Tuesday, 06 October 2020 07:56

አሁን ነው መፍራት - ለሥልጣን ያላሰፈሰፈ የለም!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(4 votes)

 ብሔራዊ መግባባት፣ ሸንጎ፣ ድርድር--ትርጉማቸው ገባኝ !
                 
          ወዳጆቼ፤ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ፣ ከኢቢሲ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ሰምታችሁልኛል? የእናንተን አላውቅም። ለእኔ ግን ተመችቶኛል፡፡ (ጉደኛ ነበር!) ለነገሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበተ ርዕቱ ናቸው፡፡ ንግግር ብቻ ሳይሆን ጽሁፉም ይዋጣላቸዋል፡፡ ሃሳብና ይዘት ከሌለ ግን አንደበቱም ብዕሩም ተዓምር እንደማይፈጥር እሙን ነው፡፡ ያለማጋነን ቃለ ምልልሳቸውን እንደ ትረካ ነው ደጋግሜ የሰማሁት። ኖቤላቸውን ለማስነጠቅ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎቻቸውን በተመለከተ የሰጡት ምላሽ አርክቶኛል፡፡ ("ዕድሜ ልኬን ስሸለም ነው የኖርኩት" ነው ያሉት!) "ከኖቤል የሚልቀው ሽልማቴ የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ ነው" ያሉም መሰለኝ፤ ቃል በቃል ባይሆንም፡፡ በነገራችን ላይ የጠ/ሚኒስትሩ ንግግር ብዙ ጊዜ አነቃቂና ተስፋ ፈንጣቂ ነው። (ይህን ለማጣጣም ግን ክፍት ልብና አዕምሮ ይጠይቃል!) ሆኖም ጽንፈኛ ብሔርተኞች፣ ጭፍን ተቃዋሚዎች፣ የሥልጣን ጥመኞች፣ የኢህአዴግ ዘመን ናፋቂዎች--ወዘተ በዚህ ሃሳቤ ቢበሳጩ አልቀየማቸውም (ቅናት፣ ክፋት፣ ትዕቢት፣ ዘረኝነትና ጥላቻ ---እንቅልፍ የሚነሱ ክፉ ደዌዎች መሆናቸውን አውቃለሁ!)
በጠ/ሚኒስትሩ ዙሪያ የጀመርኩትን አልጨረስኩም፤ በኋላ ላይ እመለስበታለሁ። አሁን ወደ ሌላ አጀንዳ ልሻገር፡፡  ከዚያ በፊት ግን አንድ አንገብጋቢ አጀንዳ እነሆ። እኔ የምለው--ከመስከረም 25 ወይም 30 በኋላ በኢትዮጵያ ዕውቅና ያለው መንግስት የለም" እያሉ የሚዘባርቁት ከምራቸው ነው? "በእንዲህ ቀን የዓለም መጨረሻ ይሆናል" እያሉ በየጊዜው የሚተነብዩትን ነው የመሰሉኝ፡፡ (የሚያሟርቱትን ማለቴ ነው!) በነገራችን ላይ አሁን ያለው የዐቢይ መንግስት፤ ከተጠቀሰው ቀን በኋላ በሥልጣን ላይ ከቆየ ህገ) ከሚፈርስ ሥልጣን ላይ ያለውን ህገ ወጥ መንግስት እናፍርስ፤ተባበሩን; እያሉ ነው፡፡ መንግስት  ከህገ መንግስቱ ውጭ ሥልጣን ላይ እንዳይቆይ፣ በሃይልም ቢሆን (ኢ-ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ!) እናፍርሰው ባይ ናቸው፤የፌደራሊስት ኃይሎች! ከዚያስ∙? ማን መንግስት ይሆናል? ስትሏቸው መልስ አላቸው - በዝርዝር። ግን "እኛ ነን መንግስት የምንሆነው!" አይሏችሁም። (ባይሏችሁም የዐቢይን መንግስት ጥለው ሥልጣን መያዝ ነው የሚሹት!) እነዚህ ወገኖች ብቻ ሳይሆኑ ለሁለትና ሦስት አስርት ዓመታት መንግስትን ሲታገሉ የኖሩ አብዛኞቹ ተቃዋሚዎች፤ ጊዜያችን አሁን ነው ያሉ ይመስላሉ። ሥልጣን ለመቆናጠጥ፤ ቤተ መንግስት ለመግባት! ለዚያ ደግሞ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ ናቸው። (አትጠራጠሩ!) አሁን ወደ ሌላኛው አጀንዳ እንሂድ፡፡
ወዳጆቼ፤ እስቲ ስለ አንድ አገር ያወቃቸው፣ ፀሐይ የሞቃቸው ምሁር (ጽንፈኛ ፖለቲከኛ!) ጥቂት ላውጋችሁ፡፡ ስለ እኒህ ሰው ሳላነሳ ብቀር ታሪክ ይፋረደኛል ብዬ ነው፡፡ (በተረት ውስጥ “ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሰውዬ" ነበሩ? የሚባሉትን ሰው ይመስሉኛል!”) እናላችሁ -- እኒህ የፖለቲካ ልሂቅ ትኩረቴን የሳቡት፣ በአንድ ዓመት ውስጥ “ቀንደኛ ደጋፊም” “ቀንደኛ ተቃዋሚም” ሆነው በመገኘታቸው ነው፡፡ የማን? እንዳትሉኝ! - የጠ/ሚኒስትሩ ነዋ! እና የለውጡ መንግስት! በነገራችን ላይ ሰውየውን የማውቃቸው በቴሌቪዥንና በዩቲዩብ ብቻ ነው፡፡ በእርግጥ የመረጃ ክፍተቴን የቅርብ ወዳጆቼ ሞልተውልኛል፡፡ ከእኒህ ወዳጆቼ እንደተነገረኝ ከሆነ፤ ሰውየው ከባህር ማዶ ወደ አገር ቤት የመጡት የለውጡ መንግስት ሥልጣን በተቆናጠጠ ማግስት ነው፤ ምናልባት ለመንግስት ሹመት፡፡ (በአጭር ተቀጨ እንጂ!) እናላችሁ -- በዚያ ሰሞን ሚዲያ እየለዋወጡ፣ ሰፊ ማብራሪያና ትንተና ይሰጡ ነበር፡፡ ስለ ቄሮ፣ ስለ ህወሓት፣ ስለ ለውጡ አመራር፣ ስለ ወደፊቷ ኢትዮጵያ፣ ስለ ድል አጥቢያ አርበኞች፣ ስለ ተቃዋሚዎች-- ወዘተ ይተነትናሉ፤ ይተነብያሉ፡፡
አብዛኛውን ትንተና የሚሰጡት ደግሞ በጠ/ሚኒስትሩና በለውጡ መንግስት ላይ ነበር፡፡ የዶ/ር ዐቢይ የግል አድናቂ ነበሩ (የዛሬን አያድርገውና!!) ከማንዴላ ጋር ሲያነጻጽሯቸው ሁሉ ሰምቻለሁ፤ በአርት ቲቪ፡፡ ብዙዎቹን የጦቢያ ተቃዋሚዎች ሊያጨስ ይችላል ብዬ ከምገምተው የፖለቲከኛው ሃሳብ ውስጥ ከምርጫ ጋር የተያያዘው ተጠቃሽ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ምርጫ ቢካሄድ ሁሉም በየብሄሩ ይመርጣል እንጂ በሃሳብ ላይ ተመስርቶ ድምጽ አይሰጥም ያሉት ተንታኙ፤ "ህዝቡም ፖለቲከኞቹም ከጎሳ ፖለቲካ እስኪላቀቁ ድረስ ምርጫ አያስፈልግም" የሚል ጽኑ አቋም ነበራቸው፡፡ "ኢትዮጵያ ቢያንስ ለ10 ዓመት ምርጫ ማድረግ የለባትም" ባይ ነበሩ - ያኔ! (ተቃዋሚዎች አልሰሟቸው!)
…እናም የጠ/ሚኒስትሩን የሥልጣን ጊዜና የሽግግር ዘመን በፈቃዳቸው ከ2 ዓመት ወደ 10 ዓመት አራዝመውት ቁጭ አሉ። በድብቅ ወይም በምስጢር አይደለም፡፡ በግላጭ ነው - በአርት ቲቪ! የሚገርመው በዚህ ጉዳይ ላይ ተቃዋሚዎችን ማወያየት እንኳን እንደሚያስፈልግ አላነሱም፡፡ ለጊዜው ከጠቅላዩ ውጭ ለጦቢያ መሪነት ሌላ ብቁ ሰው አልታያቸውም፡፡ ከእሳቸው ውጭ የሚያምኑት ፖለቲከኛ ያለ አይመስልም፡፡ (ያኔ ነው ታዲያ!)
እኚህ የዳያስፖራ ፖለቲከኛ ሌላም ነገር ብለዋል፡፡ የኦሮሚያ ህዝብ በትግሉ ከጭቆና መውጣቱንና ነጻነቱን  መቀዳጀቱን በመግለጽ፤ ከእንግዲህ 17 የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደማያስፈልጉ አስረግጠው ተናግረው ነበር - ሁለት ብቻ እንደሚበቁ በማመልከት፡፡ በነጻ አውጭነት የተቋቋሙ የፖለቲካ ድርጅቶችም ስማቸውን ብቻ ሳይሆን ግብራቸውንም መቀየር እንዳለባቸው፣ ከብሔርተኝነት በመውጣትም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳን ማቀንቀን እንደሚገባቸው ሲናገሩ ሰምቻለሁ። እንደ ሃሳብ አይደለም፤እንደ ግዴታ ነው ያቀረቡት፡፡ በአገሪቱ ስጋት ፈጥሮ የነበረውን የህግ የበላይነት ያለመረጋገጥ ጉዳይ በተመለከተ  ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ፣ የዳያስፖራ ልሂቁን የተደበቀ ማንነት ያጋለጠ ነበር፡፡ "በለውጡ መንግስት የተፈጠረውን ገደብ የለሽ ነጻነትና ዲሞክራሲ ሽፋን በማድረግ፣ ነውጠኞች አገሪቱን ወደ ጥፋትና መፈራረስ ሲወስዷት ከማየት ይልቅ ዶ/ር ዐቢይ እልም ያለ አምባገነን ገዢ ሆኖ፣ አገሪቱን ሰጥ ለጥ አድርጎ ቢገዛ እመርጣለሁ" ነበር ያሉት፡፡ (ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ትዝ አሉኝ!)
አንድ ቀን ታዲያ ከዓመት በፊት ድምጻቸውን አጥፈተው ወደ አገር ቤት የገቡት እኚህ ምሁርና  ፖለቲከኛ፤ በተመሳሳይ ድምጻቸውን አጥፍተው ወደ ባህር ማዶ መሻገራቸውን ሰማን፡፡ (ያውም ላይመለሱ!)  ምነው ሲባል? "ከሹመት ወይ ከዜግነት አንዱን ምረጡ?" ቢባሉ፤ አሻፈረኝ አሉ፡፡ እናም ደህና የተገላገሉትን የስደት ህይወት፤ እንዳዲስ ተቀላቀሉት፡፡ ከሁሉም የሚያስገርመው ምን መሰላችሁ? (ከቀንደኛ ደጋፊነት ወደ ጽንፈኛ ተቃዋሚነት የተከረበቱበት ፍጥነት!) ብዙም ሳይቆዩ፣ በኢንተርኔት ውጊያ ጀመሩ - ከባህር ማዶ ወደ ኢትዮጵያ! (የፌስቡክ ትግላቸውን አጧጧፉት፡፡) የአድማና አመጽ ቅስቀሳ ጀመሩ፡፡ በአካል ሳይሆን በሪሞት ኮንትሮል! ሞትና እስር የሌለበት የትግል አድቬንቸር! (ድንቅ የነጻነት ትግል!) ለመንግስት ሹመት የታጩት የፖለቲካ ልሂቅ፣ በአንድ ጀንበር አመጽ ቀስቃሽ ሆነው አረፉት!! (ያሳዝናል!) የእኚህ ሰውዬ ታሪክ ለእኔ እዚህ ጋ ያበቃል፡፡ “የመንግስት ቀንደኛ ደጋፊ ነበሩ፤ የመንግስት ቀንደኛ ጠላት ሆኑ” ይሄው ነው ታሪካቸው፡፡
አሁንም ወደ ሌላ አጀንዳ ልውሰዳችሁ። ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ (ከለውጡ ወዲህ ማለቴ ነው!) በአብዛኞቹ ተቃዋሚዎች ዘንድ ተደጋግሞ ሲነሳ የምሰማቸው ጉዳዮች አሉ - ብሔራዊ መግባባት፣ ድርድር፣ ሸንጎ፣ ፍኖተ ካርታ--ወዘተ የሚሉ፡፡ እኔ ግን ትርጉማቸው ገብቶኝ አያውቅም፡፡ ዘንድሮ ነው ሁሉ ነገር የተገለጠልኝ፡፡ ባይገርማችሁ የሁሉም ትርጉም አንድ ነው፤ "ከምርጫ በፊት የሽግግር መንግስት እናቋቁም፤ ከመንግስት ጋር ሥልጣን እንጋራ" ማለት ነው፡፡ እኔም በቅርቡ ነው የደረስኩበት፡፡
እውነቱን ለመናገር ሰፊ የትውልድ ልዩነት - የዘመን ርቀት አለ፤ በአሁኑ ትውልድና  በ60ዎቹ ፖለቲከኞች  መካከል፡፡ የድሮዎቹ ፖለቲከኞች ፅንፈኝነት ያጠቃቸዋል፡፡  ዛሬም ከማርክሲዝም - ሌኒኒዝም ርዕዮተ ዓለም አልተላቀቁም፡፡ ዛሬም በነፃ አውጭነት መንፈስ ነው የሚያንቀሳቅሱት፡፡ ነፃ ሊያወጡን እየታገሉ ያሉ ነው የሚመስላቸው፡፡ (ከማን እንደሆነ ባያውቁትም!) ዛሬም በህዝብ ደምና የህይወት መስዋዕትነት ሥልጣን ለመያዝ ያልማሉ፡፡ ለዚህ ነው አብዝተው አድማና ዐመጽ መጥራት የሚቀናቸው፡፡ ለዚህ ነው እንዳሻቸው በሚነዱት ቡድን ለማስፈራራት የሚሞክሩት፡፡ ለዚህ ነው ከሃሳብ ይልቅ የዘር ካርድ የሚስቡት፡፡ ለዚህ ነው በምርጫ ሳይሆን በአቋራጭ ሥልጣን ለመያዝ የሚቋምጡት፡፡  
ከ60ዎቹ የፖለቲከኞች ዘመን  ወደ ዛሬው ዘመን ልመልሳችሁ፡፡ ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ዘመን!! ዶ/ር ዐቢይ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ባደረጉት ቃለምልልስ፣ ጋዜጠኛው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የህዝብ ድጋፋቸው መቀነሱን የሚያነሱ ወገኖች እንዳሉ በመጥቀስ፣ ላቀረበው ጥያቄ ሲመልሱ እንዲህ አሉ፡-  
 “የኢትዮጵያ የለውጥ መንግስት ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ (ህዝብ ማለት ፌስቡክ የሚጠቀም፤ በየሚዲያው የሚናገር ማለት ሳይሆን ሰፊው ህዝብ) ያለው መንግስት ነው። ለዚህ ማረጋገጫው… ለምሳሌ…5ሚ. ችግኝ በክረምት እንትከል ያልነው ለየአሜሪካው ፕሬዚዳንት ቢያስቡት አያሳኩትም፡፡ ወይ በገንዘባቸው ወይ በቴክኖሎጂ ያሳኩት ይሆናል፡፡ ከ25 ሚ. ህዝብ በላይ በክረምት ዝናብ እየዘነበበት፣ ቦታ ሳይመርጥ፣ ችግኝ ገዝቶ፣ ራሱ ቆፍሮ መትከል… ቻይናም አሜሪካም አይችሉትም። እነሱ ብዙ የሚችሉት ጉዳይ አላቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ደጋፊ ብቻ ሳይሆን ለዓላማው የፀና እምነት እንዳለው በተግባር አሳይቷል፡፡ እኛ እስከ ነሐሴ መጨረሻ፣ መስከረም መጀመሪያ ድረስ ነበር ለማጠናቀቅ ያሰብነው…ሐምሌ መጨረሻ ላይ  የጨረስነው ሃሳቡን የገዛ ብቻ ሳይሆን ሃሳቡን ወደ ተግባር የቀየረ ህዝብ ስላለ ነው። አዲስ አበባን እናለማለን አንድ እራት ላይ 5 ሚ.ብር ክፈል ስንል፣ ያለ ምንም ማሰብ… አይሰርቁኝም ብሎ አምኖ፣ በአንዲት ጀንበር ከ2 ቢ.ብር በላይ ነው የሰበሰብነው፡፡ ቃል የገባነውን ሰርተናል፡፡ አሁን ምርቃት ዝግጅት ላይ ነው ያለነው፡፡”
ሌላው ጠ/ሚኒስትሩ የህዝብ ድጋፍ እንዳላቸው ለማሳየት ያቀረቡት ማረጋገጫ፣ ህዝብ ኮሮናም እያለ ጭምር ለህዳሴ ግድብ የሚያዋጣው ገንዘብ እየጨመረ መምጣቱን ነው፡፡ የኮሮና ወረርሽኝን ተከትሎ መንግስት ላቀረበው  የማዕድ ማጋራት ጥሪም ህዝብ የሰጠውን በጐ ምላሽ በማድነቅ ጠቅሰዋል። በክረምቱ ላይ በህብረተሰቡ የተከናወኑ የበጐ ፈቃደኝነት ሥራዎችንም እንደ አብነት አቅርበዋል - መንግስታቸው የህዝብ ድጋፍ እንዳለው ለማሳያነት፡፡ ህዝቡ በጠየቅነው ነገር ላይ ሁሉ ተባባሪነቱን አሳይቷል ሲሉም አወድሰውታል፡፡
እናላችሁ… የህዝብ ድጋፋቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል ለሚሉ ወገኖች፤ እኔ ግን ስጋት የለብኝም ባይ ናቸው - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ “የህዝብ ድጋፍ የሚያሳስበው… መንግስት አንድ ሃሳብ ኖሮት፣ በገንዘብ በጉልበት በጊዜ የማይተባበር ህዝብ ቢሆን ኖሮ፣ ወቀሳ በተገባው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ወቀሳ አይገባውም፤ በጠየቅነው ሁሉ ከጐናችን እየቆመ ነው ያለው፤ ድጋፍ ቀንሷል ጨምሯል የሚለውን በተመለከተ…በእኔ በኩል ለህዝብ አቅርቤ…”ይህን ብናደርግ” ብዬ ህዝብ ያጐደለብኝ ነገር የለም፡፡ ለዚህም ምስጋና ይገባዋል፡፡ ምናልባት በምርጫ ጊዜ እናየዋለን የሚባል ከሆነ… ምርጫ በዚህ ዓመት እንደሚደረግ ይጠበቃል…ያኔ የምናየው ጉዳይ ይሆናል፡፡ ለኔ ግን እዚህ ቢሮ እስካለሁ ድረስ የህዝብን ድጋፍ የምለካው… አንድ የህዝብ ጉልበት በሚያስፈልገኝ ጊዜ ከጐኔ ቆሞ ህልሞቹ እንዲሳኩ ማድረግ መቻል ላይ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ማንም የአፍሪካ መንግስት…ማንም የኢትዮጵያ መንግስትም ቢሆን በዚህ ደረጃ ድጋፍ አግኝቷል ብዬ አላስብም…” ሲሉ በኩራትና በእርግጠኝነት መንፈስ ምላሽ ሰጥተዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
በእውነቱ ያቀረቡት ማስረጃዎች በሙሉ ውሃ የሚያነሱ ናቸው፡፡ አያችሁልኝ… ጠ/ሚኒስትሩ የህዝብ ድጋፋቸውን እንዴት እንደሚመዝኑት! ተቃዋሚዎችስ …(በተለይ ደግሞ ጽንፈኞች) የህዝብ ድጋፋቸውን የሚለኩት በምን ይሆን? (እኔም እናንተም እናውቀዋለን!) በፌስቡክ ላይኮች፣ የአመጽ ጥሪያቸውን በሚፈጽሙ የነውጠኞች ብዛት፣ ተቃውሞ ሲጠሩ በሚወጣላቸው ቲፎዞ!!
በነገራችን ላይ ያለፈው ነሐሴ ከጠባ እንኳ ጽንፈኛ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች፣ ስንት ጊዜ አመጽ ጠርተው--ከሸፈባቸው?! ስንት ጊዜ በምስማር የመኪና ጐማ አተንፍሱ! ሲሉ አዘዙ? አልተሳካላቸውም እንጂ! ለማንኛውም ግን አሁን ነው መፍራት፡፡ ለምን? ፖለቲከኛ ሁሉ ለሥልጣን አሰፍስፏላ!

Read 3066 times