Thursday, 01 October 2020 11:37

ኢትዮ ቴሌኮም፤ ደንበኞች በሞባይል ስልክ ቁጥር ሊፈጸም ከሚችል ወንጀል እንዲጠነቀቁ አሳሰበ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   ኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞቹ በተለያየ አጋጣሚ የሞባይል ስልካቸው በሚጠፋበት ጊዜ ወዲያውኑ ባለማዘጋታቸው እንዲሁም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የስልክ መስመራቸውን (ሲም ካርዳቸውን) ለሶስተኛ ወገን አሳልፈው በመስጠታቸው የተነሳ ወንጀለኞች የስልክ መስመሩን ለተለያዩ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀሎች የሚጠቀሙበት በመሆኑ፣ ደንበኞች ለእንግልትና ለወንጀል ድርጊት ተጠያቂነት እየተዳረጉ መሆኑን ጠቁሞ፤ ኩባንያውንም ለከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ እየዳረጉ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
ኩባንያው በቴክኖሎጂ የታገዘ የቁጥጥርና የክትትል ሥርዓት በመዘርጋት፣ ቀደም ሲል የቴሌኮም መሠረተ ልማቶችን በመጠቀም ሲፈፀሙ የነበሩ የማጭበርበር ወንጀሎችን የቀነሰ ቢሆንም፤ ህገወጦች በደንበኞች በኩል የሚስተዋለውን ክፍተት በመጠቀም፣ የሚፈጽሙት የማጭበርበር ድርጊት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ብሏል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘም፤ በ2012 ዓ.ም ብቻ በ130 ሺህ የስልክ መስመሮች የቴሌኮም ማጭበርበር ድርጊት የተፈፀመ ሲሆን በዚህም ኩባንያው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ኪሳራ እንደገጠመው አስታውቋል፡፡
ደንበኞች የሞባይል ስልካቸው በሚጠፋባቸው ጊዜ ወደ ኩባንያው 994 የጥሪ ማዕከል በመደወል፣ በ8994 አጭር የጽሑፍ መልዕክት በመላክ ወይም ይፋዊ የማህበራዊ ድረገፆችን በመጠቀም፣ ወዲያውኑ መስመራቸውን እንዲያዘጉና በአቅራቢያቸው ከሚገኝ የሽያጭ ማዕከል ምትክ ሲም ካርድ እንዲወስዱ የጠቆመው ኢትዮ - ቴሌኮም፤ የስልክ መስመራቸውን ለሶስተኛ ወገን አሳልፈው ከመስጠት በመቆጠብም፣ ራሳቸውን ከአጭበርባሪዎች የወንጀል ድርጊት እንዲከላከሉ አሳስቧል፡፡

Read 2562 times