Monday, 12 October 2020 00:00

“ሕያው ፍቅር” - የደረጀ በቀለ የበኩር ልጅ

Written by  ደ.በ
Rate this item
(0 votes)

 የበዐሉ ግርማን ‹‹ደራሲው›› የተሠኘ መጽሐፍ ከሰባት ጊዜ በላይ ለምን እንዳነበብኩት አይገባኝም፡፡ ግን ሁሌ አዲሴ ነው፡፡ አምሥት ጊዜ ያነበብኩት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ሣልጨርስ ነበር፡፡ ግን ባነበብኩት ቁጥር ሁሌ ይደንቀኝ ነበር። ሌሎቹን ከፍ ካልኩ በኋላ ምናልባትም አንደኛውን ከሦስት ዐመት በፊት ማንበቤ ትዝ ይለኛል፡፡ የበዐሉ ስራ ባነበቡት ቁጥር ዕድሜና ዕውቀት ከፍ ሲልም አብሮ ከፍ የሚል ይመሥላል፡፡ አንዳንዴ በልጅነታችን ያነበብናቸዉን መጻሕፍት ከፍ ብለን ስናነብባቸዉ ዝቅ ይሉብናል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ደረጃቸዉን ጠብቀዉ ይዘልቃሉ፡፡ በቅርቡ ያነበብኩት የአንድ ደራሲ መጽሐፍ በድሮ ቁመናው የማገኘው መሥሎኝ፣በእጅጉ ወርዶብኝ ደንግጫለሁ፡፡
ወደ ዛሬው ርዕሰ ጉዳዬ ስመጣ፤ “ሕያው ፍቅር” የተሠኘውን የደረጀ በቀለን መጽሐፍ አስቃኛችኋለሁ፡፡ የደረጀን መጽሐፍ ለሦስተኛ ጊዜ አንብቤዋለሁ፡፡.. መጽሐፉ አሁንም በቀድሞ ቁመናዉ፣ እንዲያውም በተሻለ ፍተሻ ሲነበብ ግሩም የሚያሠኝ አቅም እንዳለው ተረድቻለሁ፡፡
በሀገራችን የአማርኛ ስነጽሑፍ ውስጥ የላቀ ስፍራ ከሚሰጣቸው የረዣዥም ልቦለድ ድርሰቶች ተርታ ሊሰለፍ እንደሚችል አስባለሁ፡፡ ለዚህም ደግሞ በርካታ ማሣያዎች ማቅረብ ይቻላል። ልቦለድ መጻሕፍት በርካታ ቅርጻዊና ጭብጣዊ ዘዉጎች አሏቸዉ፡፡ ዘመናዊ ልቦለዶችም የራሳቸው መለኪያዎች አሏቸው፡፡ አላባውያኑን አጢኖ የሀሳቡን ቁመና፣ የትረካውን ግራ ቀኝ ዳሰሳ አጢኖ፣ “እንዲህ ነው” ማለት ይቻላል፡፡ ድርሰቱ በ“እውነታዊነት” የተፃፈ ከሆነ ከአሁኑ አለም ጋር በማነፃፀር፣ ማኅበረ-ባህላዊ፣ ማኅበረ-ፖለቲካዊ፣ ስነልቦናዊ ወዘተ--መልኮች በመመዘን ገፀ ባህሪያቱ በሚናገሩት፣ በሚነገርላቸውና በሚኖሩት- የደራሲውን ልክ ማየት ይቻላል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመጡትን የአለማየሁ ገላጋይ፣ የአዳም ረታ ዐይነት ዘውጐች ትተን በዘመናዊ ልቦለድ ዐይን ከመዘንነው፣ የደረጀ በቀለ “ሕያው ፍቅር” ባለ ትልቅ ክብር፣ ባለ ከባድ ሚዛን ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ሜጋ አሳታሚ ድርጅት ገና በትኩስነቱ ካሳተማቸው መጽሐፍት አንጋፋው ሲሆን በአንባቢ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትና ከበሬታም አግኝቷል፡፡ በሬድዮ ፋና በመተረኩ በአድማጮች ጆሮና ልብም ትዝታ ያለው ነው፡፡ ዛሬም መጽሐፉን ለመዳሰስ ያነሳሳኝ በድጋሚ በሬድዮ ፋና ላይ  እየተተረከ መሆኑ ነዉ፡፡
ይህ ልብወለድ በታሪኩ ጉዞ የተለያዩ ጭብጣዊ ዘውጐችን ይነካካል፡፡ ድርሰቱ ሲጀምር ታሪክ ቀመስ ዝንባሌ አለዉ፡፡ በታሪኩ መካከልና ማጠፊያ አካባቢ ደግሞ ወንጀል ነክ ታሪኮች ሲጦዙበት ይስተዋላል፡፡ የዚህ ታሪክ ጅማሬ ብሔራዊ ቴአትር ውስጥ በሚታየው ‹‹ኦቴሎ›› የተሰኘ ቴአትር ሲሆን በመጽሐፉ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያለው ገጸ ባሕርይ ቻርሊ ቃሲዮን ይባላል፡፡ የቱጃር ልጅ የሆነችው አብነት የቴአትሩ ተመልካች ሆና፣ ሣራ ጋዴም ደግሞ ከትወና ስትወርድ በሚፈጠረው ውስብስብ ገጠመኝ ታሪኩ ወደፊት ይገሰግሳል፡፡
ሣራ ጋዴም ማናት? ስለ ራሷ ገድል መሥማት የምትፈልግ፣ በራሷ ፍቅር የወደቀች፣ የዐለም ሁሉ ተዐምራት በእርሷ የመድረክ ትወና ተውጦ እንዲረሳ የምትፈልግ አርቲስት ናት፡፡ አብነት ደግሞ ስለ ፍቅር የማታውቅ፣ “ወንድ በሩቁ” የምትል፣ ግን ደግሞ በአንድ ቀን መድረክ በቻርሊ ልቧ የተጠለፈ ምስኪን ናት፡፡ እዚያ መድረክ ስር በድንገት የተጫረችው ክብሪት እንደ ቀትር ፀሐይ ብርሃንዋ እየጨመረ፣ ታሪኩን እያፈረጠመ በመሄድ፣ እስከ ታሪኩ ፍፃሜ ድረስ በምጥና በፈተና ስትበራ ትታያለች፡፡
ቻርሊ ኮሙኒስታዊ አስተሳሰብ ያለው፣ ለጭቁኖች የሚታገል ልብ ያዳበረ ከያኒ ነው፡፡ ምናልባት ይህ የሆነው እናቱ ስለተወገሩ፣ አባቱ ፋቂ ተብለው ስለተገለሉ ሊሆን ይችላል፡፡ ሚካኤል ጐርባችሆቭ በልጅነት ዘመናቸው፣ ዘመዶቻቸው ሀብት በማፍራታቸው “ኩላክ” ተብለው ሲገደሉ ሲዋረዱና ሲታሠሩ ዐይተው የጣሉትን ኮሙኒስታዊ ስርዐትና ርዕዮት ዐለም ለማፍረስ እንደተነሱ፣ ቻርሊም የፊውዳሉ ስርዐት በቤተሰቦቹ ላይ የጫነው ቀንበር ያጐበጠው ልቡ፣ በድንገት ቀና ብሎ ያንን አስተሳሰብና የአስተሳሰቡን ስር ለመንቀል የሚታትር ይመሥላል፡፡ ስለዚህም ኢህአፓዊ ፍቅር ላይ ወድቆ “ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም!” ከሚለው ወገን ቆሟል፡፡
አብነት አብዮት አታውቅም፣ ፍቅር አታውቅም፣ ከፍቅር ነፃ ሆኖ መኖር የሚል መርህ አላት፤ የእርሷ ሕይወት የአባቷን ቤት የሂሣብ መዝገብ እያገላበጠች፣ ሣራ ጋዴም ቴአትር በጋበዘቻች ቁጥር ሄዳ መመልከት ብቻ ነው፡፡ ሌላ ጣጣ የለባትም፡፡ ፍቅርን የጠላችበት ምክንያት አላት፡፡ አባቷ፣ እናቷ ላይ የሚሠሩትን ግፍ አይታለች፤ በስተርጅና መቅበጣቸውን አውቃ ተንገሽግሻለች፡፡
ልበ-ቅኗ የቱጃር ልጅ አብነት፣ በቻርሊ ፍቅር ወድቃ ብዙ ዋጋ ከፍላለች፡፡ የሣራ ጋዴምን ምክር መሥማት ተሥኗት፣ የፍቅር ምድጃ ላይ ተጥዳ ተንተክትካለች። በሀጢአትና በግፍ የታጀበው የአባቷ ሀብት፣ ደም የተነከረ ጣዕሙ እየጐመዘዛትና እየቆፈራት ስትኖር፣ በዕድሜ ማምሻ፣ ቤታቸው የመጣው አዉሎ ነፋስ ንጧቸዉ ነበር፡፡ ሀብታቸውን ብቻ ሣይሆን የቤተሰባቸውን ሕልውና ሊነቅል ሲታገል፣ በአንድ በኩል እርሷን በፍትወት ምኞት በጉጉት ዐይን የሚያላምጠው ጠበቃ እጁ ሊያስገባት፣ በሌላ በኩል የአባቷን ሀብት ብቻ ሣይሆን የቤተሰባቸውን ሕልውና ሊነቅል ይመጣል፡፡ በአንድ በኩል፤ እርሷን በፍትወት ምኞት በጉጉት ዐይን የሚያላምጠው ጠበቃ እጁ ሊያገባት፣ በሌላ በኩል የአባቷን ሀብት ተረክቦ ከወንጀል ሊገላግላቸው ሲል የተፈጠረው አጣብቂኝ፣ አንባቢን በማያቋርጥ ልብ ሰቀላ ያወዛዉዛል።
‹የ‹‹ሕያው ፍቅር›› ገፀባህሪያት በአብዛኛዉ ለአፈጣጠራቸው ምክንያት አላቸው፡፡ ለምሳሌ ናፖሊዮን የተባለው አየር ወለድ የነበረና በኋላ የአብነት አባት፣ የአቶ መንገሻ የወንጀል ቀስት የሆነው ሰው ያለ ምክንያት ጨካኝና ገዳይ አልሆነም፡፡ እርሱን የፈጠሩት ኮሎኔል አባቱ፤ ፈረንሳዊውን ጄኔራል ናፖሊዮን ቦናፓርትን ያደንቁ ስለነበር፣ ኢትዮጵያዊው ናፖሊዮን ለመሆን ባላቸዉ ናፍቆት ብዙ ሞክረው አልሳካ ሲላቸው፣ ልጃቸው ናፖሊዮን እንዲሆን ተመኝተው፣ የሚችሉትን ሁሉ በውስጡ ጫኑበት፡፡
ናፖሊዮን ልጅ እያለ አበባ ተካይና ተንከባካቢ፣ ሰላማዊ ልጅ ነበር፡፡ አባቱ ግን ያ ሰብዕና ለህልማቸው መሳካት እንደማይሆን አስልተው፣ ሌላ ሰው ውስጡ መፍጠር አሰቡ፡፡ ለዚህም ዉጤታማነት፣ በመጀመሪያ ራሱ የተከላቸውን አበቦች እንዲጨፈጭፍ አስገደዱት፤ ቀጥለው ደግሞ ከእጁ እየጎረሰች ያደገችውን የበግ ግልገል እንዲያሥራት አዘዙት፤ አሠራት፤ ከዚያ ቀጥለው እዚያው ፊታቸው ላይ እንዲያርዳት አደረጉት፡፡ በቃ! እንደ ናፖሊዮን ንጉስ ሆኖ ዘውድ ባይደፋም፣ ጄኔራል ሆኖ ጦር ባይመራም፣ ገዳይ የሆነ ልብ አብቅሎ፣ ደም መርገጥ ለመደ፡፡ አባቱ የሠሩት ናፖሊዮን በብዙ የግፍ መንገድ በጭካኔ አለፈ፡፡
መጽሐፉ የዘመን መንፈስና ከባቢንም ለማሣየት ታሪኩ ከረገጣቸው የታሪክ መስኮች የወሰዳቸው አሻራዎች አሉት፡፡ ለምሣሌ በዘመኑ የነበረውን የዳንስ ዐይነት ይነግረናል። ዛሬ የተረሱ ያኔ ትኩስ የነበሩ ማሪንጌቻች፣ ትዊስት ብሊፕስ ወዘተ--እያለ። እነዚህ ነገሮች በሕይወት ተፈራ “ማማ በሰማይ ላይ; መጽሐፍ ውስጥ የሚንፀባረቁ መሠል የዘመኑ ነፀብራቆች ነበሩ፡፡ መኪኖቹም መርሰዲስ፣ ሲትረንና ኦፔል ናቸው፡፡ እንደ ዛሬው ሀገራችንና ዐለማችን በዘመናዊ አውቶሞቢሎች አልተጥለቀለቁም፤ አለባባሱ ፀጉር አበጣጠሩም የዚያ ዘመን ቀለም ማሣያ ናቸው፡፡
በሞራላዊ ገጽታው ጨካኝና ሆዳም፣ ዘማዊ ጠበቃ ባለበት ታሪክ ውስጥ ተካልኝ ባልቻን የመሠለ ውለታ ቆጣሪ ስለተደረገለት ነገር መልካም ብድራት ለመክፈል እንቅልፍ የሚያጣ፣ ደጋግሞ ለሌሎች በጐነት የሚያደርግበትን በር የሚያንኳኳ ብፁዕም አለ፡፡
የጥበብ ሕይወትን በጥልቀት የሚያንፀባርቀው “ህያው ፍቅር”፤ ከቲአትር ጐን ለጐን የሠዐሊውን የአብነት አጐት የህይወት ፍልስፍናና ጥበብ ያሣያል። የሠዐሊን ምጥ ሕልሙንና ተስፋውን እየነሰነሰ፣ የከያንያንን የሌትና ቀን ትጋትና ትግል ያካፍለናል፡፡ ፈረንሳይ ሀገር የተማረው አጐቷ፤ ኮሙኒዝምን የሚያይበት ዐይን የሁለቱን ዐለም ተቃርኖ ትርጓሜ ከፈገግታ ጋር እንድናጤነው፣ ባላንጣነታቸውን ሚዛን ላይ እንድናስቀምጠው ይጐትተናል፡፡
በቴአትሩ ዓለም ከሃያ ዐመታት በላይ ሣቅና ልቅሶ፣ ሐዘንና ደስታ፣ ድልና ሽንፈት ባለበት መድረክ ላይ “መሃይም” የተባለውን ቻርሊን ቁስል፣ የዳንኤልን የስልጣን መሠላል ጉዞና የዘመኑን የቴአትር ቤቶች መጠላለፍ---ፍንትው አድርጐ ያሣያል፡፡
ሣራ ጋዴም ስለ ሕይወቷ ግዴለሽነት ቢነገረንም እርሷ ግን የምትለው እንዲህ ነው፡- “…በዚህ ዐለም ላይ የምኖረው ለሁለት ነገር ስል ነው፡- ለቴአትር ለስነጥበብና ዳንስ።" እውነትም ይመሥላል፡፡ ለቴአትር ሣይሆን ከቴአትር ለሚገኘው አድናቆትና ጭብጨባ እንደሆነ በየቴአትሩ ፍፃሜ “እንዴት አየሽኝ“ በማለት ልቧን በምታወልቃት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጓደኛዋ፣ አብነት ስቃይ እናየዋለን፡፡
ምክንያታዊ በሆኑ የድርጊት አፅቆች የታጨቀው ድርሰቱ፤ ቀስ በቀስ እየተያያዘና ተሰብስቦ ቦግ እያለ እየበራ፤ እየሣቀ፣ እያዘነ እያሣዘነ፣ እያስማጠ እየቆነጠጠ ወደፊት ይገፋል፡፡ በተለይ የአብነት አባት አቶ መንገሻ፣ ኮንትሮባንድ ሲያስነግዱ፣ መኪናቸው በፊናንስ ፖሊሶች በመያዝዋ በተፈጠረ ተኩስ ምከንያት የመጣ ስር-ነቀል ጣጣ፣ ታሪኩን አጡዞ ልባችንን ያንጠለጥለዋል፡፡ የሚገርመው ግን በመጽሐፉ የመጨረሻ ገጽ እንኳ የታሪኩ ትኩሳት ሳያቋርጥ እየነደደ፣ ፍሙ እንደተጋገረ መዝለቁ ነው፡፡
“ሕያው ፍቅር” … ለዘመናት የሚዘልቅ ሕያው ሥራ ሆኖ፣ የደራሲውን ደረጀ በቀለ ስም ሕያው ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በአፀደ ሥጋ የሌለውን የሀገሬ ከያኒ በመጽሐፉ ሳስታውሰው ደስ ቢለኝም ልቤ ውስጥ የሚንቦለቦለው እንባ፣ የሚጋልበው ትዝታም የማዕበል ያህል የሚንጥ ነው፡፡


Read 848 times