Saturday, 03 October 2020 13:08

የማራቶን ሪከርድ ከተሰበረ የመሮጫው ጫማውና ጎዳናው ሊያነታርክ ይችላል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

• ኪፕቾጌ በ Alphafly ቀነኒሳ በ Vaporfly ይሮጣሉ
     • ‹‹የቀነኒሳን ሰብዓዊነት፤ ስኬትና የአዕምሮ ጥንካሬ አደንቃለሁ፡፡ ከከፍተኛ ስኬት በኋላ በአትሌቲክስ ውስጥ ስነምግባርን አሟልቶ መቆየት ቀላል         አይደለም›› ኤሊውድ ኪፕቾጌ
     • ‹‹ እንደ አትሌት በጣም አከብረዋለሁ፡፡ ባገኘው ስኬት ለስፖርት ታላቅ አስተዋፅኦ ነው›› ቀነኒሳ በቀለ


             የዓለም አትሌቲክስ ያለፉትን 7 ወራት በኮቪድ 19 ሳቢያ ተዘግቶ ከቆየ በኋላ ነገ የሚካሄደው 40ኛው የለንደን ማራቶን ትልቁን ትኩረት ስቧል። በተለይ ሁለቱ የረጅም ርቀት ምርጥ ሯጮች ቀነኒሳና ኪፕቾጌ በመገናኘታቸው  በኮሮና  ዘመን ላይ ያጋጠመ የመጀመርያውና ግዙፉ የስፖርት ተቀናቃኝነት እየተባለ ነው፡፡ በቦክሱ መሃመድ አሊ ከጆፍሬዘር፤ በሜዳ ቴኒስ ሮጀር ፌዴረር ከራፋኤል ናዳል፤ በእግር ኳስ ሮናልዶ ከሜሲ ያላቸውን ትንንቅ በሩጫው ኤሊውድ ኪፕቾጌና ቀነኒሳ በቀለ ላለፉት 17 ዓመታት በትራክ፤ በአገር አቋራጭ፤ በማራቶንና በጎዳና ላይ ሩጫዎች አሳልፈውታል፡፡ ሁለቱም አትሌቶችን በማናጀርነት የሚያገለግሉት ጆስ ሄርማንስ  ከግሎባል ስፖርት ኮምኒኬሽን ሲሆኑ፤ በአንድ ማልያ  የሚሮጡበት የሩጫ ቡድናቸው GSC’s NN Running Team ይባላል፡፡
ቀነኒሳና ኪፕቾጌ ከትናንት በስቲያ ለ30 ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ጋዜጠኞች ስለውድድሩ መግለጫ የሰጡት በዙም ኮንፍረንስ በመታገዝ ነበር፡፡  በውድድር አዘጋጆች ስፍራ ላይ ለምግብ ሲገናኙ ቢያንስ በ2 ሜትር ተራርቀው እንደነበር ከመግለጫው ተያይዞ የተለቀቀው ቪድዮ አሳይቷል፡፡ የለንደን ማራቶን አዘጋጆች በውድድሩ የመሮጫ ጎዳና አመቺነት፤ በአሯሯጮቹ ብርታት እና በምርጥ አትሌቶቹ ፉክክር በ2 ሰዓት ከ02 ደቂቃ ዙርያ እንደሚገባ ቢገምቱም የዓለም ሪከርድ መሰበሩን የጠበቁ አይመስልም፡፡  ኤሊውድ ኪፕቾጌ የራሱ ሪከርድ የሚሻሻልበት ሁኔታ በሰጣቸው ሁሉም አስተያየቶች ላይ ያልጠቀሰ  ሲሆን ቀነኒሳም ቢሆን ሪከርድ ስለሚሰብርበት እድል ከመናገር ዝምታውን መርጧል፡፡ በማራቶን ውድድሩ ላይ አትሌቶች በሚያስመዘግቡት ሰዓት የኦሎምፒክ ሚኒማን ማሟላት ይችላሉ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያያይዞ  ሞፋራህ በአሯሯጭነት መመደቡ የሚነሳ ይሆናል፡፡ ሞ ፋራህ ከእነቀነኒሳ ጋር ይፎካካራል በሚል ያልተጠበቀ ሲሆን ዘንድሮ በለንደን ማራቶን ሚናው በተለይ የእንግሊዝ አትሌቶች ከ2 ሰዓት 10 ደቂቃ በታች በመግባት ሚኒማ እንዲያሟሉ ማገዝ ነው፡፡
‹‹በጎዳና ላይ ሩጫ ከዓመት በኋላ ለመወዳደር ከፍተኛ ጉጉት አድሮብኛል የሚለው ኪፕቾጌ  የማራቶኑ የመጀመርያው ግማሽ ሰዓት በጣም ሊፈጥን እንደሚችል እጠብቃለሁ፡፡›› ብሎ ሲናገር‹‹ በለንደን ማራቶን በተለይ ኪፕቾጌ የሚወዳደር ከሆነ ፍጥነት ያለው ውድድር እና አሯሯጮችም የሚተጉበት ነው ብሏል ቀነኒሳ በቀለ፡፡ ቀነኒሳ በቀለ ስለ ማራቶን  በሰጠው አስተያየት ደግሞ ‹‹በማራቶን ውድድር ምን ሊከሰት እንደሚችል መገመት ይከብዳል፡፡ ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች ይገጥማሉ፡፡ 100 % ወይንም 110 % የተሟላ አቋም ይዞ እየተሮጠ በውድድሩ መሃል ያልተጠበቀ ነገር ሊፈጠር ይችላል፡፡›› የሚል ሃሳብ ሰጥቷል፡፡
 ከ4 ዓመታት በፊት ሁለቱ አትሌቶች በለንደን ሲገናኙ ቀነኒሳ ለ18 ዓመታት ከቆየበት ጉዳት አገግሞ ነበር የገባው፡፡ በወቅቱ አሰልጣኙ ሬናቶ ካኖቫ የነበረ ሲሆን በማራቶኑ የመጀመርያ ግማሽ በፈጣን አሯሯጥ ጉልበቱን የጨረሰው ቀነኒሳ 2:03:05 በሆነ ጊዜ ኪፕቾጌ ሲያሸንፍ እሱ 2:06:36 በሆነ ጊዜ 3ኛ ነበር የወጣው፡፡ ኤሊውድ ኪፕቾጌ የለንደን ማራቶንን ለአምስተኛ ጊዜ ለማሸነፍ የሚፈልግ ሲሆን በ2015፤ በ2016፤ በ2017 እና በ2019 እኤአኣ ላይ ለአራት ጊዜያት አሸናፊ ነበር፡፡ ቀነኒሳ በቀለ በለንደን ማራቶን ላይ ሲሳተፍ ለአራተኛ ግዜ ሲሆን በ2016 ሶስተኛ፤ በ2017 ሁለተኛ እንዲሁም በ2018 ስድስተኛ ደረጃዎችን አግኝቷል፡፡
በነገው ውድድር ሁለቱ አትሌቶች በሚታጠቋቸው የናይኪ ልዩ የመሮጫ ጫማዎችም አነጋጋሪ ሆነው ሰንብተዋል፡፡ ኪፕቾጌ የናይኪን አልፋ ፍላይ ኔክስት Air Zoom Alphafly Next%  የሚያደርግ ሲሆን ቀነኒሳ በኩሉ በ2019  በበርሊን ማራቶን 2 ሰዓት ከ01 ደቂቃ ከ41 ሰኮንዶች የሮጠበትን ቫፐር ፍላይ ኔክስት Nike ZoomX Vaporfly Next%, እንደሚጠቀም ታውቋል፡፡ ናይኪ ለኤሊውድ ኪፕቾጌ ባዘጋጀው አዲስ መሮጫ ጫማ Alphafly Next% Kenya ለኬንያ ክብር መስጠቱን አሳይቷል፡፡ የመሮጫው ጫማ በኬንያ የባንዲራ ቀለማት የደመቀ ሲሆን በቀኝ ጫማው ተረከዝ ላይ “EK” የሚሉት ፊደላት ሰፍረዋል። ‹‹አልፋ ፍላይ ጫማን ሞክሬው የተወሰኑ ችግሮች ነበሩት፡፡ እንድላመደው ግዜ ይጠይቃል፡፡ በአሮጌው ቫፐር ፍላይ ነው የምሮጠው፡፡›› በማለት ቀነኒሳ ስለጫማው አስተያየት ሲሰጥ  ‹‹ናይኪ የሩጫ ኩባንያ ነው፡፡ ኬንያ የሩጫ አገር ናት፣ እኔም ሯጭ ነኝ፤ የጫማው ውጤታማነት በዚህ ሁሉ የታጀበ ነው ›› ሲል ደግሞ ኪፕቾጌ ተናግሯል፡፡  ኤሊውድ ኪፕቾጌ ከዓመት በፊት በናይኪ በተሰራው ተመሳሳይ ጫማ በልዩ ውድድር ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች መግባት ችሎ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ ለፈጣን አሯሯጡ ጫማው ከፍተኛ እገዛ አድርጎለታል በሚል ትችት ገጥሞት ነበር፡፡ ከለንደን ማራቶን በፊትም ተመሳሳይ ጥያቄ ተነስቶ ምላሽ ሲሰጥ‹‹  ምንም ቢሆን የሚሮጡት እግሮቼ ናቸው፡፡ ቴክኖሎጂ የስፖርቱ አካል ነው። ለሩጫ ቴክኖሎጂ የሚሰጠው ድጋፍ ውስን ነው። ዋናው ጠንካራ ልምምድ እና ስነምግባር ነው፡፡ ምርጥ መሆንና በራስ መተማመን ነው፡፡›› ብሏል፡፡
‹‹የቀነኒሳን ሰብዓዊነት፤ ስኬት እና የአዕምሮ ጥንካሬ አደንቃለሁ፡፡ ከከፍተኛ ስኬት በኋላ አሁንም በአትሌቲክስ ልምምድ ውስጥ ስነምግባርን አሟልቶ መቆየት ቀላል አይደለም›› በማለት ኤሊውድ አድናቆቱን ሲገልፅ፤ ቀነኒሳ በኩሉ ‹‹እንደ አትሌት በጣም አከብረዋለሁ፡፡ ያገኘው ስኬት ለስፖርት ታላቅ አስተዋፅኦ ነው›› በማለት ለኤሊውድ ኪፕቾጌ ያለውን ክብር አስታውቋል፡፡
በ2020 እኤአ ከስድስቱ ትልልቅ የማራቶን ሊግ ውድድሮች  መካሄድ የቻሉት የቶኪዮ እና የለንደን ማራቶን ናቸው፡፡ የቦስተን፤ የበርሊን፤ የቺካጎ እና የኒውዮር ማራቶኖች እንደተሰረዙ ይታወቃል፡፡ በማራቶኑ ላይ በሁለቱም ፆታዎች ለሚያሸንፉት 30ሺ ዶላር የተዘጋጀ ሲሆን የዓለም ሪከርድ የሚሰበር ከሆነ 120 ሺ ዶላር ቦነስ ሽልማት ተዘጋጅቷል፡፡ በሕልማት ገንዘቡ ላይ 50 በመቶ ቅናሽ እንዲደረግ ያስገደደው በኮቪድ 10 ስፖንሰሮች ላይ የደረሰው ጉዳት ነው፡፡ ባለፉት አመታት በሁለቱም ፆታዎች ለሚያሸንፉት የገንዘብ ሽልማቱ 55ሺ ዶላር የነበረ  ሲሆን በድምሩ 313ሺ ዶላር እንዲሁም ለሪከርድ እና ምርጥ ሰዓት እስክ 850ሺ ዶላር ነበር የቀረበው፡፡ ኤሊውድ ኪፕቾጌ በ39ኛው የለንደን ማራቶን ላይ የቦታውን ሪከርድ አስመዝግቦ ሲያሸንፍ 42ሺ ዶላር እንደነበረም ተዘግቧል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያዊው የማራቶን  አሰልጣኝ ሃጂ አዴሎ እና በሴቶች ምድብ ተወዳዳሪ የነበረችው  ደጊቱ አዝመራው የኮቪድ 19 ምርመራ አድርገው ፖዘቲቭ ሆነው በመገኘታቸው የውድድር ተሳትፏቸው እንደተሰረዘባቸው ታውቋል፡፡ በለንደን ማራቶን ላይ ከተሳታፊ አትሌቶች እስከ ውድድር አዘጋጆች አስፈላጊውን የኮቪድ 10 ምርመራ ክትትል እና የመከላከል ተግባር ላይ በክፈተኛ ደረጃ እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡  አትሌቶች፤ የውድድር አዘገሃጆች እና ሌሎች የውድድሩ አካላት በማናቸውም እንቅስቃሴያቸው አስፈላጊውን ርቀት እንዲጠብቁ የሚጠቁምና የሚያግዝ አስደናቂ ቴክኖሎጂ በስራ ላይ እንደሚውልም ተገልጿል፡፡ ለ100 ሯጮች እና ለ500 የውድድር አዘጋጆችና ሌሎች ባለሙያዎች የሚታደለው ቴክኖሎጂ The Bump device ብለውታል፡፡   ማራቶኑ በሚሮጥበት ጎዳና  ላይ ታዳሚዎች በፍፁም እንዳይገኙ የተከለከለ ሲሆን፤ ቀለበታማው የሩጫ ጎዳና 6 ጫማ በሚረዝም አጥር የሚከበብ ይሆናል፡፡1.3 ማይሎች በሚዞረው ቀለበት ላይ አትሌቶቹ 19. ዙሮችን በመሮጥ የማራቶኑን ርቀት የሚሸፍኑ ሲሆን የመሮጫው ጎዳና አራት መታጠፊያዎች ያሉት፤  ለጥ ያለ እና ፈጣን እንደሚሆን ተነግሯል፡፡ በተጨማሪም ለውድድሩ ፍጥነት እንዲያግዝ የሌይዘር ጨረር እንደሚዘረጋም ታውቋል፡፡
የዓለምን ሪከርድ ከያዘው ኤሊውድ ኪፕቾጌ     2:01:39 እንዲሁም ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት ካስመዘገበው ቀነኒሳ በቀለ 2:01:41 ባሻገር በወንዶች ምድብ የሚሮጡት አትሌቶች ምርጥ ሰዓታቸው መጠቀስ ያለበት ነው፡፡ የ28 ዓመቱ ሞስነት ገረመው  ምርጥ ሰዓቱ    2:02:55 ሲሆን በ39ኛው የለንደን ማራቶን እና በ2019 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሁለተኛ ወጥቷል፡፡ የ26 ዓመቱሙሌ ዋሲሁን   2:03:16 ምርጥ ሰዓቱ ሲሆን በ39ኛው የለንደን ማራቶን 3ኛ ደረጃ ነበረው፡፡ 2:03:36 ምርጥ ሰዓት ያለው ሲሳይ ለማ 29 ዓመቱ ሲሆን በ2019 የበርሊን ማራቶንና በ2020 የቶኪዮ ማራቶን  3ኛ ደረጃ ነበረው፡፡ ታምራት ቶላ 2:04:06 በሆነው ምርጥ ሰዓት ሲሳተፍ የ24 ዓመቱ ሹራ ኪታራ በ2:04:49 ምርጥ ሰዓቱ ሲሳተፍ በ39ኛው የለንደን ማራቶን 4ኛ ደረጃ እንዲሁም በ019 የኒውዮርክ ማራቶን 5ኛ ደረጃ አግኝቶ ነው፡፡Read 1242 times