Sunday, 06 September 2020 15:50

ኢዜማ እና አነጋጋሪ የጥናት ሪፖርቱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

“ከመላው የሀገሪቱ ክፍሎች በመጡ ዜጐች የተቋቋመችው አዲስ አበባ በተለያዩ የአስተዳደር ብልሹነቶች ምክንያት ሁሉንም ዜጐች እኩል ተጠቃሚ ማድረግ ሳትችል ቀርታለች” የሚለው የሰሞኑ የአዲስ አበባ የመሬት ወረራና የህገወጥ ኮንዶሚኒየም እደላን የተመለከተው የኢዜማ ሪፖርት፤ “ከቅርብ ወራት ወዲህ በከተማዋ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች የመንግስታዊ መዋቅሮች ድጋፍ ያለው የመሬት ወረራና ኢ-ፍትሃዊ የሆነ የኮንዶሚኒየም ቤቶች እደላ መከናወኑ ትልቅ ቅሌት ሆኗል” ይላል፡፡
ሦስት አይነት መልክ ያለው የመሬት ወረራ ተፈጽሟል የሚለው ሪፖርቱ፤ የተፈፀመው ድርጊትም ማንኛውንም የህዝብ ወይም የመንግስት የሆነ መሬትን ከህግ ውጪ በግለሰብ ወይም በቡድን የመያዝ ተግባር ነው ይላል:: የመጀመሪያው የህገ ወጥ መሬት ወረራ ዘዴ በጅምር ቤት ስም ከባለ ይዞታዎች ህጋዊ ባልሆነ መንገድ በመግዛት ግንባታ የሚካሄድበትና ለመኖሪያነት የሚውልበት በተለምዶ #ጨረቃ ቤት; የሚል መጠሪያ የተሰጠው ነው፡፡ ይህም በካሬ ሲሰላ በነፍስ ወከፍ ከ75 እስከ 250 ካ.ሜ የሚደርስ ነው፡፡
ሁለተኛውና በከተማዋ እየተስፋፋ የመጣው የመሬት ወረራ አይነት መንግስት በባዶ ቦታነት መዝግቦ ወደ መሬት ባንክ ያስገባውንም ሆነ ያላስገባውን መሬት በቡድንና በግለሰብ ደረጃ በማጠር መያዝና ለሌላ ወገን ማስተላለፍ ነው:: ሦስተኛው በህግ ሽፋን ስም የሚፈፀም ወረራ ሲሆን፤ በመንግስት መዋቅር ውስጥ በተዘረጋው ሰንሰለት በጥቅም ተጋሪነትና በዝምድና ሠፋፊና ቁልፍ ቦታዎች በልጅ በሚስትና በዘመድ አዝማድ ስም የሚያዝበት መንገድ ነው ይላል -ኢዜማ በጥናት ሪፖርቱ፡፡
የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በተመለከተ ደግሞ በ1997 እና 2005 ከተመዘገቡት 947ሺህ ዜጐች ውስጥ እስካሁን የተሰጣቸው 178ሺ 600 ያህል መሆናቸውን በመጠቆም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከ95ሺህ በላይ ኮንደሚኒየሞች በህገ ወጥ መንገድ ለማይመለከታቸው ወገኖች መተላለፋቸውን ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡ የተመረጡ ኮንዶሚኒየሞች ለቅርብ ወዳጆችና ዘመድ አዝማድ የማደል ተግባርም በባለስልጣናት መካሄዱን ሪፖርቱ አትቷል፡፡
ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ በአጠቃላይ በከተማዋ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መጠንና ስፋት የመሬት ወረራና ህገወጥ የመኖሪያ ቤቶች እደላ ተደርጓል ብሏል - ሪፖርቱ፡፡ የከተማዋ አስተዳደር እያየና እየሰማ በህገወጥ ወረራ የተያዙ ቦታዎች በፍጥነት ካርታና ፕላን ተሠርቶላቸው ለሦስተኛ ወገን በሽያጭ መተላለፋቸውን፣ በምንም መስፈርት ልዩ የቤት ተጠቃሚ መሆን የማይገባቸው ቤት እንደተሰጣቸው፣ መታወቂያም እንዲያገኙ መደረጉ ተጠቁሟል፡፡
የኢዜማ የጥናት ቡድን፣ በዋናነት ጥናት ባደረገባቸው አምስቱ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ አካባቢዎች ላይ ባሳባሰበው ግኝት፤ በአጠቃላይ ከ213 ሺህ 9 መቶ ካሬ ሜትር በላይ መሬት በህገ ወጥ መንገድ  መወረሩን አረጋግጧል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በንፋስ ስልክ ላፍቶ 96ሺህ 8መቶ ካሬ ሜትር፣ በየካ ክፍለ ከተማ 58 ሺህ ካሬ ሜትር፣ በኮልፌ ቀራኒዮ 21ሺህ 1 መቶ ካሬ ሜትር፣ በአቃቂ ቃሊቲ 22ሺህ 5 መቶ ካሬ ሜትር ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ከአዲስ አበባ የመሬት ወረራና የኮንዶሚኒየም ቤቶች ህገወጥ እደላ ጋር በተያያዘ ኢዜማ በዝርዝር ይፋ ካደረገው ሪፖርት ባሻገር በግኝቶቹ ላይ በቀጣይ ሊወሰዱ በሚገባቸው እርምጃዎች ዙሪያ የፓርቲው  ም/ሊቀ መንበርና የጥናት ቡድኑ መሪ ዶ/ር ጫኔ ከበደ፣ ከአዲስ አድማስ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል::  


             ኢዜማ እስከ ዛሬ የት ቆይቶ ነው አሁን ይሄን ሪፖርት ይዞ የቀረበው የሚሉ ወገኖች አሉ…
እንዲህ ያለ ነገር የሚነሳው የኢዜማን መርህ ካለማወቅ ነው፡፡ ኢዜማ ምክንያታዊና በመረጃ ላይ የተመሠረቱ ስራዎችን ነው የሚሠራው፡፡ በማስረጃ ላይ የተመሠረቱ ጥቆማዎችና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ነው የሚያቀርበው፡፡ ይሄን መርህ ተከትለን ነው ጥናቱን የሠራነው፡፡ ዘገየ ለተባለው ነገር ከዚህ ቀደም በርካታ መግለጫዎችን ስንሰጥ ቆይተናል፡፡ ይሄ ለየት የሚለው የምርመራ ስራ የተሠራበት ስለሆነ ነው፡፡ እኛ በመርሃችን እንደ ሌሎች አንድን ጉዳይ ጽንፍ ይዞ ማስጮህን አንፈልግም፡፡ በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ መሄድ ጥሩ አይሆንም፤ መሬት የረገጠ ዲሞክራሲ እንዲኖር ጭምር አርቆ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
ጥናቱ በአጠቃላይ በአዲስ አበባ የተፈፀሙ የመሬት ወረራዎችን የሚያሳይ ነው?
አዲስ አበባ ካሉት 10 ክ/ከተሞች መካከል መሬት ማስፋፊያ የሆኑና ጥቆማ የደረሰንን አካባቢዎች ብቻ ነው መነሻ አድርገን ያጠናነው፡፡ በዚህ መሠረት 5 ክፍለ ከተሞችን ነው ያየነው፡፡ በእነዚህ ክፍለ ከተሞችም ቢሆን ናሙና ነው የወሰድነው፤ 1ሺህ 2 መቶ ጥቆማዎች ደርሰውን ነበር፤ ከእነዚህ ውስጥ ለጥናቱ 23 ጥቆማዎችን ነው ለማጣራት የሞከርነው፡፡ ሁሉንም የአዲስ አበባ ክፍለ ከተማዎች ሽፋን የሚሰጥ አይደለም፡፡ ጥናቱ ግን ሳይንሳዊ መንገድን ተከትሎ በጥንቃቄ የተሠራ ነው፡፡ በሌሎች ክፍለ ከተማዎች ችግሩ የለም ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን እኛ ጥናቱን ያቀረብነው መንግስት ምላሽ ይሰጥ ዘንድ መነሻ እንዲሆን ነው፡፡
ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ፣ የመሬት ወረራዎች ተፈጽመዋል የሚሉ ሪፖርቶች ይቀርቡ ነበር፡፡  የእናንተን ግኝት ከዚህ ቀደም ከነበረው ምንድን ነው የሚለየው?
ለውጡን ተከትሎ የመጣው የመሬት ወረራ እጅግ በጣም አይን ያወጣ ነው፤ ነገር ግን ከዚያ በፊትም የነበረ ነው፡፡ ከሌሎች አካባቢዎች እንጨት ጭነው መጥተው መሬቱን እየተከፋፈሉ የሚያጥሩ፣ በአዲስ አበባ ወረዳዎች ባሉ ኃላፊዎች ካርታና ፕላን እየተሰጣቸው ቤት የሚቀልሱ፣ ሱቅ የሚሠሩ፣ መኖሪያ ቤት የሚገነቡ፤ ነገር ግን በአዲስ አበባ አስተዳደር ዳታ ቤዝ ውስጥ ሲፈለጉ የሌሉ ናቸው፡፡ ለልማት ተነሽ አርሶ አደሮች በሚል ስም ብዙዎች ጉዳዩ የማይመለከታቸው ተጠቃሚ ሆነው አግኝተናል፡፡ የአርሶ አደር ቤተሰቦች ልጆች በተገቢው መንገድ ካሣ አልተከፈላቸውም፤ ሊካሱ ይገባል የሚል አቋም አለን፡፡ ከተማው ሲሰፋ መቋቋሚያ የሚሆን፣ ልጆቻቸውና እነሱ በተገቢው መንገድ አላገኙም የሚለውን የምንጋራው ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸው እንዲቋቋሙ ምንድን ነው ሊደረግ የሚገባው በሚለው ላይ  ባለድርሻዎች የተሳተፉበት ምክክር ነበር ሊደረግ የሚገባው፡፡
አሁን ከንቲባው ብቻ እየወሰነ በሚያስተላልፈው ትዕዛዝ ነው ኮንዶሚኒየም እደላም ሆነ የመሬት ወረራ የተካሄደው፤ ብዙ እጣ የወጣባቸውም እጣ ያልወጣባቸውም ኮንዶሚኒየሞች በሙሉ እንዲታገዱ ተደርገው ለአርሶ አደሮች በሚል ስም የማይመለከታቸው ሰዎች እንዲሰጣቸው ተደርጓል፡፡ ይሄ ህጋዊና ፍትሃዊ አይደለም፡፡ በቆጠቡ ሰዎች ብር የተሠራን ኮንዶሚኒየም፣ ለሌሎች አሳልፎ መስጠት ከህግ ውጪ ነው:: ተገቢም ከሆነ  ሌላ መሬት ወይም ቦታ ተፈልጐ ነው ተሠርቶ፣ ሊሰጥ የሚገባው:: አርሶ አደሮችም በዚህ መልክ ነው መስተናገድ የነበረባቸው:: በአጠቃላይ ህግን ያልተከተለ፣ ኢ-ፍትሃዊ አሠራር ነው ሲከተሉ የነበሩት፡፡ ህግን የጣሰ፣ ማን አለብኝነትን ያከለ አካሄድ ነው፡፡ እንደውም ባለ ተራነትን ያዘለ፣ ምን ያገባችኋል የሚሉ አባባሎችን ነው ስንሰማ የነበረው፡፡ የከተማዋን ህዝብ ፍላጐትና ፍፁም ለህግ የመገዛት ስልጡንነት ያላገናዘበ አካሄድ ነው የታየው፡፡ ህዝቡ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ቆጥቦ የገዛውን ቤት ማግኘት አለበት፡፡
ጥናታችሁ ከብሔር አንጻር ጉዳዩን ለይቶ ተመልክቶታል? በስፋት ለአንድ ብሔር አባላት ነው የተሰጠው የሚባል ነገር በስፋት ይሠማል--?
አዎ በጥናታችን ውጤት ላይ እንደጠቀስነው፤ የአካባቢው የኦሮሞ አርሶ አደሮችን ሳይሆን ከሌላ ቦታ የመጡ የብሔሩ አባላትን ነው ተጠቃሚ ለማድረግ የተሞከረው፡፡ የዝምድና የወዳጅነት ሁኔታዎች ናቸው የታዩት፡፡ ምናልባት የዲሞግራፊ ቅየራ አካሄድ ነው የሚል ታሳቢ አድርገናል፡፡ ሁሉንም ሳይሆን በዘመድ በአዝማድ የተወሰኑ የኦሮሞ ብሔር አባላትን ለመጥቀም በሚመስል መልኩ ነው ቤቶቹ የተሰጡት እንጂ እንደተባለው አርሶ አደሮችን ለመጥቀም ያለመ አይደለም፡፡ ጉዳዩ በትክክልም ብሔር ተኮር እንቅስቃሴ ነው፡፡
መንግስት ከዚህ በፊት ህገወጥ ወረራ እያለ ቤቶች ሲያፈርስ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈጸመ የሚሉ ትችቶች ሲሰነዘሩ ቆይተዋል፡፡ አሁን ደግሞ ህገወጥ የመሬት ወረራ ሲፈፀም ዝም ብሏል የሚል አቤቱታ ነው እየቀረበ ያለው፡፡ እነዚህን ሁለት አካሄዶች እንዴት ማስታረቅ ይቻላል?   
ምናልባት ሁለቱን ለማስታረቅ የህግ የበላይነትና መመሪያዎችን ህጐችን ማክበር በቂ ይሆናል፡፡ አዲስ አበባ የመሬት ፖሊሲ አላት፣ አዲስ አበባ የኢንቨስትመንት መመሪያ አላት፡፡ እነዚህን አስፈፃሚው መስሪያ ቤት በዚህ የመጠቃቀም ሰንሰለት ውስጥ ገብቶ መመሪያና አሠራርን ወደ ጐን ትቶ ነገሩን ያለ አግባብ ሲጠቀምበት ነው የምንመለከተው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ችግሮች ሊቀረፉ የሚችሉት ህግን ብቻ መሠረት ተደርጐ ሲሰራ ነው፡፡ ቁርጠኝነቱ ካለ መሬት ሳይወረር መከላከል ይቻላል፡፡ ለዚህ ግልጽ የሆነ አሠራር መዘርጋት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በየወረዳው ባሉ መስሪያ ቤቶች የተሠገሠጉ ሰዎች፤ ብሔር ለይተው የሚፈልጓቸውን ለመጥቀም የሄዱበት አካሄድ ነው ትልቁ ስህተት፡፡ በአጠቃላይ ህጐችን ተርጉሞ ወደ ተግባር የመለወጥ ችግር ነው፡፡ ይህ ችግር የሚመነጨው ደግሞ ከማን አለብኝነትና ብሔር ጉያ ውስጥ ለመወሸቅ ከመሞከር ነው፡፡  
ለዚህ ታዲያ ተጠያቂው ማን ነው?
ተጠያቂው እገሌ ነው ብለን የግለሰብ ስም መጥቀስ አንፈልግም፡፡ በአጠቃላይ የመጀመሪያው ተጠያቂ የአዲስ አበባ አስተዳደር ነው፤ ከንቲባ ጽ/ቤት፡፡ ምክንያቱም ሁሉንም የከተማዋን አስፈፃሚ አካላት የሚመራ ነው፡፡ ከንቲባውን ጨምሮ በተዋረድ በየቢሮው ያሉ ተጠያቂ ናቸው፡፡ ሁለተኛ ተጠያቂ የሚሆኑት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ም/ቤት አባላት ናቸው፡፡ የም/ቤቱ አባላት አዋጅ ሲጣስ፣ በአዋጅ ላይ አዋጅ ሲወጣ ምን ይሠሩ ነበር? ለወከላቸው ህዝብ ምን እያደረጉለት ነው? ስለዚህ ሁለተኛ ተጠያቂ የሚሆኑት የም/ቤቱ አባላት ናቸው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ተጠያቂዎች ደግሞ የፍትህ አካላት ናቸው:: የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና የደንብ ማስከበር ጽ/ቤት የሚባሉት፣ ሁለቱም አካላት ተጠያቂ ናቸው፡፡ እንዲህ አይነት ወረራ ሲፈፀም ቁጭ ብለው እያዩ፣ አንዳንዴ እንደውም ተከላካይ ሲሆኑም ይስተዋላል፡፡ የተሰጣቸውን ስልጣንና ህግ ለምን አልተጠቀሙም? ፖሊስና ደንብ ማስከበር ጽ/ቤቱ፡፡ የአዲስ አበባን ህዝብ መብት ማስከበር ነበረባቸው:: የመንግስትና የህዝብን ሃብት ከህገወጦች በመከላከል ኃላፊነታቸውን መወጣት ነበረባቸው፡፡
አሁን መፍትሔው ምንድን ነው ትላላችሁ?
በየክፍለ ከተማና ወረዳው፣ መሬትና ቤቶችን በተመለከተ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በአስቸኳይ መቆም አለባቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በከንቲባ ጽ/ቤት በኩል ይፋዊ አቋም ተይዞ መግለጫ ሊሰጥበት ይገባል፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ገለልተኛ አካል ተቋቁሞ ጉዳዩን ድጋሚ ማጣራት ይገባል፡፡ የኛን ጥናት መሠረት አድርገው አጥንተው ወደ መንግስት መመለስ ያለባቸው ቤቶችና መሬቶችን መልሰው፣ እንደገና ያለ ፕላን የተያዙ ቦታዎች ወደ መንግስት ተመልሰው መታየት አለባቸው፡፡ ህዝቡ መሬታችን ተመልሷል፡፡ ከዚህ በኋላ በህግ እየተመራን፣ የመሬት ባለቤት መሆን እንችላለን የሚል እምነት እስኪኖረው ድረስ እንዲህ አይነት ጉዳዮችን የከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት መስራት አለበት፡፡
አጥፊዎችን በህግ ተጠያቂ ማድረግ የሚቻልበት መንገድ አለ?
እኛ ሪፖርታችንን ለጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ ለፖሊስና ለሌሎችም አካላት እንዲጣራ የቅሬታ ማመልከቻ እናስገባለን:: ሙስና ይኖራል ከተባለም ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጉዳዩን በተገቢው እንዲመለከተው እንጠይቃለን፡፡ የኢዜማ የህግ ክፍል እነዚህን ያለመታከት ይከታተላል:: የህግ አካላት ወንጀሉን እንዲያጣሩት እስከ መጨረሻው ግፊት እናደርጋለን፡፡ የህግ ተጠያቂነት ሠፍኖ፣ የባከነው ሃብት ለህዝብ እንዲመለስ እንታገላለን፡፡ በሌላ በኩል፤ይሄ ነገር ፖለቲካዊ አንድምታም አለው፡፡ አዲስ አበባ የኛ ነች ከሚል መነሻ የኦሮሞን ብሔረሰብ በከተማዋ የመሰግሰግ ፖለቲካዊ ውሣኔ ነው፡፡ ይሄን ያደረገው ክፍል ሆን ብሎ የተወሳሰበ ማህበራዊ ግንኙነት የመፍጠር አካሄድ ነው የተከተለው፡፡ ይሄ ማህበራዊ ትስስርን በእጅጉ ስለሚጐዳ ነገሩ ችግር ከመፍጠሩ በፊት እንዲቆም እንጥራለን:: ከተማዋ ከአካባቢው የኦሮሞ ማህበረሰብ ጋር እንድትቃረን የሚያደርግ አካሄድ በመሆኑ፣ ይሄ ተገቢነት የሌለው አካሄድ እንዲቆም ያስፈልጋል፡፡ የማህበራዊ ትስስር መረበሽ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ጥናትም አለው::
አጠቃላይ የገበያ ትስስሮች ሊቆሙ ይችላሉ:: ይሄ ከሆነ ድሃው ህብረተሰብ በእጅጉ ይጐዳል:: 75 በመቶ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የያዘች ከተማ እንደመሆኗ መጠን፣ ከኦሮሚያ አልፎ በሌሎች ክልሎች ላይ ተጽእኖ ሊፈጥር ይችላል:: አንደምታው ጥሩ አይደለም፡፡ ነገርየው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊፈጥር የሚችል ነው:: ስለዚህ የፖለቲካ ልሂቃኖች ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል፡፡
በጉዳዩ ላይ ከአዲሷ ም/ከንቲባ ጋር ተወያይታችኋል፡፡ ምን ምላሽ አገኛችሁ?
የውይይት ጥሪው የደረሰን ከምክትል ከንቲባዋ ነበር፡፡ ከአጥኚው ቡድን ጋር መነጋገር እፈልጋለሁ፤ ቡድኑ ያገኘውን ግኝት እኛም መካፈል እንፈልጋለን፤ ያንን በውይይት አንሸራሽረን ማግኘት የሚገባንን እውቀት ከጨበጥን በኋላ የግኝቱን ውጤት አጣርተን እንወስናለን ነው ያሉት፡፡ እነሱ መርምረው አሳማኝ እርምጃ ካልወሰዱ፣ እኛ ጉዳዩን ወደ ህግ ማቅረባችንን እንቀጥላለን፡፡

Read 9463 times