Tuesday, 13 October 2020 00:00

የ2020 የኖቤል አሸናፊዎች ይፋ እየተደረጉ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  የታላቁ የኖቤል ሽልማት የ2020 የየዘርፉ አሸናፊዎች ካለፈው ሰኞ አንስቶ ይፋ በመደረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ እስከ ትናንት ድረስ የፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ህክምና እና ስነጽሁፍ ዘርፍ አሸናፊዎች ታውቀዋል፡፡
የዘንድሮ የኖቤል ተሸላሚዎችን ባለፈው ሰኞ ይፋ ባደረገው የህክምናው ዘርፍ ባለድሎች የጀመረው የሽልማት ድርጅቱ፣ ሃርቬይ አልተር፣ ሚካኤል ሃግተን እና ቻርለስ ራይስ የተባሉት ሶስት የዘርፉ ተመራማሪዎች ሽልማቱን መጋራታቸውን አብስሯል፡፡ ሶስቱ የህክምናው ዘርፍ ዶክተሮች ለዘንድሮው የኖቤል ሽልማት የበቁት በ“ሄፒታይተስ ሲ ቫይረስ” ዙሪያ ባደረጉት ከፍተኛ ምርምር ተጠቃሽ ግኝት በማፍለቃቸው እንደሆነ የጠቀሰው ተቋሙ፣ በምርምራቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ታማሚዎችን ከሞት መታደጋቸውን አመልክቷል፡፡
ማክሰኞ ዕለት ይፋ የተደረገው የዘንድሮው የፊዚክስ ዘርፍ አሸናፊዎች ዝርዝር ደግሞ፣ በህዋው መስክ በተለይ ደግሞ በ“ጥቁሩ ሽንቁር” ዙሪያ ፈርቀዳጅ የምርምር ውጤት ያበረከቱት የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲው ሮጀር ፔንሮሴ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ ምሁራኑ ሬንሃርድ ጌንዜል እና አንድሪያ ጌዝ ለሽልማት መብቃታቸውን ገልጧል፡፡
የሽልማት ድርጅቱ ረቡዕ ዕለት ይፋ ባደረገው መረጃ ደግሞ፣ “ጄኔቲክ ሲዘርስ” በሚል የዘረመል ተኮር ምርምራቸው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡት ጀርመናዊው ኢማኑኤል ቻርፔንቲየር እና አሜሪካዊቷ ጄነፈር ዶዳን የኬሚስትሪ ዘርፍ ተሸላሚ እንደሆኑ አስታውቋል፡፡ ከትናንት በስቲያ ሃሙስ ስዊድን ውስጥ ይፋ የተደረገው መረጃ ደግሞ፣ አሜሪካዊቷ ገጣሚ ሉውዚ ግለክ የአመቱ የኖቤል የስነጽሁፍ ዘርፍ ተሸላሚ መሆኗን አመልክቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ባለፈው አመት አሸናፊ የሆኑበት የሰላም ዘርፍ የዘንድሮ አሸናፊ ትናንት በኖርዌይ ይፋ የተደረገ ሲሆን አሸናፊውም፣ ………………መሆናቸው ታውቋል፡፡
የ2020 የኖቤል የኢኮኖሚክ ሳይንስ ዘርፍ አሸናፊ ከነገ በስቲያ ስዊድን ውስጥ ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡
የዘንድሮው የኖቤል ሽልማት ከአምናው ከሚለይባቸው ጉዳዮች መካከል የሽልማት ገንዘቡ በ1 ሚሊዮን የስዊድን ክሮና ያህል መጨመሩ እንደሚገኝበት ተገልጧል፡፡ የኖቤል ሽልማት ስነስርዓት እ.ኤ.አ ከ1901 እስከ 2019 በነበሩት አመታት በድምሩ 597 ጊዜ ያህል የተካሄደ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 923 ሰዎችና 27 ተቋማት ተሸላሚ ሆነዋል፤ ከእነዚህ ተሸላሚዎች መካከልም 54 ሴቶች እንደነበሩ ከድርጅቱ ድረገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በኖቤል ሽልማት ታሪክ በለጋ እድሜ በመሸለም ቀዳሚነቱን የያዘችው በ2014 ላይ በ17 አመቷ የሰላም ዘርፍ ተሸላሚ የሆነችዋ ማላላ ዩሱፋዚ ስትሆን፣ አምና በ97 አመት ዕድሜያቸው በኬሚስትሪ ዘርፍ የተሸለሙት ጆን ቢ ጉድናፍ ደግሞ የዕድሜ ባለጸጋው ተሸላሚ ናቸው፡፡


Read 2849 times