Saturday, 19 September 2020 12:58

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በተፈፀመ ጥቃት የበርካቶች ህይወት ጠፍቷል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   “በአካባቢው የሚፈፀሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶች አሳሳቢ ሆነዋል”

         በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በተፈፀሙ ጥቃቶች ከ120 በላይ ዜጐች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ያስታወቀ ሲሆን፤  የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ፤ በክልሉ እየተፈፀመ ያለው ግድያና የሰብአዊ መብት ጥሰት አሳሳቢ ሆኗል ብሏል፡፡
ከጳጉሜ 1 ቀን 2012 ጀምሮ በመተከል ዞን 6 ወረዳዎች ውስጥ በአማራና በአገው ተወላጆች ላይ ቀስትን ጨምሮ በተለያዩ የጦር መሣሪያዎች በተፈፀሙ ጥቃቶች 120 የሚደርሱ ዜጐች መገደላቸውን ብሉምበርግ ከ “አብን” ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ ዘግቧል፡፡  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈፀመው ግድያና መፈናቀል በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑን የገለፀው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፤ መንግስት በጉዳዩ ላይ አፋጣኝ እርምጃዎችን ሊወስድ ይገባል ብሏል፡፡
ኮሚሽኑ በክልሉ መተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ፣ ኢጳር ቀበሌ እንዲሁም ወንበራ ወረዳ መልካን ቀበሌዎች፣ እጅግ አሳሳቢ መረጃዎች እየደረሱት መሆኑን ጠቁሞ፣ በጳጉሜ 1 እና 3 መካከል ባሉ ቀናትም ሁለት ጊዜ ጥቃቶች መፈፀማቸውን ከክልሉ መንግስት ጭምር ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
በታጣቂዎች በሁለት ዙር በተፈፀሙ ጥቃቶች፣ በዜጐች ላይ ግድያ መፈፀሙንና በመቶዎች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸውን እንዳረጋገጠ የጠቆመው ያለው ኮሚሽኑ፤ ከተፈናቃዮቹ መካከል 300 ያህሉ ሁኔታዎች ሲረጋጉ ወደቀዬአቸው ተመልሰዋል  ብሏል፡፡
በክልሉ በዜጐች ላይ እየተፈፀሙ ያሉ ጥቃቶችን ከማስቆም ጐን ለጐን በአካባቢው ተደጋጋሚ ጥቃቶች ማጋጠማቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት ገለልተኛ፣ ፈጣንና ውጤታማ ምርመራዎችን በማካሄድ፣ በጥፋተኞች ላይ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡
ከዚህ ጥቃት ጋር በተያያዘ የፌደራል መንግስት ቸልታ እንዳሳሰበው የገለፀው የኢትዮጵያ ዜጐች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በበኩሉ፤ “በክልሉ በንፁሃን ዜጐች ላይ የሚደርሰውን ተደጋጋሚ ጭፍጨፋ መንግስት በአፋጣኝና በዘላቂነት ማስቆም አለበት” ብሏል፡፡
“በክልሉ በንፁሃን ዜጐች ላይ የሚደርሰው ተደጋጋሚ ጭፍጨፋና በመንግስት በኩል የሚሠጡ ችግር ፈቺ ያልሆኑ ምላሾች የችግሩ ምንጭ አካባቢውን የሚያስተዳድረው የመንግስት መዋቅርና ችግሩን በቸልታ እያየ ያለው የፌደራል መንግስት ነው ብለን እንድናምን አስገድዶናል” ያለው ኢዜማ፤ ከዚህ በፊት ለተፈፀሙ ተመሳሳይ ጥቃቶች እርምጃዎች ባለመወሰዳቸው ዛሬም የዜጐች ስቃይ እንዲቀጥል አድርጓል ብሏል፡፡
“አሁንም ክልሉን በሚመሩ ኃላፊዎች ላይ ማጣራት ተደርጐ እርምጃ ካልተወሰደ፣ ግድያና ማፈናቀሉ ይቆማል ብዬ አላምንም” ያለው ፓርቲው፤ በፌደራል መንግስት በኩል እንደነዚህ ያሉ ጥቃቶች ከመድረሳቸው በፊት የመከላከልና በፍጥነት የማስቆም ስራ  ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ብሏል፡፡
“መንግስት ቀዳሚ ተግባሩ የዜጐችን በህይወት መኖር ማክበርና ማስከበር ነው፤ ይሄን ማድረግ ያልቻለ መንግስት ስለ ልማትና ብልጽግና የማውራት የሞራል ልዕልና ሊኖረው አይችልም” ብሏል - ኢዜማ - በመግለጫው፡፡
የሰሞኑን ጥቃት ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ማንነትን መሠረት አድርገው የሚፈፀሙ ጥቃቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ጥሪ ያቀረበው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስቴ የምሁራን መማክርት ጉባኤ በበኩሉ፤ በተለይ በአማራ፣ አገውና ሌሎች ህዝቦች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች አሳሳቢ እየሆኑመ ጥተዋል ብሏል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት በሰጠው መግለጫ፤ “በክልሉ የተፈፀመው ጥቃት ከክልሉ የፀጥታ ሃይል በላይ አልነበረም፤ ሊከሰትም አይገባውም ነበር” ብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሠራዊቱ በአካባቢው የማረጋጋት ስራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁሞ፤ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ከ25ሺህ በላይ ዜጐችን ወደቀዬአቸው ለመመለስም ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክቷል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ ስር የሚገኘው ማህበረ ቅዱሳን በበኩሉ፤ 80 ምዕመናን ተገድለው 1 ቤተክርስቲያን ላይ የቃጠሎ ሙከራ እንደተደረገበትና 52 ያህሉ መዘጋታቸውን ያስታወቀ ሲሆን ከ7ሺህ በላይ ዜጐች መፈናቀላቸውንም አመልክቷል፡፡
Read 646 times