Saturday, 21 July 2012 11:34

በማለዳ የጠለቀው የሥነግጥማችን ብርሃን - ብርሃኑ ገበየሁ

Written by  ዳዊት ፀሐይ
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያ ስለ ሥነግጥሟ የሚቆረቆርላትና የሚጮህላትን፤ ከዕድሜው አብላጫውን ጊዜ ለሥነግጥም በመሥጠት ሲመራመርና ሲያስተምር የኖረውን አንድ ሰው ካጣች ድፍን ሁለት ዓመት ሆነ፡

የዛሬ ሁለት ዓመት በዚሁ ጊዜ ነበር የሥነጽሑፍና የሥነግጥም መምህርና ተመራማሪ ብርሃኑ ገበየሁ በሞት የተለየን፡፡

ሞቱ እጅግ ቅፅበታዊ፣ አስደንጋጭና ለማመን የቸገረ ነበር፡፡ ከጥቂት ሠዓታት በፊት አብረውት ምሳ የተመገቡ ወዳጆቹ፣ ከደቂቃዎች በፊት ሲያወራቸው የነበሩ የቤተሰቡ አባላት ይህ አስደንጋጭ ዜና በወቅቱ እንቆቅልሽ ሆኖባቸው አመዳቸውን ቡን አድርጎት ሰንብቷል፡፡ ብርሃኑን የሚያውቁትን በሙሉም እንደዚሁ፡፡

ብርሃኑ ገበየሁ በአማርኛ ሥነግጥም ዙሪያ ለበርካታ ዓመታት ጥልቅ ምርምር ሲያካሂድና ሲያስተምር የቆየ ሲሆን፤ በመጨረሻም የዚሁ የምርምርና የማስተማሩ ውጤት የሆነውና ንድፈ-ሐሳብ፣ ማብራሪያና ትንታኔ የያዘውን “የአማርኛ ሥነግጥም” የተሰኘውን መጽሐፍ ያበረከተ ምሁር ነው፡፡

ሰውየው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት በቆየባቸው ዓመታት ለሥነግጥም በነበረው ጥልቅ ፍቅር፣ በልዩ የማስተማር ክህሎቱና በአንዳንድ ጠባዮቹ ትኩረት የሚስብ ሰው እንደነበር የሚያውቁት ይመሠክራሉ፡፡

ብርሃኑ ግጥምን ነገሬ ብሎ የያዘው ገና በጊዜ ነው፡፡ ይህንንም በተመለከተ መጽሐፉ መታሰቢያ እንዲሆናቸው ከጠቀሳቸው ሰዎች መካከል አንዷ ለሆኑት ለእናቱ ያሰፈረው እንዲህ ይላል፡- “በመተረክና በመተረት፣ በመመሰልና ቃል በመንጠቅ (ግጥምን አስታውሶ ላሉበት ሁኔታና ስሜት መገላጫነት በመገልገል) ረገድ ላቅ ያለ ችሎታ ለነበራት፤ ምናልባትም የቃልን ኃይልና ፍቅር ወይ በዝርያ ወይ አብሮ በመኖር (በጡቷ) ላጋባችብኝ…”

ይህ ሰው በዘመኑ ግጥም ከእርሱ ሳይለይ፣ እርሱም ከግጥም ሳይለይ ከሚወደው ሥነግጥም ጋር አብረው ኖረዋል፡፡ ስለ ሥነግጥም ሲያወራ ውሎ ቢያድር የሚጠግብ አልነበረም፡፡

ብርሃኑ ከ1986 እስከ 1989 ዓ.ም በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ፣ ከዚያ በኋላም በተቀሩት ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥነጽሑፍና በሥነግጥም መምህርነትና ተመራማሪነት እንደዚሁም ተማሪዎችን በማማከር አገልግሏል፡፡

የሁለት ማስተርስ ዲግሪዎች ባለቤት የነበረና በሥራዎቹም እስከ ረዳት ፕሮፌሰርነት ደረጃ የደረሰ ሲሆን፤ ሆላንድ አገር የፒኤችዲ ዲግሪውን በመሥራት ለማጠናቀቅና ተቋቁሞውን (Defense) ለማቅረብ ጥቂት ጊዜያት እንደቀሩት፣ ገና ብዙ መሥራት በሚችልበት በ45 ዓመት እድሜው ሐምሌ 12 ቀን 2002 ዓ.ም በአጭሩ ተቀጨ፡፡

በወቅቱ የብርሃኑ ህልፈተ-ህይወት በሚያውቁት ዘንድ እጅግ አስደንጋጭና አሳዛኝ ክስተት ነበር፡፡

የዶክትሬት ዲግሪውን ሲሠራ አማካሪው የነበሩት ጆን አቢንክ ሞቱን ተከትሎ ባወጡት ይፋዊ የሀዘን መግለጫ፣ ብርሃኑ የተለየ ብሩህ አዕምሮ የነበረው ባተሌ ምሁር እንደነበረ ጠቅሰው፤ “ከማንኛውም ሰው ማንኛውንም እውቀትና መረጃ ለማግኘት ወደ ኋላ የማይልና በሕይወቴ ከማውቃቸው እጅግ አዋቂና ሊቅ ሰዎች አንዱ ነው፡፡” ሲሉ ገልፀውታል፡፡

ሪፖርተር ጋዜጣ “የሥነግጥሙ ብርሃን ጠለቀ” በሚል ዜናውን ያሰራጨ ሲሆን፤ እዚሁ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የወጣ ጽሑፍም “ለግጥም ተፈጥሮ በግጥም የተዘከረ የሥነጽሑፍ ልሂቅ” ሲል ገልፆታል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገበየሁ በባህል፣ በሥነጽሑፍ፣ በሥነግጥምና ፎክሎር ዙሪያ ሠፊና ጥልቅ እውቀት የነበረው ሲሆን ለዘርፉ ከነበረው የተለየ ፍቅር የተነሳም ብዙ ብዙ ውጣ ውረዶችን ያሳለፈ ሰው ነበር፡፡

የግጥም ነገር ቀልቡን ሲያናውዘው፣ ሲያባክነውና፣ ሲያንከራትተው፤ ሲያስገርመውና ሲያፈላስፈው፤ አንዳንዴም ሲያነጫንጨው መኖሩን በቅርብ የሚያውቁት ከመናገራቸውም ባለፈ በመጽሐፉ ውስጥ እንዲህ ተብሎ የተጠቀሰ ሐሳብ እናገኛለን፡-

“ልጄ ቴዎድሮስ ብርሃኑ፣ ‘አንተ ብርሃኑ ግን ለምን ግጥም ትወዳለህ?’ እያልክ ደጋግመህ ስትጠይቀኝ አጥጋቢ ምላሽ ልሠጥህ አልተቻለኝም ነበር፡፡ ዛሬም ጥያቄህን በወጉ አልመልሰውም፡፡ በአካልና በአዕምሮ ጎልምሰህ ይህንን መጽሐፍ ለማንበብ በምትበቃበት ጊዜ ያኔ አባትህ ለምን ስለ ግጥም እያሰበና እየጻፈ በዝምታ ውቅያኖስ ይሠጥም እንደነበረ፣ ስለምንስ ለውጥና ሽርሽር እያማረህ እያወቀ የልጅነት ፍላጎትህን ችላ ይል እንደነበረ ትረዳለህ ብዬ አስባለሁ”፡፡ ከዚህ አባባልም ብርሃኑ የተለከፈበት የሥነግጥም ፍቅር የቤተሰቡን ጉዳይ ሳይቀር ችላ እንዳስባለው መገንዘብ ይቻላል፡፡

ስለ ግጥምና ገጣሚያን አውርቶ የማይጠግበው ብርሃኑ፤ በኖረባቸው ዓመታት ለሥነግጥም የነበረውን ልባዊ ፍቅር በተግባር አስመስክሮ ያለፈና ምሁራዊ ግዴታውንም የተወጣ ሰው ነው፡፡

 

 

Read 3125 times Last modified on Saturday, 21 July 2012 11:43