Print this page
Tuesday, 13 October 2020 15:06

‹‹ጉራጌ ዘር የለውም፤ ዘሩ ሥራ ነው››

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

- ድምጻዊ ኤልያስ ተባባል

          በ1970ዎቹ አጋማሽ ባሳተመው የመጀመሪያ አልበሙ ነው ከሕዝብ ጋር በስፋት የተዋወቀው፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት ኑሮውን በአሜሪካ ያደረገው ድምጻዊ ኤልያስ ተባባል፤ ወደ ትውልድ ሀገሩ ከተመለሰ ገና ሁለት ወሩ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ከጉራጌ ተወላጆች ጋር ጥልቅ ወዳጅነትና ትስስር እንዳለው የሚናገረው ድምጻዊው፤ የዘንድሮ የመስቀል በዓልን በወዳጆቹ ግብዣ፣ በጉራጌ ዞን መሠረተ ወገራም ነው ያከበረው፡፡ ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 16 ቀን 2013 ጋዜጠኛ ብርሃኑ ሰሙ፣ ድምጻዊ ኤልያስን በመሠረተ ወገራም አግኝቶት አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡ እነሆ፡-


             ከማሲንቆ ጋር የተዋወቅኸው እንዴት ነው?
የልጅነቴን የመጀመሪያ 8 ዓመታት ያሳለፍኩት በትውልድ ሀገሬ ጎንደር ነው። በአዲስ አበባ ጊዮርጊስ አካባቢ ትዳር መሥርታ ትኖር የነበረችው እህቴ፣ ወደዚህ እንደመጣ ምክንያት ሆነችኝ፡፡ ምሽት ላይ በገዳም ሠፈር የማየው ሙዚቃ ቀልቤን እንደሳበው ያስተዋለችው እህቴ፤ ወደ ትውልድ መንደሬ ልትመልሰኝ ሞክራ ነበር። አሻፈረኝ አልኩ፡፡
የራሴን መንገድ ይዤ መጓዝ የጀመርኩትም በዚያ አጋጣሚ ነበር፡፡ ከዚያም የምሽት ሙዚቃ ቤት ተቀጠርኩ፡፡ ድምጻዊያኑ እረፍት ሲያደርጉ ማሲንቋቸውን እያነሳሁ በመነካካት ነው፣ ከመሣሪያው ጋር የተዋወቅሁት፡፡ 12 ዓመት ሲሞላኝ በሙዚቃ ሙያ መሰማራት እንደምችል እርግጠኛ ነበርኩ፡፡   
በማሲንቆ ማንጎራጎር መተዳደሪያህ የሆነው ከመቼ ጀምሮ ነው?
በ1972 ዓ.ም ለአምባሳደር ቴአትር ቤት፣ የባሕል ሙዚቃ ቡድን ለማደራጀት ማስታወቂያ ሲወጣ፣ ተመዝግቤ ውድድሩን አለፍኩ፡፡ በወቅቱ ከተቀጠሩት መካከልም፡- ፀሐዬ ዮሐንስ፣ አበበች ደራራ፣ ንዋይ ደበበ … ይገኙበታል፡፡ ብዙም ሳይቆይ ቴአትር ቤቱ የፊልም ማዕከል ይሁን ተባለና፣ እኛ ወደ ራስ ቴአትር ተዛወርን፡፡
እስቲ የሲኒማ ራስ ትዝታዎችህን አጫውተኝ---?
እኛ ወደ ቴአትር ቤቱ እንደተዛወርን ከፍተኛ መነቃቃት ተፈጠረ፡፡ በየሳምንቱ ረቡዕ ከሰዓት በኋላ ለሕዝብ የሚቀርብ ‹‹የኪነ ጥበባት ምሽት›› ተጀመረ፡፡ በተለይ የባህል ሙዚቃ ቡድኑ በተመልካች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን አገኘ፡፡ በሙዚቃው እኔን ጨምሮ ፀሐዬ ዮሐንስ፣ ንዋይ ደበበ፣ አበበች ደራራ፣ መሐመድ አወል፣ ሻምበል በላይነህ … በቴአትሩም ጥላሁን ጉግሳ፣ ደበሽ ተመስገን፣ እንቁሥላሴ ወርቅአገኘሁ፣ አይናለም ተስፋ … ከሕብረተሰቡ ጋር እንድንተዋወቅ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል። ዝግጅቱን ለማየት የሚመጣው ሕዝብ ሰልፍ፣ ከሲኒማ ራስ እስከ ተክለ ሃይማኖት ይደርስ ነበር፡፡   
የመጀመሪያ ካሴትህን ለማውጣት የገጠሙህ ተግዳሮቶች ምን ነበሩ?
በራስ ቴአትር የባህል ሙዚቃ ቡድን ዐባል ሆኜ በመስራት ላይ እያለሁ ነበር ካሴት ለማሳተም እንቅስቃሴ የጀመርኩት፡፡ አሳታሚ ማግኘቱ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ብዙ ቦታ ዞሬ ተስፋ ወደመቁረጡ በደረስኩበት ሰዓት አምባሰል ሙዚቃ ቤት ሄድኩ፡፡ መደብሩ ውስጥ ገብቼ ያገኘሁትን አንድ ወጣት ‹‹የሙዚቃ ቤቱን ባለቤት ፈልጌ ነበር›› ስለው፤ ‹‹እኔ ነኝ ምን ፈልገህ ነው?›› አለኝ፡፡ በወቅቱ አቶ ፍቃዱ ዋሪን አላውቀውም ነበር። ራሱን ካስተዋወቀኝ በኋላ የሄድኩበትን ጉዳይ ነገርኩት፡፡ በዕለቱ እግዚአብሔር ሲረዳኝ ደራሲ ተስፋ ለሜሳ በሙዚቃ ቤቱ ውስጥ ነበር፡፡ ስለ እኔ ማንነትና ሥራዎች በማድነቅ፣ ለአቶ ፍቃዱ ዋሪ ነገረው፡፡  አምባሰል ሙዚቃ ቤትም ካሴቴን ሊያሳትምልኝ ከስምምነት ላይ ደረስን፡፡ ስምምነት ካደረግን ከሦስት ሳምንት በኋላም ካሴቱ በ1976 ዓ.ም ለገበያ ቀረበ፡፡ ሥራው ወዲያው ነበር ተቀባይነት ያገኘው፤ እኔንም ከዘመኑ ዝነኞች አንዱ አደረገኝ፡፡
የአንተ ካሴት በታተመበት ዘመን፣ አምባሰል ሙዚቃ ቤት ከነበረበት ሠፈር በስተጀርባ፣ በቀድሞ ከፍተኛ 7 ቀበሌ 32 (ቁጭራ ሠፈር) እና ቀበሌ 34 (ቀጤማ ተራ) መንደሮች፣ የበርካታ ‹‹አዝማሪ››ዎች መኖሪያና መሰባሰቢያ እንደደነበሩ ይታወቃል፡፡ ስለነዚህ ሰፈሮች የምታውቀው ታሪክ አለ?
በዘመኑ በየሆቴልና መዝናኛ ስፍራዎች ምሽት ላይ የሚታዩ በርካታ ማሲንቆ ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ እኔ በመርካቶም ሆነ በሌሎች አካባቢ የምሽት ሥራ ላይ ብዙ አልተሳተፍኩም፡፡ ለተወሰኑ ጊዜያት ግን በ‹‹እናት ጓዳ›› ተጫውቻለሁ፡፡ ከመርካቶው ይልቅ በመገናኛ፣ በካሳንችስና በቦሌ (እስራኤል ጋራዥ) አካባቢ የነበረውን እንቅስቃሴ የተሻለ አውቃለሁ፡፡ በዚያ ዘመን ማሲንቆ ተጫዋቾች ተበራክተው ነበር፡፡ ምክንያቶቹ ብዙ ቢሆኑም ለኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምና ለመንግስታቸው ከፍተኛ አድናቆት አለኝ። ዋነኛው ምክንያቴ ከእኛ ሙያ ጋር የሚያያዝ ነው፤ ‹‹አዝማሪ››ዎች ክብርና እውቅና ያገኙበት ዘመን ነበር፡፡ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ለዚምቧቡዌና ለናምቢያ ነጻነት የታገሉ ኢትዮጵያዊ መሪ ናቸው፡፡ ዘመኑ አንድነት የሚሰበክበት፣ ኢትዮጵያዊነት የሚኮራበት ነበር፡፡ በዘመኑ ከሚነገሩ መፈክሮች አንዱ ‹‹የብሔረሰቦች እኩልነት በትግላችን ይረጋገጣል!›› የሚል ነበር፡፡ በደርግ ዘመን በዘርህ ምክንያት አትገደልም፡፡ በሕግ ያልተዳኘ ሞት የበዛበት ዘመን ቢሆንም፤ ሟች የሚሞተው ‹‹ፀረ - ኢትዮጵያዊ›› ተብሎ ነው፡፡ ጎሳህንና ዘርህን ጠልቶ ሕይወትህን ሊቀማ ገጀራ የሚያነሳብህ ማንም አልነበረም፡፡ አብዛኛው ሕዝብ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ተመሳሳይ ስሜት ነበረው፡፡ የአንድነት ጉዳይ ለጥያቄ የሚቀርብበት ዘመን አልነበረም፡፡
ካሴትህ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱና ዝነኛ መሆንህ ምን አስገኘልህ?
ከዚያ በኋላ ተጋብዤ የምጫወትባቸው መድረኮች ተበራከቱ፡፡ የ‹‹አደይ አበባ የኪነ ጥበብ መድረክ›› ላይ ከተሳተፉት አንዱ መሆን ችያለሁ፡፡ በበርካታ የዓለም ሀገራት በመዞር የኪነ ጥበብ ዝግጅቱን ባቀረበው ‹‹ሕዝብ ለሕዝብ›› የሙዚቃ ዝግጅት ላይ መሳተፍ በቀላሉ የማይገኝ ትልቅ ዕድል ነበር፡፡ ለአፍሪካ ሙዚቃ ኮሌክሽን በጃፓን ከተመረጡ 4 ሙዚቀኞችና ሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች አንዱ ሆኜ፤ የዘፈን ሥራዬ በJVC ካምፓኒ ተቀርጾ ለዓለም ገበያ ቀርቧል፡፡
ከሀገር የወጣህበት ምክንያት ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው ይባላል …
ግንቦት 19 ቀን 1982 ዓ.ም ነው ከሀገር የወጣሁት፡፡ አወጣጤ ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ባይሆንም፤ የተከፋሁበት ነገር ስለነበር፤ ላለመመለስ ወስኜ ነው ወደ አሜሪካ የሄድኩት፡፡ አሜሪካ ከሄድኩ በኋላ ሁለት ሲዲ አውጥቻለሁ፡፡ የሚበዛውን ጊዜዬን ያሳለፍኩት ግን ከሙያዬ ውጪ በሆነ ሥራ ላይ ነው፡፡ እኔ በትምህርት ጥግ ድረስ መድረስ ባለመቻሌ፣ ቁጭቴን የተወጣሁት እህት ወንድሞቼን አስተምሮ፣ ለቁም ነገር በማብቃት ነው፡፡ ለ30 ዓመታት ነው በአሜሪካ የቆየሁት፡፡ በቀሪው ዘመኔ፣ በሙዚቃው ዘርፍ የራሴን አስተዋጽኦ የማድረግ ዓላማና እቅድ አለኝ፡፡
የመስቀል በዓልን ከጉራጌ ማህበረሰብ ጋር ስታከብር የመጀመሪያህ ነው?
ከዚህ ማሕበረሰብ ጋር ሰፊ ሊባል የሚችል ትውውቅና ቀረቤታ አለኝ፡፡ በትዳር ለ25 ዓመታት አብራኝ የዘለቀችው ባለቤቴ የዚህ ብሔረሰብ ተወላጅ ናት፡፡
አባቷ አቶ ተክሌ ጉንጆ ከቀድሞ ዘመን የመርካቶ ባለሀብቶች አንዱ ሲሆኑ በስማቸው የሚጠራ ትልቅ ሆቴል ሁሉ ነበራቸው፡፡ በዘንድሮ የመስቀል በዓል ጋብዞኝ ወደ መሠረተ ወገራም ይዞኝ የመጣው ከ35 ዓመት በፊት ጀምሮ የማውቀው አቶ በላይ ካሳ ኢርከታ ነው። ጉራጌዎች እንደ መስቀል በዓላቸው ብዙ የሚስብ ነገር ያላቸው ሕዝቦች ናቸው። የትም ቢሄዱ ኢትዮጵያዊነታቸውን ያስቀድማሉ፡፡
ከየትኛውም ብሔርና ዘር ጋር በጋራ ለመኖርና ለመስራት አይቸገሩም። ለመስቀል በዓል በተገኘሁበት መሠረተ ወገራም ኦሮሞዎች፣ ትግሬዎች፣ አማሮች … ተጋብዘናል፡፡ ጉራጌ ዘር የለውም፣ ዘሩ ሥራ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ብርሃኑ ሰሙ የጋዜጣው ነባር ጸሃፊ ሲሆን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 1806 times
Administrator

Latest from Administrator