Saturday, 03 October 2020 13:05

ዳሽን ባንክ ለ “ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት 30 ሚ.ብር ለገሰ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  - ባሳለፍነው ዓመት ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት 169 ሚ. ብር ለግሷል
            - ዘንድሮ 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ያከብራል
                     

             ዳሽን ባንክ በጐርጐራ፣ በወንጪና ኮይሻ ለሚሰሩ ልማቶች የሚውል 30ሚ ብር መለገሱን አስታወቀ፡፡
ባንኩ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ መስከረም 21 ቀን 2013 ዓ.ም ረፋድ ላይ በዋና መስሪያ ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው ይህ ገንዘብ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ለ “ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት ለሶስቱ ቦታዎች ግንባታና ልማት ላደረጉት ጥሪ የተሰጠ ምላሽ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ እንደገለፁት 30ሚ ብሩ ለጐርጐራ፣ ለወንጪና ለኮይሻ ለእያንዳንዳቸው የ10 ሚ ብር ድጋፍ የተሰጠ ሲሆን በአዲሱ የበጀት ዓመት ባንኩ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የበጀተው የመጀመሪያው በጀት እንደሆነም ዋና ሥራ አስፈፃማው ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈፃሚው በመግለጫቸው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሁኔታዎች ለተፈጠሩ ችግሮች ዘርፈ ብዙ ምላሽ ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው በአጠቃላይ 169 ሚ. 806ሺ 333 ብር መለገሱንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ከነዚህም መካከል ለኢትዮጵያ ቅርሶች ትረስት 120 ሚ ለፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል 718ሺ 333 ብር፣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ 1.5 ሚ. ለትግራይ ተፈናቃዮች 10ሚ፣ ለአማራ ተፈናቃዮች 10ሚ ብር፣ ለአምቦ ከተማ ልማት 10 ሚ ብር፣ ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ 10 ሚ ብር ለመልካም አስተዳደር ስራ 20 ሚ ብር ለብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር 5ሚ ብር ለሜሪጆይ ልማት ድርጅት 50ሺህ ብር፣ ለአዲስ አበባ ከተማ ተማሪዎች የደብተር ወጪ 1ሚ.150ሺህ ብርና ለሌሎችም በርካታ ድጋፎች በድምሩ 169ሚ ብር ወጪ ማድረጉን አቶ አስፋው ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ባንኩ በ25 ዓመት ጉዞው የሀገሪቱ የፋይናንስ ምሰሶ ሆኖ በአገር ኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ልማትና በሰዎች የኑሮ እድገት ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ ማሳረፉን የገለፁት ዋና ሥራ አስፈፃሚው በላሊበላ የአየሩን ሁኔታ ለማስተካከልና አካባቢውን ለማልማት ከዛፍ ተከላ ጀምሮ የአካባቢውን ወጣቶች ከቱሪስት እንዳይለምኑ በማድረግ በኩልም በርካታ ስራና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልፀው ዘንድሮ ባንኩ 25ኛ ዓመቱን በተለያዩ ክብረበዓሎች እንደሚያከብርም ተናግረዋል፡፡
ባንኩ እስካሁን 425 ቅርንጫፎችን በመላው አገሪቱ ከፍቶ ሲሰራ የነበረ ሲሆን በትላንትናው እለት በቤተልና በመርካቶ ሁለት ተጨማሪ ቅርንጫፎችን በመክፈት አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ብዛት ወደ 427 ከፍ ማድረጉም ተገልጿል፡፡  




Read 2473 times