Saturday, 19 September 2020 13:42

ጐርፍን ተጐንብሶ የሚያሳልፍ ሰንበሌጥ፤ ቀና ለማለት ይበቃል! - የዶርዜዎች ተረትና ምሣሌ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

  በሀገራችን እውቅ እውቅ ኮሜዲያን እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ተዋናይ ወጋየሁ ንጋቱ (ሀገር ፍቅርና ብሔራዊ ቴአትር)፣ ተዋናይ አበራ ጆሮ (ሀገር ፍቅር ቴአትር)፣ ኮሜዲያን መላኩ አሻግሬ ፣ ኮሜዲያን ተስፋዬ ካሣ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ዛሬ ኮሜዲያን መላኩ አሻግሬ (ነፍሱን ይማረውና!) በህይወቱና በመድረክ ላይ ከተጫወታቸው አስቂኝ ትዕይንቶች አንዱን እንደ ትርክት እናወጋለን፡፡
በተለይ ዛሬ በሀገራችን የአስቂኝ ተውኔት ነገር ለዛውን እያጣና እየተሟዘዘ መምጣቱን የቲያትር ቤት መድረክ ትዕይንቶች የሚከታተልና ሬዲዮና ቴሌቪዥን የሚያይ የሚሰማ አድማጭ ተመልካች ሁሉ የታዘበውና የሚያውቀው ነው፡፡ ዛሬ ድንገት አስተዋጽኦ ቢሆንልን በሚል ከጥንቶቹ አንዱን እናስታውሳለን፡፡ እሱም ጋሽ መላኩ አሻግሬ እንደ ሽፍንፍን ያሉ ድንቅ ቧልታዊ ተውኔቶችን ከደረሱና ከተጫወቱ ተዋንያን መሀል ስመ ጥር የሆነ ባለሙያ ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ጋሽ መላኩ አሻግሬ በማዕከላዊ ምርመራ ድርጅት እሥር ቤት ይታሰራል፡፡ የታሠረበት ምክንያት “በአንድ መጠጥ ቤት ውስጥ የወቅቱን የሀገራችንን የኢትዮጵያ መሪ “ባሪያ ብለህ መሳደብህን የሀገር ፍቅር ካድሬ ሰምቶ፣ መስክሮ፣ ከሶሃል” የሚል ነበር፡፡
ይህም በወቅቱ በሀገራችን የፖለቲካ ቋንቋ “የአፍ - ዕላፊ ወንጀል” በመባል የሚታወቅ ነው፡፡ (በወቅቱ ብዙ የእላፊ ወንጀሎች ተብለው የሚያሳስሩ “እላፊዎች” ነበሩ፡፡
አስረጅ፡- “እግር - እላፊ” የኢትዮጵያን ድንበር በእግር ተሻግሮ ወደ ጐረቤት ሀገር መኮብለል፡፡
“ልብ - እላፊ” - መንግሥትን ለመገልበጥ ማሰብ፣ ማሴር፣ ማደም፡፡
“ጭን - እላፊ” - በወቅቱ በምሥራቅም፣ በሰሜንም ጦር ግንባር ጦርነቶች ይካሄዱ የነበረ ሲሆን፤ ወደ ጦር ግንባር የዘመተ ሚኒሻ ወይም መደበኛ ወታደር ሚስት በመድፈር የታሰሩ እስረኞች፤ የታሰሩበት ምክንያት በሚለው ቅጽ ላይ #በጭን - እላፊ; ተብሎ ይነቆጣል ማለት ነው፡፡ ወዘተ…
ብዙ የሀገራችን እውነት ሲቆይ ተረት ይመስላል፡፡ ከላይ በተጠቀሰው ዓይነት እንግዲህ ከእለታት አንድ ቀን ተዋናይና ደራሲ መላኩ አሻግሬ፤ በአፍ - እላፊ ታስሮ ማዕከላዊ ምርመራ ድርጅት ይመጣል፡፡
መዝጋቢው እሥረኛም ፎርሙን ወይም ቅጹን አዘጋጅቶ ይመዘግበዋል፡፡
መዝጋቢ  - “ስሞትን ማን ልበል?”
መላኩ   -  “መላኩ አሻግሬ” ይላል፤አቶ መላኩ፡፡
መዝጋቢ  -  “የት ተወለዱ?”
መላኩ   -  “አዲስ አበባ”
መዝጋቢ  -  “ሥራዎት?”
መላኩ   -  “ትወና፡፡ የትያትር ደራሲ፡፡”
መዝጋቢ  -  “የሚሰሩበት መሥሪያ ቤት?”
መላኩ   -  “ሀገር ፍቅር ቲያትር”
መዝጋቢ -  “የታሠሩበት ምክንያት?”
መላኩ   -  (አቶ መላኩ ያመነታል)
መዝጋቢ -  “ግዴለም አይፍሩ፤ ለፎርሙ እኮ ነው፡፡ እኔም እንደርስዎ ያው እስረኛ ነኝ፡፡ ነጠላ ጫማዬን አያዩም?” ብሎ እግሩን አንስቶ ለአቶ መላኩ ያሳያል፡፡
ከዚያም፤ “እሺ አቶ መላኩ ይንገሩኝ? የታሠሩበትን ምክንያት--የፖለቲካ ዘለፋ… አፍ - እላፊ… ህገወጥ ንግግር? የሀገሪቱን መሪ በመሳደብ…የቱን ብጽፍ ይሻላል?;
አቶ መላኩም - “ይኸውልህ የኔ ልጅ፤…እንግዲህ የሀገር ፍቅር ቲያትር ሠራተኛ አይደለሁ?;
መዝጋቢ     - #አዎን;
አቶ መላኩ -  #ያሳሰረኝ የሀገር ፍቅር ካድሬ አደለ?”
መዝጋቢ   -  “አዎን”
አቶ መላኩ - “የሀገሪቱን መሪ ሰደብክ ብለው አይደል ያሰሩኝ?”
መዝጋቢ   - “አዎን”
አቶ መላኩ - “እንግዲያው የታሠረበት ምክንያት የሚለው ጐን ምንም ምንም ሳትጨምር - “በሀገር ፍቅር ምክንያት በልልኝ፡፡”
*   *   *
በዚያው በሀገር ፍቅር ቲያትር (ነፍሱን ይማረውና) መሠንቆ በመጫወት የሚታወቅ የነበረው ድምፃዊ ጌታመሳይ አበበ ነበር፡፡ ከጌታመሳይ ዜማዎችና ግጥሞች አንዱ የሚከተለው የሚገኝበት ሲሆን፤ይሄንኑ ግጥምና ዜማ አንድ ፈረንጅ ሀገር ኗሪ የሆነ ኢትዮጵያዊ ለፈረንጁ ህብረተሰብ ሊጫወተው ፈልጐ በዚያው በጌታመሳይ ዜማ እንደሚከተለው ተርጉሞ ይዘፍነዋል፡፡ ዘፈኑ፡-
#የሽንብራው ጥርጥር የዛፎቹ ፍሬ
የትም የትም ዞሬ ትዝ አለኝ ሀገሬ፡፡”
በሚለው ዜማ የቀረበ ነው፡፡ ለትርጉም የበቃውና የቀረበው ግጥም ግን እንዲህ ይላል በአማርኛ ፡-
“ክፉንም ደጉንም አብረን ተካፍለናል
ትላንት ዛሬ አይደለም ምን ያስጨንቀናል”
የእንግሊዝኛ ትርጉሙ፡-
 “The good and the bad things we have shared  together
 Yesterday is not today, why do we bother?”
 የሚል ነው፡፡ የእንግሊዝኛው ግጥም በአማርኛ ዜማ ሲተረጐም እጅግ አስቂኝ ሆነ፡፡ የተጨበጨበለት ነበር፡፡
የምንረግጠው አፈር የምናርፍበት መንገድ ሁሉ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ የባሕል አዳራሽ መስካሪ ነው፡፡ በኮሮና ምክንያት ማደግያ ቦታ ብናጣ፤ ግቢ ውጪያችን በበሽታ የተከበበ ነው ብንባልም ከጥንቃቄ ጉድለት ከፍጹም እንዝላልነት በስተቀር በቀላሉ የሚጐዳን ሁኔታ ውስጥ አንመሰግም፡፡
“ዛር ልመና ሳይያዙ ገና
ከተያዙ ብዙ ነው መዘዙ”
--የሚለውን የጥንት የጠዋት እምነትና አስተሳሰብ ዛሬም አበክረን ማውጠንጠን የእግር መንገድ ብቻ ሳይሆን ዋና አውራ ጐዳናችን ሊሆን ይገባዋል፡፡ እና ደግሞ በወጉና በጥናት ላይ ተመስርቶ ማቀድን መተግበርንና ውጤቱን የት ደረስክ ማለትን በጐ የሚጠይቅ ምግባር ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ለሀገራችን አይነተኛ ችግር፤ ከሰው ሃይል አመዳደብና አቀናጅቶ ከመምራት ክህሎት ማጣት የመጣ ነው፡፡ ሁለቱንም ችግሮች በአግባቡ መፍታት ዋና ነገር ነው፡፡
በኮሮና አንፃር ሲጤን፤ የትምህርት ዘመን መዛባት ከሁሉም አሳሳቢው ስጋት ነው፡፡ የነገን ተረካቢ ትውልድ የጉዞ አቅጣጫውን ለመወሰን ብርቱ መንፈሳዊና ማቴሪያሊያዊ ብቃት ልንላበስ ይገባናል፡፡ በዓለም ላይ የኮሮናንና የትውልድን የነገ ህልውና አሰናስለን፣ የትምህርት ቤቶችን ለጤና አስተማማኝነት ካላሰብንበት በደብዛዛው ማየት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ከኪንደር ጋርደን ህፃናት ወጣቶችና ጐልማሳዎች እንዲሁም አዋቂዎች ድረስ ሥራዬ ብሎ ሁኔታቸውን የሚያጠና፣ ያሉበትን ደረጃ የትምህርት ዘመን ከመጐዳቱ በፊት የሚያቅድና የሚተገብር እንዲሁም አስፈላጊውን እርምጃ የሚወስድ ጠንካራ የመንግሥት አቅም እንደ ታላቅ ኃይል ሊታመንበት ይገባል፡፡ አሁን ባለን አንድም የበሽታውን አደገኛነት ያለማመዛዘን፤ አንድም የመንግሥት ተፃራሪ ኃይሎችን ቸል ባይነት የሚጠቁም ጠንካራ አስጠንቃቂና አስታዋሽ ደወል (Alarm) ያስፈልጋል፡፡ በሱቅና በሱፐር ማርኬት ደጃፍ የታሰረው ገመድ የማስጠንቀቂያ ደወል እንጂ የአትሌቶች የሩጫ መፈፀሚያ፣ የሪኮርድ መስበሪያ ኬላ አይደለም፡፡ በገመድ ስር መሹለክማ ተለምዶ ሃይ ባይ ያጣ ሆኗል፡፡ አንድ ሰሞን ማህበራዊ መራራቅ ተብሎ ነበር፡፡ ያንድ ሰሞን ቅንጦት መስሎ ከታየ ግን ሰነባብቷል፡፡ እንጠንቀቅ!
“ቅንዝንና የቀን ጐባጣን
ስቀህ አሳልፈው ሲያምርህ ሰው መሆን!”
-- ያሉትን ደራሲ አፈወርቅ ዮሐንስን አለመዘንጋት ነው፡፡
ብልህ ህዝብ አይቸኩልም!
ፈጥኖ ለመናገር አይጣደፍም!
የተናገረው ልክ ሆኖ ሲገኝም፤ “አላልኳችሁም!” ብሎ አይደገግም!
መርዶ ነግሮ ሰው ሲያለቅስ “እኔ ባመጣሁት ለቅሶ አዳም ተሰቀሰቀሰ; ብሎ በመርዶው አይኩራራም፡፡
ይልቁንም በማስጠንቀቅና ልብ አርጉ በማለት ያዝናል፡፡ ስለዚህም ህዝብና መሪውን ከጥፋት ያድናል!
ያም ሆኖ ኢትዮጵያ በፈጣሪዋ ፀጋ የምትኖር ሀገር ናት፡፡ ይቅር መባባልን ታከብራለች፡፡ ለእርቅና ለሽምግልና ቦታ ትሰጣለች፡፡  ከሁሉም በላይ ደግሞ ተመስገን ማለትን በቅጡ ታውቃለች፡፡
“ተመስገን ይሏል ሰው ባያሌው ታሞ
ካማረሩትማ ይጨምራል ደሞ!”
-- የሚለውን ለዘመናት በማክበሯ በምስጋናዋ ኖረናል፡፡
ያም ሆኖ ብልህነት አላጣችም፡፡ ያለ የሌላትን ኃይል አንድ ጉዳይ ላይ በማዋል አቅሟን አላሟጠጠችም፡፡ በዚያ ላይ ክፉ ጊዜ ከመጣ፣ ህዝቧም እሷም መላውን ያውቃሉ፡፡ ጐርፍን ተጐንብሶ የሚያሳልፍ ሰንበሌጥ፤ ቀና ለማለት ይበቃል!!


Read 19508 times