Sunday, 06 September 2020 16:13

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 ሀገር ይሁን ሰላም
ያንቺ ደህና መሆን፣
አያስጨንቀኝም፣ ሀገር ይሁን ደህና
ሰላም ይሁን ቀዬው፣
አያሰማኝ እንጂ፣ አንድም የሞት ዜና
በመርዶ ነጋሪ፣
አልቃሽ እና አስለቃሽ፣ አይመልከት አይኔ
ያንቺን ጤና መሆን፣
አትንገሪኝ ደግመሽ ፣ምን ሊጠቅመኝ ለኔ?!
ያንቺ ደህና መሆን፣
ካሳደገኝ ወገን፣ከሀገር አይበልጥም
እንደዚህም ስልሽ፣
የራስሽ ጉዳይ፣ማለቴ አይደለም
እኔ አንቺን ምወድሽ ፣
ሳልጨምር ሳልቀንስ፣ ያገሬን ያህል ነው
“ያ ማለት ምንድ ነው”
በሌላ አማርኛ…
ሀገር ሰላም ሲሆን፣ሰላም ነሽ ማለት ነው፡፡
***
ሀገሬ “አኩኩሉ…”
የፅልመትን ሸክም፣
መቻል ያቃታቸው፣ዶሮዎች በሙሉ
መንጋቱን ስናውቀው
ንጋት ያበስራሉ፣ኩኩሉ እያሉ፡፡
በዶሮ አንደበት
አኩኩሉ ማለት
ትርጉሙ ሌላ ነው፣
ከእግዜር የተላከ፣አንዳች ታላቅ ሚስጢር
እሱም…
“ተነሺ” ማለት ነው፣
ልጆቿን ታቅፋ፣የተኛችን ሀገር፡፡
ገር ጆሮዋን ይዛ
ትርጉሙ ባልገባት፣የዶሮዎች ቋንቋ
ቅዠት ነው ሚባለው!!
ሁሉም በተኛበት፣
ሀገር ላይ እየኖርክ፣ብቻህን ስትነቃ
በእንቅልፋሞች አለም፣
የንጋት ላይ ጩኸት፣ለሰምቶ አዳሪ
ስታረድ ንቃ ነው!
ከቅዠት አለምህ፣በዶሮዎች ጥሪ፡፡
ከሰው ልጆች ህይወት፣
የንጋትን እንቅልፍ፣አጥብቆ በጠላ
በተሳለ ቢላ
ዶሮ አንገቱን ታርዶ፣ወጥ ሆኖ ተበላ፡፡
በዶሮ አንደበት፣
“አኩኩሉ” ማለት
ትርጉሙ ሌላ ነው፣
ከእግዜር የተላከ፣አንዳች ታላቅ ሚስጢር
እሱም…
“ተነሺ” ማለት ነው፣
ልጆቿን ታቅፋ፣የተኛችን ሀገር፡፡
“አኩኩሉ”
“አኩኩሉ”
ሀገሬ አኩኩሉ፡፡
(ከገጣሚ ኤፍሬም መኮንን “የወፍ ጐጆ ምህላ” የተሰኘ የግጥም መድበል የተወሰደ)


Read 2462 times