Tuesday, 13 October 2020 15:08

"ድሃ እና ቅቤ" - (ምሳሌያዊ ወግ)

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 በአንድ ሴሚናር ላይ አነቃቂ ትምህርት የሚሰጠው ኮበሌ፤ ለታዳሚው አንድ ልምምድን ያዝዛል፡፡
“ሁላችሁም እስቲ ቅንጡ መኪና ገዝታችሁ አስቡ!” አላቸው፡፡
ታዳሚው በእዝነ ልቦናው ያሻውን ቅንጡ አውቶሞቢል ሸመተ፡፡
“እስቲ አሁን ደግሞ መኪና ውስጥ ግቡበትና ሞተሩን አሙቁት!” አለና ዙሪያ ገባቸውን ይሰልላቸው ጀመር፡፡
“መኪናውን በፍጥነት ማብረር ጀምሩ! ንዱት በደንብ ንዱት! እጃችሁን በመስኮት አውጥታችሁ፣ ንፋሱ ሁለመናችሁን ሲያረሰርሳችሁ ይሰማችሁ፤ ንዱት፣ ንዱት!” እያለ ትዕዛዙን ቀጠለ፡፡
የሴሚናሩ ታዳሚው በልምምዱ በስሜት ከፍታ ውስጥ ገብቷል፡፡ ሁሉም ያለሙትን ቅንጡ አውቶሞቢል፣ በመረጡት ጎዳና ላይ እያከነፉ ነው፡፡ ልምምዱን አቋርጦ ወጣ፡፡ “ምን ነክቶህ ነው አቋርጠህ የምትወጣው?” ተብሎ በተጠየቀ ጊዜ፤ “አይ እኔ መንጃ ፍቃድ የለኝም!” ሲል አስገራሚ ምላሽ ሰጥቷል ይባላል፡፡
የወጓን ፍሬ ነገር ቀልዱ አስቀድሞ ሹክ ይለናል፡፡ የሴሚናሩ ታዳሚዎች፣ በድሃ ይመሰላሉ፤ መኪናው ደግሞ ገና ያላገኙት ሕልማቸው ወይም ቅቤያቸው ነው፡፡ ድሃ በሕልሙ ቅቤ ባይጠጣ፣ የሚለው ሀገርኛ ብሂል፣ በውስጡ ብዙ የሚመነዘር ቁምነገርን አዝሏል፡፡ ድሃ እና ቅቤ፤ ጫፍና ጫፍ የቆሙ፤ የሁለት ዓለም ኹነቶች  ናቸው፡፡ በመካከላቸው ጊዜ የሚባል ህላዌ አለ፡፡ የነጣጠላቸው የጊዜ ድልድይ ሲሰበር፣ ሁሉም ነገር ያከትማል፡፡ ድሃው ለዘመናት የባተተለት ሕልሙ፣ በእጁ ይገባል፡፡ መባተቱ ግን፤ ይለጥቃል፤ መቋጫው አድማስ ነው፡፡ ደግሞ ሌላ ቅቤ ለመጠጣት ይባዝናል፡፡ ሰዶ ማሳደዱ፣ እስከ ዕድሜ ማክተሚያ ድረስ ይዘልቃል፡፡
ቅቤው ዝና፣ ንዋይ፣ደስታንና ክብርን ሊወክል ይችላል፡፡ የእነዚህ ሁሉ ነዳይ ሰው፣ ድሃ ነው፡፡ ድህነት አንጻራዊ ነው፡፡ ጋሪ ያለው ባጃጅን ይመኛል፤ ባጃጇ በእዝነ ኅሊናው የምትንቆረቆር ቅቤው ልትሆን ትችላለች፡፡ ባጃጇ የምናብ ጠኔውን የምታጠረቃ ቅቤው ነች፡፡ በእርግጥ ያለሙትን ቅቤ ማግኘት ኩነኔ አይደለም፡፡ ጣጣው የሚመጣው፤ ቅቤውን ከቃረሙ በኋላ የሚፈጠረውን የስሜት መዘበራረቅ መሸከም የሚያስችል ጫንቃ ከሌለን ነው፡፡ ለዚህ እኮ ነው፤ ስኬታማ እየሆንን በሄድን ቁጥር፣ የደስታ ምንጮቻችን እየተመናመኑ የሚሄዱት፡፡
ምኞት፣ ጉጉት ወይም እጥረት በራሱ መርገም አይደለም፡፡ አንዳንዴ እንደውም ለመኖራችን ትልቅ ዋስትና ይሆናል፡፡ በማግኘትና በእጦት መካከል የጊዜ ወሰን አለ፡፡ ይህም  ሁልጊዜ እየታደስን እንድኖር የሚረዳን አጋራችን ሊሆን ይችላል። ሁሉ በእጃችን በደጃችን ሲሆን፣ ሌላ የመንፈስ ጦርነት ውስጥ እንገባለን፡፡ ጥበቃ ያከትማል። ነገን ማለም ከንቱ ይሆናል፡፡ ያን ጊዜ መሸሸጊያችን ምን ይሆናል?
እኔ ባቅሜ አርቴፊሻል እጥረት በመፍጠር፤ የሥነልቦና ሚዛኔን ለመጠበቅ እተጋለሁ፡፡ ጎተራዬን ሆን ብዬ በማጉደል፤ በጥበቃ ውስጥ ያለውን ደስታ አጣጥማለሁ። ማለዳ አፌ ላይ የማደርገውን ቁራሽ በመዝለል፣ ምሳዬን በጉጉት እጠብቃለሁ፡፡ ምሳዬ ደርሶ ጎተራዬን ሳደላደል፣ ከወትሮው የተለየ የከፍታ ስሜት ይሰማኛል፡፡ የአእምሮ ምግብ ጥበቃ /ቅቤ/ ነው፡፡ የሚጠበቅውን ነገር በሙሉ ከነጠቅነው፤ ነገር አለሙን ያጨልምብናል፡፡
ለዚህም እኮ ነው፣ ታላቁ እስክንድር፣ የመጨረሻውን ባላንጣ ካሸነፈ በኋላ፣ ቤት ዘግቶ ስቅስቅ ብሎ ያነባው፡፡ “የቀረውን አንድ ባላንጣዬን ድል ነሳሁት፡፡ ከእንግዲህ ወዲያ ጉጉትም ሆነ ምኞት የለኝም፡፡ አንድያ የተስፋ ጥሪቴን ተነጠቁ፡፡” ነበር ያለው፡፡ መንፈሳዊ ክፍታ ውስጥ ካልገባን በስተቀር፣ በዓለም ላይ  የተመኘነው ሁሉ እጃችን ሲገባ፣ እንደ እኛ ብስጩ አይገኝም፡፡
አእምሮ እንዳልተገራ ፈረሰ ነው፡፡ በየደቂቃው እንደ ማእበል ይናጣል፡፡ አንዱን ይዞ ሌላውን ይጥላል፡፡ ጠብ እርግፍ ብሎ ያገኛትን ጉብል ከጎኑ በሻጣት ማግሥት፤ ከነመፈጠሯ የሚረሳት ኮበሌ፤ ጊዜን እጀ ሰባራ ማድረጉ አይቀርም፡፡ ጉብሏን የግሉ ሲያደርጋት፤ በአእምሮው ውስጥ ማርጀት ትጀምራለች፡፡ ጉጉቱን ይነጠቃል። ሁለመናዋን ይለምደዋል፡፡ “ባልተቤትህ ውብ ናት" ሲሉት፤ "ያልተነካ ግልግል ያውቃል፡፡ አሁን ምኗ ነው የሚያምረው?!” ይላል፤ ሌላ በመተካተ ስሜት፡፡
በጊዜ ማእቀፍ ጠብቀን የምንቃርመው ደስታ፣ "ስሄድ አገኘኋት፣ ስመለስ አጣኋት; እንደሚባለው ነው፡፡ እድሜው አፍታ - ጤዛ ይሆናል፡፡ ለዓመታት የዘለቀ የስሜት መቃተታችንን የሚመጥን፤ የሥነልቦና እርካታን አያጎናጽፈንም፡፡ ቆብ ደፍቶ ሰዎቹ ሁሉ በአድናቆት ሲሰግዱለት እያለመ፤ ከኮሌጅ የሚማር ቀለም ቆጣሪ፣ ከቅቤ ነዳይ ጎራ ይመደባል፡፡ የሚማረው ትምህርት፣ ልክ እንደ ታክሲ ወረፋ ይታክተዋል፡፡ ደስታው፣ ቅቤው፣ ምረቃው ነው፡፡ ትልቁ መርዶ፤ ያ ሁሉ ዘመን የቃተተለት ግብ፣ ጠኔ ያጠናገረውን ስሜቱን ማረስረስ አለመቻሉ ነው፡፡
ይኸ ሁሉ መብሰክሰኬ፤ ለውጥን ተጠይፈን፤ ባለንበት እንደ ኩሬ ረግተን እንኑር፤  የሚለውን መፈክር ለማሰማት አይደለም፡፡ ሥነልቦናዊ ቁርኝትን እንበጥሰው፡፡ አእምሮ የለመደውን የስሜት ቀለብ፣ ግልምቢጥ እናድርግበት፡፡ እንቀያይርበት፡፡ ደስታን ከስኬቱ ሳይሆን፣ ከሂደቱ መቃረም ይልመድብን፡፡ ከተራራው ይልቅ ወደ ተራራው በሚያዘልቀን ጎዳና ላይ፣ በምናዘግመው፣ በእያንዳንዱ እርምጃ እንመሰጥ፡፡ ከቅቤ ይልቅ፤ ቅቤውን ለማግኘት በምናፈሳት ጠብታ ላብ፣ ሐሴት እናድርግ፡፡
ባትተን የምናሳካው ግብ፣ የጊዜ ባሪያ እንደሆነ ለማወቅ አስረጂ አያስፈልገንም። ከስኬቱ የምናገኘው የስሜት ከፍታ፣ ጥቂት ተፍገምግሞ፣ መልሶ ወደነበረበት የስሜት እንጦሮጦስ ሲወርድ፤ በተደጋጋሚ ጊዜ ታዝበናል፡፡ ጠቢባን ደስታ ስኬትን እንጂ፤ ስኬት ደስታን አያመጣም ይላሉ። ህልማችንን - ቅቤያችንን፤ የእርካታችን ምንጭ አድርገን መቁጠር ዳፋውን ያከፋብናል፡፡
ቻይናዊያን፤አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር፣ በአንድ እርምጃ ይጀመራል ያሉት ያለነገር አይደለም፡፡ የግባችንን ፍሬ ወይም ቅቤውን የምናጣጥመው፤ ልክ አንድ ሺኛው ኪሎ ሜትር ላይ ስንደርስ መስሎ ከታየን፣ ተላላ እንሆናለን፡፡ እያንዳንዱ እርምጃ በራሱ ፍጻሜ ነው፡፡ ስኬት ነው፡፡ ቅቤ ነው፡፡ የእያንዳንዱ እርምጃ ስኬት ጥምር ውጤት፤ ዐሥር ሺህ ኪሎ ሜትሩን ይፈጥረዋል። ደስታን ከእያንዳንዷ ሽርፍራፊ ቅጽበት ለመቃረም አንሞክር፡፡ ይኽ ዓይነት የልቦና ውቅር፣ ከጊዜ ቀንበር ነጻ ያወጣናል፡፡

Read 2400 times