Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 04 August 2012 09:44

“ጋዜጣ ላይ ብንጽፍም ባንፅፍም ስጋቱ አለ”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“ፍትህ” ጋዜጣ እንዴት ተመሰረተ?

ጋዜጣው በ2000 ዓ.ም መጋቢት ወር ላይ ነው የተመሠረተው፡፡ በወቅቱ የነፃው ፕሬስ ጉዞ ላይ የራሱን አሻራ ያሳርፋል በሚል ነው አመሰራረቱ፡፡ ምክንያቱም ከምርጫ 97 በኋላ በርካታ ጋዜጦች ላይ መንግስት በወሰደው እርምጃ የፍርሃት ድባብ ሠፍኖ ነበር፡፡ ያንን ድባብ ለመግፈፍ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን በሚል ነው “ፍትህ” የተመሰረተችው፡፡ እንደሚታወቀው ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ 21 አመት ሞልቶታል፡፡ ጋዜጣው ሲመሠረት ኢህአዴግ 17 አመቱ ነበር፡፡  እናም ይሄንን ሁሉ አመት አገር ሲያስተዳድር የነበረው እራሱ አጋፋሪ ሆኖ ባፀደቀው ህገመንግስት ሳይሆን በጉልበቱ ነበር፡፡ ይበልጥ ደግሞ የምርጫ 97ን ጦስ ተከትሎ የተነሳውን ረብሻ ተገን በማድረግ፣ ጉልበቱን ከሚገባው በላይ አጠንክሮ ያሉትን ጋዜጦች ካጠፋ በኋላ፣ የቀሩትን ደግሞ በአስፈሪ ድባብ ውስጥ እንዲወድቁ አደረጋቸው፡፡ “ፍትህ”ም ያንን የፍርሃት ድባብ ለመግፈፍ ነው የተቋቋመችው፡፡

ጋዜጣውን ከመመስረትህ በፊት ምን ነበር የምትሠራው?

“ፍትህ”ን ከመመስረቴ በፊት የውጪ ኦዲተር ሆኜ ሠርቻለሁ!! ከዛ ነው በቀጥታ ወደዚህ የመጣሁት፡፡

አጀማመሩ ላይ የጋዜጣዋ ቅጂ አነስተኛ የነበረ ይመስለኛል፡፡ ይዘቱስ?

በአገሪቱ የጋዜጣ ህትመት ብዛት ትንሽ የምትባል ነበረች፡፡ ከዛም ባሻገር ጋዜጣዋ ብዙ ችግሮች ስለነበረባት አንዳንዴ ትወጣለች አንዳንዴ አትወጣም፡፡ ቢሮአችንም የተዘረፈበት አጋጣሚ ነበር፡፡ እናም ዘረፋ ከተፈፀመ በኋላ ጋዜጣዋን እንደ አዲስ ነው የመሠረትኩት፡፡ ጋዜጣው የነበረበትን መንገድ ገምግሜ፣ ወደ ሌላ አዲስ ምዕራፍ እንዲመጣ ለማድረግ መጀመሪያ ዕቅዱን በወረቀት ላይ ነው ያወጣሁት፡፡ ያ ዕቅድ ተተግብሮ ነው አሁን ስኬቱ እየታየ ያለው፡ እናም እስከ 2002 ክረምት ድረስ ጋዜጣው በኪሳራ መንቀሳቀሱ ብቻ ሳይሆን ከአገሪቱ በጣም ትንሽ የሚባል ጋዜጣ ነበር፡፡ የተለየ እቅድ፤ የተለየ ስትራቴጂ አውጥቼ ነው ጋዜጣው የደረሰበት ስኬት ላይ ልንደርስ የቻልነው፡፡

ጋዜጣው ላይ ሁለት ዓይነት አስተያየቶች ይሰነዘራሉ፡፡ አንደኛው ተወዳጅ የሆነችው ስለምታጋንን ነው የሚል ሲሆን ሌላኛው ምስጢር ስለምታወጣ ነው ይላሉ፡፡ አንተ ምን ትላለህ?

የተጋነነ ነገር ይፃፋል በሚለው ከሄድን አሁን እንደውም ያንን አይነት ነገር የለውም የተጋነነ ስራ ይሠራ የነበረው በኪሳራው ጊዜ ነው፡፡የመጀመሪያዎቹን ህትመቶች ማየት ቢቻል… በጣም የተጋነኑ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ የተጋነኑ ሲባል ደግሞ በሬ ወለደ እየተባለ ይፃፍ ነበር ማለት አይደለም፡፡ በሬ ወለደና የተጋነነ የተለያዩ ናቸው፡፡ የተጋነነ ሲባል ምን ማለት መሰለሽ… እውነትን ይዞ በአጋናኝ ቃላት መጠቀም ማለት ሊሆን ይችላል፡፡

ሌላው የእድገት ምእራፍ የምንለው ላይ ስንመጣ… አሁን ያለንበትን የጋዜጣዋን ደረጃ ነው የምናገኘው፡፡ ይህም ጋዜጣው እራሱን አርሞ፣ ችግሮቹን ቀርፎ እንደ አዲስ ተዋቅሮ ነው እዚህ የደረሰው፡፡ ምናልባትም የ”ፍትህ”ን የመጀመሪያ አካባቢ ህትመቶች ብትመለከቺ በቂ ምስክርነት ይሰጣሉ፡፡

ፖለቲካዊ ትንታኔያችሁ ድፍረት የተሞላበት ነው፡፡ ድፍረታችሁ ከምን የመጣ ነው? አንዳንዶች የተማመኑበት የመንግስት አካል ሳይኖር አይቀርም ይላሉ…

ይሄ ሊሆን አይችልም፡፡ ጋዜጣዋን ያገደው መንግስት ሆኖ ሳለ፣ መንግስት ይደግፈናል ማለት ማሾፍ ነው፡፡ የእኛ ድፍረት ለሙያው ከምንሠጠው ክብር የተነሳ ነው፡፡ ሙያው የሚጠይቀው ድፍረትን ጭምር በመሆኑ ነው፤ ከዚህ ውጪ ሌላ ነገር የለውም፡፡ የጋዜጠኝነት ስራ እንደ ባለቅኔ ሰምና ወርቅ የሚመለስበት አይደለም፤ ጋዜጠኛ “አካፋን” “አካፋ”፤ “ዶማን” “ዶማ” ሊል ይገባዋል የእኛ ድፍረት እንደዚህ ተብሎ ሊገለፅ የሚችል ነው፡፡ እናም ከስርአቱ ብልሹነትና አምባገነንነት አኳያ፣ ከመውረዱ አንፃር ስታይው… እንደውም ብዙ ገፍተን እየሠራን ነው ማለት አንችልም፡፡

ቀደም ሲል ሁለት የግል ጋዜጦች መዘጋታቸው ይታወቃል፡፡ የእነሱ አይነት ዕጣ ይደርስብናል የሚል ስጋት አድሮባችሁ ነበር?

አንድ ነገር ግልጽ መሆን አለበት፡፡ በእኛ ትውልድ እኛ የምናውቀው ይሄኛውን መንግስት ነው፡፡ እዚህ መንግስት ላይ ባንጽፍም ስጋቱ አይቀርም፡፡ ደጋፊ ሳትሆኚ በመኖርሽ ብቻ ትሰጊያለሽ፡፡ እንኳን የፖለቲካ ጋዜጣ አዘጋጅተሽ ቀርቶ፣ ስርአቱ እራሱ ዜጐችን በስጋት ላይ ለመጣል የተመሠረተ እስኪመስል ድረስ ከአፈፃፀሙ የስጋት ምንጭ የመሆን አዝማሚያ አለው፡፡ እናም ባንፅፍም ብንፅፍም፣ ቤታችን ብንቀመጥም በሌላ ሙያም ብንሰማራ ስጋቱ አለ፡ አሁንም ቢሆን ይሄ ነገር ሊከሰት እንደሚችል እናውቃለን፣ ግን አደጋ ፈርተን ወይም ደግሞ አንድ ችግር ይከሰታል ብለን አገራችንን ከማገልገል ወደ ኋላ አንልም፡፡ ይህ ነው በስራችን ላይ ደፍረን እንድንሰራ ሃይል የሰጠን፡፡

ጋዜጣችሁ ላይ ብዙ ማስታወቂያ አይታይም፡ ማስታወቂያ ሳይኖር ጋዜጣ ማሳተም ያዋጣል?

በመጀመሪያ ደረጃ በጋዜጣው ላይ ማስታወቂያ እንዳይኖር የሚያስፈራራ ሃይል አለ፡፡ ያ ሃይል መልሶ ደግሞ ያለማስታወቂያ እንዴት ኖራችሁ ብሎ ሲፈርጅ ትመለከችዋለሽ ሌላው ጉዳይ የፕሬስ አዋጅ ላይም ሆነ አሁን በፀደቀው የማስታወቂያ አዋጅ ላይ ከ60 በመቶ በላይ ማስታወቂያ ማውጣት አይቻልም እንጂ አለመጠቀምም ወንጀል ነው አይልም፡፡

ይሄም ህግ የወጣበት ምክንያት በአብዛኛው ሃገራት የተለመደ አሰራር በመሆኑ ነው፡፡ እንዲያውም 70 በመቶ ፅሁፍ መሆን አለበት ይላል፡፡ ጋዜጣ ዋናውና የመጀመሪያ ስራው ዘገባዎችንና ዜናዎችን ለህዝብ ማድረስ እንጂ የማስታወቂያ ስራ አይደለም በሚል ይመስለኛል፡፡ ወደ እኛ ሃገር ስትመጪ ደግሞ ነገሩ የዚህ ተገላቢጦሽ ነው፡፡ ሆኖም ህጉ እኛን ነው የሚያበረታታው እንጂ ተቃርኖ የለውም፡፡

ከዚህ በፊት በርካታ ክሶች እንደነበረባችሁ በጋዜጣችሁ ላይ ገልፃችኋል፡፡ ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው?

ብሮድካስት ኤጀንሲ እና ዶ/ር አሸብር የከሰሱኝን ክስ፣ ፍ/ቤት መዝገቡን ዘግቶታል፡፡ ከዛ በተረፈ ፍትህ ሚኒስቴር የከሰሰኝ ከመቶ በላይ ክሶችን በተመለከተ ቃል ከሰጠሁና ከማዕከላዊ በዋስ ከወጣሁ በኋላ እስካሁን የደረሰኝ ነገር የለም፤ ክሱ ምን ላይ እንዳለ  አቃቤ ህግ እንጂ እኔ ብዙም አላውቅም፡፡ በጥምሩ 35 ክሶችና 142 ወንጀሎች ላይ ነው ክስ የተመሠረተው፡፡

ልትከሰሱ እንደምትችሉ በተደጋጋሚ በጽሑፋችሁ ስትገልፁ ነበር፡፡ መረጃ እየደረሳችሁ ነው ወይስ በግምት?

አንደኛው ከስርአቱ ባህሪ ተነስተን ነው፡፡ ሁለተኛ የስርአቱ አፈ ቀላጤ የሆኑ ሚዲያዎች እነ “አይጋ ፎረም”፣ “ዛሚ” እና “አዲስ” ዘመን”… የመሳሰሉት በየጊዜው “ፍትህ” መከሰስ እንዳለበት የቅስቀሳ ስራ ይሰሩ ነበር፤ ይህ ደግሞ በቸልታ የሚታይ አይደለም፡፡ ለምሳሌ “አዲስ ነገር” ጋዜጣ ሲዘጋ፣ በ”አዲስ ዘመን እንደምንከሰስ በተደጋጋሚ ተፃፈብን፣ ከዛ በኋላ ደግሞ መረጃ ደረሰን” ብለዋል፡፡ ልክ ናቸው፤ ምክንያቱም በዋናነት እዚህ አገር ላይ መንግስት የማይፈልገውን አካል ከአገር ለማባረር የሚጠቀምበት መንገድ ይህ ነውና፡፡ እኛ ላይም ለረጅም ጊዜ “አዲስ ዘመን” እየፃፈብን ነው፡፡ ህግ ጥሰዋል ይከሰሱ እያለ ነው፡፡ ስለ “አዲስ ዘመን” ደግሞ “ዊኪሊክስ” የተባለው ድረ-ገጽ ይፋ እንዳደረገው፤ ጋዜጣው ላይ የሚጽፉት ከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት መሆናቸው መረሳት የለበትም፡፡

እነዛ ሰዎች አሁን መጠነኛ ዘመቻ “ፍትህ” ላይ ከፍተዋል ለምሳሌ “ፍትህ” ከሽብርተኞች ጋር ግንኙነት አላት ብለው የሚያወሯቸው ነገሮች አሉ፡፡ አሁን እኛ ውስጥ የተፈጠረው ስጋት ይህ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ሌላ የሰማነው ኖሮ አይደለም፡፡

በአንድ ወቅት “አልሸባብ” የተባለው ድርጅት ማስጠንቀቂያ ፃፈ ብላችሁ ገልፃችሁ ነበር፡፡

ሌላ ማስጠንቀቂያ ደርሶኛል - ኮ/ል ተወልደ በሚባል ሰው ስም፡፡ ማንነቱን አላውቀውም፤ ግን ሌላ ማስፈራሪያ ደርሶናል፤ እውነታው ግን “አልሸባብ” የሚባል ድርጅት ከ“ፍትህ” ጋዜጣም ሆነ ከእኔ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም፡፡ በአልሸባብ ስም እንደዚህ አይነት ታሪኮችን እየፈጠረ ያለው በእኔ እምነት እራሱ ገዢው ፓርቲ ነው፡፡

ይሔንን በጋዜጣው ላይ  መፃፉ (መግለፁ) በአንባቢው ላይ ውዥንብር አይፈጥርም?

ይሔ ምንም ውዥንብር አይፈጥርም፡፡ ይልቁኑ የውዥንብሮቹ ሁሉ ምንጭ ስርአቱ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ውዥንብሩ እንዳይኖር ህዝብንና ሀገርን ሊያረጋጋ የሚችለው እንደዚህ አይነት ሴራዎች እየተጋለጡና ወደ ህዝቡ እየደረሱ ሲሔዱ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

የታገደው ጋዜጣ የያዘው ዘገባ ምን ነበር?

የጠ/ሚኒስቴሩን ጤንነት በተመለከተ የያዝናቸው ዘገባዎች ነበሩ፡፡ የፍትህ ሚኒስትሩ ለውጪ ሀገር ሚዲያ ሲናገሩ እንደሠማሁት፤ “ፍትህን ያገድነው በጠ/ሚ ጤንነትና በሙስሊሞች ተቃውሞ ላይ ይዞት የወጣው ዘገባ ለብሔራዊ ደህንነታችን አስጊ ስለሆነ ነው” ብለዋል፡፡ እኔ በበኩሌ የጠ/ሚኒስቴሩን ጤንነት በሚመለከት ይዘን የወጣነው ዘገባ  በፍፁም ለደህንነት አስጊ ነው ብዬ አላስብም፤ ደግሞ ሊሆንም አይችልም እናም ጠ/ሚ ሞቱ ወይም አልሞቱም የሚለው ክርክር እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ጋዜጣችን ይዞት የወጣው ዘገባ ለብሔራዊ ደህንነት አስጊ አልነበረም፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የጋዜጠኝነትን ስነ ምግባር የጠበቀ ነው አዘጋገቡ፡፡ ሚዛናዊ ሆኖ የተሠራ ዜና ነው፡፡ ይሔ ለብሔራዊ ደህንነት አያሠጋም፡፡ የሙስሊሞችን ተቃውሞ በተመለከተ፣ እሱም ቢሆን ግዴታችንን ነው የፃፍነው!! እኛ ጋዜጠኞች ነን፤ መስጂድ ውስጥ ያሉ ምዕመናኖች ሀይማኖታዊ ተግባራቸውን ሲወጡ በፖሊስ ሲደበደቡ፣ የደረሠባቸውን ኢ-ፍትሀዊ ሁኔታዎች የመዘገብ ግዴታ አለብን፡፡ እኛ የማንም አገልጋይ አይደለንም፤ የህዝብ አገልጋይ ነን፡፡ እንዲህም ሆኖ እኛ እዛ ላይ የሠራነው ዘገባ ለህዝበ ሙስሊሙ ችግር መፍትሄ አፈላላጊ ተብለው የተመረጡትን የኮሚቴ አባሎች እነ አህመዲን ጀበል ከመታሠራቸው ጥቂት ሠአታት በፊት ለ”ፍትህ” የሰጡትን የተለየ ቃለምልልስ ነበር፡፡ ይሔንን የማውጣት ግዴታም አለብን፡፡ ሁለተኛ ሙስሊም ኢትዮጵያኖች ላይ እየደረሠባቸው ያለውን ጭቆና በቅርብ ርቀት  ስንከታተለው የነበረ ነው፡ ይሔ ለብሔራዊ ደህንነት ያሠጋል ከተባለ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ከዚህ ባሻገር ነገም የፍርድ ቤት ሒደት ሲያልቅና ጋዜጣውን ስንጀምረው ሙስሊሞቹ ላይ እየደረሠ ያለውን ችግር ከመዘገብ ወደ ኋላ አንልም፡፡ የትኛውም ሀይማኖት ላይ የሚመጣውን ችግር ከመስራት ወደ ኋላ አንልም፡፡ በዚህ ሳቢያ የሚመጣውን ችግር ደግሞ እንቀበላለን፡፡

የጠ/ሚ ጤንነትን በተመለከተ አቶ በረከት “በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ” ብለዋል፡፡ በጣም ጥሩ ነው፡፡ እኔ ጋዜጠኛ ነኝ፤ ይሔንን ላስተባብል አልችልም፡፡ ቢቢሲ የተባለ የዜና ወኪል ደግሞ “በጠና ታመዋል” ብሏል፤ እነሱ አጣርተው ነው ያመጡት፤ ይሔ የእነሱ መረጃ ነው፡፡ አሜሪካን ውስጥ የተቋቋመ የሽግግር ም/ቤት ደግሞ “ህይወታቸው አልፏል” ብሏል፡፡ እንግዲህ የሦስቱን ዘገባ ነው ሚዛናዊ አድርገን የሠራነው፡፡ ስለዚህም ስህተቱ የትኛው እንደሆነ ለመለየት ተቸግረን ግራ ተጋብተናል፡፡ በተለየ መልኩ “ፍትህ” በራሷ በኩል አጣርታ ጠ/ሚኒስትሩ ሞተዋል ብለን የሠራነው ነገር የለም፡፡ የሌሎቹን ዘገባ ነው ከነሚዲያው ጠቅሠን የዘገብነው ጋዜጣዋ ከመታተሟ አንድ ሳምንት በፊት የወጣው ዕትም ላይ ስለ ጠ/ሚኒስትሩ ጤንነት ከመፃፋችን በፊት የተገለፀ ነገር አልነበረም፡፡

ቀጣይ ጉዟችሁ ምን ይመስላል?

ማክሠኞ ውሳኔ ያስተላለፉትን ዳኞች አነጋግረናቸው ነበር፡የታገደው ጋዜጣ እንዲወረስ ወስነናል ብለዋል አሁን ባለው ሁኔታ የታገደውም ሆነ በቀጣይ ያለውን ሁኔታ አላወቅንም፤ ፍ/ቤት የሚሠጠውን ውሳኔ እንቀበላለን፡ ሌላው ግን መንግስት ለ21 አመት ሲጠቀምበት የነበረው ስልት… አንዳንድ ጊዜ ህጋዊ ተቋማትን አንዳንዴ ደግሞ ከህግ ውጪ ያሉ ተቋማትን ነው፡፡ በብርሃንና ሰላም በኩል የተፈፀመብን አፈናም ይህን ነው የሚጠቁመው፡፡ በነገራችን ላይ የሐምሌ 13 እትምን ነው አግደናል ያሉት፡፡ ነገር ግን ካገዱም የሐምሌ 14 ነው መታገድ የነበረበት፡፡ ሐምሌ 13 ጋዜጣችን አልታተመምና፡ ስለዚህ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ያተመው አስቀድሞ የታገደን ጋዜጣ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ይህ ደግሞ ስህተት ነው፤ ማተም አልነበረበትም፡፡ ያንን ኪሳራችንን የምንጠይቅበትን ሁኔታ ከህግ ባለሙያዎች ጋር እየተማከርንበት ነው፡፡ ሌላው ስርአቱ   ነፃ ፕሬስን ለማፈን ተቋማትን እንደ መሳሪያ እየተጠቀመ  ነው ያለው፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ ብርሃንና ሰላም ነው፡፡ ይሄ ድርጅት ረጅም አመት ያስቆጠረ አንጋፋ ድርጅት ነው፡ ሰራተኞቹ ግን ከድርጅታቸው ህገ ደንብ ውጪ የፖለቲካ ሰዎች የሚሏቸውን እየተገበሩ የዜጎችን መብት እያፈኑ ነው፡፡ “ፍትህ” ላይ የተተገበረውን ኢህአዴግ ሌላም ላይ ሊተገብረው የሚችለው ነው፡፡

ወደ ፍ/ቤት ለመሔድ አላሰባችሁም?

ጥረት እያደረግን ነው፤ ነገር ግን ጉዳዩ ያሠብነውን ያህል ያልሔደልን ፍትህ ሚኒስቴር ላይ እራሱ ግልፅነት ስለሌለ ነው፡ ጋዜጣውን ሲያሳግዱ እኛ አልነበርንም፤ በየትኛው ችሎት እንዳሳገዱ ለማሳወቅም ፍቃደኛ አይደሉም፡፡ ከታገደ በኋላም ግልባጭ አልደረሠንም፤ እንዲሠጡን በደብዳቤ ስለጠየቅን ምናልባት አሁን ሊሠጡን ይችላሉ፡፡ ያንን ሳንይዝ ደግሞ ወደ ህግ የምንሔድበት ሁኔታ አልነበረም፤ ማስረጃዎችን እያሠሳሰብን ስለጨረስን ዛሬ ወይም ነገ ክስ እንመሰርታለን፡ ክሱ ብርሃንና ሰላም ላይ ነው የሚሆነው፣ አቃቤ ህግ ላይ ልንል የምንችለው ይግባኝ ነው፡፡

መንግስት ህጉም ያዘዋል ማገድ ይችላል፤ ግን እንደዚህ “የአይንህ ቀለም አላማረኝም” እየተባለ ሳይሆን ለብሔራዊ ደህንነት አስጊ ከሆነ ነው፡፡ አሁን ያገዱበት መንገድ ግን ለብሔራዊ ደህንነትም ሆነ ለሌላ አስጊ ሆኖ አይደለም፤ ስርአቱ የጠ/ሚ መታመምን ተከትሎ በውስጡ የተፈጠረውን መከፋፈል በዚህ ለመሸፈን ብሎ ነው የሚል እምነት አለኝ፡ ብርሃንና ሠላም ግን ሙሉ በሙሉ ያለማተምና የማገድ  ስልጣን የለውም፤ የመብት ረገጣ ነው ያደረገው፤ የብርሃንና ሠላም ማኔጅመንቶች እራሳቸው ያመነጩት ነገር አይደለም፤ መጠቀሚያ ነው የሆኑት፡፡ የገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ሹማምንቶች ውሳኔ ነው፡  ስለዚህ የእነሱን ጉዳይ ነው በህግ የምናቀርበው፡፡ በእኔ እምነት የትኛውም ስራ ላይ ያለ ሠው በህሊናው ነው መስራት ያለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ብርሃንና ሠላም ያሉ ሠዎች ትልልቅ ሠዎች ናቸው፤ በዕድሜ የረጅም አመት የስራ ልምድ አላቸው፤ በድርጅታቸው መመሪያ ከመስራት ይልቅ ሌሎች ፖለቲከኞች በሚሏቸው እንደፈለጉ እየተሽከረከሩ ነው፡፡ “እኔ አልቀበልም ከህጋችን ውጪ ነው” የሚሉ ሠዎች አይደሉም፡ እና እነዚህ ሠዎች ዛሬ ለእንጀራቸውና ለኑሯቸው ሲሉ “ፍትህ”ን አፍነዋል፤ ነገ  ግን ከትውልድና ከታሪክ ተጠያቂነት አያመልጡም፡፡

ብርሃንና ሰላም ወደፊትም ባለማተም ውሳኔው ቢፀና ምን ታደርጋላችሁ?

ቦሌ ማተሚያ ቤትም አላትምም ብሏል፡፡ ሌሎች ማተሚያ ቤቶች ጋዜጣ የማተም አቅም ላይኖራቸው ይችላል፡ ስለዚህ ይሔ አደገኛ ነገር ነው፤ ይሔ ለ”ፍትህ” ብቻ ሳይሆን ለራሱ ለስርአቱም አደገኛ ነው የሚሆነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሲታፈኑ የቆዩ ነገሮች አሉ፤ ስለዚህ ለሁልጊዜም አይታተምም ከሆነ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለራሱም አስጊ ነው፡፡

ጋዜጣው ከታገደ በኋላ በ15 ቀን ውስጥ እንደምትከሰሱ ገልፃችኋል፡፡ ክስ ደርሳችኋል?

እስከ አሁን የደረሠን ነገር የለም፤ እስከሚመጣው ማክሠኞ ድረስ ጊዜ ስላላቸው እንጠብቃለን፡፡

ልጆች፤ ትዳር፣ ህይወት… እንዴት ነው?

(ረጅም ሳቅ)፤ የሚገርም ነው፣ ትዳር የለኝም፤ ጓደኛም የለኝም፤ ቤት ተከራይቼ ነው የምኖረው፡፡

በፊት ከቤተሰቦቼ ጋር እኖር ነበር፤ ከሁለት አመት ወዲህ ግን ቤተሰቦቼ ከተለያዩ የስርዓቱ ባህሪና ከኢትዮጵያ ፖለቲካ አደገኛነት ተነስተው ከዚህ ስራ እንድርቅ ጫና ስላደረጉብኝ ብቻዬን መኖር ጀመርኩ፡ ከስምንት ወራት ወዲህ ደግሞ በደረሰብን የደህንነት ስጋት እኔና ሁለቱ ምክትል አዘጋጆቼ እኔ የተከራየሁባት ቤት ውስጥ አብረን መኖር ጀምረናል፡፡

ደጋግመን እንደጻፍነው ይቺን ቤት ወዳጆቻችን “አሲምባ” የሚል ስም አውጥተውላታል፡፡ አሲምባ ደርግ ከፍተኛ በትር ያሳረፈባቸው የ “ያ ትውልድ” ወጣቶች የመሸጉባት ትግራይ ውስጥ የምትገኝ ተራራ ናት፡፡

 

 

 

 

Read 4117 times Last modified on Saturday, 04 August 2012 09:51