Tuesday, 06 October 2020 00:00

ሞት ቢዘገይ የቀረ ይመስላል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ህልም ተመልካች፣ አንድ ቀራጺ ሃውልተኛ፣ አንድ ባህታዊ ፀሎተኛ፣ ወደ አንድ መንገድ ይሄዱ ነበር፡፡ ብዙ ከተጓዙ በኋላ ህልም ተመልካቹ አንድ ህልም አየ፡፡ ይኸውም “በመንገዳችን ላይ አንድ ትልቅ ዋርካ እናገኝና ቀራጺው ጓደኛችን ያንን ዋርካ ወደ ቆንጆ ሴት ቅርጽ ሲለውጠው አየሁ” አለ፡፡
ይኼኔ ቀራጺው፡- “እውነት ዋርካውን ካገኘን ያለጥርጥር የተባለችውን ሴት እቀርፃታለሁ፡፡” አለ።
ፀሎተኛው ደግሞ፡- “ያላችሁት እውነት ከሆነ፤ እኔ አምላኬን ነፍስ እንዲሰጣት እለምነዋለሁ” አለ፡፡
ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡ ህልመኛው እንዳለውም አንድ ትልቅ የዋርካ ዛፍ አገኘ፡፡ ቀራጺውም ያንን ግዙፍ ዛፍ ቆርጦ ቅርጽ ማውጣት ጀመረ፡፡ ከብዙ ቀናት ድካም በኋላ ምን የመሰለች ውብና አስገራሚ ቅርጽ ያላት ሴት አነጸና አወጣ፡፡ ሁሉም በቁንጅናዋ እየተደመሙ ሳሉ፣ ያ ባህታዊ ፀሎተኛ “ይህች ሴት ነፍስ ቢኖራት እኮ እንዴት ያለች ተአምር ትሆን ነበር፡፡” ብሎ ነፍስ ትዘራ ዘንድ ወደ አምላኩ ፀሎት ማድረግ ቀጠለ፡፡
ከብዙ ቀንና ሌሊት ምህላ ፀሎት በኋላ ያቺ እንስት መናገርና እንደልብ መንቀሳቀስ ጀመረች፡፡ ታላቅ ተአምርም ሆነች፡፡
ሁሉም በየፊናው ይህች ቆንጆ እንስት “የኔ ናት! የኔ ናት!” ማለት ጀመረ፡፡
በመጀመሪያ በህልሙ ያያት ሰው፤
“ጐበዝ! የኔ ነገር የሚያሻማ አይደለም” ይህችን ሴት እኔ በህልሜ ባላያት ኖሮ ማንኛችሁም ቀጥሎ የሰራችሁትን ተአምር ባልሰራችሁም ነበር፡፡ ስለዚህ ይህች ሴት በዋናነት የኔ ሀብት ናት። እናም ማንኛችሁም ብትሆኑ የኔን ፍቃድ ማግኘት ይገባችኋል፡፡” ሲል የአዋጅ ያህል ጮክ ብሎ ተናገረ፡፡
ሀውልተኛው በበኩሉ፤
“ጐበዝ! ህልመኛው በህልሙ ከማየት በስተቀር ዋርካውን ወደ ቅርጽ የመቀየር ምንም ሞያዊ ክህሎት ስለሌለው፣ ምንም አይነት ተጨባጭ ተግባር የማከናወን ድርጊት አልፈፀመም፡፡ አሁንም ሌላ ዛፍ ብናገኝ ምንም ሊያደርግ አይችልም፡፡” ሲል አጥብቆ ተከራከረ፡፡
ቀጥሎ ጋዜጠኛው እንዲህ አለ፤
“ጐበዝ! ምንም አላችሁ ምንም ይህች ሴት የምትገባው ለኔ ነው፡፡ ምነው ቢሉ… በመጀመሪያ እንጨት፣ ቀጥላም የእንጨት ቅርጽ፣ እንጂ ሰው ለመሆን አትችልም ነበረና! ዋናውን ጉዳይ ባትዘነጉ ጥሩ ነው፡፡ ራሷን ብትጠይቋት በምን አንደበቷ መልስ ትሰጣችሁ ነበር?” አለ፡፡
በዚህን ጊዜ የመጀመሪያው ትገባኛለች ባይ፡-
“እንደውም እራሷ ትናገር፤ የማን እንደሆነች እንጠይቃት” አለ፡፡
ሁለተኛውም፡- “አሁን መልካም ሃሳብ መጣ፤ እራሷ ትጠየቅና ትገላግለን!” አለ፤ በእፎይታ እየተነፈሰ፡፡
ሦስተኛው፤ “እኔም በዚህ ሃሳብ እስማማለሁ፡፡ እሺ ቆንጂት አባቴ ማን ነው ትያለሽ?” አለና ጠየቃት፡፡
ይሄን ጊዜ ቆንጆዋ ሴት፡-
“በበኩሌ፤ መልሴ አንድና የማያሻማ ነው፤ ይኸውም “ሁሉም ነገር ወደመጣበት ይመለሳል” የሚለውን ቃል አትዘንጉ” አለች፡፡
ያ ዋርካ ወደነበረበት ተመልሶ ተሰነጠቀ፡፡ ቆንጆዋ ሴት ተመልሳ ወደ ዋርካዋ ገባች፡፡
*   *   *
ሁሉም ነገር ወደመጣበት መመለሱ “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” የሚለውን ቃል ያስታውሰናል፡፡ በየትኛውም መልኩ መወለድ፣ ማደግና መሞት ተመላላሽ እውነታዎች ናቸው፡፡ ከድግግሞሹ መማር ያለብን ግን እኛ ነን፡፡ ያወላለድም፣ የማሳደግም፣ የመሞትም መልክ መልክ አለውና፣ ያንን ተጠንቅቆ በማሳደግ የተሻለ ነገር መፍጠር ይሁነኝ ተብሎ መተግበር ያለበት ጉዳይ ይሆናል፡፡
ዛሬ በሃገራችን ዋና ፋይዳ ናቸው ከምንላቸው ነገሮች አንዱ ለሞያና ለባለሙያ የምንሰጠው ከበሬታ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሞያ የራሱ ባህርይ እንዳለው ሁሉ አተገባበሩም የራሱ ስልት፣ ሚዛን፣ እንዲሁም ስነምግባር አለው፡፡ በተለይ ሙያዊ ክህሎትና ስነምግባር ካልተቀናጁ፣ ግማሽ - ጐፈሬ ግማሽ - ልጭት የሚባለውን አይነት ንፍቀ - ክበብ ይፈጥራል፡፡ አንድ አስተዋይና አሳቢ - ሰው (Thinker) እንዳለው፤ አንድን ሥርዓት ሙሉ አድርጐ አለማደራጀት በሶሻሊስት ቤተ መቅደስ ውስጥ ካፒታሊስት ቄሶች ወይም ቀዳሾች እንዲቀድሱ ማድረግ ነው፡፡ አንድም፤ አንድን ማሽን ግማሹን በእጅ የሚዞር (Along) ግማሹን በአውቶማቲክ መንገድ ወይም (Digital) መግጠም ነው። ያ ሞተር ከነአካቴው እንዳይንቀሳቀስ የማድረግ እቅድ ያለን ካልሆነ በስተቀር በእውነት ውጤት ለማምጣት የማይበጅና የግብር - ይውጣ  ሥራ ነው የሚሆነው፡፡
በአንዳንድ የሥራ መስክ ሠራተኛውን በአዲስ ሠራተኛ የመለወጥ ሃሳብ ቢኖር፣ ያለውን ሠራተኛ ሙልጭ አድርጐ ማስወጣት ወይም ማባረር አደጋ እንዳለው ይነገራል፡፡ ነባሩን ሥራ የሚያስተባብር የሚያለማምድ በተለይም ለዘመናት የሠራ ሠራተኛ ብቻ ሊሠራው የሚችል ዘርፍ በጥንቃቄ ሊታይና እንክብካቤ ሊደረግለት የሚገባ ልዩ ሥራ ነው፡፡ ወረቀት የማይተካው፤ የተካበተ ልምድ ብቻ ሊሠራው የሚችል ፍፁም ወሳኝ ሥራ ያለበት ቦታ አለ፡፡ ሁሉንም ሥራ በማሽን እንተካለን ልንል ብንደፍር፤ ፈረንጆቹ እንደሚሉት፤ “even the most complicated Machine needs some one to push the button” (የመጨረሻው የረቀቀና ውስብስብ የሆነ ማሽን እንኳ የማስነሻዋን ቁልፍ የሚጫን አንድ ጣት ያስፈልገዋል እንደማለት መሆኑ ነው፡፡) ስለሆነም በመጨረሻ ሰዓት፣ ከማሽኑ ጀርባ የሚቆም አንቀሳቃሽ ሰው ያሻል ማለት ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ማሽን በመምጣቱ ምክንያት ከሥራ የሚባረረውን የሰው ኃይል ከጉዳይ ሳንጥፍ መሆኑ ነው፡፡
ዛሬ በሀገራችንም፣ በአህጉራችንም፣ በአለማችንም፤ ለያዥ ለገራዥ አስቸግሮ  የእውር የድንብር ከሚያስኬደው የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ሳንላቀቅ፤ ትምህርት ቤቶች ሊከፈቱ ይችላሉ የሚለው እሳቤ አሳሳቢነቱ ወዲህ ወዲያ የሌለው መሆኑን እየተገነዘብን፤ የሚደረገውን ጥንቃቄ - በተለይ ከሞላ ጐደል በሽታው የሌለ እስኪመስል የተዘነጋበት ወይም የተናቀበት አሊያም ወደ ድሮው ግዴለሽነት እየተመለስን ያለን በሚመስልበት ሁኔታ፤ “ሞት ቢዘገይ የቀረ ይመስላል”   የሚለውን ምሳሌያዊ አነጋገር የሚያስጠቅሰን ይመስላል፡፡ እውነቱ ግን፡- በሽታው አለ! ሰው እየሞተ ነው! በጭራሽ ሙሉ ለሙሉ ልናስወግደው የምንችልበት አቅም ላይ አይደለንም! አሁንም አንዘናጋ! ሰበብ አንፍጠር! “ዋዛ ፈዛዛ ልብ አያስገዛ” የሚለውን ተረትና ምሳሌ፤ አሁንም ልብ እንበል! ትምህርት ቤቶች ለበሽታው ለመጋለጥ አመቺ ሁኔታዎች ሊፈጠርባቸው ከሚችሉ ዋና ዋና ሥፍራዎች ውስጥ ናቸው! እንጠንቀቅላቸው! በሽታው፤ ህፃን፣ ወጣት፣ ጐልማሳ፣ አረጋዊ፣ አሮጊት አይልም፡፡ ስብስብ የሚበዛባቸው ቦታዎች ሁሉ ለወረርሽኙ መጋለጫዎች ናቸው፡፡ ቁጥጥሩ ይጥበቅ! ስህተት ካለ በጊዜ ይታረም! የሚቀመስ ያለው ለሌለው፣ ዛሬም እጁን ይዘርጋ! ባሕላዊ መተሳሰባችን ይጠንክር! ምዝበራ፣ ዘረፋ፣ ሌብነት፣ የኢኮኖሚ አሻጥር፣ ሙስና ለሀገር ንብረት አለመጠንቀቅ ወዘተ… ሞት ቢዘገይ የቀረ መምሰሉ ብቻ ሳይሆን ውድቀትም ቢዘገይ የቀረ እንዲመስለን ያደርጋልና፣ ጥንቃቄያችን ፍፁም እንዲሆን በሕዝብም በመንግሥትም ዘንድ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

Read 9386 times