Saturday, 10 October 2020 15:19

የግጥም ጥግ

Written by  ከአጥናፉ አበራ (የራዕዩ)-
Rate this item
(3 votes)

     ታውቃለህ እያለች

. . . ባሏን እንኳ ከእጇ ስትቀማት ከእቅፏ
አላማረረችህ ክፉ አልወጣት ከአፏ
የአርባ ቀን እድሏን ግንባሯን ተራግማ
ብርድ ዘልቆት ቤቷን በተስፋ አገግማ
አያርማት ልበ ቢስ
መጽናናትህን ሰምታ መጽናናት መልሳ
የልቧን መብሰክሰክ ብቻዋን ታግሳ
ማምለኳን አትተዉ ቂም አትይዝብህ
ምስህን አታስቀር አታጓድልብህ
ትለምንህ ነበር
ትማጸንህ ነበር
ነፍሱን ባርካት ስትል
ከእርግዝናዋ ጋር ወደ ደጅህ ዘልቃ
ብስራትህን ናፍቃ አቀበቱን ንቃ
ጽንሷ እሱን እንዲሆን እንዲያምር በግብሩ
በደስታዋ አልቅሳ እንዲተካ በእግሩ
እንዲባረኩላት እንባዋና ደሟ
በእንባዋ መባረክ ተግ እንዲል ህመሟ
በእንባዋ መባረክ እንዲባረክ እሱ
ትማጸንህ ነበር
ትለምንህ ነበር ‹‹ልመናዋ ክብሯ››
ልመናዋ ራሱ በአስራትህ በዝክሯ፡፡
ደጅህ ለተገኘ መጥሪያህን ለጠራ
መቀነቷን ፈ’ታ ከጉርሷም ቆንጥራ
‹‹እስቲ ቁጭ በል ብላ›› አጎዛ አንጥፋለት
ደረቷን ደልቃ ከንፈሯን መ’ጣለት
መንገድ አመላክታዉ
በወጉ ሸኝታዉ
አትጠግብ አይበቃት
መጥሪያህን ለጠራ
ባንተ ለመጣባት፡፡
ትለምንህ ነበር
ትማጸንህ ነበር
ስንት ያለመችለት
ስንት የሆነችለት
ስንት የተወችለት
የሆዷ ቡቃያ ሲደመደም በደም
ካልክ ብላ ትታዉ
ብትብሰለሰልም የአዘን ጫፉን አይታዉ
ትማጸንህ ነበር
ትለምንህ ነበር፡፡
ምን ለምኗ ብላ እንደምትለምንህ
ሳታዉቀዉ አንዳንዴ
ትማጸንህ ነበር
ማኅጸኗም ቤቷም ወና ሆነዉባት
ከነበራት ሁሉ ተስፋ ማድረግ ቀርቷት
እሱ ራሱ ሸሻት
እንጂ . . . ተስፋማ ነበራት
ከዚያ ላይ ተልኮ ፍቅሯ ሊጎበኛት
አንጋላ ልትስም የባሏን አምሳያ
ማህጸኗም ቤቷም ወና ሆነዉባት
እንዳልነበር ባይቀር ተስፋማ ነበራት፡፡
የለህም ሳትልህ ይሄንም ታግሳ
ደጃፍህን ተሳልማ በወጉ አስቀድሳ
ስትሳሳህ ስትጎዳት
ስታምንህ ስትከዳት
ፈጅተህ ዘመኗን
ቆመችዉ እርቃኗን፡፡
ዛሬ ላይ ራሱ ያንተ ቀን ነዉና
ፈክታለች - አ ምራለች
ይጫጫሳል ቤቷ
ይስባል ከሩቁ የድግሷ ቃና
ለአበሳ ብድርህ ስትከፍልህ ምስጋና::
ይገርማል አንተየ!?
ባክና አለማብቃቷ ሳስታ አለማለቋ
አለመኮነንህ እሷ አለመጽደቋ
ይገርማል!
ሰው ሆና መቅረቷ፡፡
ከአጥናፉ አበራ (የራዕዩ)-


Read 2291 times