Saturday, 12 September 2020 14:36

“ማን ያውቃል?” የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ?” (መንግሥቱ ለማ)

Written by 
Rate this item
(5 votes)

   “እውነት ሲያረጅ ተረት ይሆናል፤ አርትም ሲያረጅ ጂኦግራፊ ይሆናል” ይላሉ አበው አዋቂዎች፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ ሰፈር የሚኖሩ የእግር ኳስ ቡድን የነበራቸው ወጣቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ወጣቶች እንዳሁኑ ዘመን “ጋሼ የኳስ መግዣ አዋጡልን”፣ “ጋሼ የማልያ አነሰን አሟሉልን…” አይሉም፡፡ ይልቁንም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በተለይ በበዓላት ሰሞን የቡድናቸውን ማጠናከሪያ ገቢ ከማሰባሰብ ወደ ኋላ አይሉም ነበር፡፡
በተለይም እንደ ቡሄ ሆያሆዬ፣ እንደ መሥቀል ጭፈራ…በማድረግ ረዥም ርቀት እየተጓዙም ጭምር ገንዘብ ያጠራቅማሉ፡፡
ከእነዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ ዘዴዎች አንዱ እንደ እንቁጣጣሽ አበባ ማዞርና ከሚገኘው ሳንቲም ቀንሶ እያንዳንዱ አባል እንዲያዋጣ ማድረግ እጅግ የተለመደው የቡድን ማዳበሪያ ዘዴ ነበር፡፡
ይህንን መነሻ በማድረግ አንድ ጊዜ (በ1950 እና 1960ዎቹ ውስጥ) የተከሰተን ሁኔታ እንደሚከተለው እናቀርበዋለን፡፡
ወቅቱ የዛሬ 45 አመት ገደማ ነበር፡፡ እንደዛሬ የእንቁጣጣሽ ጊዜም ነበር፡፡ በየዘመድ ቤትና በየጐረቤቱ የሚሰጡትን አበባ ለመሥራት፣ የአበባ ዱቄት ገዝተው አበባ ሲቀቡ ከርመዋል፡፡ ከአበባ ሌላ ክንፉን የዘረጋ መላዕክ ስዕል፣ የርግብ ስዕል፣ የአበባ ማስቀመጫ “እንኳን ለቅዱስ ዮሐንስ አደረሳችሁ” የሚል የመልካም ምኞት መግለጫ ጋር የሰሩም አሉ፡፡
ሴት ሴቶቹ አበባየሆይ እያሉ ይዘፍናሉ፡፡
በዚያን ጊዜ አበባ ለማዞር በየአጐቶቻቸው፣ በየክርስትና አባቶቻቸው፣ በየአክስታቸው፣ በየእናት አባት ነፍስ አባቶች መኖሪያ ቤት ይዞራሉ… ያዞራሉ፡፡ አንዳንዱ ቤት ውሻም ያስቸግራቸዋል፡፡ ያኔ ቤተሰቡ ለአበባ አዟሪ የሚሰጠውን ገንዘብ እየጠረጴዛው ላይ አስቀምጦ ይጠብቃል፡፡ እንደ ዛሬ አልነበረም፡፡ ደግ ጊዜ ነበረ! ወጣቶቹ በየፊናቸው አበባ አዙረው ሳንቲም ሰብስበው ከተመለሱ በኋላ ሠፈር አንድ ሁነኛ ቦታ ይገናኛሉ፡፡  
የዚያን ዕለት ታዲያ በሰበሰቡት ውስጥ የቀነሱትን ቀንሰው ለካፒቴናቸው ያስረክባሉ፡፡ አንዱ ልጅ ብቻ ፈራ ተባ ሲል ይታያል፡፡ ይሄኔ የቡድኑ መሪ ይጠራጠርና “ምን ወደ ኋላ ትላለህ? አምጣ እንጂ የሰበሰብከውን?” አለው፡፡ ልጁም አወጣና ሰጠ፡፡ ካፒቴኑ ሳንቲሙን ቆጠረና “አሃ! ይሄን ብቻ ነው የሰበሰብከው?” ሲል ጠየቀው፡፡ ልጁም “አዎ ይሄን ብቻ ነው” ለማለት ፈልጐ “አ…ኦ…የ..ለ..ቸ”…እያለ ተኮለታተፈ፡፡ ተልጐመጐመ፡፡
ይሄኔ ካፒቴኑ “ምን አባክ ያንተበትብሃል? እስኪ አፍህን ክፈት” ሲለው፤ ልጁ አፉን ከፈተ፡፡
ለካ ከምላሱ ሥር የሰረቃትን አምስት ሳንቲም ላንቃው ላይ አጣብቋት ኖሯል፡፡ ጓደኞቹ ሁሉ በሳቅ ፈነዱ፡፡
*   *   *
በሀገራችን እንዲህ ያለ የዋህነት ዘመንም ነበረ፡፡ ሳንቲም በመደበቂያ ቦታ ጠፍቶ አፍ ውስጥ የሚከቱ ወጣቶች የነበሩበት ጊዜ፡፡
ታዲያ ዛሬ ኮንቴይነር ሙሉ የሰረቁ ሌቦች በሚዲያ ጭምር ተጋልጠው፣ የሀገር ሀብት ሲመዘበር የምንታዘብበት ሀገር ውስጥ እንደምንኖር ያስተዋልበት ሁኔታ ተከሰተ፡፡ እና እንደ ድሮው እምነት ማጉደል ሳይሆን ሙስና የሌብነት ወንጀል ዘረፋ፣ ምዝበራ ወዘተ ተባለ፡፡ የሀገር ሃብት አደጋ ላይ የተጣደበት ጉቦ ህጋዊ ደረሰኝ እንዲሰጥበት የተቃረበ ጊዜ ሆኗል፡፡
ቁጥጥሩ በጐላ መልክ መታሰብ ያለበት ወቅት ላይ ነን፡፡
ዛሬ የማንበብ ባህል በቅጡ ያልዳበረበት መሆኑ አሳዛኝ ነው፡፡ በመሠረቱ፤ የታሪክ መዛግብትንና መጻሕፍትን የማንበብ ባሕል ብናዳብር ብዙ እናውቃለን፡፡ ጠቀሜታውም ብርቱ ይሆናል፡፡ ለአብነት ያህል ገጣሚና ጸሐፌ - ተውኔት መንግሥቱ ለማ፤ የአባታቸውን የአለቃ ለማ ኃይሉን ታሪክ፣ አባታቸው ከራሳቸው አንደበት በመቅረፀ - ድምጽ  (በቴፕ) ቀድተው ሲያበቁ “መጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ” ብለው ጽፈው በ1959 ዓ.ም ከአሳተሙት መጽሐፍ የሚከተለውን የሰፋ ቁምነገር ለዛሬ ጭምር ረብ - ያለው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
የወቅቱን የብሔር ብሔረሰብ ጣጣ እናስተውል ዘንድም እንጠቅሰዋለን፡፡
“…አለቃ ለማ ኃይሉ፣ “አባቴ አስተማሪዬም” የሚሏቸው አለቃ ተጠምቆ ትግሬ ናቸው፡፡ በቅኔ በብሉይ መምህርነታቸው ማዕረግ አክብረው አንከብክበው አለቃ ተጠምቆን የያዟቸው ዲሞች፣ ጐጃሞች ናቸው፡፡
አለቃ ለማን ቤተኛቸው አድርገው ለወ/ሮ አበበች ይልማ የዳርዋቸው ጌታ አለቃ ወልደ ያሬድ ሸዬ ናቸው፡፡ አለቃ ለማ ራሳቸው መቄቴ፣ ላስቴ ናቸው፡፡
ይህ የሊቃውንት አባቶቻችን ታላቅነት አርአያ፤ በአሁኑ ዘመን ትግሬ ነህ፣ ጐንደሬ ነህ፣ ሸዋ ነህ፣ ጐጃም ነህ፣ ሐረርጌ ነህ፣ ወለጋ ነህ፣ በመባባልና በማባባል ጊዜና ጉልበታቸውን በከንቱነት የሚያባክኑትን፣ ሁሉ በጽኑ ይወቅሳቸዋል፡፡
የታላላቆቹ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸው፣ የመንፈስና የሃሳብ አንድነት ነበር፡፡ የነዚያ አንድነት ደግሞ የኢትዮጵያ አንድነት ምሰሶ መሆኑ፣ በእኛ በልጆቻቸው ዘንድ ተዘንጊ ነገር አይደለም፡፡
የአዲስና የሃይማኖተ አበው መምህራቸው ጌታ አለቃ ገብረመድህን፣ ፍቅረነዋይ፤ ሲፀነሱ ጀምሮ ያልተጠጋቸው መሆናቸውን ይናገሩና “ዛዲያ ማለፊያ ልጅ እኔን ወለዱ - እንደሳቸው ገንዘብ እማልወድ” ይላሉ አለቃ ኃይሉ፡፡
ይህ የታላላቆች ሊቃውንት፣ አባቶቻችን መንፈሳዊ ትህትናና የመንፈስ ልግስና በአሁኑ በእኛ ጊዜ አያስፈልግም የሚለው ማነው? ምንድነው? - መልሱን ለአስተዋይ አንባቢ ትቻለሁ።” ይሉናል፡፡
የዘንድሮው እንቁጣጣሽ ከላይ የጠቀሰውን ቁምነገር ልብ የምንልበትና አዲሱን በአዲስ መንፈስ የምንቃኝበት ይሆን ዘንድ ቅን ልቦናና አመክንዮአዊ አስተሳሰብ ይስረጽብን!!
አሜን!
መልካም አዲስ ዓመት!!   

Read 10423 times