Tuesday, 20 October 2020 00:00

ምርጫ፥ ሕገ መንግሥትና የሰሞኑ አደገኛ ፍጥጫ

Written by  ማርቆስ ረታ
Rate this item
(2 votes)

     መግቢያ
ዛሬ በአገራችን እልባት የሚያሻው አንገብጋቢ የፖለቲካ ጉዳይ፣ በሕወሓት አመራርና በፌዴራል መንግሥት መካከል የሚታየው ፍጥጫ ነው። ባደባባይ የምንሰማው የፍጥጫው ምክንያት ከምርጫ ማድረግና አለማድረግ ሕጋዊነት ጋር የተያያዘ ነው። የፌዴራል መንግሥትና ሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የፌዴሬሽን ም/ቤት በሰጠው ውሳኔ መሠረት ምርጫ ማድረግ ሳያስፈልጋቸው ስልጣን ላይ ይገኛሉ። በአንጻሩ የሕወሓት አመራር ውሳኔውን ባለመቀበል ብቻውን የክልል ም/ቤት ምርጫ ማካሄዱ ይታወሳል።
ፌዴራል መንግሥት የሕወሓትን ምርጫ እንዳልተደረገ በመቁጠር ለማለፍ መወሰኑን ካስታወቀ ከጥቂት ቀናት በኋላ 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ በያዝነው ዓመት እንደሚካሄድና ምርጫው ትግራይንም እንደሚጨምር መግለጹ ይታወቃል። በመቀጠል የሕወሓት አመራር የፌዴራሉ መንግሥት ምርጫ ባለማካሄዱ ከመስከረም 25/30 በኋላ ሕጋዊነቱ አብቅቷል፤ ውሳኔዎቹም በትግራይ ተቀባይነት አይኖራቸው ማለቱን ተከትሎ የፌዴራል መንግሥትም በሕገ ወጥ ምርጫ ከተቋቋመው የሕወሓት የክልል መንግሥት ጋር ምንም ግንኙነት እንደማይኖረው ማስታወቁን ሰምተናል።
የዚህ ነገር መጨረሻው ምንድነው? ህወሓት የመረጠው የእንቢታና የእልህ መንገድ የት እንደሚያደርሰው አስቦበት ወይስ ባወጣው ያውጣው ብሎ ይሆን? በዚህ ጽሑፍ የፌዴራል መንግስት ሕጋዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሕጋዊ ምክንያት አለመኖሩንና ሕወሓት ያካሄደውም ምርጫ ሕጋዊ አለመሆኑን በማስረዳት፤ የሕወሓት አመራር ምርጫው እንዳልተደረገ ተቆጥሮለት በዚህ ዓመት በሚደረገው 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ እንደ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ እንዲሳተፍ የተሰጠውን ዕድል ሊጠቀምበት እንደሚገባ፤ የሕወሃት አመራር ከብልጽግና አመራር ጋር ያለውን ጸብ ከቻለ በውይይት ቢፈታ፤ ካልቻለም ቢያንስ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ በምንም የማይለየውን የትግራይን ሕዝብ ጸቡ ውስጥ ባይክት እንደሚሻል ለማስገንዘብ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን እና የማይካዱ ጭብጦችን መሠረት በማድረግ ሃሳቦቼን አቀርባለሁ።
 
የፍጥጫው አመጣጥ ባጭሩ
አምና ነሐሴ ላይ ሊደረግ ታቅዶ የነበረው 6ኛው አገራዊ ምርጫ የተሰረዘው መጋቢት ወር 2012 ዓ.ም ላይ ነበር። ምክንያቱም ኮቪድ የደቀነው ስጋት ነበር። በተለይ በየካቲትና መጋቢት ወራት በአውሮፓ የረገፈውን ሰው ተመልክቶ ስጋት ያልተሰማው ብዙ አይገኝም። ስጋቱ ያስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ወለደ። አዋጁም የተለመደውን ያዘቦት ቀን አሠራርና እንቅስቃሴ፥ እንዲሁም መብቶችን ገደበ። የምርጫ ቦርድም ምርጫውን በተባለው ጊዜ ለማካሄድ እንደማይችል ገልጾ በመሰረዝ ውሳኔውን ለተወካዮች ምክር ቤት አቀረበ፤ ም/ቤቱም ውሳኔውን አጸደቀ።
በመቀጠል የፌዴራሉ መንግሥት የምርጫ ጊዜ በተራዘመበት ሁኔታ በስልጣን ላይ የሚቆይበትን የሕግ መሠረት አስመልክቶ ህጋዊ አማራጮችም አቅርቦ ሲያበቃ፣ ሕገ መንግሥቱ ግልጽ መፍትሔ የማይሰጥ በመሆኑ ፌዴሬሽን ም/ቤት ትርጉም እንዲሰጥበት ሲል ጠየቀ። ይኼኔ ተቃዋሚዎች የሕገ መንግሥት ክፍተት አለ የሚለውን የመንግሥት ድምዳሜ ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል ተነሱ። ትርጉም የማያሻውን አንቀጽ ተርጉሞ በኮቪድ ሰበብ ምርጫ ሰርዞ፣ ያለ ምርጫ ስልጣን ይዞ ለመቆየት ፈልጓል ማለት ጀመሩ።
በተለይ የሕወሓት አመራር የኮቪድ ስጋት ያላጋጠመን፥ ያስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ያልታወጀ ይመስል ምርጫ በየአምስት ዓመቱ ይደረጋል የሚለውን ድንጋጌ ይዞ፣ የተወካዮች ም/ቤት የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ያለፈው መሆኑን ብቻ የክርክሩ መነሻና መድረሻ አድርጎ፣ ፌዴራል መንግሥትን ሕጋዊነት የሌለው፣ ራሱን ደግሞ ብቸኛው ሕጋዊ መንግሥት ያቋቋመ ፓርቲ አድርጎ በማቅረብ፣ ዛሬ ካለንበት ፍጥጫ አድርሶናል።
የፍጥጫው አስኳል የሆነውን ምርጫ የማድረግና ያለማድረግ ጥያቄ በቅጡ ለመመለስ በኮቪድና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፥ እንዲሁም ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚደነግገው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ከሌሎች የተለመደውን የመንግሥት አሠራር ከሚመለከቱት ድንጋጌዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት መመልከት ያስፈልጋል።
ስለሆነም ዋነኛ የብዥታ ምንጭ የሆነውን ያስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከሕገ መንግሥቱ አንጻር እንመለከትና ቀጥለን የምርጫ መራዘም ወይም መደረግ በራሱ ሕጋዊ ወይም ሕገ ወጥ ይባል እንደሆነ እንመረምራለን።
የሕገ መንግሥቱ አውጪዎች ክፍተት ትተዋል?
በርካታ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፤ የሕገ መንግሥቱ አውጪዎች ‘የምርጫ ጊዜና ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሊገጣጠሙ ይችላሉ ብለው አስበው መፍትሄ የሚሰጥ አንቀጽ አልጨመሩም፤’ ማሰብ ነበረባቸው ማለት ባይቻልም ‘ችግሩ በሕገ መንግሥቱ አንቀጾች መሠረት ሊፈታ አይችልም’ ሲሉ ተደምጠዋል። ስህተት ነው። በመንግሥትም ምርጫ ተሰርዞ የምክር ቤቶች የሥራ ዘመን ሲገባደድ ክፍተት ይፈጠራል ማለቱ ስህተት ቢሆንም፤ እስከ ቀጣይ ምርጫ ድረስ መንግሥት በስልጣን የሚቆይበትን የሕግ አግባብ የሚመለከተውን ጥያቄ ራሴ ትርጉም ልስጥ ከማለት ይልቅ ለሚመለከተው አካል ማቅረቡ ተገቢ ነበር። እንዳስረዳ ይፈቀድልኝ።
የሕገ መንግሥቱ አውጪዎች በአገርና ሕዝብ ላይ “ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት” ለየፌዴራሉ መንግሥት የሚኒስትሮች ም/ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ስልጣን” ሲሰጡ፤ (93) ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲወጣም የተለመደው ያዘቦቱ [normal] ሕግና ሥርዓት፥ የዜጎችም መብቶች ለጊዜው እንደሚገደቡ ያውቁ ነበር። “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ጊዜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣቸው ደንቦች መሠረት የሃገርን ሰላምና ሕልውና፥ የሕዝብን ደህንነት፥ ሕግና ሥርዓት የማስከበር ስልጣን ይኖረዋል።” (93/4/ሀ) ስለዚህ ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ የተለመደው የሕግና ሥርዓት ሂደት “የሚኒስትሮች ም/ቤት በሚያወጣቸው ደንቦች” ስለሚተካ ለጊዜው ይገደባል። እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊገደቡ ከማይችሉት ጥቂት መብቶች በስተቀር የፖለቲካ መብቶችን እና የአዘቦት አሠራሮችን የሚደነግጉት አንቀፆች ሊገደቡ ይችላሉ። “የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን መሰረታዊ የፖለቲካና የዲሞክራሲ መብቶችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለማስወገድ ተፈላጊ ሆኖ በተገኘው ደረጃ እስከ ማገድ ሊደርስ የሚችል ነው።” (93/4/ለ) አደጋው ወይም ስጋቱ ተወግዶ የተለመደው ሰላማዊ ሁኔታ ሲመለስ በመብቶች ላይ የተጣለው ገደብ ይነሳል፤ ተገድበው የቆዩት ሕጋዊና ፖለቲካዊ ሂደቶችም እንደተለመደው ተፈጻሚ ይሆናሉ። ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱም እንደተለመደው ይቀጥላል።
እንግዲህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት፥ የተለመደው የአዘቦት ጊዜ ሕግና አሠራር እንደ ቀድሞው እንዲተገበር መጠበቅ፥ መጠየቅ ወይም መከራከር በሕገ መንግሥቱ መሠረት በሚታወጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና አደጋ በሌለበት ጊዜ በሚተገበረው ሕጋዊና ሕገመንግስታዊ አሠራር መካከል ያለውን ልዩነት አለማየት ነው። ሁለቱም የሕግ ዓይነቶች ሕገ መንግሥታዊ ቢሆኑም አንዱ ለአዘቦት [normal] ሌላው ለአደጋ ጊዜ የሚያገለግሉ እንደመሆናቸው፥ ለምሳሌ አንዱ መብት ሲጠብቅ ሌላው ለጊዜውም ቢሆን ይገድባል።
ስለዚህ መንግሥት በአገርና ሕዝብ፥ እንዲሁም በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ የተደቀነውን አደጋ ለማስወገድ ልዩ ያስቸኳይ ጊዜ ስልጣን ይዞ አደጋውን የመቀልበስ ኃላፊነቱን እንዲወጣ በሚጠበቅበት ሰዓት “የስልጣን ዘመኑ አብቅቷል” የሚል ወገን፥ ለክርክሩም የሕገ መንግሥቱን አንድ ወይም ሌላ አንቀጽ የሚጠቅስ ፖለቲከኛ፣ የሕግ መርሆችን ባያውቅ ቢያንስ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የደቀነውን ስጋት ለማየት አይቸግረውም። የተደቀነውን አደጋ በሚመለከት ጥርጣሬ አለኝ ማለት ሌላ ጉዳይ ነው። አደጋው መኖሩ ታምኖበት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላ ግን አዋጁን እንዳልነበረ በመቁጠር የአዘቦቱን ሕግና ድንጋጌ በመጥቀስ ሊነሳ የሚችል ምንም ዓይነት ሕጋዊ ክርክር የለም።
 
የምርጫ መራዘምና የፌዴራል መንግሥት ሕጋዊነት
የሕወሓት አመራር የያዘውን "የፌዴራል መንግሥት ሕጋዊነቱ አብቅቷል" የሚለውን አቋም በይፋ ከገለጹት የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት አንዱ አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ ናቸው። መስከረም 2012 ዓ.ም አጋማሽ ከትግራይ ቲቪ ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ፤ #ከመስከረም 25/30 በኋላ የፌዴራል መንግሥት ሕጋዊነቱን ያጣል; ብለው ምክንያቱም፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ምርጫ ስላልተደረገ፤ ስልጣኑን ለማራዘም ሲል ትርጉም የማያስፈልገውን የሕገ መንግሥት አንቀጽ ትርጉም መስጠቱ፤ ምሁራንም የምርጫው መራዘም ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ሲሉ አስተያየት መስጠታቸውን እንደሆነ ገልጸዋል።
የሕወሓት አመራር፤ የፌዴራል መንግሥትን ሕጋዊነት አልቀበልም ያለበት ምክንያት ምርጫ ሳያደርግ የሥራ ዘመኑ አልፏል በሚል ሲሆን፥ ራሱንም ብቸኛው ሕጋዊ መንግሥት ያቋቋመ ድርጅት ለማለት ያስደፈረው አምስት ዓመቱ ሳያልፍ ምርጫ አካሄድኩ በሚል ነው። በየአምስት ዓመቱ መደረግ የነበረበት ምርጫ አለመደረጉ ብቻ መንግሥት የለም ወይም ሕጋዊነቱ አብቅቷል ያስብላል? በአገርና ሕዝብ ላይ የተደቀነ አደጋ ለመከላከል የታወጀ ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ በዜጎች መብት ላይ በጣላቸው ገደቦች ምክንያት ምርጫ ለማካሄድ የሚያስፈልገውን ዝግጅት ለማድረግ ባለመቻሉ ምርጫው ቢሰረዝ፣ የምርጫው መሰረዝ ብቻ በራሱ ስህተት ነው ለማለት ምን ሕጋዊ መሠረት ይገኛል?
በበርካታ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች “ማንበብ የሚችል ሰው ሁሉ አንብቦ ሊረዳቸው የሚችልና ትርጉም የማያሻቸው” የተባለላቸው ሁለት የሕገ መንግሥት አንቀጾች እነሆ፦
አንቀጽ (54/1) “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሁሉ አቀፍ፥ ነጻ፥ ቀጥተኛ፥ ትክክለኛ በሆነና ድምጽ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዓት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ።”
አንቀጽ 58/2 “የምክር ቤቱ የሥራ ጊዜ ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እስከ ሰኔ ሰላሳ ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው። የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ይጠናቀቃል።”
ሁለቱም የሚሉት ያው “ምክር ቤቱ የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው” እና አባላቱ “በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ” ነው፤ በቃ። ምርጫ ካልተደረገ መንግሥት የለም አይሉም። አንቀጾቹን ጠቅሶ መንግሥት የለም ማለት የሚቻለው ለድንጋጌዎቹ ትርጉም በመስጠት ብቻ ነው። ትርጉም አያስፈልገውም፥ ግልጽ ነው የተባለውን ድንጋጌ ትርጉም ካልሰጡ በቀር “በየአምስት ዓመቱ ይመረጣሉ” ወይም ምክር ቤቱ “የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው” የሚለውን ይዞ ምርጫ ሳይደረግ ቢቀር “ሕጋዊነቱ አብቅቷል” ለማለት አይቻልም። ትርጉም ግድ ነበር ማለት ነው። ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም ይሰጥ ከተባለም ሁለቱን አንቀጾች ብቻ ነጥሎ ማየት አይበቃም፤ ያስቸኳይ ጊዜ አዋጁን (አንቀጽ 93) እና ሌሎችንም ማየት ግድ ይላል።
የሕገ መንግሥት ትርጉም አስፈላጊነት
ከላይ እንደተባለው በአገርና ሕዝብ ደኅንነት ላይ ስጋት የሚደቅን ዓለም አቀፍ ወረርሽኝም ሆነ ጦርነት ሲያጋጥም ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ፣ በሌሎች የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች የተደነገገው አሠራርና የዜጎች መብት እንዳስፈላጊነቱ ለጊዜው ተገድቦ ይቆያል። ሊገደቡ የማይችሉ መብቶችና የአሠራር ሥርዓቶች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን ከዚያ ውጭ እንዳስፈላጊነቱ የሚጣሉ ገደቦች በሕገ መንግሥቱ የተከለከሉ አይደሉም። በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት፥ የመሰብሰብ መብት ተገድበው መቆየታቸው ይታወቃል። በነዚህ መብቶች መገደብ ምክንያት ሊጠበቁ የማይችሉ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ የጊዜ ሰሌዳዎችም እንዲሁ መገደባቸው አይቀርም። ስለሆነም በሕገ መንግሥቱ አንቀጾች 54/1 እና 58/2 የተቀመጠው የአምስት ዓመት የጊዜ ሰሌዳም ሊተገበር የማይችል በመሆኑ የግድ መገደቡ አይቀርም።
ይህ ትርጓሜ ከእውነታው ጋር የሚስማማ ነው ባይ ነኝ፤ ሆኖም ትርጉሙን የማይቀበል አይጠፋም። እንዲያውም ከላይ የተጠቀሱት አንቀጾች “ግልጽ ናቸው፥ ትርጉም አያሻቸውም” ባዮቹ ክርክራቸውን ለመደገፍ የሚያቀርቧቸው ትርጉሞች ነበሩ። ለምሳሌ “ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መብቶችን ሊገድብ ቢችልም የመንግሥትን የስልጣን ጊዜ ግን ሊያራዝም አይችልም” የሚል “ትርጉም” ይዘው የሚከራከሩ ወገኖች ነበሩ፤ አሉ። ለፓለቲካ ዓላማቸው ማስፈጸሚያ የሚመቻቸውን ትርጉም መርጠው ቢቃወሙ መብታቸው ቢሆንም የነሱ ትርጉም የኔ ቢጤው ተራ ዜጋ ከሚያቀርበው ትርጉም በምንም አይለይም። እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የፌዴራሉ መንግሥት የመሰለውን ትርጉም በመስጠት ፋንታ ጉዳዩን ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ስልጣን ወዳለው አካል የማቅረቡን ተገቢነት ለመገንዘብ የሚቻለው።
በተጨማሪ “ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መብት ቢገድብ እንጂ የመንግሥትን ሥልጣን አያራዝምም” የሚለውን ትርጉም ሕጋዊ መሠረት የሌለው መሆኑ ቢታወቅም እንደ ሙግትም ተጨባጩን እውነታ ያገናዘበ አለመሆኑን እንመለከት። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሕገ መንግስታዊ መብቶችን ከገደበ የተጣለው ገደብ የሚያስከትለው ውጤት መኖሩ እይካድም። ምርጫ ቦርድ የምርጫ አስፈጻሚዎችንና ታዛቢዎችን ሰብስቦ ስልጠና መስጠት ነበረበት፤ ካልሰበሰበ አያሰለጥንም፤ ሊዘጋጅ አይችልም፤ ምርጫ ማድረግ አይችልም። በሌላ በኩል የኮቪድን ስርጭት ለመከላከል ሰው እንዳይሰበሰብ በሕግ [ባስቸኳይ ጊዜ አዋጅ] ተከልክሎ ነበር። የመሰሰብ መብትም ሆነ በሕግ የተጣለው ክልከላ ሕገ መንግሥታዊ ናቸው። በየአምስት ዓመቱ ምርጫ ይካሄዳል የሚለው ድንጋጌ ቢኖርም ለጊዜው መገደቡ አይቀርም። ምርጫ ማካሄድ ካልተቻለ መሰረዝ ግድ ነው።
በሕግ በተጣለ ገደብ ምክንያት ተተኪ የፓርላማ አባላት ለመምረጥ የሚያስችል ምርጫ በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ለማስፈጸም ባልተቻለበት ሁኔታ የፓርላማው የስልጣን ጊዜ የሚወስነው አንቀጽ ብቻውን ከመገደብ አምልጦ አየር ላይ ሊተገበር አይችልም። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የምርጫ ጊዜ የግድ መለወጥ ካለበትና ወደፊት መሸጋገር ካለበት በዚያ ልክ የፓርላማው የሥራ ጊዜ ምርጫ ማድረግ እስከሚቻልበት ጊዜ ድረስ የግድ መራዘም ይኖርበታል። ሕገ መንግሥቱም ይህን አይከለክልም። “...በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን መሰረታዊ የፖለቲካና የዲሞክራሲ መብቶችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለማስወገድ ተፈላጊ ሆኖ በተገኘው ደረጃ እስከ ማገድ ሊደርስ የሚችል ነው።” ይላል።(93/4/ለ)
ስለሆነም ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በየአምስት ዓመቱ የሚካሄድን የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምርጫ በየአምስት ዓመቱ እንደሚካሄድ፥ የም/ቤቱ የስልጣን ዘመን አምስት ዓመት መሆኑን የሚደነግጉትን የሕገ መንግስቱ አንቀጾች [54/1 እና 58/2] አንቀጾቹ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊገድቡ ይችላሉ። በዚህ ሁኔታ የምርጫ ጊዜ በመራዘሙ ምክንያት በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት የስልጣን ጌዜው አብቅቷል ለማለት የሚያስችል ሕጋዊ መሠረት የለም።

ሕወሓት ያካሄደው ምርጫ ሕጋዊ መሠረት የሌለው ስለመሆኑ፤
የሕወሓት አመራር ኮቪድ በተስፋፋበትና ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት ሁኔታ ምርጫ ለማካሄድ ሕጉ ይፈቅድለታል? ባጭሩ አይፈቅድለትም። በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 102 መሠረት፤ በኢትዮጵያ በፌዴራልና በክልል ደረጃ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫዎችን የማቀድና በገለልተኝነት የማስፈጸም ስልጣን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው።
ምርጫ ቦርድ ራሱ ያስቀመጠውን የምርጫ ጊዜ ለመሰረዝ መወሰኑ፤ ውሳኔውም በተወካዮች ም/ቤት መጽደቁ እየታወቀ፤ የፌዴሬሽን ም/ቤትም በኮቪድ ምክንያት የታወጀውን ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ፣ ምርጫ ለማራዘም የተደረገውን ውሳኔ ተመልክቶ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥ በቀረበለት ጥያቄ መሠረት፤ የፌዴራልና ክልል ም/ቤቶች በየስልጣናቸው እንዲቆዩ መወሰኑ ሲታወቅ፤ በማን አለብኝነት ምርጫ አካሄድኩ ማለት ሕገ ወጥነት ነው።
በምርጫ ሕግ መሠረት፤ ምርጫን በሚመለከት የክልሎች ስልጣን በአካባቢ ምርጫ [የዞን፥ የወረዳ፥ የከተማ ማዘጋጃ ቤት፥ የክፍለ ከተማ ወይም የቀበሌ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ] የተወሰነ ሲሆን፤ በዚህ ላይም ቢሆን ክልሎች ምርጫ የሚካሄድበትን ጊዜ በሕግ ከሚወስኑ በቀር አፈጻጸሙ ‘በምርጫ ሕግና የምርጫ ቦርድ በሚያወጣው ደንብና መመሪያ መሠረት ይከናወናል።’
በሕገ መንግሥቱ የተቋቋሙ ተቋሞችን ውሳኔ ሳይቀበሉ "ሕገ መንግሥት ተጣሰ" እያሉ ለመክሰስ አይቻልም። የሕወሓት ሊቀ መንበር ከ“ምርጫ”ው በኋላ የሕግ አንቀጽ እየጠቀሱ መከራከር ዋጋ እንደሌለው፤ "ወሳኙ የትግራይ ሕዝብ ምርጫ ነው” ብለው ነበር። የሕገ መንግስቱ አንቀፆች፣ አንድ ፓርቲ ሲፈልግ የሚጠቅሳቸው ሲሻው የሚጥሳቸው አይደሉም። ካከበሩ ሙሉውን ነው ማክበር፤ ለመጣስ ግን አንዱን አንቀጽ መጣስ ይበቃል። ሕግ ባለበት አገር አንቀጽማ ገና ይጠቀሳል እንጂ፤ እንዴት አይጠቀስም?!

አይቀሬው 6ኛ አገራዊ ምርጫና የሕወሓት ተሳትፎ
ሕወሓት ምንም ጥረት ማድረግ ሳያስፈልገው በስልጣን መቆየት ሲችል፣ የግድ ምርጫ ለማድረግ ሲነሳ የሕዝቦችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት መጥቀሱ ቢታወቅም፣ በምርጫ ስልጣን የያዘ ፓርቲ እንደመሆኑ ብዙ ሊያሳስበው ባልተገባ። ምናልባት ሳይመረጥ ለአንድ ቀንም ቢሆን ስልጣን ላይ ለመቆየት የማይፈልግ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት በመሆኑ ነው እንበል። በርግጥ የሕወሓት ምርጫ የክልል ም/ቤቱ የሥራ ዘመን ሳይጠናቀቅ የተደረገ ቢሆንም፣ ብቸኛው ገለልተኛ ባለስልጣን በሌለበት የተደረገ በመሆኑ፤ ከሕገ ወጥነት ሊያመልጥ አይችልም። ይሁንና በፌዴራል መንግሥት በኩል ምርጫው እንዳልተደረገ ቢቆጠርም፣ ምርጫ ማድረጉ የመርህ ጉዳይ ነው ቢል ሊያስኬድ ይችላል፤ ያለ ምርጫ፥ ያለ ውክልና ስልጣን አይያዝም የሚል መርህ ግድ ብሎት ነው እንበል።
ሆኖም ፌዴራሉ መንግሥት 6ኛውን አገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት ሲጀምር፣ ሕወሓት“አንዴ ተመርጫለሁ” በማለት በክልሉ ምርጫ እንዳይካሄድ አሻፈረኝ ቢል፣ መርህ የለሽ ሕገ ወጥነት ይሆንበታል። ምክንያቱም ሕገወጥም ቢሆን ምርጫ ማድረግን የሞት ሽረት ጉዳይ ሲያደርግ እንደ
ምክንያት ያቀረበው የክልሉን ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ቢሆንም፣ በፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚነት የሚካሄደውን 6ኛ አገር አቀፍ ምርጫ አይካሄድም ካለ፣ የእምቢታው ምክንያት የሕዝቡን መብት ማስከበር ሊሆን አይችልም። ይልቁንም እምቢታው ሕወሓት የክልሉን የመንግሥት ስልጣን በሕገ ወጥ መንገድ ነጥቆ ራሱን ስልጣን ላይ ለማቆየት ያለውን ፍላጎት የሚያረጋግጥ ይሆናል። ሕዝቡ ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱ ሊከበርለት የሚችለው ተፎካካሪዎች በነጻነት ሃሳባቸውን ለሕዝቡ አቅርበው መወዳደር ሲችሉና ምርጫውም ገለልተኛ በሆነው የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ አስፈጻሚነት ሲደረግ ብቻ ነው። ይህን መቃወም የህዝብን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ማፈን ይሆናል።
አገር አቀፍ ምርጫ እንዲደረግ ብቸኛው ባለስልጣን የሰጠውን ውሳኔ አልቀበልም የሚል ፓርቲ፤ ራሱን ከምርጫው የማግለል መብቱ የተጠበቀ ሲሆን የሌሎችን ፓርቲዎች መብት እንዲጋፋ፥ በተለይም የመራጩን ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እንዲጥስ ሊፈቀድለት አይችልም።


Read 2359 times