Saturday, 26 September 2020 00:00

ቀነኒሳ ከኪፕቾጌ በ40ኛው የለንደን ማራቶን ላይ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

• በሁሉም ውድድሮች 20 ጊዜ ተገናኝተው ቀነኒሳ በ13 ሲያሸንፍ ኪፕቾጌ በ7 ድል ቀንቶታል፡፡ ቀነኒሳ ትራክ ላይ 11 ጊዜ ሲያሸንፍ ኪፕቾጌ በ4        ማራቶኖች ተገናኝተው ሁሉንም ድል አድርጓል፡፡
     • በሩጫ ዘመናቸው ቀነኒሳ 116 ውድድሮችን አሸንፏል፤ከ1,889,563 ዶላር በላይ ከሽልማት ገንዘብ አግኝቷል፡፡ ኪፕቾጌ 69 ውድድሮችን         አሸንፏል፤ከ2,112,540 ዶላር በላይ ከሽልማት ገንዘብ አግኝቷል፡፡
     • ቀነኒሳ በሁሉም ውድድሮች 31 ሜዳልያዎች (26 የወርቅ፤3 የብርና2 የነሐስ)  ኪፕቾጌ በሁሉም ውድድሮች 17 ሜዳልያዎች (11 የወርቅ፤4 የብርና         2 የነሐስ) ሰብስበዋል፡፡


            ከሳምንት በኋላ በሚካሄደው 40ኛው የለንደን ማራቶን ላይ ኢትዮጵያዊው ቀነኒሳ በቀለና ኬንያዊው ኤሊውድ ኪፕቾጌ ይገናኛሉ። ሁለቱ የረጅም ርቀት የምንግዜም ምርጥ ሯጮች በማራቶን ውድድር ሲገናኙ ለአምስተኛ ጊዜ ሲሆን አስቀድመው በተገናኙባቸው 4 ማራቶኖች ኪፕቾጌ አሸናፊ ሆኗል፡፡
በዓለም አቀፍ ኩባንያቸው ግሎባል አትሌቲክስ ስር ሁለቱንም አትሌቶች በማናጀርነት የሚያገለግሉት  ጆስ ሄርማንስ በሁለቱ ምርጥ አትሌቶች መገናኘት የተደሰቱ ሲሆን  ለሚመዘገበው ውጤት መጓጓታቸውን ሌትስ ራን ድረገፅ በዘገባው አትቷል፡፡ ጆስ ሄርማንስ እንደተናገሩት  ከመደበኛው የለንደን ማራቶን ድባብና መሮጫ በተለየ በተዘጋጀው ጎዳና ላይ መወዳደራቸው ፈጣን ሰዓት የሚመዘገብበትን እድል የሚያሰፋው ቢሆንም፤ የዓለም ሪከርድን የሚሰበርበት ሁኔታ ግን የሚያጠራጥር ነው፡፡ ወደ ማራቶን ውድድር ከገቡ በኋላ በአሜሪካው የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ናይኪ ስፖንሰር ስር ያሉት ቀነኒሳ እና ኪፕቾጌ ኤንኤን ራነኒንግ በሚል ፕሮጀክት ባንድ ማልያ የሚሮጡ ናቸው፡፡
 በኮሮና ሳቢያ የተፈጠረው የልምምድ መስተጓጎልና  የአትሌቶቹ ወቅታዊ ብቃት በሪከርድ ሰዓት ለመሮጥ እንደማያመች ነው የሚገለፀው፡፡ እንግሊዛዊው የረጅም ርቀት ሯጭ ሞፋራህ በውድድሩ አሯሯጭ ሆኖ እንደሚሰለፍ እየተገለፀ ሲሆን ማራቶኑ በኮሮና ወረርሽኝ የዓለም ስፖርት ለወራት ከተቋረጠ በኋላየሚካሄድ ትልቅ ውድድር በመሆኑ ስኬቱ የዓለምን ልዩ ትኩረት የሚስብ ይሆናል፡፡
የለንደን ማራቶን አዘጋጆች ለውድድሩ 1.9 ኪሜትር ርዝማኔ ያለውና እንደ ቀለበት የሚዞር የመሮጫ ጎዳና አዘጋጅተዋል፡፡ ሙሉ የማራቶን ርቀቱን ለመሸፈን ተሳታፊ አትሌቶች 22 ጊዜ ቀለበታማ ጎዳናውን መዞር ይኖርባቸዋል። ዘንድሮ ብዙሃኑን የሩጫ ተሳታፊዎች የማያካትተው ውድድሩ በመንገድ ላይ ደጋፊዎችም አይኖሩትም፡፡
የመሮጫው ጎዳና በሴንት ጀምስ ፓርክ ዙርያ የሚሽከረከር ሲሆን የአካባቢው የአየር ሁኔታ በብዝሃ ህይወት የደገፈ፤ የኦሎምፒክ መስፈርትን የሚያሟላ የፎርሙላ ዋን እና የኪሪኬት ስፖርቶች መናሐርያ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ‹‹በበርካታ የተለያዩ ሁኔታዎች ላይ ለወራት ስንሰራ ቆይተናል፡፡
የሯጮቻችንን፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶቻችንን፣ የስፖንሰሮቻችንን፣ የበጎ ፈቃደኞቻችንን፣ የህክምና ባለሙያዎቻችንን  እና የከተማችንን ጤና እና ደህንነት ማስጠበቅ ሁል ጊዜ ቅድሚያ የምንሰጠው ነው፡፡›› በማለት የውድድሩ ዲያሬክተር ሁግ ብራሸር ለዎርልድ አትሌቲክስ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
የዓለም ማራቶን ሪከርድን የያዘው ኤሊውድ ኪፕቾጌ የለንደን ማራቶን ከመደበኛው ወቅት በ2 ወራት መሸጋሸጉ የዝግጅት ሁኔታዎችን እንዳስተጓጎለበት ተናግሯል፡፡ ‹‹አስቀድሜ ያቀድኳቸው ነገሮች ፈርሰውብኛል፡፡ እንደፈለግኩ በነፃነት ልምምዶችን እየሰራሁ አልነበረም፡፡ ለብቻ ስልጠና ማድረግ  ተፈታትኖኛል፡፡ ይህም በሁሉም የሰው ልጆች ያጋጠመ ተመሳሳይ ሁኔታ ነው፡፡ ሁላችንም ቅድሚያ የምንሰጠው ነገር ደህንነትን መጠበቅ ነው›› ብሏል፡፡ ከቀነኒሳ እና ከኪፕቾጌ ባሻገር በዘንድሮው ውድድር በሁሉም ፆታዎች ምርጥ የማራቶን ሯጮችም ተሳታፊዎች ናቸው። በወንዶች ምድብ ከ2 ሰዓት 5ደቂቃዎች በታች የገቡ ስምንት አትሌቶች ተሳታፊዎች ሲሆኑ ከእነሱም ማከከል በ2019 በተካሄደው የለንደን ማራቶን ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ያገኙት ኢትዮጵያውያኑ ሞሰነት ገረመው እና ሙሌ ዋሲሁን ይገኙበታል፡፡ ሲሳይ ለማና፤ ታምራት ቶላና ሹራ ኪታታ ሌሎች የኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች ናቸው፡፡ በሴቶች ምድብ በለንደን ማራቶን ላይ ከፍተኛ ትኩረት ያገኘችው ኬንያዊቷ ብርጊድ ኮሴጊ ናት፡፡ ተፎካካሪዎቿ የማራቶኑን ርቀት ከ2 ሰዓት ከ20 ደቂቃዎች በታች የገቡ 5 አትሌቶች ሲሆን፤ በ2019 የቫሌንሺያን ማራቶን ያሸነፈችው ሮዛ ደረጄ እንዲሁም በ2019 የአምስተርዳም ማራቶንን ያሸነፈችው ደጊቱ አዝመራው የሚጠበቁ ሲሆን አሸተ በክረና አለም መገርቱም ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
በለንደን ማራቶን ታሪክ የኬንያ አትሌቶች በብዛት በማሸነፍ ከኢትዮጵያ ብልጫ አላቸው። ባለፉት 39 የለንደን ማራቶን ውድድሮች በወንዶች ምድብ ኬንያውያን 15 ጊዜ ያሸነፉ ሲሆን ኤሊውድ ኪፕቾጌ በ2015 በ2016 በ2018 እና በ2019 ለአራት ጊዜ በማሸነፍ ከፍተኛውን ውጤት አስመዝግቧል፡፡ በወንዶች ምድብ ከኢትዮጵያውያን ያሸነፉት በ2003 ገዛሐኝ አበራ እንዲሁም በ2010 እና በ2013 እኤአ ፀጋዬ ከበደ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በሴቶች  የኬንያ አትሌቶች 12 ጊዜ ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን በ2001 ደራርቱ ቱሉ በ2010 አሰለፈች መርጊያ እንዲሁም በ2015 ትዕግስት ቱፋ ያሸነፉ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡

Read 1503 times