Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 28 July 2012 10:26

“የመጣነው መንገድ” ብቻ ሳይሆን “የምንሄደው መንገድም” ያሳዝናል እንዳንል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ናብሊስ” የሚለው መጽሐፍ የሚከተለውን ተረት ይነግረናል፡፡

በጥንት ዘመን አንድ በጣም ብልህ ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ነበር ይባላል፡፡ በእርሱ ዘመን አንጥረኞች፣ ሸማኔዎች፣ ቆዳ ሠሪዎች፣ የሸክላ ሥራ ባለሙያዎች እጅግ የተከበሩ ባለሙያዎች ነበሩ፡፡ ሀገሪቱ እጅግ ባለፀጋ ህዝቡም ጠግቦ የሚያድር ነበረ፡፡ ይህ ብቻ ግን ንጉሡን በጣም አላረካውም፡፡ አንጥረኞቹ አንድ ግዙፍና ያማረ ደወል አንዲሠሩለት አደረገ፡፡ ይህ ደወል ድምፁ ከሩቅ የሚሰማ ደወል ነው፡፡ በገበያ መካከል በጠንካራ እንጨቶች ላይ እንዲሰቀልና የመደወያው ገመድ እጅግ ዝቅ ብሎ ወደ መሬት እንዲወርድ አስደረገ፡፡ ንጉሡ በአንድ የበዓል ቀን ህዝቡን ሁሉ በደወሉ ዙሪያ ሰብስቦ እንዲህ አላቸው

“…ድህነትን ከሀገር አስወጥተናል፡፡ ነገር ግን በምትኩ ጥጋብ ተኩራርቶ ወደ ሀገራችን ገብቷል፡፡ ጥጋብ የሚፈጥረው ዕብሪት የትውልድን ቅስም ይሰብራል፡፡ ሰው ሲጠግብ አምባገነን ይሆናል፤” ፍርደ ገምድልነት ይበዛል፡፡ በዚም ደሀ ይበደላል፡፡ ረሃብና ጥማት አስከፊ ነው፤ ከሁሉም በላይ አስከፊ የሚሆነው ግን የፍትህ ጥማት ነው፡፡ ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ማንም የዚህች ሀገር ዜጋ አንዳች በደል ቢደርስበት ወደዚህ ደወል መጥቶ ይደውል፡፡ ዳኞችና ታዛቢዎች ወዲያው መጥተው ተሰብስበው ውሎ ሳያድር ትክክለኛ ፍርድ ይሰጣሉ፡፡ ስለዚህ የሀገሬ ህዝብ ሆይ ይህንን የፍትሕ ደወል እንደነብስህ ጠብቅ፤ በዚህ ደወል ፊት ሁሉም እኩል ይዳኛል፡፡ ምህረት ብሎ ነገር አይሠራም!...” ለዚህ ንግግር ህዝቡ ደስታውን በዕልልታና በሆታ ገለፁ፡፡ ከዚያ ወዲህ በዚህ ደወል አማካኝነት ብዙ ደወል ተሰማ፤ ብዙ ፍትሕ ተሰጠ፡፡ ብዙ አጥፊም ተቀጣ፡፡ ከዘመናት ብዛት ግን የደወሉ ገመድ በማጠሩ ሰው ተንጠራርቶ እንኳ የማይደርስበት ነው፡፡ ስለዚህ ተበደልኩ ብሎ የሚደውል ጠፋ፡፡ የመንደሩ ወጣቶች አዲስ ገመድ ሠርተው እንደገና አንጠለጠሉት፡፡

በዚህ ዘመን አንድ የታወቀ ጠበቃ ነበር ይበላል፡፡ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስበት አንድ ታማኝና ረዳት በቅሎ ነበረው፡፡ ከብዙ አደገኛ ሽፍታዎችና ከውሃ ሙላትም ጭምር ያዳነው በቅሎ ነው፡፡ ታላቁ ጠበቃ ዕድሜው ሲገፋ አራጣ ማበደርና ንብረት በዋስትና መያዝ ነው ሥራው፡፡

በወለድ አግድ የያዘው በርካታ ጋሻ መሬት አለው፡፡ የመንደሩን ሰው በአራጣ ባለዕዳ አድርጓል፡፡ ሀሳቡ ሁሉ ገንዘብ፣ ወርቅ እና ብር ብቻ ሆኗል፡፡ ሰውን ሁሉ ርቆ በመጨረሻ ከበቅሎው ጋር ቀረ፡፡ ቀን ቀን በቅሎውን ጋጣ ውስጥ ዘግቶ፣ እሱ ሀብቱን ሲቆጥር ይውላል፡፡ ሌሊት ሌባ ይመጣል ብሎ እንቅልፍ አጥቶ ያድራል፡፡ በቅሎው በረሃብ ሊሞት ሆነ! የበቅሎው የጣዕር ጩኸት ግቢውን ረበሸ፡፡ ጠበቃው ተናዶ “አንተን ከምቀልብ ጅብ ቢበላ እፀድቃለ” ብሎ ፈትቶ አባረረው፡፡

በቅሎው ላይ ህፃናት ድንጋይ ወረወሩበት፣ ውሾች ጮሁበት! የሚበላ ሲፈልግ የደወሉን በሣር የተገመደ መስቀያ አየ፡፡ ገመዱን ለመብላት ሲስበው ደወሉ መደወል ጀመረ፡፡ ያገሬው ሰው ምን መጣ ብሎ ወጣ! “ፍትሕ ይታይልኝ!” ማለቱ ነው አለ ህዝቡ! ዳኞች ተሰበሰቡ፡፡ በቅሎው ቅን አገልጋይ እንደነበረና ጠበቃው በግፍ እንዳባረረው ተነጋገሩ፡፡ ከአውሬና ከጠላት ጌታውን እንዳዳነ ህዝቡም መሰከረ! ጠበቃው ተጠርቶ በዘመኑ ለድሆች የቆመ ሃብታቸውን ያስመለሰ ሰው እንደነበርና አሁን ግን ሆዳምና ስግብግብ እንደሆነ፣ ህዘቡን በአራጣ ማስጨነቁን፣ “መቼ እንደምትበላው ባይታወቅም ሠራተኞችህን እያስራብክ ገንዘብ መሰብሰብ ብቻ ሆኗል ሥራህ!” በማለት አስረድተው፤ “ይህን ያለህን ሃብት እንድትሰበስብ ያደረገህ ይህ በቅሎ ሲሆን አንተ ግን ጉልበቱ ሲደክም ለጅብ አውጥተህ ጥለኸዋል! ስለዚህ የሰበሰብከው ሀብት ሁሉ እኩሌታው የርሱ ይሆናል፡፡ አስተዳዳሪዎች ይቀጠሩለታል፡፡ አዲስ ጋጣ ይሠራለታል! ከርስትህ ለምለሙ ሜዳ ላይ ፀሐይ እንዲሞቅበትና ሲደክመው እንዲያርፍበት ተወስኖለታል!!” ሲሉ ፈረዱ፡፡ ህዝቡ ደስታውን በሆታ ገለፀ!

***

የሀገራችን አንድ ዋና ችግር የፍትሕ መታጣትና የሙስና ቤት ደጁን ማጣበብ ነው፡፡ ገንዘብ ተበድረንም ተለቅተንም፣ ሱሪ ባንገት አስወልቀንም ሰብስበን ማን እንደሚቦጠቡጠው ሳይታወቅ ይባክናሉ፡፡ ትላንት እዚህ ግባ የማይባል ሀብት የሌለው ሰው ድንገት በአንድ ጀንበር ሚሊዮኔር ይሆናል፡፡ ወይ አልሮጠ፣ ወይ አልዘፈነ፣ ወይ አበባ አልተከለ፣ ወይ ኤክስፖርት አላረገ ወይ ነዳጅ አላወጣ…እጁን አጣጥፎ ምላሱን ዘርግፎ እንደነገ ድንገቴ (nuveau riche እንዲሉ) ድንገት ወርቅ በወርቅ መሆን አስገራሚ ነው!! አገራችን ጥቂቶች የዝሆን ጥርስ ማማ ላይ (ivory Tower እንዲል ፈረንጅ) የሚቀመጡባት፣ ብዙሃን መንገድ ላይ የሚያኩባት አገር እየሆነች ነው፡፡ ከበረሃ እስከ ከተማ ተሞተላት፣ ተሰዋባት የተባለችው አገርና ይመጣል የተባለው ለውጥ አምርተን አምርተን ኑሮ ውድነት ላይ የምናርፍ ከሆነ፣ ተምረን ተምረን ሥራ አጥነት ጥላ ሥር የምንጠለል ከሆነ፣ በብሔረሰብ ጀምረን ሃይማኖት ውስብስብ ውስጥ የምንገባ ከሆነ፣ ከዘፋኙ ጋር “የመጣነው መንገድ ያሳዝናል” ማለት ብቻ ሳይሆን “የምንሄደው መንገድም ያሳዝናል” ልንል እንገደዳለን!

 

 

Read 4317 times Last modified on Saturday, 28 July 2012 10:32