Wednesday, 14 October 2020 15:40

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by  (ብርሃኑ በላቸው ምህረቴ)
Rate this item
(0 votes)

 አንድ ስንሆን እንበረታለን፤ ስንለያይ እናንሳለን!
                   
              (ውስጤ ከሚቀር ጊዜው ሳያልፍ የሚያስከፋውን ያስከፋ በሚል የተጣፈ)
እንደኔ እንደኔ ትግራይ ትገንጠል የሚሉ ተጋሩዎች ምክንያት ሲጠየቁ “ኢትዮጵያ ገፋችን፣ በደለችን” የሚሉትን ወደ ጎን አድርገው፣ “በቃ መገንጠል አማረን” ቢሉ ነው የሚያምርባቸው።
በመገፋት ቢሆን ከአማራና ከኦሮሞ ይበልጥ አልተገፋችሁም። በመታረድም ቢሆን የጋሞን ያህል አልታረዳችሁም። በዓመት ውስጥ ብቻ 300+ አማራ መታረዱን አትረሱም መቼም። ግማሹ ኦሮሞ ዛሬም በትርምስ ውስጥ ነው። በመንጓጠጥ ቢሆን የወላይታን፣ የስልጤን፣ የጉምዝን፣ የጋምቤላን ያህል አልተንጓጠጣችሁም።
በሃይለማርያም ዘመን እንደተደረገው በፒካፕ እንደ እንስሳ ተጠፍራችሁ አልታሰራችሁም። በመረሳት ቢሆን የክንችላን፣ የዛይን፣የዲንጣን ያህል አገሪቱ አልረሳቻችሁም። ከድፍን የትግራይ ሰው ወድዶ እንጂ ተገዶ አማርኛ የሚያወራ የለም። ትግራይን ከሚያስተዳድሩ መካከል ከትግራይ ሰው ሌላ አንድም የሌላ ብሄር ሰው የሚገኝ አይመስለኝም።(ከሳትኩ እታረማለሁ) ከኢትዮጵያ መዐከላዊ ኢኮኖሚ በቂ ድርሻ እንደምታንቀሳቅሱ የታወቀ ነው። ዛሬም በአገሪቱ ሥሪት ላይ የትግራይ ሰዎች ድምፅ በቀዳሚነት ከሚደመጡት መካከል ነው። ዛሬም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ከፍተኛ ባለድርሻዎች ናችሁ።
ለተሰንበት ተንገላታች-በቃ እንገንጠል፣
ቢንያም ታሰረ-በቃ እንገንጠል፣
መንገድ ተዘጋ- እንገንጠል፣
ለማስታወስ ያህል የለተሰንበት የአንድ ቀን እንግልት፣ የ27 ዓመት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሰቀቀን ኑሮ ነበረ። ለተሰንበት ታዋቂ ሆና ተሰማላት እንጂ የብዙሃኑ ሕይወት ይኸው ነው። ዛሬም የብዙ ኢትዮጵያዊያን ኑሮ ነው። የፖለቲካ እስረኞች እስር ቤት ሞልተዋል። ብሄራቸው እንደ ኢትዮጵያ ህብረ ብሄራዊ ነው።
አገር ትገፋለችም፥ ታነግሳለችም። ታግለህ ትሰራታለህ፤ ተቸግራ ትሰራሃለች። በደምህ ትጠብቃታለህ፥ ደምህ ሆና ውስጥህ ትዘዋወራለች። ለመኖርህ ተጨማሪ ምክንያት፥ ለህይወትህ ሜዳ ትሆንሃለች።
መገንጠል ሀብታም አያደርግም፣ መገንጠል አምባገነንነትን አያጠፋም፣ መገንጠል ወገኔ የምትለውን ሰው ብዛት ከማሳነስ በቀር በራሱ ፋይዳ የለውም።
ባለፉት ሁለት ዓመታት የትግራይ ህዝብ እየተገፋ የመሰለው ሆን ብሎ እንዳይቀላቀል የነጠለው አካልም ስላለ ነው። ግማሹን እውነት ደብቃችሁ ነው ብሶቱን ብቻ የምታጮኹት። ሆን ብሎ የትግራይን ህዝብ ብቻ ነጥዬ ልጉዳ በሚል የተንቀሳቀሰ አካል አይታየኝም። የተበደለ ትግሬ የለም ማለቴ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ በደል የነበረ፣ ያለና የሚኖር ነው። የተበደሉ አማሮች፣ ወላይታዎች፣ ኦሮሞዎች፣ቅማንቶች፣ ወዘተ ቋቅ እስኪለን ሞልቷል።
ዐቢይ ከኢትዮጵያውያን ሁሉ ትግራይን ብቻ መርጦ አምባገነን እንደሆነባት ማስመሰል ግን ስህተት ነው።
ብትሄዱም ብትኖሩም ዕጣ ፋንታችን አንድና አንድ ነው።
አንድ ስንሆን እንበረታለን፤ ስንለያይ እናንሳለን!
ቱስ ባለ ቁጥር እንገንጠልን ማጮህ ይብቃ!


Read 1221 times