Saturday, 04 August 2012 09:43

የመርካቶ ሌቦችና ስታይላቸው!

Written by  ዘካሪያስ አትክልት
Rate this item
(1 Vote)

በሌቦችና በሌብነት ላይ የሚያተኩረውን ይሄን ፅሁፍ ያዘጋጀሁት የሚመለከታቸውን ወገኖች አነጋግሬ ሲሆን ዓላማውም አንባቢያን ራሳቸውን ከሌቦች እንዲጠብቁ መረጃዎችን ማቀበል ነው፡፡የመርካቶ ሌቦች በተለያዩ የአዘራረፍ ስልቶች የተካኑ ናቸው፡ አንድ ሌባ ከሌላው ሌባ በተግባር፣ በብልጠትና በስታይል እንደሚለየው ሁሉ ስያሜያቸውም እንዲሁ ይለያያል፡፡ ሿሿ፣ አስቀያሽ፣ አስማጭ ግንትር፣ ሠርሣሪ፣ ጨቡ፣ ሱቅ ለሱቅ፣ አክታ (ቀድሞ ወፍ አራችብህ የሚባለው ነው)፣ ተጫዋች፣ መንጩ፣ ቁጭ በሉ፣ ነቅናቂ…ወዘተ ተብለው ይመደባሉ፡፡ እያንዳንዱን የአዘራረፍ ስታይል እነሆ፡-

ሱፍ ለብሰው አምርዎቦት ታክሲ ሲጠብቁ ወይም ዎክ ሲያደርጉ ልክ እንደርስዎ ያማረበት ወጣት ወይም ጐልማሣ ቁርጭምጭሚትዎ ላይ በእግሩ ይመታዎታል፡፡ “ምን ነው? ምነካህ አንተ፤ ታቀኛለህ?” ቢሉም ቁርጭምጭሚትዎ እስኪቃጠል በጫማ ምላስ ኳ…ኳ ያደርግዎታል፡፡ ሃሳብዎን ሁሉ እግርዎ ላይ መጣልዎን ሲረዳ “እግርዎን እረገጥኩዎ እንዴ?” ይልዎታል፡፡ ንድድ ብለው “የሆንክ ደደብ…” ምናምን ብለው ሲሳደቡ ሰውየው ላጥ ይላል፡፡ ጌታዬ እርሶ’ኮ አሁንም አልነቁም፡፡ ሰውየው ግራ እግርዎን ሲረግጥና ሃሳብዎን እግርዎት ላይ ሲጥሉ፣ ቀኙ ኪስዎትን የሰውየው ጓደኛ አጥቦልዎታል፡፡ ይህ የአሠራረቅ ስልት ሌቦቹ “ነቅናቂ”  ይሉታል፡፡ ግራን ነቅንቆ ቀኝን ማጠብ! አይገርምም!?

ነገሩ አውቶቢስ ተራ አካባቢ ነው የተፈፀመው፡፡ ሌዘር ጃኬት የለበሰ፣ ቶርሽን ጫማ ያጠለቀ መልከኛ ወጣትና ሽበት ጣል ጣል ያለባቸው ሽማግሌ ያወራሉ፡፡ “ይኸው ፋክቱሩ… አምስት ሺህ ብር ነው የገዛሁት፤ የትራንስፖርት ስለጐደለኝ ነው፤ ይውሰዱት” ይላል ወጣቱ፤ እጁ ላይ ያለውን ሰዓት እያሳየ፡፡

“በቃ! ሁለት ሺህ ልውሰደው” ሽማግሌው ይመልሳሉ፡፡

“ከአራት ሺህ አምስት አልቀንስም፡፡ ወርቅ’ኮ ነው፡፡”

ድንገት እርስዎ እዛ አካባቢ ካሉ “ወርቅ” ሲል ክው ይላሉ፡፡

“ወርቅነቱን እያየሁት ነው፡፡ ሁለት ሺህ ልውሰደው አትጐዳም” ይላሉ፤ ሽማግሌው፡፡ ከአፍታ በኋላ “ተወው ተወው” ተባብለው ይለያያሉ፡፡ ቀጥሎ እርስዎ ጋር ይመጣል - ወጣቱ፡ “ቸግሮኝ…የትራንስፖርት…” ምናምን ይቀባጥርልዎታል፡፡ ተከራክረው ሺህ አምስት መቶ ይገዙታል፡፡ የወርቅ ሰዓት በሺህ አምስት ገዛሁ ብለው ሲዘንጡ፣ የ25 ብር የወርቅ ቅብ ሰዓት ማጥለቅዎን ከሰዓታት በኋላ ጓደኛዎ ያረዳዎታል፡፡

እንደነዚህ ዓይነት ሌቦች የሰዓት ግንትሮች - አገንታሪዎች ይባላሉ፡፡

ጐንደር በረንዳና ጐጃም በረንዳ በኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች መሸጫነታቸው ይታወቃሉ፡፡ ዘናጭ ሞባይል ለመግዛት እዚህ መንደር ብትመጡ፣ ከመሸጫ ሱቆቹ ፊት ለፊት አቀባበል የሚያደርግልዎት ግንትሮች አሉ፡፡ “ሄሎ ጀለሴ ቸስቼ ነው፡፡ ስልክ ትገዣለሽ?” ብለው የሚፈልጉትን ዓይነት ቂቅ ያለ ስልክ ያሳይዎታል፡፡ በቃ የስልኩ ውበትና ሲስተም ይመችዎትና “ስንት ነው” ይላሉ፡፡ “ሺህ ሁለት ውሰደው”

“ኧረ ቀንስ እንጂ?”

“በቃ አንድ ሺህ ውሰደው” ይሉዎታል፡፡ ዕቃ መሸጥ የሚያፍርና የሚሽኮረመም መስሎ ወደፊት እየሄደ፡፡ የልጁ ሁኔታ አሳዝንዎትና በርካሽ ማግኘትዎ አስደስትዎት “700 ብር ልውሰደው” ይሉታል፡፡

“እ…እሺ በቃ ውሰደው” ይልና ሲሜን ላውጣ ብሎ ስልኩን እሚከፍት አስመስሎ ተመሳሳዩን ቀይሮ ይሠጥዎታል፡፡ “ያው ሲም ስለሌለው አይበራም፤ ኪስህ ክተተው ሰው እንዳያይ” እያለ አቻኩሎ ብሩን ይዞ ላጥ፡፡ እርስዎ በለው ተሸቀለ! ብለው፣ ቤትዎ ደርሰው ስልኩን ሲከፍቱት በቀፎ ውስጥ አምስት አስራ ሁለት ቁጥር ሚስማሮች በማስቲሽ ተጣብቆ ያገኛሉ፡፡ “ኡ…ኡ…” ምናምን ቢሉም በሰባት መቶ ብር፣ የሞባይል ከቨርና አምስት አስራ ሁለት ቁጥር ሚስማር ይዘው እርፍ፡፡ አይገርሙም ግን ግንትሮች!!

ስኒከር ጫማ ያጠለቀ፣ አሪፍ ጃኬቱን ለቄንጥ አንገቱን አቅፎ ትከሻው ላይ ጣል ያደረገ ወጣት፤ ትክ ብሎ የኪስዎትን ቅርጽ ያጠናል፡፡ ብር የሚፈጥረውን ቅርጽ ከሌሎች ቁሶች ቅርጽ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ አርቆና አቅርቦ ተመልክቶ ኪስዎት ውስጥ ብዙ መቶ ብሮች እንዳለ ካረጋገጠ፣ ቀጥ ብሎ ወደ እርስዎ ይመጣል፡፡ “እህ…እህ…እህህ” እያለ እያሳለ ይቀርብዎታል፡፡ “እህ…ትፍ” ብሎ ብር በያዙበት ኪሶ አካባቢ ይተፋብዎታል፡፡ ንድድ ብለው በግልምጫ ትክ ብለው ሲያዩት፣ በትህትና በእጁና በሶፍት ይጠርግልዎታል፡፡

ትህትናው ተመችቶት “ኧረ ተወው” ሲሉት “ይቅርታ ወንድሜ፤ ጉንፋኑ እኮ ነው” እያለ አሁንም ይጠርግልዎታል፡፡ ለቄንጥ ያንጠለጠላት ጃኬቱን አንድ እጁን በሚጠርግበት እጁ ይዞ ሌላውን ያንዘላዝለዋል፡፡ ሸፍኖት’ኮ ነው፡፡ የሚጠርግለትን እሱና እሱ ብቻ እንዲያዩት፡፡ አጅሬው እያዋራ እየጠረገ ኪስዎ ዘው! አክታውንና ብሩን ጥርግ! በዚህ Specialized ያደረጉ ሌቦች “አክታዎች” ይባላሉ፡፡ ከመባነኑ በፊት ደግሞ “ጀለሴ፤ ወፍ አራችብህ” ብለው ጠረግጠረግ አድርገውልዎ ብሩን ጥርግርግ የሚያደርጉት “ወፍ አራችብህ” በመባል ይታወቁ ነበር፡፡

አስማጮች ደግሞ በጣም “ተጫዋች” ሌቦች ናቸው፡ ጨዋታ ከነሱ በላይ ለአሳር  ነው፡፡  ጆተኒ፣ ፑል፣ ካርታ የመሳሰሉት ጨዋታዎችን ተክነውባቸዋል፡፡ አለባበሳቸው እዚህ ግባ የማይባል ተራ ነው፡፡

ጆተኒ መጫወቻ ቦታ ላይ ሁለት ጓደኛሞች ይጫወታሉ፡ እርሶ ድንገት መንገድዎን ይዘው ሲያዘግሙ “ጀለሴ ዳኚን በናትሽ?...ፍሬንድ አንዴ ያዢልን?”... እያሉ ይወሰውስዎታል (ያሳስትዎታል) ዳኛ ካጡ ለምን አልዳኛቸውም ብለው ይዳኛሉ፡ ጓደኛሞቹ አንዱ በይ፣ ሌላው ተበይ ሆኖ ብዙ ጫወታ ይሄዳል፡ ተበይው ያሳዝንዎትና እኔስ ለምን አልነጨውም ብለው ይገባሉ፡፡ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጫወታዎች እርስዎ ይበላሉ፡፡ ተበይው ይናደዳል፡፡ (የውሸት’ኮ ነው ንዴቱ) ከዛ ንዴቱን አምቆ ይፋለማል፡፡ ያሸንፋል፡፡ ያሸንፋል… ያሸንፋል፡፡ ኪስዎት ውስጥ አንዲት ብር እንኳን ሳትቀር ይበላዎታል፡፡ እልህ ይዝዎት ስልክዎትን አሲይዘው ይጫወታሉ፡፡ አሁንም ይበላሉ፡ ሸሚዝዎትን ያሲዛሉ፤ ደግመው ይበላሉ፡፡ አስማጮች፤ ትልቅ ብቃት ያላቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡

እርስዎ ጭስስ ብለው የሚያደርጉት ሲያጡ፣ አስማጮቹ ተጠቃቅስው “አይዞሽ ጀለሴ” ብለው አጽናንተው ሞባይልዎትንና ሸሚዝዎትን ይመልሱልዎታል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ማሰማመጥ የተጀመረው በጆተኒ ቢሆንም ከጊዜው ጋር እያደገ ይገኛል፡፡ ወደ ፕሌይስቴሽንና ፑል ማጫወቻዎች የተዛወሩት አስማጮች፤ “ጆተኒ ጊዜው አልፎበታል” ይላሉ፡፡

“ይገርምሀል ዘኪ” አለኝ ካነጋገርኳቸው “ፕሮፌሽናል ሌቦች” አንዱ፡፡ “ጀለሴ ባለፈው ዓመት ምን አደረገ መሠለህ… የኮንዶሚኒየም ቤቶችን ለሣምንት አጠናቸው፡፡ ሁሉም አይተዋወቁም፤ ጐረቤት ጐረቤቱን አያውቅም፡፡ ሁለት አይሱዙ መኪና ይዞልሽ መጥቶ የሦስት ቤቶችን ንብረት፣ ምንጣፍ እንኳ ሣይቀረው ይዞ እብስ አለ፡፡ የሚገርመው እቃውን ቆሞ ያስጫነው ራሱ ነው፡፡ ጐረቤቶቹ ሲጠይቁት፤ ቤት ለመቀየር መሆኑን ነግሮ ይዞ ጭልጥ፡፡

የዚህ ዓይነት ዘራፊዎች ሠርሣሪዎች ይባላሉ፡፡ በር ሠርስረው፤ በተመሣሣይ ቁልፍ ከፍተው፣ በአጥር ዘለው የቤት ንብረትን ይዘርፋሉ፡፡ ሠርሣሪዎች በመኪናና የተለያዩ በር ለመክፈት በሚያግዙ መሣሪያዎች ይጠቀማሉ፡፡ አንዳንድ ምቹ አጋጣሚዎችን ወይም ሁኔታዎችንም ይጠቀማሉ፤ ለምሳሌ ዝናብ፣ የሠፈር ውስጥ ሁካታ፣ የእሣት አደጋ … ወዘተ ሲያጋጥማቸው ቢዚ ይሆናሉ፡፡

ሠርሣሪዎች እንደ ሌሊት ወፍ የሌት ትጉሀን ነበሩ፡፡ የህብረተሠቡ ጥንቃቄና የፖሊስ ክትትል ሲያሠለቻቸው “ሙዱን” ወደ ቀን እየለወጡት መጥተዋል፡፡

ማጣት የበረታባቸው ሠርሣሪዎች፤ ከአስራአምስት ቀን በፊት አብነት አደባባይን ለመስራት የተከለለ ከሠላሣ በላይ ቆርቆሮን የመንገድ ሠራተኛ በመምሠል፤ ሙሉ ቢጫ ቱታ ለብሠው፣ ጭንቅላታቸው ላይ እንደ ኢንጂነሮች ቆብ ደፍተው፣ ወፈርፈር ያለውን ጓደኛቸውን እንደ አዛዥ ሠይመው፤ በጠራራ ፀሀይ ቆርቆሮዎቹን ነቅለው መውሠዳቸውን ይገልፃል - ዓይኗ የተባለው አገንታሪ፡፡

መርካቶ ውስጥ በርከት ያለ ዕቃ ገዝተው፤ የዕቃው ክብደት ካየለብዎ “ወዛደር… ወዛደር” ማለትዎ አይቀርም፡፡ ኤርጋንዶ ያደረገ፣ ሽርጥ የለበሠ ወጣት “አቤት ምን ልታዘዝ?” ይልዎታል፡ “ይቺን እቃ እስከ ታክሲ መሣፈሪያ አድርስልኝ” ብለው፤ በሂሣብ ተስማምተው አሸክመው ይሄዳሉ፤ የተሸከመው ከፊት እርስዎ ከኋላ፡፡ ወዛደሩ ሲፈጥን እርስዎ ሲከተሉት በመሀላችሁ ሁለት አስቀያሾች ጥልቅ ይሉና ሀሣብዎን ይሠርቅዎታል፡፡ ወይ እንዲረግጡት ያደርጋል ወይም ቶሎ የምትበታተን ዕቃ እግርዎ ላይ ይጥላል፡፡ በትህትና ሊያነሡ ጐንበስ ሲሉ “ኧረ እኔ አነሣለሁ ይቅርታ!” ምናምን ይልዎታል፡፡ እርስዎም ለትልቅ ሠው የሚገባን ክብር ሠጥተው ቀና ሲሉ ያሸከሙት ልጅ ከዓይንዎ ተሰውሯል፡ ወደ ፊት ወደ ኋላ በዓይንዎ ቢያማትሩ የተሸከመ ሠው የለም፡ ወዛደሩ’ኮ አፍንጫዎ ስር ቁጭ ብሎ ያይዎታል፡፡ ወይም ስርቻ ውስጥ ዕቃዎን ለሌላ አስቀያሽ አስጠብቆ፣ ኮፍያ ገድግዶ፤ ሽርጡንና ኤርጋንዶውን ጥሎ ፏ ብሎ ያይዎታል - እስኪሄዱ፡፡ ይህ አሠራረቅ ማስቀየስ (አስቀያሽ) ይባላል፡፡

ሱቅ ለሱቅ ተጣባሾች (ሌቦች) ከሌሎች ይለያሉ፡፡ አንዱ ደርዘን ልብስ ማከፋፈያ ውስጥ ለሁለትና ለሦስት ይገቡና አንዱ “ይሄ ሱሪ ስንት ነው?” “መጨረሻው?” እያለ የነጋዴውን ሀሣብ ወደ ራሱ ሲያመጣ፣ ሌሎቹ አንዳንድ ሱሪ አጣጥፈው ጀርባቸው ውስጥ ይሸጉጣሉ፡፡ ከዛማ ይመርሹታል (ይሄዳሉ)፡፡ እንዲህ ናቸው የሡቅ ተጣባሾች፡፡

የሡቅ ለሡቅ ተጣባሾች በብዛት ሴቶች ናቸው፡፡ አንዳች የሚያህል ቦርሣ ይይዙና አንዷ ስትታልል ሌላዋ ቦርሣዋን ትሞላለች፡፡ አይ ቴክኒክ! አይ ቅልጥፍና! አጃኢብ ያሠኛል፡፡

ወዳጅዎ ከአሜሪካ ብር ልክዎሎት ወደ ባንክ ሄደው ብርዎን ይቀበላሉ፡፡ ኪስዎ ውፍርፍር ሲልብዎ በውይይት ወይም በሚኒባስ መሄድ ይደብርዎትና ላዳ ይጠራሉ፡፡ ላዳዋ ከች ትልና በርካሽ ገንዘብ ይስማማሉ፡፡ ታዲያ ሹፌሩ ብቻ አይደለም መኪና ውስጥ ያለው፡፡ ተሣፋሪ የመሠሉ ጐልማሣም ካጠገብዎ ይኖራሉ፡፡ ሹፌሩ ኩርባ ኩርባ መንገድ እየመረጠ እያንገጫገጨ ይወስድዎታል፡፡ ጐልማሣው ስለ መንገዱ፣ ምናምን አንዳንድ ወሬ እያመጣ ይቀርብዎታል፡፡ ያሠቡት ቦታ ሣይደርሡ ሹፌሩ መኪናው የተበላሸ አስመስሎ “ውረዱልኝ፤ ሂሣብ አልፈልግም” ብሎ ይማፀንዎታል፡፡ ካልከፈልኩ ምን አከራከረኝ፤ እንደውም በነፃ ተሸኘሁ ብለው ወርደው በእግርዎ ይሄዳሉ፡፡ ልክ ቤትዎ ሲገቡ ኪስዎ ተቀዶ ብርዎት የለም፡፡ እንዴት መሠልዎ የሠረቅዎት? ጐልማሣው ከቀረበዎት በኋላ ሀኪሞች (ሠርጀሪዎች) የሚሠሩበትን አይነት ምላጭ ወይም ሌሎች ምላጮችን ተጠቅሞ የሱሪዎትን ኪስ በስታይል ይቀዳል፡፡ ለመቅደድ’ኮ አይታገልም፡፡ ሹፌሩ አለለት፡፡ ገጭ ገጭ ሲል ምላጭዋን ማስተካከል ነው፡፡ በቃ፤ ከዛ ብርዎትን ይዘረፋሉ፡፡ ይህን አዘራረፍ ሿሿ ይሉታል፡፡

ሿሿዎች በውይይትና ሚኒባስ ላይም አልፎ አልፎ ይከሠታሉ፡፡ ሌላው ስታይላቸው… የክፍለአገር ሚኒባስ ውስጥ ሠባት ስምንት ሿሿዎች ሆነው ይገባሉ፡፡ እርስዎም አብረው አሉ፡፡ የሆነ ቦታ ላይ “ፍተሻ አለ ውረዱ” ይላል ሹፌሩ፡፡ “አልወርድም ሞቼ እገኛለሁ!” ምናምን ሲሉ ዝንጥንጥ ያሉ ሿሿዎች “መቼም ከህግ አንበልጥ እንፈተሽ” እያሉ ተከታትለው ሲወርዱ ሲያዩ ጤነኞች መስለዎት እርስዎም ዱብ ይላሉ፡፡ መኪናዋ በር ላይ ስልክዎትን ብርዎትን፣ ወርቅዎትን አስረክበዋል፡፡ በቃ እርስዎን ሣይጭኑ ሽብልል ይላሉ፡፡ “ቆይ አለቀውም” ብለው ታርጋው ላይ ሲያነጣጥሩ ታርጋው አይታይም፡፡

ሿሿዎች በከተማ ስለተነቃባቸው አሁን አሁን በብዛት ወደ ክፍለ ሀገር የሚጓዙ መኪኖች ውስጥ ገብተዋል፡፡ ሙዳቸውንም ከመንገዱና ከሚሄዱበት ክፍለ ሀገር ሁኔታና ጠባይ ጋር ይቀያይራሉ፡፡ ያነበቡትን በልቦናዎ ያሳድርልዎ! ራስዎን ከሌቦች ይጠብቁ!

 

 

 

Read 6030 times Last modified on Saturday, 04 August 2012 09:50