Saturday, 19 September 2020 13:53

2013ዓ/ም የሰላም፤ የጤና፤ የእድገት ይሁንልን፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 2012 ከተሰናበተ እና 2013 እንኩዋን ደህና መጣህ ከተባለ እነሆ አንድ ሳምንት ሞላው፡፡ ማንኛውም አዲስ ነገር ሲገጥም ለተወሰኑ ጊዜያት የማይረሳ ትውስታ እንደሚኖረው እሙን ነው። ስለሆነም የአለም ህዝብ ከ2019 በኢትዮጵያ ደግሞ ከ2012 አጋማሽ ጀምሮ የማይረሳ ትውስታ የሚኖረውና አሁንም ገና እዚህ በቃ ያልተባለው (COVUD-19) የኮሮና ቫይረስ ጉዳይ በዚህ አምድ ሲዘገብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ አበይት የሆኑትን በ2013 የመጀመሪያው ወር ላይ ለማስታወስ እና ለጥንቃቄ እንዲረዱ ለንባብ ብለናቸዋል፡፡
የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር  በተለይም በእርግዝና ላይ ላሉ ሴቶች ለጥንቃቄ እንዲረዳ የተለያዩ አለም አቀፍ መረጃዎችን አጣቅሶ ለንባብ ያለው በቅድሚያ ነበር፡፡ ከነጥቦቹም መካከል የሚከተሉት ይኙበታል፡፡
 1. የኮሮና ቫይረስ በነፍሰ ጡር እናቶች ላይ ምን ያስከትላል?
እስከ አሁን ባለው መረጃ መሰረት የነፍሰ ጡር እናቶች ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል በተለየ ሁኔታ ከባድ የሆነ የጤና እክል አልታየባቸውም። ሆኖም አዲስ ቫይረስ ስለሆነ በሽታው እንዴት የነፍሰ ጡር  ጤንነትን እንደሚያውክ ገና በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም። አብዛኛው የነፍሰ ጡር እናቶች ግን ቀላል ወይም መለስተኛ የሆነ የጉንፋን በሽታን የሚመስል ምልክት ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በቫይረሱ ከፍተኛ የሆነ የጤና እክል የሚታይባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች፤ አዛውንቶች፣ የተዳ ከመ የበሽታ መከላከል አቅም ያላቸው ወይም የሰነበተና የታወቀ በሽታ ያላቸው ናቸው።
እርግዝና ሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅሙን ስለሚቀንስ፤ አንድ ነፍሰ ጡር ሴት በትንፋሽ ለሚተላለፉ የበሽታ አምጪ ቫይረስ  ያላት ተጋላጭነት እጅግ ከፍ ያለ ነው። ነፍሰ ጡሯ የሰነበተና የታወቀ በሽታ ለምሳሌ የአስም ወይም የስኳር ህመምተኛ ከሆነች፤ ኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ የሆነ የጤና እክል ሊያስከትልባት ይችላል።
2. የነፍሰ ጡር እናት በምርመራ የተረጋገጠ የኮሮና ቫይረስ ህመምተኛ ከሆነች፤ ጽንሱ ላይ ምን ሊከሰት ይችላል?
የኮሮና ቫይረስ አዲስ የበሽታ አምጪ ህዋስ በመሆኑ ባህሪው ገና ያልታወቀ ፤ ከፍተኛ ምርምር  እየተደረገበት ያለ ቫይረስ ነው። እስከ አሁን ያሉት ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ግን፤ ቫይረሱ ውርጃን ስለማስከሰቱ ወይም እድገት ላይ ወዳለው ሽል ስለመተላለፉ የሚያሳይ መረጃ የለም።
ሌሎች ነጥቦችም ከላይ ከተጠቀሱት መሰረታዊ ነጥቦች ጋር የተላለፉ ሲሆን እነዚያ ግን በማን ኛውም ጊዜ ለማንኛውም ሰው እየተነገሩ ካሉት በግል እና በሕክምና አገልግሎት ሊወሰዱ ከሚገ ባቸው የጥንቃቄ አተገባበሮች መካከል ናቸው፡፡
የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር ካወጣቸው ጠቃሚ ነጥቦች በተጨማሪም የአለም የጤና ድርጅት ከተለያዩ አካባቢዎች ለሚደርሱት ጥያቄ ዎች የሰጠው መልስ በዚሁ አምድ ለንባብ መባሉ ይታወሳል፡፡ ከጥያቄና መልሶቹ መካል ቀንጨብ ያደረግናቸው የሚከተሉት ናቸው፡፡  
በእርግዝና ላይ ያለች ሴት ሕመሙ ሳይሰማት አስቀድማ የኮሮና ቫይረስን ምርመራ ማድረግ አለባትን?
የህክምና ምርመራ ማድረግ ይገባታል አይገባትም የሚለውን ከመወሰን በፊት ሁኔታው እንደሚ ኖሩበት ቦታና ሁኔታ የሚለያይ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን WHO የሚሰጠው ምክር አለ፡፡ በእርግዝና ላይ ያሉ ሴቶች የኮሮና ቫይረስ ስሜት ሲኖራቸው ከምንም ነገር በማስቀ ደም ምርመራ ማድረግ አለባቸው፡፡ የኮሮና ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ካለ ልዩ እና የተለየ እንክ ብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡
COVID-19 ከእናትየው ወደ ጽንሱ ወይንም ወደ ጨቅላው ይተላለፋልን?
አንዲት እርጉዝ ሴት የኮሮና ቫይረስ ቢኖርባት ወደ ጽንሱ ወይንም በማህጸን ውስጥ ወደአለ ህጻን መተላለፉ እስከአሁን ድረስ ግልጽ አይደለም። እስከአሁን ድረስ ቫይረሱ በጽንሱ ላይ ወይንም በተወለደው ልጅ ላይ ለመተላለፍ የሚያበቃው ምክንያት በሽርትውሀም ይሁን በእናት ጡት ወተት አልተገኘም፡፡  
በእርግዝናና ልጅ በመውለድ ጊዜ ምቹ የሆነ የጤና አገልግሎት ይኖራልን?
ሁሉም በእርግዝና ላይ ያሉ ሴቶች እና የኮሮና ቫይረስ እንዳለባቸው የተገመተ ወይንም የተረ ጋገጠላቸው ሴቶች ጥራት እና ብቃት ያለው የጤና አገልግሎትን ከመውለዳቸው በፊትም ይሁን ከወለዱ በሁዋላ የማግኘት መብት አላቸው፡፡ ይህም ልጅ ከመወለድ በፊት ፤አዲስ የተወለዱትንና ከተወለዱ በሁዋላ ያሉትን ጨቅላዎች የጤና ክትትል ይጨምራል፡፡  
ደህንነቱ የተጠበቀ እና ጥሩ የሚባል ልጅ አወላለድ የሚከተሉትን አገልግሎት ማግኘት ይፈልጋል፡፡
ክብርና ጥሩ ቀረቤታ ባለው መንገድ የጤና አገልግሎትን ማግኘት፤
በመውለድ ጊዜ የሚተማመኑበት፤ የሚፈልጉትን የሚያሟሉበት እድል መኖር፤
ከአዋላጅ የህክምና ባለሙያዎች ጋር ግልጽ የሆነ ግንኙነት፤  
ተገቢ የሆነ ህመምን የሚያስታግስ ዘዴ መኖር፤
ምጥ እንደአመጣጡ እንዲስተናገድ እና በምን መንገድ ሊወለድ እንደሚችል ማሳወቅ፤
የመሳሰሉት ተግባራት በማዋለድ ስራ ላይ ከተሰማሩት ባለሙያዎች ይጠበቃል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ሌላው ለንባብ የቀረበው ነገር ያልታቀደ እርግዝናን የመከላከል እና ጽንስን በህጋዊ እና ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ የማስወገድ ተግባር ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ April/2020 ጉትማቸር እንደተነበየው በታዳጊ አገራት አገልግሎቱ ወደ 10% የሚቀንስ ሲሆን ኮሮና ቫይ ረስን ለመከላከል በወጣው ራስን ከቫይረሱ የመከላከል ህግ ምክንያት በቤት መቆየት የሚለው አሰራር ችግሩን ወደ 15 ሚሊዮን ተጨማሪ ያልታቀዱ እርግዝናዎች እንዲከሰቱ ምክንያት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህም ውጤቱ 168,000 ተጨማሪ የጨቅላ ዎች ሞት፤ 28,000 ተጨማሪ የእናቶች ሞት እና ሶስት ሚሊዮን ደህንነቱ ያልተጠበቀ የጽንስ ማቋረጥ ይከሰታል ተብሎ ይገመታል፡፡
የጉትማቸር ኢንስቲቲዩት ጥናት እንደሚያስረዳው የኮሮና ቫይረስን በመፍራት ያልተፈለገ እርግዝናን ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ ለማስወገድ አገልግሎቱን ማግኘት ባልቻሉ ሀገራት ሴቶች ደህንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ ድርጊቱን መፈጸማቸው ስለማይቀር ቢያንስ ቢያንስ 22,800 ሴቶች በየአመቱ ሊሞቱ ይችላሉ ተብሎ ይገመታል።
ሜሪ ስቶፕስ ኢንተርናሽናል በ34 ሀገራት ያለውን አፈጻጸም በሚመለከት ባወጣው ሪፖርት የሚያሳየው እ.ኤ.አ ከ January- June ከሁለት ሚሊዮን በታች የሚሆኑ ሴቶች የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት ያገኙ ሲሆን ይህም ቀደም ሲል ከነበሩት ተመሳሳይ ጊዜያት እጅግ በጣም የተለየ ነው። ጥናቱ እንደሚገምተው በዚህ ጊዜ የተከሰተው የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት ዝቅተኛ መሆን ምናልባትም ወደ 1.5 ሚሊዮን ያልተፈለገ እርግዝና በህገወጥ መንገድ እንዲ ቋረጥና 900,000 ያልታቀደ እርግዝና እንዲከሰት እንዲሁም ወደ 3,000 ሞቶችን እንደሚያስ ከትል ነው፡፡
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት COVID-19ን ለመከላከል በቤት ውስት መቆየት፤ የመጉ ዋጉዋዣ ሁኔታዎችን መፍራት ፤አገልግሎቱን ለፈላጊዎች የማዳረስ ችግር፤እንዲሁም በአንዳ ንድ ቦታዎች የኮሮና ቫይረስን መከላከል ቅድሚያ ተሰጥቶት ለስነተዋልዶ ጤና አገል ግሎት ይውል የነበረውን አቅም ወደዚያ ማዞር፤በሕክምናው ወቅት ሊከሰት ይችላል የሚባለውን ኢንፌ ክሽን መፍራት…ወዘተ የመሳሰሉት የተለመደውን አሰራር እንዳይረብሹት ስጋት አለ፡፡ ከላይ የተገለጹት ምንያቶች ሁሉ ተዳምረው የብዙዎችን ህይወት የሚቀጥፈው ያልታቀደ እርግዝናን ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ መከላከልና አስቀድሞም መከላከል የሚያስች ለውን አገልግሎት ችላ ማለትም እንዳይኖር በአለም አቀፍ ደረጃ በተለይም ታዳጊ በሆኑት ሀገራት ልብ ሊባል የሚገ ባው ነገር መሆኑን ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡


Read 18524 times