Sunday, 13 September 2020 00:00

“ከብረው ይቆዩ ከብረው…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

  እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁማ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንቁጣጣሽ፣ እንኳን መጣሽ
በአበቦች መሀል እንምነሽነሽ
እየተባለ ተዚሟል…ለብዙ ዘመናት:: ምንም እንኳን በአስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ብንሆንም፣ ምንም እንኳን የተሰናበትነው ዓመት መከራችን ከበዛባቸው የቅርብ ዓመታት አንዱ ቢሆንም፣ ምንም እንኳን የአብዛኞቻችን ጓዳ ሲሳሳ የከረመበት ዓመት ቢሆንም፣ ምንም አንኳ ከመደጋገፍ ይልቅ መገፈታተር የበዛበት ዓመት ቢሆንም…“እንቁጣጣሽ፣ እንኳን መጣሽ…” እንላለን፣ በአበቦች መሀል መምነሽነሽ እንፈልጋለንና!
ስሙኝማ… በዓላትን ሞቅ፣ ደመቅ ያሉና የተለዩ ቀናት የሚያደርጓቸው፣ ወይም ለ‘መራቀቅ’ ያህል “እኛን፣ እኛን እንዲሸቱ” የሚያደርጓቸው ባህላዊ ስነስርአቶቹ ናቸው! እንደ አሁኑ ነጭ የገና ዛፍ ሳሎናችን በማቆም ስልጣኔያችን ዘጠነኛው ደመና ላይ ሳይደርስ ማለት ነው፡፡
ወግና ልማዳችን የወረስነው ከአበው
የአውዳ’መቱ ትዝታ አይጠፋም ሕያው ነው
ሀቁ ይሄ ነው፡፡ ስንት ምእተ ዓመታት ዘልቀው የመጡ በጎ ልማዶችን እንዲህ በቀላሉ መናድ አይቻልም፡፡ እናላችሁ….ፈረንጅ “…ኤንድ ዘ ሳድ ስቶሪ…” እንዲል አሳዛኙ ታሪክ ምን  መሰላችሁ…ሀገር ምድሩን የ‘ናይት ክለብ’ ጨረባ ተዝካር አይነት ማድረግ ስልጡን የበዓል አከባበር የሚመስለን መብዛታችን…‘ስልጡን የበዓል አከባበር’ ምን ማለት እንደሆን አንድዬ ይወቀው፡፡
ስሙኝማ…ስለ ስልጣኔ ሲነሳ የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ፡፡ በዛ ሰሞን…አለ አይደል… ዘመን ከ‘ሀገር ልጅነት’ ወደ ‘ጎረቤትነት’ ከለወጣቸው ከላይኞቹ ጋር ተፈታትነን አልነበር! ከዚያማ “ውጡልን!” “ጥፉልን!” እየተባለ እነሱም የእኛን፣ እኛም የእነሱን አስወጥተን የነበረ ጊዜ ማለት ነው፡፡ እናላችሁ… መሀል አዲስ አበባ አሪፍ ቢዝነስ የነበራቸው ሰውዬ እዛኛው ከተማ ሲደርሱ ምን ብለው አሙን አሉ መሰላችሁ… “በሹካ መብላት እንኳን ያስተማርናቸው እኛ ነን፡፡” ቂ…ቂ…ቂ.. ‘ኮሚኩ’ ነገር ምን መሰላችሁ… አልፎ፣ አልፎ አሪፉ ቀልድ የሚመጣው ቀልድ ባለፈበት ያላለፉ በሚመስሉ ሰዎች መሆኑ ነው! ወይ ሹካ!
እናማ…የስልጣኔ ውሀ ልክ በሹካ መብላትና ነጭ ‘የገና ዛፍ’ ሳሎን ላይ ማስቀመጥ ሆኖ የሚገርመው ወደፊት ያለመራመዳችን ሳይሆን ወደ ኋላ በሚያስከፋ መልኩ አለመንሸራተታችን ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት በሆነ ኤምባሲ ግብዣ ላይ የሆኑ የሀገራችን ሰዎች ጥቅል እንጀራ በቢላ እየቆረጡ፣ በሹካ እየወጉ ሲበሉ ታይተዋል ሲባል ሰምተናል:: (በእንጀራ ወጥ ‘እያጠቀሱ’ መብላት ማለት ነው! “ኸረ ሼም ነው!” የምትለዋ የወጣቶቹ እዚህ ላይ ነበር አንጀት የምታርሰው!)
ስልጣኔ ማለት ያኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ውሀ ቧንቧ ሲገባ…አለ አይደል…
እንዲህ ያለ ንጉሥ፣ የንጉሥ ቄናጣ
ውሀ በመዘውር አየር የሚያወጣ
ያደፈው ሊታጠብ የጠማው ሊጠጣ
አሁን ከዚህ ወዲያ ምን ጥበብ ሊመጣ
እንደተባለው… አለ አይደል… “አሁን ከዚህ ወዲያ ምን ጥበብ ሊመጣ” የሚያሰኝ ነገርዬ ሲኖር ነው፡፡ ዘንድሮ ጥቅል እንጀራ ‘በሹካ መውጋት’ ስልጣኔ ሆነና እኛም ግራ ገባን፡፡ እኔ የምለው… እኛ ሰውዬ “በሹካ መብላት እንኳን ያስተማርናቸው እኛ ነን፣” ያሉት እኛ “እንጀራን መጠቅለያ አምስት ጣት ብቻማ ያንሰናል፣” የምንለውን ሳይሆን በ‘ሹካ ወጊዎቹን’ ይሆን እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ… በሹካ ከመውጋት ስልጣኔ ወደ ሹካ መፈብረክ ስልጣኔ ያሸጋግረንማ!
እናማ… ነገሮች የከተፋ ቤት አዝማሪ የፕሮሞሽን ሥራ ሲመስሉ አሪፍ አይደለም:: ልክ ነዋ…አዝማሪ ቤት እንደ እኛ አይነቱ ከሜትር ከአርባ በስንት መከራና በአውራ ጣት በመቆም ትንሽ ሚሊሜትር ከፍ የሚለው “የእኔማ መለሎ፣ የእኔማ ቁመታም፣” ሲሉት እየተነሳ መቶ ብሯን በላይ በላይ ነው የሚለጥፈው፡፡ አዝማሪው እኮ በሆዱ… አለ አይደል… “ይሄ ሰውዬ እየሸለመኝ ያለው ያልኩት የእውነት መለሎ የሆነ መስሎት እንዳይሆንና የሚሲንቆዬ ክር ጧ እንዳትል!” ይል ይሆናል፡፡
በአዝማሪው “መለሎ፣” “ቁመታም፣” የተባለው ሰው…በእውነተኛው ዓለም ላይ… “አሁን ይህን የመሰለ ከቁመት ቁመት የለው፣ ከመልክ መልክ የለው፣ ዘቅዝቀው ቢነቀንቁት ሰባራ ሳንቲም ጠብ አይለው… ምኑን አይታ ነው የተጣበቅችበት!” አይነት ቅስቀሳ የሚካሄድበት እኮ ነው፡፡ እናማ… ዘንድሮ ማጥላላት፣ ማሳጣት፣ የሰውን ስም እንዳይሆን ማድረግ የጉድ እንደሆነ ሁሉ እርስ በእርስ መሞጋገስም አለ፡፡ ታዲያላችሁ… በአብዛኛው የዘንድሮ መሞጋገስ ከአዝማሪ ቤት “የእኔማ መለሎ፣ የእኔማ ቁመታም፣” አይለይም፡፡ ብቻ ሰላሙን በኩንታል፣ በኩንታል ያምጣልንማ፡፡
ፍቅር ከእኛ እንዳይለየን
እንዲሳካልን ኑሯችን
መጨቃጨቅ ይወገድና
ሰላም ይሁን ለሁላችን
ተብሎ ተዘፍኖ ነበር… ዘመን የማይሽረው መልእክት፡፡
ስሙኛማ…ድሮ ጆፌ መጣል የሚሉት ነገር ነበር አይደል! “እንትናው እንታንዬዋ ላይ ጆፌ ጥሏል፣” ይባል ነበር፡፡ ዘንድሮ የእሱና እሷ ጆፌ መጣጣል ‘መክፈቻ ዜና’ መሆኑ ቀርቷል፡፡ ልከ ነዋ… ስልጣን ላይ ጉብ ሊል ጆፌ የጣለ ቡድንና ግለሰብ አገሩን ሞልቶታላ! በአንድ ሌሊት ሚሊየነር ለመሆን ጆፌ የጣለ የጉድ ነዋ! ይህ ደግሞ ዝም ተብሎ አይደለም፡፡ የምር እኮ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… እዚህ ሀገር ‘በአንድ ሌሊት’ በሚባል ፍጥነት ሚሊየነር መሆን ይቻላል የሚባል ነገር አለ፡፡ እና ሁላችንስ ጆፌ ብንጥል ምን ይገርማል! እናላችሁ… በሁሉም ነገር፣ በተለይ ደግሞ በወንበር ላይ ‘ጆፌ ጣዮች’ በዛንና ሰዋችንም መከራው በዛበት፡፡
ክረምት አልፎ በጋ መስከረም ሲጠባ
አሮጌው ዓመት፣ አልፎ አዲሱ ሲገባ
ፈሳሽ የወንዝ ውሀ ተውሳኩን ይውሰደው
ጤና መሆንን ነው እኛ የምንወደው
አሪፍ አይደለች! ደጋግሞ በ‘ራድዮን’ ይዘፈንልንማ! ልክ ነዋ… ዘንድሮ ‘ወሳጅ’ ፈሳሽ የወንዝ ውሀ የሚያስፈልገው ስንት ነገር አለ መሰላችሁ! “ምናለ ጥርግርግ አድርጎ በወሰደልን! የምንላቸው ብዙ፣ በጣም ብዙ ነገሮች መኖራቸውን ለመጥቀስ ያህል ነው፡፡
የምር ግን… አንዳንድ ደጋግ ነገሮችን ባንረሳም ክፉ ነገሮች አጥልተውባቸው እንዴት ይታዩ!  አዲሱን ዓመት በ‘ሪሳይክሊንግ’ የተፈበረከ የ‘አሮጌው ቅሪት’ ሳይሆን፣ ’ዘ ሴም ኦልድ ስቶሪ’  የሚባልለት ሳይሆን…የእውነትም አዲስ! አዲስ! አዲስ! ያድርግልንማ!
መልካም የበዓል ሰሞን ያድርግላችሁ!
እንቁጣጣሽ፣ እንኳን መጣሽ
በአበቦች መሀል እንምነሸነሽ
ተብሎ ተጀምሮ….
ከብረው ይቆዩ ከብረው
በዓመት ወንድ ልጅ ወልደው
ሠላሳ ጥጆች አስረው
ከብረው ይቆዩ ከብረው
ይባልም ነበር፡፡ ሀገርና መላው ህዝቧ ከብረው ይኑሩ፣ ከብረው ይቆዩ…እስከወዲያኛው!!
ደህና ሰንብቱልኝማ!!

Read 1988 times