ16 ዓመታት በፊት በሆላንድ ሄንግሎ በተካሄደው የ5ሺ ሜትር ሩጫ ላይ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የዓለምን ሪከርድ ሲያስመዘግብ በተመሳሳይ በወቅቱ ቴክኖሎጂ የተመረተውን የNike ZOOMX የመሮጫ ጫማ ተጠቅሞ ነበር፡፡ በወቅቱ የዓለም ሪከርድ እንዲያስመዘግብ የነበረው ልዩ ብቃት እና ምቹ አየር ንብረት አስተዋፅኦ እንደነበራቸው ተወስቷል፡፡
ኡጋንዳዊው አትሌት ጆሽዋ ጄፕቴጊ በ2019 እና በ2020 የውድድር ዘመናት ባስመዘገባቸው ውጤቶች በረጅም ርቀት ሩጫ ታሪክ ውስጥ እንዲጠቀስ አድርጎታል፡፡ ባለፉት 4 የውድድር ዘመናት በአገር አቋራጭ፤ የጎዳና ላይ ሩጫ እና ትራክ ውድድሮች በወርቅ ሜዳልያዎች እና በምርጥ የሪከርድ ሰዓቶች ብቃቱን አስመስክሯል፡፡ ከአዲሱ የ5ሺ ሜትር ትራክ የዓለም ሪከርዱ በፊት በ5ኪሜ፤ በ10 ኪሜና በ15 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫዎች በፊት ሌሎች 3 የዓለም ሪከርዶችን አስመዝግቧል:: በ10ሺ ሜትር የወቅቱ የዓለም ሻምፒዮን ሲሆን፤ በዓለም አገር አቋራጭ በሁለቱም የአዋቂ ውድድሮች ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን ተጎናፅፏል፡፡  በስነፅሁፍ የባችለር ዲግሪ ያለው ኡጋንዳዊው ጆሽዋ ቼፕቴጊ  በሚቀጥሉት 4 የውድድር ዘመናት በ10ሺ ሜትር እና በ5ሺ ሜትር የትራክ ውድድሮች ላይ በትልልቅ ውድድሮች ተጨማሪ የሜዳልያ ሽልማቶችንና ፈጣን ሰዓቶችን  ማስመዝገብ እንደሚፈልግ ሲናገር፤ በ5ሺ ሜትር ከ12 ደቂቃ 30 ሰከንዶች በታች በ10ሺ ሜትር ደግሞ ከ26 ደቂቃዎች በታች መግባት እንደሚቻልም ገልጿል፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ላይ በ5ሺ ሜትር የትራክ ውድድር በሁለቱም ፆታዎች የዓለም ሪከርዶች ሊሻሻሉ እንደሚችል ባለሙያዎች እየተናገሩ ሲሆን በ2021 እኤአ ላይ ቶኪዮ በምታስተናግደው ኦሎምፒያድ ላይ አስደናቂ ውድድሮች እንደሚጠበቅ ተስፋ አድርገዋል::  በ5ሺ ሜትር ወንዶች የውድድር ዘመኑን የደረጃ ሰንጠረዥ የሚመራው ኢትዮጵያዊው ሰለሞን ባረጋ ሲሆን ከአንድ እስከ 10 ባለው ደረጃ ከእሱ ጋር አራት የኢትዮጵያ አትሌቶች ተመዝግበዋል፡፡ የኡጋንዳ፤ የአሜሪካና የእንግሊዝ አትሌቶችም በፈጣን ሯጭነታቸው፡፡ በሴቶች ውጤታማዎቹ አትሌቶች ከኬንያ እና ከኢትዮጵያ የሚገኙ ቢሆንም ታንዛኒያ፤ ኡጋንዳ፤ አልጄርያና ሞሮኮም ምርጥ አትሌቶችን አፍርተዋል፡፡ የእንግሊዝ፤ ጀርመንና፤ ሆላንድ አትሌቶችም ከአንድ እስከ 10 ባለው ደረጃ ገብተዋል፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ማህበር የውድድር ዘመኑ የውጤት ደረጃ ላይ 5 ኬንያውያን ሲገኙ ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ፋንቱ ወርቁ እና ለተሰንበት ግደይ ናቸው፡፡
የዓለም ሪከርድን በማሻሻል ሂደት ላይና በመጨረሻዎቹ የሪከርድ ወሰኖች
በ5ሺ ሜትር የትራክ ውድድሮች  በሁለቱም ፆታዎች በተመዘገቡት የዓለም ሪከርዶች ላይ ኢትዮጵያውያን አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ የቀነኒሳ በቀለ የዓለም ሪከርድ ከሳምንት በፊት በኡጋንዳዊው አትሌት ጆሽዋ ቼፕቴጊ ከመሻሻሉ በፊት ላለፉት 16 ዓመታት የተቀናቀነው አልነበረም፡፡ በብዙዎቹ  የ5ሺ ሜትር ፈጣን ውድድሮች ላይ የቀነኒሳን ክብረወሰን ላይ ለመቅረብ የተቻለው አምስት ሰከንዶች እስኪቀሩ ነው፡፡ በትራክ ሩጫ ላይ ደግሞ እያንዳንዷ ሰከንድ ዋጋዋ የሰዓታት ይሆናል፡፡
የጆሽዋ ቼፕቴጊ አዲስ የዓለም ሪከርድ የተመዘገበው ሁለት ሰከንዶች በማሻሻል ሲሆን በወንዶች 5ሺ ሜትር  ከ1884 እኤአ ጀምሮ የተመዘገቡት ሪከርዶች 38 ደርሰዋል:: በሪከርድ የማሻሻል ሂደቱ ላይ ከጅምሩ የእንግሊዝ፤ የፊንላንድ አትሌቶች ዱካቸውን አሳርፈዋል፡፡ በተለይ ባለፉት 30 ዓመታት ግን የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ከፍተኛውን ድርሻ ወስደዋል፡፡ የዓለም ሪከርዱ ለ6 ጊዜያት በኬንያውያን ሲሻሻል 5 ጊዜያት  ደግሞ ኢትዮጵያውያን አስመዝግበውታል፡፡ ኡጋንዳዊ አትሌት በሪካርዱ የማሻሻል ሂደት  ታሪክ ያስመዘገበው ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡  
በ5ሺ ሜትር ለመጀመርያ ግዜ የዓለምን ሪከርድ ለማስመዝገብ የበቃው ኢትዮጵያዊ ኃይሌ ገብረስላሴ ሲሆን ከ1994 እስከ 1998 እኤአ ድረስ ለአራት ጊዜያት ሪከርዶቹን በማሻሻል ከፍተኛውን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ በተለይ በ1994 እኤአ ላይ ኃይሌ ገብረስላሴ በሆላንድ ሄንግሎ በተካሄደ ሩጫ በ12 ደቂቃ ከ56.96 ሰኮንዶች በ5ሺ ሜትር የመጀመርያውን የዓለም ሪከርድ ሲያስመዘግብ በሞሮካዊው ሳይድ አውይታ ለ6 ዓመታት ተይዞ የቆየውን ሰዓት በመስበር ነው፡፡
በ2004 እኤአ ላይ በሆላንድ ሄንግሎ ቀነኒሳ በቀለ በ12 ደቂቃ ከ37.35 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ያስመዘገበው ሪከርድ የሚታወሰው አትሌቱ ክብረወሰኑን ለማስመዝገብ ባደረገው ልዩ አሯሯጭ ነው፡፡ ይሄው የቀነኒሳ ምርጥ ሰዓት  ላለፉት 16 ዓመታት ሳይሰበር በመቆየት በትራክ የሩጫ ውድድሮች ታሪክ ልዩ ተጠቃሽ ይሆናል፡፡
ታዋቂው ራንኒንግ ዎርልድ ባንድ ወቅት በሰራው ጥናታዊ ዘገባ መሰረት በሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ብቃት በ5ሺ ሜትር ሊመዘገብ የሚችለው ሪከርድ በሚቀጥሉት የውድድር ዘመናት የመሻሻል እድል ይኖረዋል፡፡ በወንዶች ምድብ  የዓለም ሪከርድ ከ10 ዓመታት በኋላ 12 ደቂቃ ከ09.39 እንዲሁም ከ20 ዓመታት በኋላ ደግሞ 11 ደቂቃ ከ56.19  ሰኮንዶች ሊሆን እንደሚችል በጥናት ተገምቷል፡፡ በጥናቱ በ5ሺ ሜትር ወንዶች የመጨረሻው የሪከርድ ወሰን  የተባለው ደግሞ 11 ደቂቃ ከ11.61 ሰከንዶች ነው፡፡
በሴቶች 5ሺ ሜትር የትራክ ውድድር ላይ የተመዘገበው የዓለም ሪከርድ  በኢትዮጵያዊቷ  ጥሩነሽ ዲባባ ከተያዘ 13 ዓመታት ተቆጥረዋል:: ከ1922 እኤእ ጀምሮ 27 የዓለም ሪከርዶች በሴቶች 5ሺ ሜትር ላይ ተመዝገበዋል፡፡ ከ2004 እኤአ ጀምሮ የተመዘገቡትን አራት አዳዲስ ሪከርዶች ደግሞ  ኢትዮጵያዊያን  አሳክተዋቸዋል፡፡ በ2004 እኤአ ላይ በትራክ 5ሺ ሜትር ውድድር የዓለምን ሪከርድ 14 ደቂቃ ከ24.68 ሰኮንዶች ያስመዘገበችው በትውልድ ኢትዮጵያዊ ብትሆንም በዜግነት ለቱርክ የምትሮጠው ኢልቫን አብይ ለገሰ ነበረች፡፡ ከኢልቫን አብይ ለገሰን በኋላ የዓለም ሪከርድን በ2006 እና በ2007 እኤአ በማከታተል የሰበረችው፤ ኢትዮጵያዊቷ መሰረት ደፋር ናት፡፡ ከመሰረት በኋላ ላለፉት 13 ዓመታት ሳይሰበር የቆየውን የዓለም ሪከርድ በ2007 እኤአ በኖርዌይ ኦስሎ ያስመዘገበችው ጥሩነሽ ዲባባ ናት፡፡ 14 ደቂቃ ከ11.15 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ፡፡
 በራንኒንግ ዎርልድ ጥናታዊ ዘገባ መሰረት በሰው ልጅ ብቃት በ5ሺ ሜትር በሴቶች ሊመዘገብ የሚችለው ሪከርድ  ከ10 ዓመታት በኋላ 13 ደቂቃ ከ41.56 ሰከንዶች ከ20 ዓመታት በኋላ ደግሞ 13 ደቂቃ ከ37.25 ሰኮንዶች ሊሆን ይችላል፡፡  12 ደቂቃ ከ33.36 ሰከንዶች ደግሞ የመጨረሻው የሪከርድ ወሰን ነው፡፡Read 1209 times