Sunday, 25 October 2020 15:30

ከህወሓት የሚጠበቅ የጀግንነት ሥራ?!

Written by  ማርቆስ ረታ
Rate this item
(0 votes)

 "ዛሬ እንኳን የኛ ለምትሉት ሕዝብ እዘኑለት!"
                    
         ማጠቃለያ
ሕወሓት የፌዴራሉ መንግሥት ሕጋዊነት አብቅቷል ለማለትም ሆነ ራሱን ብቸኛ ሕጋዊ መንግሥት ያቋቋመ ድርጅት አድርጎ ለመመልከት ብቸኛ መለኪያ አድርጎ የወሰደው የራሱን ምርጫ ማድረግና የፌዴራሉን አለማድረግ ነው ብለናል። ሕወሓት ምርጫ በማድረጉ አከበርኳቸው፥ የፌዴራሉ መንግሥት ደግሞ ምርጫ ባለማድረጉ ጣሳቸው የሚላቸው አንቀጾች [54/1 እና 58/2] ናቸው። ሁለቱም አንቀጾች ምርጫ በየአምስት አመቱ እንደሚካሄድ የሚደነግጉ መሆናቸውን ተመልክተናል። ሆኖም ድንጋጌዎቹ ቢኖሩም በአገራችን በነበረው ተጨባጭ ሁኔታ፣ የምርጫ የማድረግና ያለማደረግ ጉዳይ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ቁልፍ ሚና የነበራቸው የኮቪድ ስጋት፥ ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፥ የምርጫ ቦርድ ውሳኔና የሁለቱም ምክር ቤቶች ውሳኔዎች ናቸው። ሕወሓት ግን እነዚያን ውሳኔዎች በመጻረር፣ ምርጫ የማድረጉን ተገቢነት ለማስረዳት “ምርጫ በየአምስት ዓመቱ ይደረጋል” የሚለውን ድንጋጌ ብቻ ይዞ ቢከራከር አያስኬደውም። ሕወሓት በተለይ ለምርጫ ቦርድ ውሳኔ ዋነኛ ምክንያት የሆነው ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ባለመገንዘቡ፣ “ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መብቶችን ሊገድብ ቢችልም፣ የመንግሥትን የስልጣን ዘመን አያራዝምም” የሚል ሕጋዊ መሠረት የሌለውን “የባለሙያዎች” ምክር በማዳመጡ ስህተት ውስጥ ወድቋል።
ከላይ በቀረቡት ነጥቦች መሠረት፣ መግቢያው ላይ የተነሱትን ሁለቱን የሕጋዊነት ጥያቄዎች ለመመለስ፤ ሕወሓት ያደረገው ምርጫ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 መሠረት ያልተደረገ በመሆኑ ሕገ ወጥ ነው።
የሕወሓት አመራር የፌዴራሉ መንግሥት ምርጫ ባለማድረጉ ምክንያት ከመስከረም 25/30 በኋላ ሕጋዊነቱ አብቅቷል ለማለት ሕጋዊ መሠረት የለም።     
ቀጣይ እርምጃዎች
የሕጉ ነገር እንዲህ ከሆነ የቀረን ጥያቄ፤ ፍጥጫውን እንዴት እናርግበው? የሚለው ነው።
የሕወሓት እርምጃዎች የሕግ ድጋፍ እንደሌላቸው ስንገነዘብ፣ የሕወሓት አመራር ሌላውን መክሰስ ትቶ፣ የገዛ ጥፋቱን አምኖ አካሄዱን ለማስተካከል ካልወሰነ በቀር፣ የተካረረው ፍጥጫ የሚረግብበትን መንገድ ለመጠቆም እጅግ ያስቸግራል። የፌዴራሉ መንግሥት፣ ሕገ ወጡን ምርጫ አይቶ እንዳላየ በማለፍ ያሳየው ትእግስት የሚመሰገን ነው። እንደ ፌዴራሉ መንግሥት ሁሉ፣ ሕወሓትም ነገሮችን ከእልህ በጸዳ የይቅርታ መንፈስ በመመልከት፣ ፍጥጫውን ለማርገብ መወሰን አለበት። በዚህ መንፈስ ሁለቱም ወገኖች የሚከተሉትን እርምጃዎች መውሰድ ይችላሉ፦   
የሕወሓት አመራር የፌዴራል መንግሥት ሕጋዊነቱን አጥቷል የሚለውን ሕጋዊ መሠረት የሌለውን አቋሙን ያርም፤ ስሕተቱን ተቀብሎ ለፌዴራሉ መንግሥት ተገቢውን እውቅና እንደሚሰጥ በይፋ ያስታውቅ፤
ራሱ ያደረገውን ምርጫ እንዳልተደረገ በመቁጠር፣ ከሕገ ወጡ ምርጫ በፊት ለነበረው የክልል መንግሥት እውቅና እንዲሰጠው የፌዴራሉን መንግሥት ይጠይቅ፤
የፌዴራል መንግሥትም አስቀድሞ በሰጠው ውሳኔ (ቃል)መሠረት፤ በትግራይ ተካሄደ የተባለውን ምርጫ እንዳልተደረገ በመቁጠር፣ ሕወሓትም እንደ ሌሎች ፓርቲዎች ሁሉ በቀጣዩ ምርጫ እንዲሳተፍ ይፍቀድለት፤
ከሕወሓት አመራር የሚቀርብለትን ጥያቄ ተቀብሎ ከምርጫ በፊት ለነበረው ምክር ቤት ተገቢውን እውቅና ይስጥ።
እውነት ለመናገር ከላይ የቀረበውን መተግበር ማንንም አይጎዳም፤ አገርን ግን ይጠቅማል፤ ሁሉም እፎይ ይላል። ሕጋዊ መሠረት የሌለው ሥራ አንዴ ከተሠራ በኋላ ስህተትን ተቀብሎ፥ አርሞና ተራርሞ ከመሄድ የተሻለ ብዙ አማራጭ ባይኖርም፣ የተለያዩ ሰላማዊ የመፍትሔ አማራጮችን ለማፍለቅ የሚችሉ አስተዋይ ሽማግሌዎች አይጠፉ ይሆናል። ከሆነ መልካም።
በአንጻሩ ሕጋዊ መሠረት በሌለው ፍጥጫ እንግፋበት ቢባል፣ መጨረሻው ምን ይሆናል? ሕወሓት በጀመረው መንገድ ልሂድ ቢል መዳረሻው የት ይሆናል? ፍጥጫውን እንደ ትግል ብንቆጥረው ድሉ ምን ይሆናል? ፌዴራል መንግሥት ሕግና ሥርዓት የማስከበር ግዴታ ያለበት መሆኑ ይታወቃል። ስለዚህ ለፌዴራል መንግሥት ድል ማለት በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሕግና ሥርዓት መስፈኑን ማረጋገጥ መሆኑ አይቀርም፤ ይኸውም የውዴታ ግዴታው ነው። በበኩሉ፤ ሕወሓት ሕገወጥ እርምጃዎቹን እንደ ትግል የሚመለከት ቢሆን፣ ድል አደረግኩ የሚለው ምን ሲሆን ነው? የሕወሓት የድል ትርጓሜ ምንም ይሁን ምን ከሕግ ውጭ ለማሳካት ከመሞከር መቆጠብ ግድ ነው። በተለይ የጦርነትን አማራጭና ብቅ ጥልቅ የሚለውን የዋዛ ዋዛ (de facto)ሀገረ መንግሥትነትን አደገኛ መንገድ መዝጋት አለበት። እንዳስረዳ ይፈቀድልኝ።
ትግራይን እንደ ዋዛ ከኢትዮጵያ መለየት አይቻልም።  
ከሕወሓት አመራር መካከል የትግራይ ሕዝብ፣ ከገዛ አገሩና ከወገኑ መለየት አለበት የሚል እምነት የያዘ ቢኖር፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት መጠየቅ ይችላል። ይህን ለማድረግ ጸብ አያስፈልግም፤ ጦርነት አያስፈልግም። ከሕግ ውጭ ሕዝቡን በውሸት ሰበካ ወደ ግጭት ለማስገባት መሞከር፣ በኢትዮጵያና በትግራይ ላይ የሚፈጸም ወንጀልና ክህደት ነው።
ዲፋክቶ (de facto) የሚባል እንደ ዋዛ፥ ቀስ በቀስ ይፈጠራል ተብሎ የሚታሰብ አገረ መንግስትነት፣ ማዕከላዊ መንግሥቱ በፈረሰበት አገር ውስጥ ተኩኖ ሊታሰብ የሚችል መሆኑ ይታወቃል። የሕወሓት አመራር ስልጣን ከእጁ ከወጣ በኋላ "ኢትዮጵያ ትፈርሳለች፥ መንግሥት አልባ ትሆናለች" የሚል ድምዳሜ ላይ ሳይደርስ አልቀረም። እግዚአብሔር ይመስገን፤ አልፈረሰችም፤ መንግሥት አልባም አልሆነችም። ዛሬም የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አለ። ያለ ሕግ በዋዛ ዋዛ [በተጨባጭ ላለማለት] ወይም ዲፋክቶ (de facto) ሳይሆን በሕግ ወይም ዲጁሬ (de jure) የሚታወቅ መንግሥት ነው። የትግራይ ክልል፤ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሪፑብሊክ አባል መሆኑ በሕግ የታወቀ ነው። መንግሥትና ሕገ መንግሥት ባለበት አገር፤ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ሕጋዊ እውቅና ያለውን የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ወደ ዲፋክቶ መንግሥትነት ለመለወጥ አይቻልም። ስለሆነም በፌዴሬሽኑ ጥላ ሥር ሆኖ፣ ከሌሎች አገሮችና ድርጅቶች ጋር በተናጠል ለመገናኘትና ቀስ በቀስ፥ እያዋዙ ዕውቅና ለማግኘት መሞከር ወንጀል መሆኑ ታውቆ በሩ መዘጋት አለበት።
ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመለየት የሚፈልጉ የሕወሓት አመራር አባላት፣ ፍላጎታቸው ከሕዝቡ ጥቅም ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው አሳምረው ያውቁታል። ዛሬ “ታግለን ነጻ ባወጣን፣ አሃዳዊው ኃይል ሊወጋን ነው” በማለት በፍርሃት የሸበቡት ሕዝብ፤ የግድ እንዲመርጣቸው ማድረግ ቢችሉም፥ ከኢትዮጵያ እንገንጠል ቢሉት እንደማይሰማቸው ያውቁታል። ሕዝቡ ይሰማናል የሚሉ ከሆነ፣ ሕጉን በተከተለ መልኩ፣ ሕዝቡ ምርጫውን እንዲገልጽ ዕድል መስጠት ይቻላል፤ ሳይቸኩሉ፤ ሳያዋክቡት።
የሕወሓት አመራር፤ ነጻ አገር የመመስረት ነሻጣውን ለማሳካት ቢፈልግ፣ ቅድሚያ በቀጣዩ ምርጫ ተወዳድሮ የክልሉን ምክር ቤት በቂ ወንበሮች መያዙን ያረጋግጥ። ከዚያ በኋላ ጥያቄውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቅርብ። የፌዴሬሽን ምከር ቤትም፣ በሦስት ዓመት ውስጥ ሪፈረንደም ያዘጋጅለታል። ከዚያ የሚሆነው ይሆናል።
መቼም ለቸኮለ ሰው ሦስት ዓመት ረዥም ጊዜ ነው። ታዲያ አገር መገንጠልን የሚያክል ትልቅ ነገር ፈልጎም ተቸኩሎም አይሆንም። ከዚያ ውጭ ሕዝቡን በሐሰት ወደ ግጭትና ደም መፋሰስ በማስገባት፣ በከንቱ ከሚፈሰው ደም፣ ለመገንጠል የሚሆን ምክንያት ለማግኘት መሻት፣ ደንታ ቢስነትና የለየለት ፀረ ሕዝብነት ነው።
ክፍል ሁለት
የሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ ፍላጎቶች ተቃርኖ
የሕወሓት አመራር አባል የሆኑት አቶ አስመላሽ፤ ከላይ በጠቀስነው መስከረም አጋማሽ ላይ በተለቀቀው ቪዲዮ፤ የቀድሞ ኦህዴድና ብአዴን አመራር፣ በለውጡ ዋዜማ የፈጠሩትን “ኦሮማራ” ተብሎ ስለሚታወቀው “ጥምረት” ተጠይቀው የተናገሩት፣ ባንድ በኩል በፓርቲ መሪዎችና በሕዝቦች ጥቅም መካከል ያለውን ልዩነት፥ በሌላ በኩል፤ የሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፍላጎት፣ ጥቅምና አንድነትን በሚመለከት ምንም ብዥታ እንደሌለባቸው የሚያረጋግጥ ነው ለማለት ይቻላል። ልጥቀስ፤
“ጥምረቱ፤ የኦሮሞና አማራን ሕዝብ ጥቅም የሚወክል አይደለም። ምክንያቱም የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች ጥቅም፤ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን የተለየ አይደለም። ጥቅማቸው አንድ ነው። ሕዝብና ሕዝብ የሚያጣላ ነገር የለም። ይሄ ጥምረት ግን ልሂቃን ተሰብስበው የፈጠሩት ጥምረት ነው። ጥምረቱ ለመሸዋወድ የተመሠረተ ነው።” ብለዋል።
የአቶ አስመላሽን ትንታኔ ወስደን፣ በሕወሓት አመራርና በትግራይ ሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት እንመለክት።
በመሠረቱ የትግራይ ሕዝብ ችግርም ሆነ ጥቅም ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ የማይለይ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም፣ በአቶ አስመላሽ አንደበት፤ በዚህ ጊዜ መነገሩ ግን በሕወሓትና ኦሮማራ-ነበር-ብልጽግና አመራር መካከል ያለው ጸብና ፍጥጫ፣ የትግራይን ሕዝብ የማይወክል መሆኑን ብቻ ሳይሆን፣ ይህን አሳምረው በሚያውቁት በአቶ አስመላሽና ጓዶቻቸው የተያዘው ጠብ አጫሪ አቋም፣ በስሙ የሚምሉለትን የትግራይን ሕዝብ ጥቅም የሚጎዳ መሆኑን ለመገንዘብ ይረዳናል።
ዘርዘር ለማድረግ ያክል ከአቶ አስመላሽ ትንታኔ የሚከተሉትን እንገነዘባለን፦
1) በሕወሓትና “የኦሮማራ ጥምረት” በመሰረቱት ልሂቃን መካከል የተፈጠረው ጸብ ወይም “መሸዋወድ” በልሂቃን መካከል የተፈጠረ መሆኑን፤ 2)“ኦሮማራ ጥምረት” አይወክላቸውም የሚሏቸው፣ የኦሮሞና አማራ ሕዝቦች ጥቅም፣ ከትግራይ ሕዝብ ጥቅም ጋር አንድ መሆኑን፤ 3) እንደ አማራውና ኦሮሞው ሁሉ የትግራይ ሕዝብ ጥቅም፣ “ከሌሎች ኢትዮጵያውያን የተለየ” አለመሆኑን፤ 4) ሕወሓት ሸወዱኝ ከሚላቸው የቀድሞ ኦሮማራ፥ ያሁኑ ብልጽግና አመራር ጋር ያለው ጸብና ቁጭት፣ የትግራይን ሕዝብ የሚወክል አለመሆኑን በግልጽ እንደሚገነዘቡ፤ 5) የሕወሓት አመራር፣ የትግራይን ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በመጥቀስ ያካሄዱት ሕገወጥ ምርጫም ሆነ በፌዴራል መንግሥት ላይ የሚሰነዝሩት ትንኮሳና በእብሪት የገቡበት አደገኛ ፍጥጫ፣ የትግራይን ሕዝብ እንደማይወክል ከማረጋገጡም ባሻገር አቶ አስመላሽና ጓዶቻቸው የሚያራምዱት ሕገወጥ አካሄድና ጠባጫሪነት፣ ከሕዝቡ ጥቅም ጋር የሚጋጭ፤ የአውቆ አጥፊ ሥራ መሆኑን ያስረዳል።
ሕወሓት፤ ከትግራይ ልጆች ጉዳት ሲያተርፍ የኖረ ድርጅት ስለመሆኑ፤
የሕወሓት አመራር፤ የክልሉ ሕዝብ በሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ እንደሚጠላ፥ እንደሚገለልና እንደሚፈናቀል፥ በሌሎች ኢትዮጵያውያን ዘንድ በጥርጣሬ ዓይን እንደሚታይ በመግለጽ፥ መጣብህ፥ አለቀልህ እያሉ ራሱን ከገዛ ወገኖቹ ለይቶ እንዲመለከት ሲኮረኩሩት መኖራቸው ይታወቃል። ሆኖም የትግራይ ሰው፣ በሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ፣ በጥርጣሬ ዓይን መታየት የጀመረበት ጊዜና መነሻው ለብዙዎች ግልጽ ላይሆን ይችላል።
ጊዜው 1970 ዓ.ም ነበር። መነሻውም የሕወሓት አመራር ከልቡ አፍልቆ የተገበረው የተንኮል ሥራ ነበር።
እነሆ ማስረጃ። ከአቶ ገብሩ አስራት መጽሐፍ በረዥሙ ልጥቀስ፦
“.. . በ1970 ዓ.ም ደርግ ካካሄደው የማጋለጥና የመመንጠር ዘመቻ በኋላ ቁጥራቸው የማይናቅ የትግራይ ተወላጆች ደርግን ማገልገል ጀምረው ነበር። እነዚህም በሁሉም የአውራጃና የወረዳ ከተሞች ህዝቡን ያውኩ ስለነበር፣ ሕወሓት እነሱን ለማጥፋት አንድ ዘዴ ቀየሰ። የሐሳቡ አመንጪ እውቁ የከተማ የሕዝብ ግንኙነት ሠራተኛ ተክሉ ሐዋዝ ሲሆን ዕቅዱን ለማስፈጸም ሦስት ታጋዮች እንዲመደቡለት ጠየቀ። ሦስቱ ታጋዮች ከተማ ገብተው ህዝቡን የሚያውኩትን ግለሰቦች ደርግ ራሱ እንዲያጠፋቸው የተቀየሰውን የረቀቀ ዕቅድ እንዲያፈጽሙ ተልዕኮ ተሰጣቸው። ተክሉ አንድ ረዥም የሐሰት ደብዳቤ አዘጋጀ። ከተክሉ ሐዋዝ በወቅቱ የፖለቲካ ኃላፊ ለነበረው ዓባይ ፀሐዬ የተላከ የሚል ነው።  ‘ጥብቅ ምስጢር’ የሚል ተጽፎበት በሙጫና ስቴፕልስ ታሸገ። ደብዳቤው ውስጥ በኮድ የተጻፈ የብዙ ሰዎች የስም ዝርዝር ሰፍሯል። ከስም በተጨማሪ ማን ከማን ጋር በሕዋስ እንደተደራጀና የአመራር ኮሚቴ አባላቱ ማንነት በማመልከት ሐሰተኛውን ‘የከተማ መዋቅር’ ቁልጭ አድርጎ ያሳይ ነበር። ስሞቹ በኮድ ፣ ኮዱ የደርግ ባለሙያዎች በቀላሉ እንዲፈቱት ተደርጎ የተዘጋጀ ነበር። በደብዳቤው ሕወሓትን ሲያውኩ የነበሩት አብዛኞቹ የደርግ ጋሻ ጃግሬዎች ስም ሰፍሮ የሕወሓት እጅግ ታማኝ አባላት እንደሆኑ ተጠቁሟል። እንዲያውም ከአንዳንዶቹ ስም ጎን ሆን ተብሎ አስተያየት ጭምር ታክሎበታል፤ ‘ይህ ሰው ቁልፍ ሚን የሚጫወትና ከበላዮቹ ጋር እየተገናኘ ጠቃሚ ምስጢር የሚያቀብለን ነው’ የሚለው ተሰምሮበት ነበር። በኮዱ መሠረት አ=12 ብ=16 ር=70 ሃ=20 በ=08 ላ=63 ቸ=74 ው=32 ሆኖ እንዲወከል ተደርጎ በደብዳቤው ’12 16 70 20 08 63 74 32 ጥሩ እየሠራ ነው’ የሚል ብቻ ተጽፏል። ኮድ ሰባሪ ባለሙያዎች ቁጥሩን በቀላሉ ሰብረው አብርሃ በላቸው ይሉና፣ ከሚቀጥለው ሃረግ ጋር በማዛመድ፣ ‘አብርሃ በላቸው ጥሩ እየሰራ ነው’ ብለው ያነቡታል። ሌሎቹንም እንዲሁ።
“ሦስቱ ታጋዮች ደብዳቤውን እንደያዙ አክሱም ለሚገኘው አስተዳደር እጃቸውን ሰጡ። ከተኽሉ ሐዋዝ ለዓባይ ፀሐዬ የተጻፈ ደብዳቤ ይዘው መምጣታቸውን ገለጹ። የአክሱም ካድሬዎችና አስተዳዳሪዎች ተክሉ ሐዋዝና አባይ ፀሐዬ በድርጅቱ ውስጥ ያላቸውን ሚና ያውቃሉ። ምስጢራዊ የተባለውን ደብዳቤ ይዘት በመገመት ባስቸኳይ መቀሌ ለነበሩት የበላያቸው አስታወቁ። የበላይ ኃላፊውም እጅግ ተደስቶ፣ ወዶ ገቦቹ ባስቸኳይ ወደ መቀሌ እንዲላኩ አዘዘ። ታጋዮቹ ከነደብዳቤው በሄሊኮፕተር መቀሌ ተላኩ። ደብዳቤው ተከፍቶ የኮድ ባለሙያዎች በቀላሉ ፈቱት። ደብዳቤው ሲነበብ በርካታ በታማኝነታቸው የታወቁ የኢሠፓአኮ ካድሬዎችና አስተዳዳሪዎች፣ የሕወሓት አባላት መሆናቸው ተረጋገጠ። ለደርግ እጅግ ታማኝ የነበሩት እነ አብርሃ በላቸውና አፈወርቅ አለም ሰገድ ሳይቀሩ ስማቸው ዝርዝሩ ውስጥ ተገኘ። በሁኔታው እጅግ የተደናገጠው ደርግ፤ ወዲያውኑ ሁሉንም ለቃቅሞ አስሮ በግርፋት ፍዳቸው አሳያቸው።
“•••ከመቀሌ ማዕከላዊ ምርመራ ለደኅንነት ሚኒስትሩ ኮ/ል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ በተጻፈ ደብዳቤ፤ ‘ራሱን ህወሓት ብሎ የሚጠራው ጸረ አንድነት የወንበዴዎች ድርጅት በረሓ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ሌላ፣ በከተማ በቂና ወቅታዊ መረጃ፥ የማቴርያልና ሞራል ድጋፍ ለማግኘት በየክፍላተ ሃገራት የወንበዴ ሕዋስ [ሴል] በመዘርጋት፣ የትግራይ ክፍለ ሃገር ተወላጆችን በአባልነት በማሰባሰብ ፀረ አንድነት ድርጊቱን በማካሄድ ላይ ይገኛል... የማዕከላዊ ምርመራ ቅርንጫፍ የሆነው የትግራይ ክፍለ ሃገር ማዕከላዊ ምርመራ ዋና ክፍልም፣  የአብዮቱ ወገኖች መስለው ስዉር ጸረ ሕዝብ ደባ በመፈጸም ላይ የሚገኙትን የውስጥ ቦርቧሪዎችን ለማጋለጥና የወንበዴውን ሴል ለመበጣጠስ በወሰደው እርምጃ፣ 209 የሕወሓት ወንበዴ አባላት በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራውን በሰፊው ቀጥሏል’ ይላል።
“ሕወሓት በዚህ ዘዴ ቀንደኛ የደርግ ካድሬዎችና ታጣቂዎች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ አደረገ። የኢሠፓአኮ ማ/ኮ አባልና የፖለቲካ ት/ት ቤት ከፍተኛ ባለስልጣን የነበረው ታደሰ ገ/እግዚአብሔር ሳይቀር በቁጥጥር ሥር ውሎ መጨረሻ ላይ ከወኅኒ ቤት ተወስዶ በደርግ አፋኞች ተገደለ። የክፍለ ሃገሩ ተቀዳሚ ምክትል ሊ/መ የነበረው ኅሩይ አስገዶም፣ የሕወሓት የውስጥ አርበኛ ነው ተብሎ እጁን ለመያዝ ሲሞከር በተከፈተው ተኩስ ሞተ። ሕወሓት ውስጥ በደኅንነት ሥራ ተመድቦ ሲሠራ ቆይቶ እጁን ለደርግ ፣ በጸጥታ ሥራ ተመድቦ የነበረው አለማየሁ በቀለም እንዲሁ በሰርጎ ገብነት ተጠርጥሮ እጁን እንዲሰጥ ሲጠየቅ፣ እምቢ ብሎ በጥይት ተመትቶ ሞተ።
“በተደረገው የምንጠራ ዘመቻ ከአንድ ሺ በላይ የማኅበራት መሪዎች፥ የመንግሥት ሹመኞች የኢሠፓአኮ ካድሬዎችና ታጣቂ ሚሊሻዎች ታስረዋል። (“ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ”፥ ገጽ 127 እስከ 129]
ይህን ተግባር የሕወሓት አመራር ለትግሉ ሲል የወሰደው ብልህ እርምጃ ነው በማለት የሚያሞካሽ አይጠፋ ይሆናል። ያኔ የተነዛውና ጥርጣሬ ያጫረው መርዝ ግን ዛሬ ድረስ መዝለቁን መካድ አይቻልም።
ከላይ የተጠቀሰው በወቅቱ የነበሩትን የትግራይ ተወላጅ የደርግ አባላት ለጥቃት ያጋለጠ ሲሆን ከዚያ ባሻገር ደርግ በሕዝቡ ላይ የነበረውን እምነት ያስለወጠ ነው ለማለት ይቻላል። የደርግ ጥርጣሬና እርምጃዎችም ለሕዝቡ የስጋት ምንጭ እየሆነ፣ በሁለቱም ወገን አለመተማመን በመስፈኑ፣ ሕወሓት የዘራው ጥርጣሬ ደርግ በስተመጨረሻ ሲያራምደው ለነበረው በሕዝቡ ላይ ያነጣጠረ የሚመስል አቋም ሳይዳርገው አልቀረም። ሕወኃትም ያን የጥርጣሬ መርዝ ከረጨ በኋላ ደርግ የሚሰነዝረውን ጥቃት ሸሽቶ ለሚመጣው መጠጊያና አለኝታ ሆኖ በመቅረብ አትርፏል።
ሕወሓት በራሱ ላይ የተነጣጠረውን የደርግ መንግሥት ጥቃት፣ በሕዝቡ ላይ እንደመጣ የፀረ ሕዝብና ጨፍጫፊ መንግሥት ሥራ በማቅረብ፣ በሕዝቡና በድርጅቱ መካከል ልዩነት የሌለ አስመስሎ ሲያቀርብ ኖሯል። ዛሬም አያሌ የዋህ ተንታኝ፤#ሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ነው አይደለም; የሚል አሳዛኝ ጥያቄ ማንሳቱም ከዚያ ድሮ ከተዘራው ጥርጣሬ መቀዳቱ አይቀርም።
የሕወሓት አመራር መንግሥት ከሆነ በኋላም፣ የትግራይን ሕዝብ ማሸበሩን አልተወም። ችግር ባጋጠመው ጊዜ ሁሉ የትግራይን ሕዝብ ለጥቃት ሲያጋልጥ መኖሩ አልያም “ና ሙትልኝ” ሲል መኖሩ ይታወቃል። ለምሳሌ በምርጫ 97 የቅንጅት ሰፊ ተቀባይነት አስደንግጦት፣ "ኢንተርሃምዌ መጣብህ" በማለት ሕዝቡን አሸብሮ ከጎኑ እንዲሰለፍ ማድረጉ ይታወቃል። ልክ በረሃ እያለ የውሸት ሰነድ አዘጋጅቶ ንጹሐን አገር ወዳድ የትግራይ ልጆችን እንዳስመታ ሁሉ፣ ዛሬም በመላው ኢትዮጵያ ያሉት የትግራይ ልጆች ቢመቱለት ደስታውን አይችለውም። የሕወሓት አመራር፤ የፌዴራል መንግሥትን ስልጣን ለቆ ከሄደ በኋላም የራሱን ሽሽትና ፍርሃት ወደ ሕዝቡ በማጋባት፥ በራሱ ላይ የሚሰነዘረውን ክስና ስድብ፣ በህዝቡ ላይ የተሰነዘረ በማስመሰል፥ ያልተባለውን ተባለ፥ ያልተደረገውን ተደረገ በማለት፥ ስብከቱን አልቀበል ያለውንም “ባንዳ” የሚል ስም ሰጥቶ ከሥራ በማፈናቀል፣ በትግራይ ተወላጁ ደምና መስዋዕትነት፣ የራሱን ሕይወት ለማቆየትና የክልል ስልጣኑን ዕድሜ ለማራዘም ይዳክራል። በመላው ኢትዮጵያ፣ ለአስርት ዓመታት ተጭኖ የነበረው የጭቆና ቀንበር ከነዝርፊያው፥ መሬት ወረራው፥ ከነጭንቀቱ ዛሬ ትግራይ ላይ ብቻ ተንሰራፍቶ ይገኛል።
   የሕወሓት አመራር፤ የዛሬ 30 እና 40 ዓመት በርካታ ታጋዮች ፈንጂ ረግጠው እንዲሞቱላቸው አድርገው ሲያበቁ፥ ያ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለለትን የሟች ጓዶቻቸውን ፍትሕና እኩልነትን የማረጋገጥ አደራ በመብላታቸውም ሳያዝኑ፥ ጭራሽ አሁን ደግሞ የነዚያን ጀግኖች ልጆች፥ ብሎም የልጅ ልጆች በሐሰተኛ ሰበካ “ኑ ሙቱልን” በማለት ለጦርነት ይቀሰቅሳሉ። የሕወሓት አመራር ነገር ሁሌም #እናንተ ሙቱልኝ፤ እኔ ልሰንብት; ነው።
ዛሬ ደግሞ የያዙት ዕቅድ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ በምንም የማይለየውን የትግራይ ሰው፣ እንዲሁ በከንቱ ከገዛ ያገሩ ልጆች ጋር ደም ማቃባት ሳይሆን አይቀርም። ሆኖም ደም በማቃባት እንለየዋለን ካሉ፣ የተለየ ጥቅም ሳይኖረው ከገዛ ወገኑ ለመለያየት ካጩት፣ ጠላቶቹ እነሱና እነሱ ብቻ ናችው።
እስቲ ዛሬ እንኳን የኛ ለምትሉት ሕዝብ እዘኑለት!
የትግራይ ሕዝብ ወዶም፥ ተገዶም ለሕወሓት አመራር በትግል ጊዜ ስንቅ፥ ትጥቅና ወጣት አቅራቢ ሆኖላችሁ፥ ወደ ስልጣን ስትወጡ መወጣጫ መሰላል፥ ወንበራችሁ ሲነቃነቅ የግዱን ድጋፍ ሆኗችሁ ኖሯል። እነሆ ከስልጣን ስትወርዱ ደግሞ መደበቂያ ሆኗችኋል። እንደገና ጦርነት? አያሳዝናችሁም? ከዚያ በላይ ምን ይኁንላችሁ? ዛሬስ ሙትልን የምትሉት ለምን ዓላማ ነው? ለመገንጠል? ለምን? ምነው አሁን እንኳን ብትተዉት? ምነው ለኢትዮጵያውያን ከመጣው ነጻነትና ተስፋ ቢቋደስበት?
ዛሬ በኢትዮጵያ የሕዝቦችን እኩልነት ለማረጋገጥ ቆርጦ የተነሳ፥ ጠመንጃን ከፖለቲካ ቋንቋነት ውጭ ለማድረግ ግማሽ መንገድ ሳይሆን ሙሉውን መንገድ ተጉዞ፣ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ካሉበት ድረስ ሄዶ እጃቸውን ስሞ አገር ቤት ያስገባ፤ እናንተንም የይቅርታ እጁን ዘርግቶ በትዕግስት የሚጠብቅ መንግሥት መኖሩን ታውቃላችሁ። ተጠቀሙበት። ካላመናችሁት በሽማግሌ ፊት በር ዘግታችሁ አስምሉት። ካልተጣላኸን ግን አትበሉት። የጠየቃችሁትን ሁሉ ሲሰጣችሁ የኖረውን፥ የኛ የምትሉትን ሕዝብ ታይቶ በማይታወቅ ትእግስት ከሚጠብቃችሁ የኢትዮጵያ መንግሥትና ከገዛ ወገኑ ጋር ደም አታቃቡት። ፍጥጫውን አርግቡት። ዛሬ ከናንተ የሚጠበቅ የጀግንነት ሥራም ይኸው መሆኑን እወቁት።


Read 3274 times