Sunday, 06 September 2020 15:49

ልማድ ሲሰለጥን ተፈጥሮ ይሆናል

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ከእለታት አንድ ቀን አንድ ንጉሥ ሦስት ልጆቹን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፡- “ልጆቼ፤ እንግዲህ የመሞቻ ጊዜዬ መድረሱ እየታወቀኝ መጥቷል፤ ስለዚህም ሃብቴን ለሦስታችሁም ለማውረስ እንድችል አንዳንድ መመዘኛዎችን ላስቀምጥላችሁና መመዘኛዎቹን በትክክል ያለፈ ልጅ፡-
አንደኛ- እንደ ደረጃው ከሃብቴ ከፍተኛ ድርሻውን ያገኛል፡፡
ሁለተኛ፡- የመረጣትን ቆንጆ ሴት እድርለታለሁ፡፡
ሦስተኛ፡ አዲስ ቤተመንግስት አንጬ እዚያ ውስጥ በደስታና በተድላ እንዲኖር አደርገዋለሁ::” አላቸው፡፡
ለመመዘኛ የሚቀርቡለት ጥያቄዎች ሦስት ናቸው፡-
አሸናፊ የሚሆነው ልጅ፣ ሦስቱንም ጥያቄዎች በአመርቂ ሁኔታ የመለሰ እንደሆነ ነው፡፡
ጥያቄዎቹም፤
ሀ/ ምን አይነት ሚስት ለማግባት ትፈልጋለህ?
ለ/ ብትነግስ ምን አይነት አገዛዝ መግዛት ትሻለህ?
ሐ/ በሀገር ላይ ጠላት ቢነሳ ምን ምን ታደርጋለህ? የሚሉ ነበሩ፡፡
ልጆቹም የአንድ ሳምንት ጊዜ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ሦስቱም ልጆች በየፊናቸው ሲያስቡበት ቆይተው፤ በቀጠሮአቸው መሠረት ወደ ንጉሡ ተመለሱ፡፡
ንጉሡ አማካሪዎቻቸውን ሰብስበው ይጠብቁ ነበረና፤ ልጆቹ በዙፋኑ ፊት ቃላቸው ተሰማ፡፡
አስገራሚው ነገር የውድድሩ አሸናፊ የሆነው፤ የመጨረሻ ትንሹ ልጅ ነው፡፡
በትንሹ ልጅ መልስ መሠረት፤ የመጀመሪያውን ጥያቄ የመለሰው እንዲህ ብሎ ነው፡-
“ማግባት የምፈልጋት ሴት፡- የምወዳት ብቻ ሳትሆን የምትወደኝ፣ የምትታዘዘኝ ብቻ ሳትሆን አማክረኝ እንመካከር የምትለኝ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ንጉሥ በመሆኔ ሳይሆን   ሰው በመሆኔ ያገባችኝ ከሆነች ነው፡፡
በመጨረሻም፤ ከጐረቤት ጋር ተግባብታ መኖር የምትችል መሆን ይኖርባታል” አለ፡፡
“ለሁለተኛው ጥያቄ መልሴ፡-
ህዝብን በኃይል ሳይሆን በፍቅር መምራት የሚችል መሪ መሆን፡፡
ለሦስተኛው ጥያቄ መልሴ፡-
ጠላትን የምመክተው በህዝቤ አቅምና በፈጣሪ ቸርነት መሆኑን ነው” አለ፡፡
ሦስተኛው ልጅ፣ ሦስቱንም ጥያቄዎች በትክክል መልሶ አሸንፎ፣ የአባቱን ዙፋን ወረሰ፡፡
ሽልማቱ ያ ነውና!
*   *   *
የአገራችንን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህልውና በአግባቡ ለማስጠበቅ የሴቶችን ተሳትፎ ሥራዬ ብሎ ማጠናከር እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ እስካሁን እንደታየው ቁልፍ ቁልፍ የሥልጣን ሥፍራዎች ላይ በመንግሥት በኩል ሴቶችን ለመሾም የተደረገው ጥረት አበረታች አቅጣጫ ነው:: በቂና አመርቂ እንዳልሆነ ግን በገሃድ የሚታወቅ ሀቅ ነው፡፡ ምነው ቢሉ? ከመፈክርነት ያለፈ፣ ተግባራዊ ጥቅም፣ ገና ለብዙሃን ሴቶች ሲያተርፍ ስላልታየ ነው፡፡
ከቶውንም የማህበረሰባችንን ግማሽ አካል ወደ ጐን ትቶ እድገት አመጣለሁ ማለት “እንስራዋን ጥላ ወንዝ ወረደች”  የሚባለውን አይነት ወለፈንድ ነገር ነው፡፡ በኛ ሀገር ህሊናዊና ነባራዊ እውነታ ላይ አጽንኦት ሰጥተን ስናነፃጽር፤ የፍትህ መጓደል፣ የእኩልነት አለመኖርና የድህነት አረንቋ ውስጥ መዘፈቅ ሁነኛ ሽግግርና አመርቂ እመርታ እንዳናሳይ የጋረዱን ሦስት አሽክላዎች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ እኒህን እንቅፋቶች ሳናስወግድ መሠረታዊ ለውጥ እናመጣለን ብሎ መፍረምረም “ሂማሊያን በሁለት ቆራጦ እግር መውጣት” እንደሚባለው አይነት ከንቱ ህልም ነው፡፡
ስለዚህም አስቀድመን የፍትህ ጐደሎ ሥፍራ መሙላት፣ እኩልነትን ማስከበርና የሁሉ ጠቅላይ የሆነውን ድህነትን መዋጋት፣ የጉዳያችን ሁሉ ፊታውራሪ ፍሬ ጉዳይ ነው፡፡
በመሠረቱ የምንመኘውን እድገት በውል ለማድረግ ወሳኙ ሃይል ህዝብ ነው፡፡ ስለሆነም፤ የምንወደውና የሚወደንን ህዝብ ማግኘት መታደል ነው፡፡ ቀጥሎም ምከረኝ አማክረኝ የሚልና ህዝብን የሚሰማ “መካር የሌለው ንጉሥ ያለአንድ ዓመት አይነግስ” የሚለው ተረት የገባው መሪ ማግኘት የበለጠ መታደል ነው፡፡ ሰው የመሆንን መሠረታዊ ህላዌ ስናከብር፣ በሰብአዊና በዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ላይ ያለን አቋም እየጠራና እየጐለበተ ይመጣል፡፡ ይህም ለህፃናት፣ ለሴቶች ለወጣቶች፣ አረጋዊያን፣ ለባለሙያዊ ህብረተሰብ ክፍል የምንሰጠውን ሥፍራ በማስፋት ረገድ ሰፊ ሚና እንዲጫወት ያደርገዋል፡፡ በውጪ ጉዳይ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ረገድም የራሳችንን ቤት ብቻ ሳይሆን የጐረቤታችንንም ደህንነት ስንንከባከብ፣ የጋራ ህልውናችን የተጠበቀና የተሟላ ይሆናል፡፡ “ደጅ ያለው ሰንበሌጥ ማድቤት የተሰቀለው ሰፌድ ይንቀጠቀጣል” ይሏል ይሄ ነው፡፡ አፍንጫን ሲመቱት አይን ያለቅሳል እንደማለት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከዛሬ ቸል ብለነው የቆየነው የባህላዊ ፖለቲካ አካሄዳችንም አንዱ የማህበረሰባችን ትኩረት - ሳቢ አጀንዳ ነው፡፡ የረጅም ጊዜ ባህላችንና ታሪካችን እንዲሁም ማህበራዊ እሴቶቻችን በፖለቲካዊ ህይወታችን ላይ የሚሳርፉትን መዳፍ ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ ይኸውም የምዕራቡንም አለም ሆነ የምስራቁን ዓለም አካሄድ በግድ በዓይኑም በሰበኸቱም መኮረጅ የለብንም ማለት ነው፡፡ የራሳችንን ተገቢ ባህልና ታሪክ መሠረት ያደረገ አካሄድ እንድናውጠነጥን፤ አንድም ባህላችንን በፍፁም አክብሮት መፈተሽ፣ አንድም የአለም ፖለቲካን ነገረ ሥራ መመርመር የማታማታ የሚበጀንን ራስ ተኮር፣ ሥርዓት የመገንባትን የመሠረት ድንጋይ እንድናቆም ያግዘናል፡፡
ይህ ከባድ ቁምነገርን ያዘለ ነው፡፡ የምሁራንን ምርምር እዚህ ላይ ማተኮር ይኖርብናል:: በመሆኑም ሌላው ቀርቶ ስለ ዲሞክራሲ እንኳን ስናጤን፣ በመልኩም በገበሩም የውጪውን ዲሞክራሲ እንደ ደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) ብናሰፋ፣ በሰፋን ጠጠበን ንትርክ ጊዜ ከማበከን የሰው ሃይል ከማልኮስኮስና ያልባለቀ ለውጥ አሊያም ጭንጋፍ አብዮት ከማምጣት የላቀ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ንጥር ያለ የራሳችን ስርዓተ ህንፃ ለማቆም ድካሙና ሙግቱ እንደማይቀርልን ተገንዝበንም ቢሆን፤ ሥጋትና ትዕግስት ማድረጋችን ግድ ነው፡፡ በተለመደውና ዓለም ይሄድበታል ያልነውን መንገድ ለአመታት ያለ ፍሬ የተጓዝነውን ከማጤን በመነሳት ወደ ውስጥ፣ ወደ ራሳችን ዓይናችንን ብንገራ ምን አልባት ተጨባጭና ቅዠታዊ ያልሆነ ጉዞ እንጓዝ ይሆናል:: አዲስ አቅጣጫና ፈር ራሳችንን የሚመስል እንፍጠር፡፡ “ዛሬ ለወግ ያደረግሽው፣ ወይ ለነገ ይለምድብሻል ልማድ ፊት እንዳያሳዩት ነው፣ ወይ ይጠፋል ወይ ያጠፋል፡፡
ከርሞም የሰለጠነ እንደሁ ተፈጥሮ ይሆናል፡፡” የምንለው ለዚህ ነው!
አዲሱ ዓመት አዳዲስ የመፍትሔ አቅጣጫዎችና አማራጮች የምንፈጥርበት፤ የምንረጋገምበት ዘመን ሳይሆን የምንደናነቅበት፤ ጥላቻ የምንረጭበት ሳይሆን ፍቅር የምንዘራበት ዓመት እንዲሆን ከልብ እንመኝ፤ አጥብቀንም እንሻት!! ሁሉም ነገር ከሃሳብ ከምኞት ከመሻት ይጀምራል፡፡ በጐ በጐውን እንመኝ!!         


Read 11832 times