Print this page
Tuesday, 06 October 2020 07:51

ውዝፍ ፍትሕ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)

ከሰኔ 22 ቀን  2012 ዓ.ም ወዲህ ያለውን ጊዜ ብቻ ወስደን ብናይ፣ የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን  ‹‹እንቃወማለን›› በሚል ሰበብ፣ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች በተፈጸመ የሰዎች ግድያና የንብረት ማውደም ተግባር እንዲሁም በያዝነው መስከረም ወር 2013  መጀመሪያ ላይ በቤኒሻንጉል ክልል ዳንጉር አካባቢ በተፈጸመ ግድያና ንብረት ማውደም፣ በአጠቃላይ ከአንድ ሺ አራት መቶ በላይ ሰዎች በድርጊቱ  ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መንግሥት ጠቁሟል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገራችን ልዩ ልዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ  ወንጀሎች  ተይዘው በቁጥጥር ስር የዋሉ  ሰዎችን ቁጥር ስንጨምርበት ደግሞ  ፍትሕ ፈላጊውና ፍርድ ጠባቂው እጅግ ብዙ መሆኑን እንረዳለን፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን በመጡ ጊዜ ‹‹ሳናጣራ አናስርም፤ አስረን  ምርመራ አናጣራም.. በማለት የገቡትን ቃል፣ መንግሥት አክብሮ እንዲራመድ ሁኔታው እድል የሰጠው አይመስልም፡፡ እሳቸው ‹‹የከረመ ብሶት መገለጫ ነው›› ያሉት የየአካባቢው ግጭቶች፤ ወደ ልማድ ተሻግረው እንደ ተገቢ ነገር፣ አንዱ ከሌላው የሚቀበለው ወይም የሚከተለው የትግል መንገድ ሆኗል። በግልጽ አነጋገር የወንጀለኛውን ቁጥር ጨምሮታል፡፡
ግጭቶች ከተከሰቱ በኋላ ከየአካባቢው ሕዝብ፣ ከሃይማኖት መሪዎችና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር የክልልና የፌዴራሉ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ስብሰባዎች አካሂደዋል፡፡ ስብሰባዎቹ  የተበዳዮቹን ጩኽት የሕዝቡን ሥጋትና ተስፋ እንዲሁም ከመንግሥት ምን እንደሚጠበቅ  ከማሳየትና ከማስረዳት ያለፈ ያመጡት ለውጥ አለ ማለት አይቻልም፡፡
የሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ ከሆነው ተነስተው ‹‹ከላይ እስከ ታች በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተቀምጠው ወንጀለኞችን የሚደግፉ"  እንዳሉ  ጠ/ሚኒስትሩ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል።  የተወሰኑት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ሌሎችም ከሥራ መታገዳቸውን አያይዘው ተናግረዋል፡፡ ይህ የአሳቸው ንግግር አሁን ሁለት ዓመት ሊሞለው ከተቀረበው፣ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል (ቃል በቃል ባይሆንም) ‹‹በየአካባቢው በሚደርሰው መፈናቀል፣ የሰዎች በመገደልና ንብረት በማውደም የተሳተፉ ሰዎችን  በተፈለገው መጠንና ፍጥነት ወደ ፍትሕ ማቅረበና ማስቀጣት ያልተቻለው የየአካባቢ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከጉዳዩ ጀርባ ስላሉና በብሔር ምክንያት አንዱ ሌላውን በመሸፋኑ ነው›› ሲሉ ከተናገሩት ጋር ተደምሮ የሚታይ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እጅግ በጣም ዘግይተው የደረሱበት መደምደሚያ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ከሚቀር ይጥቆር የሚበልለት ንግግር ነው፡፡
ይህ ደግሞ መንግሥት ፍትሕ የመስጠት አቅሙ ምን ያህል ነው? ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድደን ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
በአባ ቶርቤ (ማነህ ባለ ሰምንት) እየተባለ ስንት ደሀ በገሬና የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደተገደሉ የሚያሳይ የተሰበሰበ መረጃ አላገጠመኝም፡፡ እንደ ጥቅምቱ 2012 ዓ ም እና እንደ ሰኔ 2012 ዓ ም ግድያች  በአንድ ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሟች ባይኖርም ሕይወት የጠፋባቸው ንብረት የወደመባቸው ፍትሕ ሊሰጥባቸው የሚገባ ድርጊቶች አሉ፡፡ ለአይነት የሚከተሉትን ልጥቀስ፤
በአማሮ ኬሎ 105 ሰዎች የተገደሉበት 114 ሰዎች የቆሰሉበት፤
በአርማጭሆ፣ በጭልጋና በሞጣ መደስጊድና ቤተ ክርስቲያን የተቃጠሉበት እንዲሁም በደቡብ ክልል የተቀጠሉ በርካታ የጸሎት ቤቶች፤
በከምሴ፣ በአጣዬ፣ በማጀቴና በለሌሎች አከባቢዎች ከፍተኛ ጥፋት ያደረሱ፤
በኦሮሚያ፣ በትግራይና በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተገደሉ ተማሪዎች፤
በቢሻንጉል ክልል በተደጋጋሚ በደረሰ ጥቃት  ነፍስ  ያጠፉና ንብረት ያወደሙ፤    
 እንደነዚህ  አይነቱን ትተን  የቢሻንጉል ክልል ሁለት ባለ ሥልጣናት፣ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ  እንዲሁም ጎጃም ውስጥ ቆለላ በተባለ ቦታ ወሰን ተፈራና ማንደፍሮ አቤ የተበሉ የሕክምና ተመራማሪዎች መገደልን እንውሰድ፡፡ ከሌላው አንጻር በነዚህ ሰዎች ላይ ግድያ የፈጸሙትን ተከታትሎ ለሕግ ማቅረብ የቀለለ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ የእነሱም ገዳዮችና ሌሎች እልፍ ወንጀለኞች ተይዘው ቢሆን እንጂ ወንጀላቸው ተጣርቶ ለፍርድ ቀርበው ቅጣታቸውን ተቀበሉ የሚል ነገር አልተሰማም፡፡ ከዚህ የተነሳ የፍትሕ ያለህ!!! ፍትሕሰ ወዴት ናት? ብሎ መጮህና መጠየቅ ዛሬ በኢትዮጵያ ምርጫ አይደለም፤ ግዴታ ነው፡፡
የዜጎች ሕይወትና ሃብት ማንም ጉልበት ያለው የሚያዝዝበት፣ ሲፈልግ የሚያድነውና ሲፈልግ የሚያጠፈው መሆን የለበትም። በመንግሥት ጥበቃ ሊያገኝና ከብር ሊሰጠው ይገባል፡፡
አሕዴግ የመንግሥት ሥልጣን እንደያዘ ሰሞን ጎማ የሰረቀን ሌባ በጥይት ግንበሩን በማለት ይቀጣ ነበር፡፡ በኋላ ሠልጥኖ ለሰዎች በቁመታቸው ልክ ወንጅል በማዘገጀትና እነሱን ለማንገላታት የሚያገለግል ሕግ በመደንገግ የግፍ አገዛዙን ቀጠለ፡፡ ፍርድ ቤቶች ከላይ በመጣ ትእዛዝ በሰዎች ላይ ሲፈርዱ ኖሩ፡፡
ይህ በፍትሕ ተቋማት ላይ ከፍተኛ አለመታምን አሳደገ፡፡ በዚያ ዘመን በየአካባቢው በሚቀሰቀሱ የብሔር ግጭቶች በዙዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሰባዊ መብት ገባኤ መበደላቸው ከመዘርዘሩ ሌላ ፍትሕ ያገኙ አልነበሩም፡፡ በዚህ ለውጥ ላይ ነን በምንልበት ዘመንም ያ አሠራር እየቀጠለ ነው፡፡ ተበዳዮች ቁስላቸውን እያከኩ ይገኛሉ፡፡
አዲሱ የቆየውን እያስረሳው፣ የቆየው አፈር እየለበሰና ሳር እየበቀለበት ቢሄድም በደሉ በተፈጸመበት እያንዳንዱ ሰው ላይ ግን ሁል ጊዜም አዲስና ትኩስ ነው። በየአካባቢው በተከሰቱ ሁከቶች ጀርባ የየአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት መሳተፋቸው ተደጋግሞ በሕዝብ የተነገረ ነው፡፡ በቅርቡ  በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲነገር ግን እንደ አዲስ መደመጡ አልቀረም፡፡ በደል የደረሰበት ሕዝብ ፍትሕ መጠበቁና መጓጓቱ ግልጽ ነው፡፡ መንግሥት ለተገፉ ፍትሕን ማስገኘት አለበት፡፡
የፌዴራሉ አቃቤ ሕግ ከሁለት ሳምንት በፊት በሰጠው መግለጫ፣ የድምጻዊ አጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተካሄደው ግድያ፣ 167 ሰዎች መገደላቸውን 360 ሰዎች መቁሰላቸውን እንዲሁም  4 ነጥብ 67 ቢሌን ብር ግምት ያለው ንብረት መውደሙን ገልጧል፡፡ በዚህ ወንጀል ፈጻሚነት በተጠረጠሩ፣ በፌዴራል ደረጃ 3.377 በኦሮሚያ አቃቤ ሕግ በ2.351 በድምሩ 5.728 ሰዎች ላይ ክስ መመሥረቱን አሳውቋል፡፡ መለካም ተግባር ቢሆንም ሌሎች ፍትሕ ፈለጊዎችና ጠባቂዎች መኖራቸው መዘንጋት እንደሌለበት አጥብቄ አሳስባለሁ፡፡ የፌደራሉም ሆነ የክልል ኣቃቤ ሕጎች ፍትሕ ለተጠሙ እንዲደርሱ ሊተጉ ይገባል፡፡
ከወንጀለኛው ብዛትና ከወንጀሉ ከፋት አንጻር የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የፖሊስ፣ ያቀቤ ሕግና የደኝነት ተቋማትን ማጠናከር ሥራዬ ብለው ሊይዙትና ሊያስቡበት ይገባል፡፡ ለተንቀሰቃሽ ስልክ ሌባ ፈጣን ችሎት አቁሞ ዳኝነት የሚያዩ ክፍሎች  በሕዝብ ላይ በሚፈጸሙ ለመናገር በሚዘገንኑ ክፉ  ወንጀሎች ላይ የሚያሳዩትን  ቸልታና ዳተኝነት  ዘወር ብለው ሊያዩት ግድ ነው፡፡ በቃ መባል አለባቸው፡፡
መንግሥት የተከማቸን በደል በፍትሕ ያጠራ ዘንድ ማሰሰብ የሁላችንም ግዴታ አድረገን ብንወስደው ደስ ይለኛል፡፡
በነገራችን ላይ ፍርድ ቤት በዋስ እንዲለቀቁ የተወሰነላቸው ሰዎች ከለውጥ በፊት ይደረግ እንደነበረው ሁሉ የዋስትና መብታቸው በፖሊስ እየተገፈፈ በእስር እንዲቆዩ እየተደረገ መሆኑ እየተዘገበ ነው። መንግሥት ጤና አይደለም? ከሕግ በላይ የሆኑትን ሃግ የሚላቸው ማነው?
በሕግ አምላክ ታረሙ!!!!   

Read 7374 times