Saturday, 05 September 2020 13:25

አዳማ ኃይሌ ሪዞርት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

Image may contain: sky, pool, cloud, grass, outdoor and nature በ500 ሚ. ብር ወጪ በአዳማ የተገነባው “አዳማ ሀይሌ ሪዞርት” ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ሶስት አመታትን የፈጀው ሪዞርቱ፤ ባለ አራት ኮከብ ደረጃ ያለው ነው ተብሏል፡፡ አምስት አይነት ደረጃ ያላቸው 106 የመኝታ ክፍሎች፣ ከ60-1ሺህ ሰው በብቃት ማስተናገድ የሚችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ የስብሰባ አዳራሾች፣ የአዋቂና የልጆች የመዋኛ ገንዳዎች፣ ሁለት ደረጃቸውን የጠበቁ ሬስቶራንቶች፣ የውጭ መመገቢያ፣ የስቲም ሳውናና ማሳጅ አገልግሎት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች፣ የልጆች መጫወቻ፣ በቂ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች የያዘ ነው፡፡  
“ይህንን ሁሉ ኢንቨስትመንት ዘርግተህ እንዴት ለፖለቲካ ቀውስ ኢንሹራንስ አልገባህም?” በሚል ከአዲስ አድማስ ለቀረበለት ጥያቄ ኃይሌ ሲመልስ፤ “እኔ እውነቱን ልንገራችሁ… ለፖለቲካ ቀውስ ብዬ ኢንሹራንስ መቼም ቢሆን አልገባም፣ መንግስት የመጠበቅ ግዴታ አለበት፤ እኔ ኢንሹራንሴ እግዚአብሔር ነው፤ ለፖለቲካ ቀውስ ተብሎ የሚገባ ኢንሹራንስ በየትኛውም ዓለም አላየሁም” ብሏል፡፡
በቅርቡ በኦሮሚያ በተከሰተው ሁከትና ግርግር የወደሙትን የዝዋይና የሻሸመኔ ሆቴልና ሪዞርቶችን በተመለከተም፤ “መንግስት የሚያደርገውን አድርጐ እነዚህ ሆቴሎች ዳግም ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃት አለባቸው” ያለው ኃይሌ ገ/ስላሴ፣ ውድመቱ ከደረሰ ሁለት ወራት ቢያልፍም እስካሁን መንግስት ምንም ያለው ነገር የለም ብሏል፡፡
ከ10 ዓመት በፊት የመጀመሪያውን ኃይሌ ሪዞርት በሐዋሳ የመሰረተው አትሌቱ፤ እስከ 2025 (እ.ኤ.አ) 20 ሆቴሎችን የመክፈት ዕቅድ ያለው ሲሆን ባለፈው ሐሙስ ያስመረቀውም ሰባተኛውን ሪዞርት መሆኑ ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል፤ በወላይታ ሶዶና በጐርጐራ የሚገነቡትም ስራቸው ተፋጥኖ ይቀጥላል ብሏል ኃይሌ፡፡  

Read 3036 times