Wednesday, 14 October 2020 15:42

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

‹‹የሐሳብ ቀን-ዘሎች››
                                 (አሳዬ ደርቤ)

           በእኔ ዘንድ የእረፍት ትርጉሙ ቁጭ ማለት ሳይሆን ‹‹ሥራ መሥራት›› ነው። ከየትኛውም ነገር በላይ የሚያዝናናኝ ደግሞ የምወደውን ሥራ መሥራት ነው። ስለሆነም ቢሮ ውዬ ስመለስ ቤት ገብቶ ከማረፍ ይልቅ መጻፍ ደስ ያሰኘኛል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም፤ በጥሩ እንቅልፍ ካሳለፍኩት ሌሊት ይልቅ ለመንፈሴ የሚጥም ሼጋ ጽሑፍ ስሞነጫጭር ያደርኩበት ሌሊት ማለዳዬን ውብ ያደርገዋል፡፡
ይህ ሁኔታ ግን ኪነ-ጥበባዊ ይዘት ላላቸው ጽሑፎቼ እንጂ ሳልወድ በግዴ ከአክቲቪስት ጎራ ተሰልፌ እዚህ ሶሻል ሚዲያው ላይ የምለጥፋቸውን ጽሑፎች አይመለከትም፡፡ እነሱ ሰላሜን እና ግማሽ ጎፈሬዬን የሚነጥቁኝ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ ግን የሆነ ጥቃት ሲፈጸም ‹‹ምን አገባኝ›› ብዬ ከመተኛት ይልቅ ለውጥ አመጣሁም አላመጣሁም ‹‹ያገባኛል›› በሚል ስሜት ማለት ያለብኝን ነገር ማስተጋባት፣ ለመላጣ ጭንቅላቴ ምቾት ይሰጠዋል፡፡ አካበድኩ መሰል! .
በሌላ መልኩ ግን የወቅቱ የፖለቲካ አየር ፌስቡካችንን የኀዘን ድንኳን አድርጎት በመክረሙ የተነሳ እለታዊ አጀንዳዎችን ችላ ብሎ ሌሎች ነገሮችን ሶሻል-ሚዲያው ላይ ለማጋራት ጊዜው ባይፈቅድልንም አልፎ አልፎ ግን ግላዊ ዝንባሌዬን ባለመተዌ ይሄው ሦስተኛ መጽሐፌን ለማሳተም በቃሁ፡፡
መጽሐፉ ‹‹የሐሳብ ቀንዘሎች›› ይሰኛል፡፡ በወሎ አማርኛ ከሐሳብ ዛፍ ላይ የተመለመሉ ቅርንጫፎች እንደማለት…ሽፋኑ ላይ ያለውን ምሥል እንዳሻችሁ ተርጉሙት… የመጽሐፉን ውስጣዊና ውጫዊ ዲዛይን ያቀናበረው ታዋቂው ባለሙያ ሙሉቀን አስራት ሲሆን ለየት ባለ የሕትመት ጥራት ታትሞ ሼልፍ ላይ ውሏል፡፡ ይሄውም መጽሐፍ 275 ገጾች ያሉት ሲሆን በውስጡም ከ25 በላይ ወጎች እና ተረኮች ተካትተውበታል፡፡ በይዘት ረገድ ደግሞ ከሚያስጨንቀው ይልቅ ፈገግ የሚያስብለው ላይ፣ ከዛሬ ይልቅ ትናንት እና ነገ ላይ፣ ከሶሻል ሚዲያው አጀንዳ ይልቅ ምድራዊው ላይ የሚያተኩር ሲሆን ትወዱታላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
.አከፋፋዮቹ ጃዕፋር መጽሐፍት መደብር (ለገሃር) እና ጦቢያ መጽሐፍት መደብር (ካሳንችስ) ሲሆኑ ከነገ ጀምሮ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ በሁሉም መጽሐፍት መደብሮች ታገኙታላችሁ፡፡ በቀጣይ ሳምንት ደግሞ በክልልና በዞን ከተሞች የምናደርስ ሲሆን ባሕር ማዶ ላላችሁ ደግሞ በአድራሻችሁ የምንልክ ይሆናል፡፡



Read 6508 times