Print this page
Sunday, 25 October 2020 15:27

"የብሔር ክፍፍልን ለማከም ህገ መንግስትን መሰረት ያደረጉ ፌዴራላዊ አማራጮች"

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(1 Vote)

 የኢትዮጵያ ምሁራን “የጋን መብራት ናቸው” እየተባሉ ይታማሉ፡፡ በኔ እምነት፤ ይህ “ሀሜት”፣ ሀሜት ብቻ አይደለም፡፡ እውነትነትም አለው። “ያ ባይሆን ኖሮ ዛሬ የሀገሪቱ መመሰቃቀል መልክ ይይዝ ነበር” የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን ማህፀነ-ለምለም ናት፡፡ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር በመሆኑ “ዳተኛ ምሁራን” የመኖራቸውን ያህል፣ ድምጻቸውን አጥፍተው፣ ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ይበጃል ያሉትን ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ ትጉሃንም አሉን፡፡
በዚህ ረገድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ አደባባይ ብቅ ማለት ከጀመሩ ምሁራን አንዱ ዶ/ር ሰሚር ዩሱፍ ነው፡፡ ዶ/ር ሰሚር የፖለቲካ ሣይንስ ምሁር ነው፡፡ ብዙዎቻችሁ ታውቁት ይሆናል። ካልሆነም አሁን እወቁት፡፡ የዶ/ር ሰሚር ዩሱፍን ያህል የኢትዮጵያን ወቅታዊ ፖለቲካ (Contemporary Politics) ጥሩ አድርጎ የተነተነ ምሁር እስካሁን አላጋጠመኝም፡፡ (ሌላ ተንታኝ የለም ማለት ግን አይደለም)
ዶ/ር ሰሚር በሀገሩ ጉዳይ የማይተኛ መሆኑን ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በተከታታይ የሚያቀርባቸው ወቅታዊ የፖለቲካ ጥናታዊ ጽሑፎች ህያው ምስክር ናቸው፡፡ ባለፈው መስከረም ወርም “Constitutional Design Options for Ethiopia: Managing Ethnic Divisions” (ህገ መንግስታዊ የመፍትሄ አማራጮች ለኢትዮጵያ፤ የጎሣ መከፋፈልን ለማከም) በሚል ርእስ ሰፋ ያለ ትንተና አቅርቧል፡፡ ይህንን ጽሁፍ ሳነብ እጅግ ተማረክሁ፡፡ ብዙዎች ቢያነቡት ይጠቅማል የሚል ሃሳብም በልቤ አደረ። እናም አንኳር አንኳር ሃሳቦቹን በማንሳት ለጋዜጣ በሚመች መልኩ ለማቅረብ ይህቺን ማስታወሻ አዘጋጀሁ፡፡
በዚህ ወቅት የሀገሪቱ የመንግስት አደረጃጀትን በተመለከተ ከፌዴራላዊ አወቃቀር ውጪ የማይታሰብ ቢሆንም፤ “ፌዴሬሽኑ ምን ይምሰል?” የሚለው ጥያቄ ግን ጉልህ የመወያያ አጀንዳ ነው፡፡ ብዙዎች ጊዜያቸውን የሚያባክኑበት ጉዳይም ሆኗል። ሁሉን የሚያስማማ መፍትሄ ግን ሊገኝ አልቻለም። የፖለቲካ ኃይሎች የየራሳቸውን አማራጭ ባገኙት መድረክ ላይ ከማቅረብ ውጪ የጋራ መድረክ ፈጥረው ወደ ስምምነት የሚያመራ ድርድርና ውይይት ሲያደርጉ አልታየም፡፡
አሁን በሀገራችን ያለው ብሔረሰብን/ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌዴራላዊ አወቃቀር፤ “የሀገሪቱን ችግር ይፈታል፣ መፍትሄ ይሆናል” ተብሎ የዛሬ 30 ዓመት በነበሩ ፖለቲከኞች የተወሰነ ነበር። መፍትሄ ሊሆን አለመቻሉን ግን የእስካሁኑ ሂደት አሳይቶናል፡፡ መፍትሄ ሊሆን ያልቻለው ችግሩ ሀገሪቱ “ፌዴራላዊ አወቃቀርን” በመከተሏ አይደለም፡፡ ችግሩ ፌዴራላዊ አወቃቀሩ “ቋንቋን ብቻ” መሰረት ያደረገ መሆኑ ነው በሚለው ሃሳብ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡
የንጽጽር ፖለቲካን (comparative politics) የሚያጠኑ ምሁራንና ህገ መንግስቶችን በንጽጽር የሚያጠኑ የህግ ሊቃውንት፣ ልዩነታቸው የበዛ ማህበረሰቦችንና “የብሄር ጥያቄዎችን” ለመፍታት የሚያስችሉ፣ የተለያዩ አማራጮችን ያቀርባሉ፡፡ እነዚህንም አማራጮች በሁለት ከፍለው “ኅብራዊ ወይም የመቻቻልን መንገድ የመረጡ አማካዮች (consociationalism and centripetalism - grouped as accommodationist designs) እና ሪፑብሊካን ወይም ሊበራል የአንድነት ኃይሎች፣ (republicanism and liberal integrationism, grouped as integrationist mechanisms)” በማለት ይከፍሏቸዋል፡፡
ዶ/ር ሰሚር ሁለቱም አማራጮች ጠንካራና ደካማ ጎን እንዳላቸው ይጠቅስና እነዚህ አማራጮች በየራሳቸው መፍትሄ ሊያመጡ እንደማይችሉ ያብራራል፡፡ መፍትሄው መገንጠልን በሚያቀነቅኑና አንድነትን አክርረው በሚዘምሩ መካከል፤ ለሁለቱ ፍላጎቶች መልስ ለመስጠት የሚችል ህገ መንግስትን መሰረት ያደረገ “አማራጭ - ዲዛይን” መሆኑን በማስገንዘብ ስድስት ያህል አማራጭ ሞዴሎችን በመፍትሄነት አቅርቧል ሰሚር፡፡
በአሁኑ ወቅት “የአንድነት ኃይሎች” ተብለው የተፈረጁና ራሳቸውን “ፌዴራሊስት” ብለው የሰየሙ ኃይሎች የርዕዮተ-ዓለም ፍጥጫ ላይ ይታያሉ። እናም እነዚህ የተፋጠጡ ኃይሎች፣ ከሚያቀርቧቸው ሁለት አማራጮች ባሻገር ተጨማሪ ሦስተኛ፣ አራተኛ፣… አማራጮች ለውይይት መቅረባቸው አስፈላጊ ነው። ዶ/ር ሰሚር አማራጮችን አንድ፣ ሁለት፣… ብሎ ከማቅረቡ በፊት የብሄር/ጎሳ ልዩነቶች የሚተነተኑበትን ንድፈ ሃሳባዊ ማእቀፎችና ሞዴሎችን በማቅረብ ጠንካራና ደካማ ጎናቸውን ተንትኗል፡፡ በመጨረሻም ለብሄር/ጎሳ ችግሮች እልባት የሚያስገኙ ህገ መንግስትን መሰረት ያደረጉ አማራጮችን አቅርቧል፡፡
“እኔ ከምከተለውና ከማምንበት አማራጭ መፍትሄ ውጪ ያሉ ነገሮች ሁሉ አማራጭ ተደርገው ሊወሰዱ አይገባም” ብሎ ግግም ማለት የሀገራችን ፖለቲከኞች የተለመደ፣ የገነገነ፣ ባልቴት አስተሳሰብ ነው። የዶ/ር ሰሚር ጽሁፍ የሚመክረን፤ ከዚህ ዓይነቱ አንድ ቦታ ላይ መቸከል በመነቃነቅ፣ ለዘመናችን የሚመጥን የፖለቲካ ጨዋታ እንድንጫወት ነው፡፡
የሀገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች አንድና ብቸኛ፣ ህገ መንግስትን መሰረት ያደረገ፣ ቁርጥ ያለ መልስ መስጠት አስቸጋሪ ነው፡፡ የአንድነት ኃይሎች በሚፈልጉት መልኩ ብቻ ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ ኅብረ-ብሄራዊ ፌዴራሊስቶችን አያስማማም። ኅብረ-ብሄራዊ ፌዴራሊስቶች በሚፈልጉት መልኩ ብቻ ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ የአንድነት ኃይሎችን ያስቆጣል። እናም ከተለያዩ አማራጮች ላይ የተለያዩ ሃሳቦችን በመውሰድ የተቀየጠ ድብልቅ ህገ-መንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ ነው መፍትሄው፡፡ በዚህም መሰረት ዶ/ር ሰሚር 6 አማራጭ ሞዴሎችን አቅርቧል። (ዝርዝሩን https://issafrica.org/research/monographs/constitutional-design-options-for-ethiopia-managing-ethnic-divisions በሚል ሊንክ ኢንተርኔት ላይ እንድታነቡ እየጋበዝኩ፣ ዶ/ር ሰሚር በጽሁፉ ሦስተኛ ምዕራፍ ላይ ያቀረባቸውን ሞዴሎች በራሴ ቋንቋ አሳጥሬ ላቅርባቸው)
ሞዴል አንድ፡- ድምፅ ማሰባሰብን መሰረት ያደረገ፣ ሊበራል የስልጣን ክፍፍል እና ሁሉን አቃፊ ኅብረ-ብሄራዊ ፌዴራሊዝም (Liberal Power Sharing with Vote Pooling and Inclusive Multinational Federalism)
ይህ ሞዴል፤ በፌዴራል አስፈጻሚ ደረጃ የተጠቃለለ ስልጣን እንዲኖርና በምርጫው ሂደት ድምፅ ማሰባሰብን ይፈቅዳል፡፡ በዚህ ሞዴል የስልጣን ክፍፍል የሚደረገው በብሄር ኮታ አስቀድሞ የሚወሰን ሳይሆን አንድ ፓርቲ ባለው ድጋፍ የሚወሰን ይሆናል፡፡ ይህም ለኅብረ-ብሄራዊ ፓርቲዎች ሰፊ እድል የሚሰጥ ይሆናል፡፡ በማእከል ደረጃ የስልጣን ክፍፍል የሚደረገው ፓርቲዎች ባላቸው መቀመጫ ብዛት ቅደም ተከተልና በተመጣጣኝ ውክልና ድንጋጌ (sequential and proportional allocation rules) መሰረት ነው፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሰረት ፓርቲዎች በህግ አውጪው ፓርላማ ባላቸው መቀመጫ መሰረት፣ በስራ አስፈጻሚው ውስጥ የሚኒስትርነት ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ ብዙ መቀመጫ ያለው ፓርቲ ብዙ የሚኒስትር ስልጣኖችን ያገኛል። ሁሉም ነገር የሚከናወነው ፓርቲዎች በሚያደርጉት ድርድርና ስምምነት ይሆናል፡፡ በክልል ደረጃ የሥራ አስፈጻሚ ኃላፊነቶች በተመሳሳይ ሁኔታ የሚፈጸም ሆኖ አናሳ የህዝብ ቁጥር ላላቸው ማህበረሰቦች መነሻ የሚሆን የመቀመጫ ቁጥርን በማስቀመጥ (fixed proportional number of seats) ሁሉን አቃፊ አሰራርን መከተል ይቻላል፡፡ ከክልል በታች ባሉ መንግስታዊ መዋቅሮች ኅዳጣን (አናሳ የህዝብ ቁጥር ያላቸው) ማህበረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበትን መንገድም ታሳቢ ማድረግ ይቻላል፤ ይላል ሰሚር፡፡
ሞዴል ሁለት፡- ነጠላ ተሻጋሪ ድምፅ ከሁሉን አቃፊ ኅብረ-ብሄራዊ ፌዴራሊዝም ጋር (Single Transferable Vote with Inclusive Multinational Federalism)
በዚህ ሞዴል በፌዴራል መንግስት ውስጥ አስቀድሞ የታወቀ መደበኛ የስልጣን መጋራት አይኖርም፡፡ በፓርላማው አብላጫ ድምፅ መሠረት መንግሥት ይቋቋማል። ሆኖም በምርጫ ሥርዓቱ አማካይነት የተመጣጠነ ውክልና ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህ የምርጫ ስርዓት ተግባራዊ የሚደረገው መደበኛ ሊተላለፍ የሚችል ድምጽ አሰጣጥና ተመጣጣኝ የውክልና ዘዴን (standard transferable vote + proportional representation) አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ ይህም ማለት፡- አንድ መራጭ ከቀረቡት እጩ ተወዳዳሪዎች ውስጥ የሚፈልጋቸውን በቅደም ተከተል ይመርጣል፡፡ የሚያሸንፈው ከፍተኛ ድምፅ ያገኘው ብቻ ሳይሆን ከየወረዳው የተሰበሰቡ አነስተኛ ድምፆችም ይደመሩና ወደ መቀመጫ እንዲለወጡ ይደረጋል ማለት ነው፡፡
በእንዲህ ያለው የምርጫ ስርዓት ለአሸናፊነት የሚያበቃው አብላጫ ድምጽ ማግኘት ብቻ ሳይሆን፤ በሕግ አውጭው አካል ውስጥ ለፓርቲዎች ህዝብ የሚሰጣቸውን ድምፅ መሰረት ያደረገ አነስተኛ የማለፊያ የድምፅ ቁጥር (passing threshold) ማካተትን ይጨምራል። በዚህ ጊዜ የብሄር ፓርቲዎቹ በሕግ አውጭው ውስጥ መንግስት የመመስረት እድል ለማግኘት ከራሳቸው ብሄረሰብ በሚያገኙት የድምፅ ብዛት ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም ብሄረሰቦች ጭምር ድምጽ ማግኘት ግድ ይሆናል ማለት ነው፡፡
በሀገሪቱ ውስጥ የትኛውም ብሔረሰብ/ጎሳ አብላጫ ድምጽ (Majority Vote) የሚኖረው ባለመሆኑ መንግሥት ለማቋቋም በተወሰነ ደረጃ ከሌሎች ብሔረሰቦች ድምፅ ማሰባሰብ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ፓርቲዎች ከምርጫ በፊት ተጣምረው በጋራ መስራት ካልቻሉ ከምርጫ በኋላ መንግስት ለመመስረት መቀናጀት ግድ ይሆናል፡፡ ጥምር መንግስት የሚመሰረተው በርካታ መቀመጫ ባገኘው ፓርቲ እና አብሮ ሊሰራ በፈለገው ፓርቲ መካከል በሚደረግ ድርድር ይሆናል፡፡
ሞዴል ሦስት፡- ድምፅን ማሰባሰብ ከአቃፊ ኅብረ-ብሄራዊ ፌዴራሊዝም ጋር (Vote Pooling with Inclusive Multinational Federalism)
ይህ ሞዴል ከተሻጋሪ ድምጽ ይልቅ በድምፅ ማሰባሰብ ላይ ያተኩራል፡፡ ሞዴል አንድ ኅብረ-ብሄር ገጽታዎች ያሉት ሲሆን ይሄኛው ሞዴል ግን አማካይ መሆን ላይ ያተኩራል፡፡ ሁለቱም ሞዴሎች በተመሳሳይ ሁኔታ የክልል አስተዳደራዊ ቀመርን፣ ብሄር ተኮር ተመጣጣኝ ውክልናን፣ በጎሳ መስመር የተቀረጹ የአስተዳደር አካባቢዎችን እና የተበታተኑ ወይም ትናንሽ የራስ ገዝ አስተዳደሮችን በመከተል የሚፈጸም በመሆኑ ድምፅ ማሰባሰቡ የአቃፊነትንና የአቻቻይነትን ሚዛን ይጠብቃል ተብሎ ይታሰባል፡፡
የአማራጭ ድምፅ (alternative vote) የምርጫ ስርዓት ወይም መራጮችን የማሰባሰብ አካሄድ፤ በጎሳ መስመር በተቀረጹ አካባቢዎች ብሔር ዘለል ድምጽ ማሰባሰብን የሚያበረታታ ነው፡፡ የዚህ ሞዴል አንዱ ጠቀሜታ ከድምፅ ማሰባሰብ ጋር የተቆራኘ መሆኑ ነው፡፡ ማእከላዊነት ላይ ያተኮረ የምርጫ ሥርዓት ድምጽን የማሰባሰብን አካሄድ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያደርሳል፡፡
ይህ ሞዴል የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖችን በአስፈፃሚ አካላት ውስጥ በቀጥታ እንዲገቡ ከማድረግ ይልቅ የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል አጀንዳዎች ያላቸው ፓርቲዎች የተለያዩ ብሄረሰቦችን ድጋፍ ሊያገኙ የሚችሉበትን ስርዓት እንዲፈጥሩ የሚያደርግ ነው። አንዳንድ ተደማጭነት ያላቸውን እና ተቃራኒ ቡድኖችን አንድ ላይ ላያሰባስብም ይችላል። ድምፃቸው በአስፈፃሚው አካል ውስጥ ያልተካተቱ ወገኖች ስርዓቱን የተረጋጋ ለማድረግ ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል። እነዚህ ኃይሎች በዚህ ሞዴል እምነት እንዲያድርባቸው የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ሊኖራቸው ይችላል፡፡
ሞዴል አራት፡- ጥምር የስልጣን ክፍፍል ከተመጣጣኝ ውክልናና ከብሔራዊ ፌዴራሊዝም ጋር (Corporate Power Sharing with PR and National Federalism)
ይህ ሞዴል በአስፈጻሚው ውስጥ የብሔረሰብ ኮታዎች እና ሊበራል ኅብራዊነት ተጣምረው ተግባራዊ እንዲደረጉ ያደርጋል። ፓርቲዎች በብሄር ላይ የተመሰረቱ ወይም ኅብረ ብሄራዊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እናም በመቀመጫ ብዛት ቅደም ተከተልና በተመጣጣኝ ውክልና (sequential and proportional allocation) መሰረት በሕግ አውጪው ውስጥ ባላቸው ድርሻ መሠረት በማዕከላዊ መንግስት ስራ አስፈጻሚ ይወከላሉ፡፡ በሕግ አውጭው አካል ውስጥ ፍትሃዊ ውክልና እንዲኖር ለማድረግ ይቻል ዘንድ የምርጫ ስርዓቱ ተመጣጣኝ ውክልና ይሆናል፡፡
በዚህ አማራጭ ዲዛይን ውስጥ ልዩ የሆነው ነገር ማንኛውም ፓርቲ ምንም ያህል የካቢኔ መቀመጫዎች ይኑሩት ለእያንዳንዱ ብሄር በተቀመጠው ኮታ መሠረት “ትክክለኛውን” የብሄረሰብ ተወካይ ያስቀምጣል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይህንን ሳያሟሉ የፈለጉትን ሰው ማስቀመጥ ሹመቱን ውድቅ ያደርገዋል፡፡
በፌዴራል ደረጃ የሚደረግ እንዲህ ያለው ግልጽ የሆነ ብሄረሰብን መሰረት ያደረገ የሥልጣን ክፍፍል እና ተመጣጣኝ ውክልና በክልል ደረጃ ያለውን ውክልና በተመሳሳይ መልኩ ለማመጣጠን ይረዳል። በዚህም መሠረት ፌዴራላዊ አደረጃጀቶች ብሄረሰቦችን ወደ ብዙ አካባቢያዊ አስተዳደሮች እንዲከፋፈሉ እና የጎሳ ብሄርኛነትን ጥያቄ ከስር መሰረቱ ለመፍታት እንዲሰሩ ያደርጋል፡፡
አዲስ የሚቋቋሙ የፌዴራል ክልሎች የሥራ ቋንቋዎቻቸውን፣ የክልል ምልክቶቻቸውን፣ ሕገ-መንግሥቶቻቸውን ወዘተ. ከሀገራዊ ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ይወስናሉ። በእያንዳንዱ ክልል ውስጥ ከድንበር ጋር የማይያያዝ ለብሄረሰቦች ባህላዊ የራስ ገዝ አስተዳደር በሕገ-መንግስቱ እውቅና እንዲሰጠው ይደረጋል፡፡ በአንድ ክልል ውስጥ ያሉ ኅዳጣን ማህበረሰቦች ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቶች እንዲኖራቸው ማድረግም አስፈላጊ ይሆናል፡፡
ሞዴል አምስት፡- ፕሬዝዳንታዊነት በድንጋጌዎች ስርጭትና በድምፅ ማሰባሰብ ከአቃፊ ኅብረ-ብሄራዊ ፌዴራሊዝም ጋር (Presidentialism with Distribution Rules and Vote Pooling, with Inclusive Multinational Federalism)
ቀደም ሲል በቀረቡት አማራጭ ሞዴሎች ታሳቢ የተደረገው የፓርላሜንታዊ የመንግሥት ቅርጽ ነው፡፡ በዚህ ሞዴል ልዩ ሆኖ የቀረበው ነገር የመንግስት አወቃቀር ፕሬዚዳንታዊ ይሆናል የሚለው ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ የሚመረጡት በቀጥታ በመራጩ ህዝብ ይሆናል፡፡
በዚህ ሞዴል በወሳኝነት መታየት የሚገባው ነገር ፕሬዝዳንቱ የሚመረጡት በአብላጫ ድምፅ (50+1) ቢሆንም ከዚህ ድምፅ ውስጥ የተወሰነው (በመቶኛ ተሰልቶ) በልዩ ሁኔታ ከተወሰኑ ክልሎች እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል። ይህ የሚደረግበት ምክንያት ፕሬዚዳንታዊ እጩው የሁሉንም ብሔረሰቦች አጀንዳዎች ይዞ ለውድድር እንዲቀርብ ለማስገደድ ነው። የሕግ አውጭውን አካል በአማራጭ ድምፅ፣ ድምፅን በማሰባሰብ ወይም በአብላጫ ድምጽ እንዲመረጥ ማድረግ ይቻላል፡፡
አሁን ያለው ክልላዊ አስተዳደር ባለበት የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ኅብረ-ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ በተመጣጣኝ ውክልና እና በእያንዳንዱ ክልል ለሚገኙ አናሳዎች ድንበር የተበጀለት ወይም ድንበር - የለሽ የራስ ገዝ አስተዳደር እንዲኖር ይደረጋል። ፕሬዚዳታንዊው እና ማዕከላዊ የምርጫ ዲዛይኖች ክልላዊ አስተዳደርን ሚዛናዊ ማድረግ ይችላሉ፡፡
ብዝሃነት ባለበት ማህበረሰብ ፕሬዝዳታዊ ስርዓት የሚያስገኘው ዋነኛ ጥቅም የፖለቲካ መረጋጋትና ጠንካራ አንድነት መፍጠሩ ነው። ኢትዮጵያ በፕሬዚዳንት ብትመራ የመገለል ስሜት ይፈጠራል የሚል ስጋት ሊኖር አይችልም፤ ምክንያቱም አካባቢን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት አይነካም። እናም ይህ ሞዴል እንደ ሰላም ሰጭ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
ሞዴል ስድስት፡- ኅብራዊነት ወደ ቋሚ ስርዓት ለመሸጋገር (Consociationalism as a Prelude to a Permanent System)
ከላይ የተጠቀሱት አማራጮች ስራ ላይ ሊውሉ የሚችሉት በአገሪቱ ውስጥ ባሉ ሁሉም ዋና የፖለቲካ ኃይሎች መካከል መግባባት ላይ ከተደረሰ ብቻ ነው፡፡ በፖለቲካ ኃይሎች መካከል መግባባት ካልተቻለ፤ አብሮ መስራትና መተማመን እስኪፈጠር ድረስ ለተወሰኑ ዓመታት የሽግግር ጊዜ በማካሄድ አብሮ መስራትን መለማድና ከላይ የተዘረዘሩትን አማራጭ ሞዴሎች ስራ ላይ ማዋል ይቻላል። በዚህ “የሽግግር ጊዜ” ደግሞ የተለያዩ አማራጮችን ስራ ላይ ማዋል ይቻላል፡፡ ሊበራል ኅብራዊነትን ስራ ላይ በማዋል ብዙ መቀመጫ ያገኙ የፖለቲካ ኃይሎች ጥምረት፣ በአነስተኛ የመነሻ ወለል የተመሰረተ ተመጣጣኝ ውክልናና ለተወሰኑ አካባቢዎች የራስ ገዝ አካባቢዎችን አሁን ባሉበት ሁኔታ በማቆየት የሽግግርና የመተማመን ጊዜ መፍጠር ይቻላል፡፡
ፓርቲዎች ለአምስት ወይም ከዚያ በላይ ዓመታት በጋራ አስተዳደር አብሮ መስራትን ከተለማመዱ በኋላ ወደ ቋሚ የአስተዳደር ስርዓት መሸጋገር ይቻላል፡፡ በዚህም ሂደት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተስማሙበትን ሞዴል ከሽግግሩ በኋላ ስራ ላይ ማዋል ይቻላል። በጊዜያዊነት ሥልጣንን በመጋራት አብሮ መስራት የሚያስገኘው ጥቅም የፖለቲካ ኃይሎች አንዳቸው የሌላውን ዓላማ፣ መርሐ-ግብር እና ባህሪ ጠንቅቀው እንዲያውቁ እና በሂደቱ ውስጥ ግንኙነቶችን እና የጋራ ሀሳቦችን እንዲያሻሽሉ የሚረዳ እድል መፍጠሩ ነው፡፡ እንዲህ ያለው በስምምነት የሚፈጠር ሕገ-መንግስታዊ የሽግግር ጊዜ መፈጠሩ በፓርቲዎች መካከል ያለውን የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዳይወሳሰብና መደነጋገር እንዳይኖር ያደርጋል፡፡
ማጠቃለያ
የተለያዩ አማካይ የሆኑና አንድነትን የሚያጠናክሩ ዘዴዎችን አጣምሮ የያዘ፣ ብዙም ውዝግብ የማይነሳበት፣ ሕገ-መንግስትን መሰረት ያደረገ አማራጭ ለወደፊቷ ኢትዮጵያ አስፈላጊ መሆኑን ዶ/ር ሰሚር ባቀረበው ጥናት አመላክቷል። ከላይ በተዘረዘሩት አማራጮችም ይሁን ወይም በሌሎች አማራጮች ለሁለት ነገሮች ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ዶ/ር ሰሚር ያስገነዝባል፡፡ እነዚህም ሁለት ነገሮች፡- የግለሰብን መብት ማስጠበቅ እና ብሄራዊ አንድነትን ማጎልበት ናቸው፡፡
በፌዴራል ስርዓት የሚኖር ስልጣንን የማማከል አሰራር ጥንቃቄን እንደሚጠይቅ ዶ/ር ሰሚር ያስገነዝባል፡፡ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ የተማከለ አስተዳደር አንድነትን ያጠናክራል። በከፍተኛ ሁኔታ የተከፋፈሉ ግዛቶች ባሉበት ሀገር ጠንካራ የሆነ ማዕከላዊነትን መከተል ወደ ጥልቅ ማህበራዊ ክፍፍል ሊያመራ ይችላል። ኢትዮጵያ አንፃራዊ የተማከለ ፌዴራላዊ ስርዓትን ከግምት ውስጥ ማስገባት አለባት፡፡ ይህም ማእከላዊነት ከሀገራዊ አንድነት እና ራስን በራስ ከማስተዳደር መብት ጋር የማይጋጭ መሆን አለበት፡፡ በፌዴራል የቋንቋ ፖሊሲ ዙሪያ የሚደረግ ውይይትም ሁሉንም ያቀፈ ጠንካራ ሀገርና አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመፍጠርን አስፈላጊነት ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት ይላል ሰሚር፡፡
አከራካሪ የብሔርተኝነት እንቅስዋሴዎች የኢትዮጵያ የፖለቲካ ውቅር ዘላቂ ገጽታ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ እነዚህ የብሔርተኝነት መንፈሶች በዛ ያሉ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ የፖሊሲ ሃሳቦችን አፍልቀዋል፡፡ እናም በዚህ ወቅት የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ በዓለም ዙሪያ በሌሎች ሀገራት ተግባራዊ የተደረጉ የተለያዩ ተቋማዊ አሠራሮችን በጥንቃቄ ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ስለሆነም የፖለቲካ ልሂቃንና የአካዳሚክ ምሑራን ዋና ተግባር ምርጥ ተሞክሮዎችን ከሌሎች ትምህርት በመውሰድ በአገሪቱ ውስጥ ካሉ ልዩ የፖለቲካ ሁኔታዎች ጋር በማስማማት ማላመድ ነው። ከስኬቶቻቸው እና ከውድቀቶቻቸው ብዙ መማር ይቻላልና!
በመጨረሻም አንድ ነገር ልበል። የሰሚር የምርምር ሰነድ አማራጮችን ብቻ አይደለም ያቀረበልን፡፡ እውቀትንና መረጃን መሰረት ያደረገ፣ ንድፈ-ሃሳባዊ ማእቀፍን የተንተራሰ፣… ምሁራዊ ውይይት ማድረግ ወደ መፍትሄ ሊመራ የሚችል አካሄድ መሆኑን ያመላከተ አዲስ መስመር ነው፡፡ የሰሚር ጽሑፍ በሁለተኛ ደረጃ የሚያስገነዝበን ነገር ህገ መንግስትን በማሻሻል ሂደት ሊታዩ የሚገባቸውን ግብዓቶችና የማግባቢያ ሃሳቦች መሆኑንም ማስተዋል ይቻላል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የተለያዩ ልቦለዳዊ ትርክቶችን መሰረት ያደረጉ፣ ታሪክ ላይ የተቸከሉ ልዩነቶችን ለማጥበብ የሚረዱ አቅጣጫዎችን ያመላክታል፡፡ እኛም እንያቸው - በርካታ የዓለም ህዝቦች ችግሮቻቸውን የፈቱት በነዚሁ መንገዶች ነውና!
ከዚህ በፊት እንዳልኩት የፖለቲካ ጥያቄ መልስ ሊያገኝ የሚገባው በፖለቲካ ሂደት በሚፈጠር የፖለቲካ ውይይትና ድርድር ነው እንጂ በኩርፊያና ማዶ ለማዶ ሆኖ ደረቅ ቃላት በመወራወር አይደለም፡፡ ድርቅናና እልህም የፖለቲካ መንገዶች አይደሉም፡፡ ይህንን ሀቅ አምኖ መቀበል ግድ ነው፡፡
ጸሐፊውን በEmail: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1630 times