Sunday, 25 October 2020 00:00

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ)

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 • ከኮሮና እግድ በኋላ በመጀመርያ የወዳጅነት ጨዋታቸው በሜዳቸው ተሸንፈዋል፡
   • ከ1 ወራት በፊት ለ38ኛ ጊዜ ዋና አሰልጣኝ (ውበቱ አባተ) ተቀጥሮላቸዋል፡፡
   • በ33ኛው የአፍሪካና በ22ኛው የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያዎች ተሳታፊ ናቸው፡፡ በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃና በትራንስፈርማርከት የዋጋ    ተመን ከተፎካካሪዎቹ ያንሳሉ፡፡
   • ታሪክ 75 ዓመት ሊሞላው ነው ፡፡ ከ56 ብሄራዊ ቡድኖች ጋር 388 ግጥሚያዎችን አድርጓል፡፡ በ142 ጨዋታዎች አሸንፏል፤ በ82 አቻ ወጥቷል፤    164 ጨዋታዎች ተሸንፏል፡፡


             በኮሮና ሳቢያ ያለፉትን 7 ወራት ያለ ውድድር የቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከትናንት በስቲያ የመጀመርያ የወዳጅነት ጨዋታውን አድርጎ በዛምቢያ ቡድን 3ለ2 ተሸንፏል፡፡ ወደ መደበኛ ልምምድ ከገባና አዲስ ዋና አሰልጣኝ ከተመደበለት አንድ ወር የሆነው ብሄራዊ ቡድኑ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ እስከ 86ኛው ደቂቃ ድረስ የዛምቢያ ቡድንን 2-1 ሲመራ ቢቆይም ባለቀ ሰዓት በተቆጠሩ ጎሎች በሜዳው ሽንፈት ገጥሞታል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ የ3ኛና 4ኛ ዙር ጨዋታዎችን ከኒጀር ጋር በደርሶ መልስ ያደርጋል፡፡    
በአዲስ አበባ በሚገኘው ዘመናዊው የካፍ አካዳሚ ያለፈውን 1 ወር ሲዘጋጁ የቆዩት ዋልያዎቹ ከዛምቢያ አቻቸው ጋር ሲገናኙ  አዲሱ ዋና አሰልጣኝ የመጀመርያ የብሄራዊ ቡድን ጨዋታውን በሃላፊነት ሊመራ በቅቷል፡፡ በወዳጅነት ጨዋታው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመጀመርያውን ጎል በ13ኛው ደቂቃ ላይ  በጌታነህ ከበደ ካስቆጠረ በኋላ የዛምቢያ  ቡድን በሙጋምባ ካምፖምባ ጎል በ39ኛው ደቂቃ ላይ አቻ ሆኗል፡፡ በ43ኛው ደቂቃ ላይ በአስቻለው ታመነ አማካኝነት ዋልያዎቹ ወደ መሪነት ቢመለሱም የዛምቢያው አልበርት ካዋንዳ በ86ኛው እና በ90ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች 3ለ2 ተሸንፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከሰባት ወር በላይ ያለውድድር ነው የቆየው፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ውድድሮችና መደበኛ የልምምድ መርሃ ግብሮች በተጠና መንገድ ባለመካሄዳቸው በተጫዋቾች ብቃት ላይ  ከፍተኛ ተፅእኖ አሳድሯል፡፡ ወደ የተሟላ አቋም በመመለስ በአፍሪካ ዋንጫ እና በሌሎች የማጣርያ ውድድሮች በንቃት እና በውጤታማነት ለመሳተፍ ከወዳጅነት ጨዋታዎች ባሻገር በርካታ ስራዎች ይጠበቃሉ፡፡
ዋልያዎቹ በአህጉራዊ ውድድሮች ላይ ባለፉት 5 የውድድር ዘመናት የነበራቸው ተሳትፎ ደካማ እንደነበር የሚስተዋል ሲሆን በኮቪድ ሳቢያ የተፈጠሩ ችግሮች ብሄራዊ ቡድኑን ወደየባሰ አዘቅት እንዳይከቱት የሚያሰጋ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ አህጉራዊ ውድድሮች ለመመለስ ከኮቪድ 19 በኋላ ፈተናዎቹ በዝተዋል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በአዲሱ ዋና አሰልጣኝ እየተመራ በሜዳው ያደረገውን የወዳጅነት ጨዋታ መሸነፉ ጥሩ ምልክት አይደለም፡፡ ዋልያዎቹ በነጥብ ጨዋታዎች ላይ ከሜዳቸው ውጭ ተደጋጋሚ ሽንፈት እየገጠማቸው የቆየ ሲሆን በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎችም ላይ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ አለመቻላቸው በተለያዩ የማጣርያ ውድድሮች የሚኖራቸውን ስኬት ይወስነዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አቋም መውረድ ባለፉት 6 ዓመታት 4 ዋና አሰልጣኞችን ያለ በቂ ምክንያት መቀያየሩ፤ ለተለያዩ ውድድሮች በሚያደርጋቸው ዝግጅቶች በቂ የአቋም መፈተሻ ግጥሚያዎችን አለማግኘትና ልዩ  ትኩረት አለመስጠት፤ በሜዳው የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች በተለያዩ ስታድዬሞች ማከናወኑና ሌሎች አስተዳደራዊ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ:: ይህ የስፖርት አድማስ ዘገባ በዋልያዎቹ ዙርያ ያሉትን ወቅታዊ እና ታሪካዊ ሁኔታዎች የሚዳስስ ነው፡፡
አዲሱ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ
ከወር በፊት ለዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ በእግር ኳስ ፌደሬሽን የተሾመው ውበቱ አባተ ሲሆን በብሄራዊ ቡድኑ የ75 ዓመታት ታሪክ ውስጥ በሃላፊነቱ ላይ 38ኛው ቅጥር መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከሹመቱ በኋላ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ መሆን የልጅነቴ ህልሜ ነበር፡፡  በመሳካቱ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል” ብሎ ነበር፡፡ ብሔራዊ ቡድኑን ለማሰልጠን ለአራትና አምስት ጊዜ መወዳዳሩን በወቅቱ የገለፀው ዋና አሰልጣኝ ውበቱ፤ በአንድ አጋጣሚ ሃላፊነቱን እንደሚረከብ በይፋ ተገልፆ ውሳኔው እንደተቀየረበት አስታውሷል፡፡ ከዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በፊት ብሄራዊ ቡድኑን ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት በሃላፊነት ይዞ የነበረው ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ልምድ ያለው ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ሲሆን፤ ዋና አሰልጣኙ ከኮሮና ወረርሽኝ በፊት  በተካሄዱ ጨዋታዎች ጥሩ መሻሻል ማሳየት ቢጀምርም ፌደሬሽኑ የነበረውም ኮንትራት ባለማደስ አዲሱን አሰልጣኝ ሾሟል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን  በመግለጫው እንዳመለከተው ለዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሰጠው ሃላፊነት ለሁለት ዓመት በኮንትራት የሚቆይ ሲሆን ብሄራዊ ቡድኑን  ለ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እንዲያሳልፍ እና ለ22ኛው የዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ማጣሪያ እንዲያደርስ እቅድ መቅረቡንና በስምምነቱ መሰረት 125 ሺህ ብር ወርሃዊ ደመዎዝ እንደሚከፈልም ታውቋል። ዋና አሰልጣኝ ውበቱ ከብሄራዊ ቡድኑ በፊት ታላላቅ የሚባሉ የሀገራችንን ክለቦችን አሰልጥኗል፡፡ እነሱም አዳማ ከነማ፣ ፋሲል ከነማ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ሀዋሳ ከነማ፣ ደደቢት እና ሰበታ ከነማ ናቸው፡፡ በተለይም በ2003 ዓ.ም ኢትዮጵያ ቡናን የፕሪሚዬር ሊጉ ሻምፒየን ያደረገበት ውጤት ከፍተኛ ስኬቱ ነው፡፡ ከአገር ውጭ በተጨማሪ በነበረው ልምድ ወደ ጎረቤት ሀገር ሱዳን በማቅናት አልአህሊ ሸንዲን ያሰለጠነ ሲሆን፤ በሱዳን ቆይታው ክለቡን በሊጉ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ እንዲጨርስ በማድረግ ለአፍሪካ ኮንፌደሬሽንስ ዋንጫ ተሳታፊነት ለማብቃት ችሏል፡፡
የተሰናበቱት ኢንስትራክተር አብርሃም
ከዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በፊት በሃላፊነቱ ላይ የነበረው ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት ለ2 ዓመታት ያህል መርቷል፡፡ ወርሀዊ ደሞዙ ከጥቅማ ጥቅም ውጪ 125 ሺህ ብር የነበረ ሲሆን  በሰውነት ቢሻው ሰብሳቢነት ከሚመራው ብሄራዊ ቴክኒክ ኮሚቴው ጋር ሲሰራ እንደነበርና የቀድሞ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች የነበሩት ፋሲል ተካልኝ እና ሙሉጌታ ምህረት  በምክትል አሰልጣኝነት አብረው እያገለገሉ ቆይተዋል፡፡ የ49 ዓመቱ ኢንስትራክተር  አብርሃም በአገር ውስጥ ከሚገኙ አሰልጣኞች ባለው ዓለም አቀፍ ልምድ እና የሙያ ብቃት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ከወረደበት አቋም እንደሚመልሰው ተስፋ ነበር፡፡ ኢንስትራክተሩ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በፊት በኢትዮጵያ እግር ኳስ በነበረው ተመክሮ የቡና፣ የኒያላ፣ የወንጂ ስኳር እና የእህል ንግድ ክለቦችን አሰልጥኗል፡፡  ከዚያም በየመን እግር ኳስ የሚጠቀስ ታሪክ የነበረው ሲሆን በቴክኒክ ዲያሬክተርነት እንዲሁም በዋና አሰልጣኝነት የየመን ብሄራዊ ቡድን ለሶስት አመታት እንዳገለገለም ይታወቃል፡፡
ኢንስትራክተር አብርሃም በአፍሪካ እግር ኳስ በአሰልጣኝነት፤ በአሰልጣኞች አሰልጣኝነት ከፍተኛ ደረጃ እንደደረሰና በአገር ውስጥ እና በአህጉራዊ መድረኮች በመስራት ልዩ ልምድ ማካበቱም ይታወቃል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ከወር በፊት ግብፅ ባስተናገደችው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በካፍ የቴክኒክ ጥናት ቡድን ሲያካትተው፤  የአሠልጣኞች አሠልጣኝ ተብለው ከሚጠቀሱ አፍሪካዊ ኢንስትራክተሮች አንዱ ስለሆነ ነበር:: ኢንስትራክተር አብርሃም በአፍሪካ ዋንጫው የቡድኖቹን ቴክኒካዊ ብቃት ከመገምገም ባሻገር የየጨዋታውን ኮከብ ተጨዋቾች ምርጫ በማከናወን ልዩ ሚናውንም ተወጥቷል፡፡ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት የዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ  በ10 ጨዋታዎች በሃላፊነት የመራ ሲሆን በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ የአይቬሪኮስት ብሄራዊ ቡድንን ያሸነፈበት ውጤት ትልቅ ታሪክ ነው፡፡
የዋና አሰልጣኞች ቅጥርና ቆይታ
በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የ75 ዓመታት ታሪክ የዋና አሰልጣኝ ሹመት ከ2 ዓመት በላይ እንደማይዘልቅ ይስተዋላል፡፡ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የ2 ዓመታት የስራ ቆይታከተቋረጠ በኋላ በታሪክ የነበሩ  አሰልጣኞችን ቆይታና ዜግነት ከዚህ ጋር አያይዞ ማነፃፀር ይቻላል። በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የቅርብ ጊዜ ታሪክ  በዋና አሰልጣኝነት ለረጅም ግዜ በመቆየት ግንባር ቀደም የሆኑት ለሁለት ጊዜያት በሃላፊነቱ የሰሩት ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ናቸው፡፡ በመጀመርያ ቅጥራቸው ለ609 ቀናት ከዚያም በሁለተኛ ጊዜ ቅጥራቸው 830 ቀናት በድምሩ 1439 ቀናትን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት በመምራታቸው ነው፡፡ በሃላፊነቱ ረጅሙን ቆይታ በማድረግ በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሱት ጀርመናዊው ፒተር ሽናይተገር በ1095 ቀናት አገልግሎታቸው ሲሆን፤ ኢንስትራክተር ዮሐንስ ሳህሌ ለ398፤ ፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ ለ364 ቀናት፤ አሸናፊ በቀለ ለ309 ቀናት፤ ስኮትላንዳዊው ኢፌም ኦኑራ ለ293 ቀናት፤ ፈረንሳዊው ዲያጎ ጋርዜቶ ለ190 ቀናት፤ ቤልጅማዊው ቶም ሴንት ፌንት ለ161 ቀናት እንዲሁም ገብረመድህን ሃይሌ ለ159 ቀናት በሃላፊነቱ ላይ መቆየት ችለዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በፊት ከ1956 ጀምሮ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 37 ግዜ የዋና አሰልጣኝ ቅጥሮች ተካሂደዋል፡፡ ከኢትዮጵያዊ ዜግነት ውጭ የነበራቸው አሰልጣኞች ብዛት ሲሆኑ ሌሎቹ 23 ቅጥሮች በኢትዮጵያውያን ተሸፍነዋል፡፡ የውጭ አገራት አሰልጣኞች ከግሪክ፤ ቼኮስላቫኪያ፤ ዩጎስላቪያ፤ ሃንጋሪ፤ጀርመን፤ ጣሊያን፤ስኮትላንድ፤ ቤልጅዬም፤ ፖርቱጋል የተገኙ ነበሩ፡፡
በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ እና በ22ኛው የዓለም ዋንጫ የምድብ ቅድመ ማጣርያ
ከኮሮና እግድ በኋላ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ይፋ ባደረገው እቅድ መሰረት በ2021 በካሜሮን ወደ የሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚካሄዱት የምድብ ማጣርያዎች በህዳር ወር  ይቀጥላሉ፡፡ በሌላ በኩል በኳታር ለሚካሄደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ በአፍሪካ ዞን  የሚካሄዱት  የምድብ ቅድመ ማጣርያዎች ደግሞ ከስድስት ወራት በኋላ በግንቦት ወር እንደሚጀምሩ ቀጠሮ ተይዟል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኮቪድ ሳቢያ ለ7 ወራት ያለውድድር ከቆየ በኋላ የመጀመርያ ዓለም አቀፍ የነጥብ ጨዋታውን በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ነው የሚቀጥለው፡፡ በህዳር ወር ላይ በምድብ ማጣርያው የ3ኛ እና የ4ኛ ዙር ጨዋታዎች ከኒጀር አቻው በደርሶ መልስ ጨዋታዎች የሚገናኝ ይሆናል፡፡ ዋልያዎቹ  በሚገኙበት ምድብ 11 የመጀመርያ ጨዋታቸው ከሜዳቸው ውጭ በማዳጋስካር የተሸነፉ ሲሆን በሁለተኛ ዙር ጨዋታ ደግሞ በሜዳቸው አይቬሪኮስትን በማሸነፍ ተፎካካሪነታቸውን አድሰዋል። በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ  በምድብ 11 አይቬሪኮስት፣ ኒጀር፤ ማዳጋስካርና ኢትዮጵያ መደልደላቸው ይታወቃል፡፡  ምድቡን በሁለት ጨዋታዎች 6 ነጥብና 5 የግብ ክፍያ የሰበሰበችው ማዳጋስካር እየመራች ሲሆን ኢትዮጵያና አይቬሪኮስት እኩል  በ3 ነጥብን የለምንም ግብ ክፍያ ሁለተኛ እንዲሁም ኒጀር ያለምንም ነጥብ በአምስት የግብ እዳ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በ22ኛው የዓለም ዋንጫ በአፍሪካ ዞን  የምድብ ቅድመ ማጣርያ ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ ስድስት የተደለደለው ከጋና፤ ደቡብ አፍሪካ እና ዚምባቡዌ ጋር ነው፡፡ የምድቡ የመጀመርያ ዙር ጨዋታዎች ከ7 ወራት በኋላ በሚገለጽ መርሃ ግብር ይቀጥላሉ፡፡
ዋልያዎቹ በትራንስፈርማርከት በ500ሺ  ዩሮ ዋጋቸው ተተምኗል
23 ተጨዋቾች የሚገኙበት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን  ስብስብ በትራንስፈርማርከት የተተመነው በ500ሺ  ዩሮ ነው፡፡ በአማካይ እድሜው 24.8 ዓመት ሆኖ የተመዘገበው ቡድኑ ዋጋው ለተመን የበቃው ከአገር ውጭ ይጫወታሉ ተብሎ በተጠቀሱት ሽመልስ በቀለና ጋቶች ፓኖም አማካኝነት ነው፡፡ ለግብፁ ማስር አልማክሳ የሚጫወተው ሽመልስ በቀለ  በአሁኑ ወቅት የብሄራዊ ቡድኑ ውድ ተጨዋች ሲሆን ዋጋው በ300ሺ ዩሮ ተተምኗል፡፡ ሌላው የብሄራዊ ቡድን ተጨዋች ጋቶች ፓኖም ለሳውዲ አረቢያው አል አንዋር በመጫወት በ200ሺ ዮሮ ዋጋ አግኝቷል፡፡
በትራንስፈርማርከት ላይ በሰፈረው መረጃ መሰረት 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ከኢትዮጵያ ጋር የተደለደሉት ቡድኖች በዋጋ ተመናቸውም ብልጫ ያሳያሉ፡፡ በአማካይ እድሜው 27.8 ዓመት ሆኖ የተመዘገበውና 26 ተጨዋቾችን ያሰባሰበው የኒጀር ብሄራዊ ቡድን በትራንስፈርማርከት ዋጋው የተተመነው በ3.5 ሚሊዮን  ዩሮ ነው፡፡ ከኒጀር ቡድን 21 ተጨዋቾች ከአገራቸው ውጭ የሚጫወቱ ሲሆን ፤ውድ ዋጋ ያለው ለእስራኤል ክለብ የሚጫወተው አህመድ አሊ በ1.2 ሚሊዮን ዩሮ ዋጋው እንደሆነ ከ25ሺ ዩሮ እስከ 300ሺ ዩሮ የዋጋ ተመን ያላቸው ከ13 በላይ ናቸው። ትራንስፈርማርከት 27 ተጨዋቾች የሚገኙበትን የማዳጋስካር ብሄራዊ ቡድን በ10 ሚሊዮን ዩሮ ዋጋ ያወጣለት ሲሆን 21 ተጨዋቾች ከተለያዩ አገራት መሰባሳባቸውን አመልክቷል። በማዳጋስካር የተጨዋቾች ስብስብ ከ20 በላይ ተጨዋቾች በትራንስፈርማርከት ዋጋ ያላቸው ሲሆን ከ1 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ዋጋ የተሰጣቸው አምስት ናቸው፡፡ አኒኬት ከፍተኛ ዋጋ ያለው የማዳጋስካር ተጨዋች ሲሆን በ2.4 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመን ነው፡፡ በምድቡ ከአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች በተጨዋቾች ስብስቡ ከፍተኛ የዋጋ ተመን ግንባር ቀደም የሆነው የአይቬሪኮስት ብሄራዊ ቡድንም ይገኛል። ትራንስፈርማርከት 27 ተጨዋቾች የተሰባሰቡበት የአይቬሪኮስት ብሄራዊ ቡድን የዋጋ ተመን 226.83 ሚሊዮን ዩሮ መሆኑን ሲያመለክት፤  በአገር ውስጥ የሚጫወተው 1 ብቻ ሲሆን 26 በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች የሚጫወቱ ምርጥ ፕሮፌሽናሎች እንደሆኑ ጠቅሷል፡፡ በአይቬሪኮስት በረኞች ከ1.5 ሚሊዮን ዩሮ በላይ፤ ተከላካዮች 48 ሚሊዮን ዩሮ በላይ፤ አማካዮች 42 ሚሊዮን ዩሮ በላይ እንዲሁም አጥቂዎች ከ130 ሚሊዮን ዩሮ በላይ የዋጋ ተመን ሲሆን ውዱ ተጨዋች በ50 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመን ዊልፍሬድ ዘሃ ነው፡፡
ዋልያዎቹ በፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ በ1061 ነጥብ ከዓለም 146ኛ ፤  ከአፍሪካ 41ኛ
በወርሐዊው የፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ መሰረት የአፍሪካን አህጉር በአንደኝነት የምትመራው በ1549 ነጥብ ሴኔጋል ናት፡፡ ቱኒዚያ በ1507 ነጥብ፤ አልጄርያ በ1489 ነጥብ፤ ናይጄርያ በ1488 ነጥብ እንዲሁም  ሞሮኮ በ1461 ነጥብ እስከ አምስተኛ ደረጃ አከታትለው ይዘዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአሁኑ ወቅት በፊፋ የዓለም እግር ኳስ ደረጃ በ1061 ነጥብ ከዓለም 211 አገራት 146ኛ ፤  ከአፍሪካ 54 አገራት ደግሞ በ41ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ በተለይ ባለፉት 4 የውድድር ዘመናት ደረጃውን ለማሻሻል አልቻለም፡፡ ከአፍሪካ በደረጃው የበለጣቸው እነ ብሩንዲ፤ ቦትስዋና፤ ደቡብ ሱዳን፤ ሞሪሽየስ ስዋቴሜ ኤንድ ፕሪስፒ፤ ጅቡቲ፤ ሶማሊያ እና ኤርትራን ነው፡፡ ታንዛኒያ፤ ሩዋንዳ፤ ሱዳን፤ ኡጋንዳ፤ ኒጀር፤ ዚምባቡዌ፤ ዛምቢያ… ከበላዩ ናቸው፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ እና በዓለም ዋንጫ ማጣርያዎችም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በየምድቡ አብረውት ከተደለደሉት ቡድኖች በደረጃው ዝቅ ብሎ ይገኛል፡፡ በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ከኢትዮጵያ ጋር በምድብ 11 ከተደለደሉ ቡድኖች በፊፋ ደረጃቸው  አይቬሪኮስት በ1378 ነጥብ ከዓለም 61ኛ ከአፍሪካ 12ኛ፤ ማዳጋስካር በ1264 ነጥብ ከዓለም 92ኛ ከአፍሪካ 20ኛ እንዲሁም ኒጀር በ1167 ነጥብ ከዓለም 112ኛ ከአፍሪካ  28ኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ ለ22ኛው የዓለም ዋንጫ ለሚደረግ የቅድመ ምድብ ማጣርያ ላይም በምድብ 6 ከኢትዮጵያ ጋር  የተደለደሉት  ጋና በ1438 ነጥብ ከዓለም 48ኛ ከአፍሪካ 6ኛ፤  ደቡብ አፍሪካ በ1332 ነጥብ ከዓለም 72ኛ ከአፍሪካ 14ኛ እንዲሁም ዚምባቡዌ በ1180 ነጥብ  ከዓለም 111ኛ ከአፍሪካ 27ኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡
ዋልያዎቹ በ75 ዓመታት ከ56 ብሄራዊ ቡድኖች ጋር 388 ግጥሚያዎች  142  ድል ፤ 82 አቻና 164 ሽንፈት
የእግር ኳስ ስታትስቲክሶችና ታሪኮችን በድረገፁ የሚያሰባስበውና የሚያሰራጨው 11v11.com እንደሚያመለክተው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዞናዊ፤ አህጉራዊ፤ ዓለም አቀፋዊ የውድድር መድረኮች መሳተፍ ከጀመረ 75 ዓመታት ሊሞላው ነው፡፡ በምስራቅ አፍሪካ፤ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በዋና እና የማጣርያ ውድድሮች እንዲሁም በወዳጅነት ከ56 ብሄራዊ ቡድኖች ጋር 388 ግጥሚያዎችን አድርጓል፡፡ በ142 ጨዋታዎች ድል አድርጎ በ82 አቻ ሲወጣ 164 ጨዋታዎች ተሸንፏል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ከሚገናኛቸው 3 ብሄራዊ ቡድኖች ጋር የውጤት ታሪኩም ይህን ይመስላል፡፡ ከአይቬሪኮስት ብሄራዊ ቡድን ጋር በ4 ጨዋታዎች ተገናኝቶ 2 እኩል ጊዜ ተሸናንፈዋል፡፡ ከማዳጋስካር 3 ግዜ ተገናኝቶ 2 ጊዜ ሲያሸንፍ በ1 ተሸንፏል። ከኒጀር ብሄራዊ ቡድን ጋር በተመሳሳይ 3 ጊዜ ተገናኝቶ በ2 ሲያሸንፍ አንዱን ተሸንፏል፡፡ በሌላ በኩል በ22 የዓለም ዋንጫ የምድብ ቅድመ ማጣርያ ከሚገናኛቸው ቡድኖችም ያለው ታሪክ 11v11.com አስቀምጦታል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከጋና ብሄራዊ ቡድን በ4 ጨዋታዎች ተገናኝተው ያሸነፈው አንዴ ሲሆን በ3 ተሸንፏል፡፡ ከደቡብ አፍሪካ ጋር 2 ጊዜ ተገናኝተው አቻ የተለያዩ ሲሆን ከዚምባቡዌ ደግሞ 3 ግዜ ተጋጥመው እኩል አንድ ጊዜ ሲሸናነፉ በ1 ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የ75 ዓመታት ታሪክ በከፍተኛ ግብ አግቢነት ጌታነህ ከበደ በ17 ጎሎች በአንደኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣል፡፡ ሉችያኖ ቫሳሎ በ16 ጎሎች ሁለተኛ ሲሆን፤ መንግስቱ ወርቁ በ13 ጎሎች ሶስተኛ ፤ ሳላዲን ሰኢድ በ9 ጎሎች አራተኛ እንዲሁም ሽመልስ በቀለ፤ ዳዊት ፈቃዱ፤ አስናቀ እና ባየ ሙሉ በ4 ጎሎች 5ኛ ደረጃን ተጋርተዋል፡፡ በሌላ በኩል ለብሄራዊ ቡድኑ በበርካታ ጨዋታዎች በመሰለፍ አንደኛ ደረጃ የያዘው 31 ጨዋታዎችን ያደረገው ሽመልስ በቀለ ነው፡፡ ጌታነህ ከበደ እና አስቻለው ታመነ በ23 ጨዋታዎች፤ ሳላዲን ሰኢድ እና ጋቶች ፓኖም በ19 ጨዋታዎች፤ ኡመድ ኡክሪ እና ስዩም ተስፋዬ በ18 ጨዋታዎች፤ ሉችያኖ ቫሳሎ በ17 ጨዋታዎች፤ ሳላዲን በርጌቾ በ16 ጨዋታዎች፤ አበባው ቡጣቆ መንግስቱ ወርቁ በ15 ጨዋታዎች ለብሄራዊ ቡድኑ በመሰለፍ ተከታታይ ደረጃ ይወስዳሉ፡፡
የመረጃ ምንጮች
/www.fifa.com/fifa -world -ranking/ranking-table/men/CAF
www  .transfermarkt.com
/www.11v11.com/teams/eth iopia/tab/stats/

Read 2107 times Last modified on Sunday, 25 October 2020 15:22