Tuesday, 27 October 2020 00:00

የቀጣዩ ምርጫ ተስፋዎችና ስጋቶች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 - ዛሬ የብልጽግና ቲሸርታቸውን የለበሱት የቀድሞ የኢህአዴግ ካድሬዎች ናቸው፡፡ - ኢህአፓ
          - ህግና ስርዓት በአገሪቱ ገና አልሰፈነም - ኢዴፓ


        በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተራዝሞ የነበረው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ዘንድሮ እንዲካሄድ በመንግስት መወሰኑ ተስፋ እና ስጋቶችን የደቀነ ሆኗል፡፡ ይራዘም አይራዘም በሚል ሃሳብ ሊያወዛግብ የቆየው፡፡ ምርጫው በብዙ ችግሮችና ስጋቶች የታጀበ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች ይገልፃሉ። ለመሆኑ የምርጫው ስጋቶች ምንድን ናቸው? ከምርጫው የሚፈለገው ውጤት እንዲገኝ ከማን ምን ይጠበቃል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹን አነጋግሮ ሃሳባቸውን እንደሚከተለው አቀናብሯል፡፡


            “ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ መግባባት ይቅደም”
                አቶ ጌታነህ ባልቻ፤ የባልደራስ አመራር


          ከፊታችን ያለው ምርጫ፤ የተጨናገፈው የለውጥ ጉዞ የሚስተካከልበትን መደላድል ለመፍጠር የሚያስችል ከሆነ፣ እንደ ተስፋ የምናየው ነው፡፡ አንድ ምርጫ የሚካሄደው ተወዳዳሪዎች ስላሉ ብቻ አይደለም፤ የዲሞክራሲ ተቋማትም ያስፈልጋሉ፡፡ ምርጫ ለማካሄድ የዲሞክራሲ ተቋማት ወሳኝ ናቸው፡፡ የሲቪክ ተቋማት፣ ነፃና ገለልተኛ ፍ/ቤት፣ ፖሊስ፣ የምርጫ አስፈፃሚ ተቋም ያስፈልጋሉ፡፡ አሁን እንደምናየው፤ ዳኞች እንኳን ውሣኔ አሳልፈው፣ ፖሊስ ውሣኔውን የማያከብርበት ሁኔታ እየተከሰተ ነው፡፡ ማረሚያ ቤትና ሌሎች አካላትም በተመሳሳይ ፍ/ቤት የሚያዛቸውን ጉዳይ እንኳ ለመቀበል ሲቸገሩ ነው በግልጽ እያየን ያለነው፡፡ ይሄ እየሆነ ያለው ደግሞ ምንም በሌለበት በአሁኑ ወቅት ነው፡፡
በምርጫ ወቅት ቢሆንስ? “ህልውናችንን እናጣለን” በሚል ፍራቻ የሚያደርጉትን ነገር ከወዲሁ መገመት አያስቸግርም፡፡
እነዚህ ተቋማት አሁን ባሉበት ሁኔታ የሚቀጥሉ ከሆነ፣ ለምርጫው ትልቅ ስጋት ይፈጥራሉ፡፡ ከዚህም አንፃር በቅድመ ምርጫም ሆነ በድህረ ምርጫ ሀገሪቱን ለተወሳሰበ ፖለቲካዊ ቀውስ የሚዳርግ ግጭት ይፈጠራል የሚል ስጋት አለን፡፡ ይህን ስጋት ለመቀነስ በመጀመሪያ ደረጃ፤ ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣት ጥረት ብናደርግ መልካም ይሆናል፡፡ ተቋማትን ለመገንባት የሁሉም ድርሻ የሚካተትበት አካሄድ ብንከተል፣ ስጋቶችን ሊቀንስ ይችላል፡፡ ነገር ግን አሁን በተያዘው አካሄድ የምናደርገው ምርጫ ብዙም ውጤት ያለው አይሆንም፡፡ ነገር ግን ብሔራዊ መግባባት እየተባለ የሚደረገው ውይይት አግላይ መሆኑን እያየን ነው፡፡
ይሄ ደግሞ ውይይቱ ውጤታማ እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ የሚካሄደው ብሔራዊ መግባባት ሁሉን አቀፍ ሊሆን ይገባዋል፡፡


_____________


          “ከምርጫው በፊት የምርጫ ስርአቱ መለወጥ አለበት”
               አቶ ሠለሞን ተሰማ፤ የኢህአፓ ሊቀ መንበር

 
     የኛ ፓርቲ ምርጫው ዘንድሮ  መደረግ አለበት ብሎ ያምናል፡፡ አሁን ባለው የመንግስት አስተዳደር ግን ለምርጫው የሚደረገው ዝግጅት እጅግ በጣም ደካማ ነው። ለምርጫው አስፈላጊ የሆነው የህዝብና ቤት ቆጠራም አልተካሄደም። በሌላ በኩል ደግሞ በከተሞች አካባቢ መራጭ ለማዘጋጀት በሚመስል መልኩ፣ የዲሞግራፊ ለውጦች የማድረግ ግብግብ አለ፡፡ በአዲስ አበባና በብዙ ከተሞች ላይ የሚታይ ችግር ነው፡፡
በሌላ በኩሉ፤ የስርአቱ መዋቅሮች ገና የገለልተኝነት ስነልቦናን አላዳበሩም፡፡ ገለልተኝነት የላቸውም፡፡ አስፈፃሚው፣ ህግ አውጪውና  ህግ ተርጓሚው አካል በፍፁም እኛ የምናልመውን አይነት ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ደረጃ ላይ አልደረሱም፡፡ ይሄ መንግስት የገባውን  ቃል ለመፈፀም በሚያስችል ሁኔታ በመሬት ላይ ሰርቷል ወይ? የሚለው ጥያቄ ሆኖ ያለ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር፤ በአገሪቱ ለምርጫ የሚሆን ነባራዊ ሁኔታ አለ ማለት ያስቸግራል፡፡  ምርጫም ጥሩ ውጤት ላያመጣ ይችላል የሚል ስጋት አለ።
በዋናነት ቀጣዩን ምርጫ ተዓማኒና ውጤታማ ለማድረግ፣ የምርጫ ቦርድ በማዕከል ላይ ብቻ ያደረገውን መዋቅራዊ ለውጥ፤ ወደ ክልል ዞንና ወረዳ ማውረድ መቻል አለበት፡፡ በቦርዱ በክልል ዞንና ወረዳ ያለውን የአደረጃጀት ሁኔታ በግልጽ ማወቅ አይቻልም፡፡ ብዙም የተሠራበት አይመስልም፡፡ ክልልና ዞን አሁንም የሚመሩት በፊት ምርጫን የማጭበርበር ሚና በነበራቸው ግለሰቦች ነው፡፡ የቀድሞ የኢህአዴግ ካድሬዎች ናቸው፤ የብልጽግና ቲ-ሸርታቸውን የለበሱት፡፡ ስለዚህ ምርጫ ቦርድ በማዕከል ደረጃ ያደረገውን የመዋቅር ለውጥ፣ በክልል ዞንና ወረዳ ደረጃም ማውረድ አለበት፡፡ ሁለተኛው ችግር፤ የሲቪክ ማህበራትና የሙያ ማህበራት ነፃና ገለልተኛ ሆነው የተቋቋሙበት ሀገር ባለመሆኑ ቀጣዩን ምርጫ በመታዘብ ሂደት ላይ ከወዲሁ ጥያቄ እንዲነሳባቸው ያደርጋል።
ከገዥው ቡድን ጋር በደንብ የሚተዋወቁ፣ የገዥውን ቡድን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚተጉ ናቸው፡፡ ሌላው የመገናኛ ብዙሃን ሁኔታ ነው፤የመገናኛ ብዙሃኑ በለውጡ ሰሞን መሻሻል ያሳዩ ቢሆንም የቀድሞ ማንነታቸው ተመልሰዋል፡፡ የፀጥታና የፖሊስ መዋቅር አካባቢም በስም ተለውጠናል ተቀይረናል ይበሉ እንጂ በተግባር ምን ያህል ርቀት ሄደዋል የሚለው አሁንም አጠያያቂ ነው፡፡ ምናልባት የተሻለ ገለልተኛ ለመሆን እየጣረ ያለው የመከላከያ ሠራዊቱ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ሌሎቹ ገለልተኛ ናቸው ለማለት ያስቸግራል። በዚያ ላይ የክልል ልዩ ሃይል  የሚባሉት በስልጣን ላይ ካለው መንግስት ጋር የሚሞዳሞዱ መሆናቸው ለምርጫው አደጋ ይጋርጣል፡፡ የፍትህ አካላት የገለልተኝነት ጉዳይም እንዲሁ ያሳስባል። የፍ/ቤቶችና አቃቤ ህግ ገለልተኛነት በእርግጥ አለ ወይ? የአስፈፃሚው አካል አሁንም  እንደፈለገ የሚቆለምመው የፍ/ቤት የህግ ተርጓሚ አካል ነው ያለው፡፡ አቃቤ ህግ እንደፈለገ የሚቆለምመው ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ሲታሰቡ ምርጫ ከቀድሞዎቹ እንዴት የተለየ ሆኖ ሊካሄድ እንደሚችል ከወዲሁ ጥርጣሬ ይፈጥራል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ የምርጫ ስርአቱ መለወጥ አስፈላጊነት ነው፡፡ እስካሁን ያለው የምርጫ ስርዓት፤ አብላጫ ድምጽ ያገኘው ፓርቲ መንግስት ይመሠርታል የሚል ነው ነው፡፡ እስከዛሬ በነበረው ምርጫ ኢህአዴግና አጋሮቹ የሚያገኙት ድምጽ 15 በመቶ ቢሆን ነው፤ ሌላው 85 በመቶ የሚሆነው የሌሎች ነው። ድምፆች በዚህ መልኩ ስለሚበታተኑ ነው ኢህአዴግ ከዚህም ከዚያም ያሰባሰባቸው ድምፆች አሸናፊ ያደርጉት የነበረው፡፡ ከዚህም አንፃር የምርጫ ስርአቱ ከፍተኛ ችግር ያለበት በመሆኑ መቆራቆስን ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት አለን፡፡ ስለዚህም አብላጫ የምርጫ ስርአታችንን ቅይጥ የምርጫ ስርአት መለወጥ አለብን፡፡ በእርግጥ አሁን የምርጫ ስርዓት ባለው ሁኔታ፣ይህ የሚደረግ አይመስለኝም፡፡ ቢሆን ግን ለሀገሪቷ ጥሩ መፍትሔ ይሆን ነበር፡፡
የዘንድሮ ምርጫ አሁን ያለውን አገዛዝ ከማስቀጠል ውጪ ያን ያህል ውጤት የሚያመጣ አይመስለንም። ያው የተለመደው አይነት ምርጫ ነው የሚሆነው፡፡ ይህ እንዳይሆን ከተፈለገ፣ በርካታ ማሻሻያዎች መደረግ አለባቸው፡፡ በፓርቲዎች መካከል ከወዲሁ ውይይትና ድርድር መካሄድ አለበት፡፡ የብልጽግና ሰዎችም ስልጣን ልናጣ እንችላለን ከሚል ስጋት መውጣት ለትክክለኛ ምርጫ ራሳቸውን ማዘጋጀት ይገባቸዋል፡፡ ከሁሉም ቀዳሚ በሆነው የሀገር ጉዳይ ላይ ተወያይቶ፣ አንዳች ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡ ያንን ማድረግ ከተቻለ የምርጫ ጉዳይ ቀላል ይሆናል፡፡


__________________


               “የተጀመረው የብሔራዊ መግባባት ውይይት ብዙ ስጋቶችን ይቀርፋል”
                      (አቶ ግርማ በቀለ፤ የህብር ፓርቲ ሊ/መንበር)

         ለቀጣይ ምርጫ የመጀመሪያው ስጋት፣ በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ ውጥረት ነው። በሌላ በኩል፤ ብሔርና ሃይማኖት ተኮር ግጭቶች እየተስፋፉ የመጡበት ጊዜም ነው፡፡ ይሄ ችግር ባልተፈታበትና ውጥረቱ ባልረገበበት ሁኔታ ውስጥ ምርጫ ማካሄድ ማለት አደገኛ ነው፡፡
ለሚከሰቱ ውጥረቱን የበለጠ እንዳያባብሰው ስጋት አለን፡፡ ሌላው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው አለመተማመን ነው፡፡ ይህ ከምርጫ ጋር ተያይዘው ለሚከሰቱ ተፈጥሮአዊ ውጥረቶች ተጨማሪ ስጋት ነው የሚሆነው፡፡
አንዱ ወደ ሌላው ክልል እንዳይገባ የሚደረጉ የፖለቲካ አሻጥሮች፣ ሁኔታውን ያጋግሉታል የሚል ስጋት አለን፡፡ ሌላው፤ የምርጫ ቦርድ አቅምና አቋም ጉዳይ እንዴት ነው የሚለው ነው።
ቦርዱ ምርጫውን በማስፈፀም ሂደትም ሆነ ከምርጫ በኋላ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ምን ያህል ዝግጁ ነው የሚለው የሚያሳስብ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ስጋት ውስጥ ግን እኔ ተስፋ የማደርገው፣ የተጀመረውን የብሔራዊ መግባባት ውይይት፣ ነው። በዚህ ውይይት፣ በተለይ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከተስማማንና ምርጫውን ከውጥረት ነፃ በሚያደርጉ ነገሮች ላይ ከተግባባን፣ ስጋቱን ሊቀንሰው ይችላል፡፡ ነገር ግን ይሄን ስል ምርጫው የግድ ዘንድሮ መካሄድ አለበት የሚለውን በመቀበል እንዳልሆነ መታወቅ አለበት። መነጋገሩ ግን ውጥረቶቹን ሊያረግብ ይችላል፤ ለዚህም ጠንክረን እየሠራንበት እንገኛለን የተጀመረው የብሔራዊ መግባባት ውይይት ተስፋ የሚደረግበት ነው ወይ ከተባለ፣ እኛ በእጅጉ እናምንበታለን፡፡ ብዙ ለውጥ የሚያመጣ ነው፡፡ የታሠሩ የፖለቲካ ሰዎች መኖራቸውም ጭምር ነው፡፡
ብሔራዊ ውይይቱን አስፈላጊ ያደረገው፣ችግሩም በውይይቱ ይፈታል የሚል እምነት አለን፡፡ ከፀሐይ በታች የሆኑ ማናቸውንም ጉዳዮች ነው በውይይት ለመፍታት እየተሞከረ ያለው፡፡ ስለዚህ ውጥረቶችንና ችግሮችን ለመቅረፍ ያስችላል የሚል ተስፋ አለን፡፡ ከምርጫው በፊት የተጀመሩ ውይይቶች ግን መቋጫ ማግኘት አለባቸው ያ ሲሆን ነው ስጋቱ የቀነሰ ምርጫ ማካሄድ የምንችለው፡፡ ምርጫው ዘንድሮ ይደረግ አይደረግ የሚለውን ጨምሮ፣ ምን አስቻይ ሁኔታዎች አሉ፣ የምርጫውን ሂደትና ከምርጫው በኋላ ያለውን ሁኔታ እንዴት ሠላማዊ እናደርገዋለን… በሚሉት ጉዳዮችም መስማማት አለብን፡፡
የምርጫ ቦርድ ገለልተኝነትን በራሱ መገምገም ያለበት ሲሆን እስከ ምርጫ ጣቢያ ያሉ አስፈፃሚዎችን ገለልተኝነትም ማረጋገጥ መቻል አለብን፡፡ ምርጫው ከሃሜት የፀዳ ሆኖ ውጤት እንዲያመጣ ብዙ ነገሮች ግልጽ እየሆኑ መሄድ አለባቸው፡፡_____________


                  “27 አመት ምርጫ አድርጐ በማያውቅ ሀገር ለምርጫ መቻኮል ተገቢ አይደለም”
                       (አቶ አዳነ ታደሰ፤ የኢዴፓ ፕሬዚዳንት)

          ኢዴፓ  ምርጫው መካሄድ የለበትም ሲል በምክንያትነት ሲያቀርባቸው የነበሩት ጉዳዮች  እንደተጠበቁ ሆነው፣ ሌሎች የፖለቲካ ውጥረቶችም እየተከሰቱ፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ  የበለጠ የተወሳሰበ ሆኗል፡፡ ውጥረቶቹም ከመርገብ ይልቅ በእጅጉ ተባብሰዋል፡፡ እነዚህን ውጥረቶች መቀነስ ባልተቻለበትና የተረጋጋ ሁኔታ ባልተፈጠረበት ድባብ፣ ወደ ምርጫ ብንገባ፣ ሀገሪቱ ወዳልተፈለገ የህልውና አጣብቂኝ ውስጥ ትገባለች ብለን እናምናለን።
ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደምንለው፤ ህግና ስርአት በሀገሪቱ ገና አልሠፈነም፡፡ የህግና ስርአት አስጠባቂው አካል መዋቅሩም በሚፈለገው ልክ አላደገም፡፡ ህግና ስርአት ባልተከበረበት ሁኔታ ደግሞ ወደ ምርጫ ቅስቀሳ መግባት፣ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል። በትግራይና በፌደራል መንግስት መካከል ያለው የፖለቲካ ቅራኔ በራሱ እጅግ እየተባባሰ በመጣበት ሁኔታ ስለ ምርጫ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ በተጨማሪም፤ የክልልነት ጥያቄ ከምንጊዜውም በላይ ጣራ ነክቶ፣ በደቡብ ክልልና በፌደራል መንግስቱ መካከል ያለው ፍጥጫ አስደንጋጭ ምልክቶች እየታየበት ነው፡፡ ለፌደራል መንግስት የመታዘዝ ፍላጐት እያጡ ያሉ የክልልነት ጥያቄዎች እየታዩ ነው፡፡   የፌደራል መንግስትን ህልውና አንቀበልም የሚል ክልልም ተፈጥሯል፡፡
በሌላ በኩል የኮሮና በሽታ ስርጭት እየጨመረ መጣ እንጂ አልቀነሰም፡፡ አሁን በቅርቡ ደግሞ እንደምናየው፤የአንበጣ መንጋ ብዙ የሀገራችን ክፍሎች ላይ ባደረሰው የሰብል ውድመት ገበሬዎችን ስጋት ውስጥ ከቷል፡፡ በአንበጣው ወረርሽኝ ምክንያት እየደረሰ ያለው አደጋ፣ ምን ይዞ እንደሚመጣ ገና በግልጽ አልታወቀም፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ ሊመጣ የሚችለውን የረሃብ አደጋም ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ችግሩ ሲከሰት እንዴት ነው ልንፈታ የምንችለው የሚለው በሚገባ መታየት አለበት፡፡
ምርጫ ቦርድስ ምን ያህል ተዘጋጅቷል? የሚለው ሌላው ጥያቄ ነው፡፡ እንደምናየው ቦርዱ፤ የምርጫ ጊዜ ሠሌዳ እንኳ አውጥቶ፣ የምርጫ እንቅስቃሴ ውስጥ አልገባም። ውይይትም እስካሁን አልተጀመረም፡፡ ታዲያ እነዚህ ሁሉ ባሉበት ምን አይነት ምርጫ ነው የሚካሄደው?
ስለዚህ የሚበጀው እነዚህን ችግሮች በዝርዝር አስቀምጠን፣ በችግሮቹ ዙሪያ በመወያየት፣ ምን እናድርግ የሚለውን መመካከርና የመፍትሔ አቅጣጫ መዘየድ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ፣ የሀገር ህልውና ሊያሳስበን ይገባል፡፡ 27 አመት ምርጫ አድርጐ በማያውቅ አገር፤ አሁን ለምርጫ መቻኮል ተገቢ አይደለም፡፡ በጥድፊያ የሚደረገው ምርጫ ካለፉት አምስት  ምርጫዎች የተሻለ አይሆንም፡፡ በህዝብ ሃብትና ንብረት ላይ እንደ መቀለድ ነው የሚታሰበው፡፡
በሌላ በኩል፤ ጠንካራ የፖለቲካ ተፎካካሪ ናቸው የሚባሉ የፓርቲ መሪዎች ታስረው ባለበት  ሁኔታ መንግስት ብቻውን በተጣደፈ ሁኔታ“ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” በሚል ብሒል፣ ምርጫ በጥድፊያ የሚያካሂድ ከሆነ፣ ከቀድሞዎቹ ምርጫዎች ስህተት አለመማር ይሆናል፡፡ “የምርጫ ቲያትር” ለመስራት ከሆነ፤ የ2008 ሁኔታ ነው ተመልሶ የሚመጣው፡፡          
ታዲያ ምን ይበጀል ከተባለ የሚሻለው፣ ሁሉም አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠን፣ የፖለቲካ ችግሮቻችንን በመፍታት፣ የተሻለ ዲሞክራሲያዊ ሂደትን የሚያስጀምር ሂደት መጀመር ነው፡፡ ለዚህ ነው ኢዴፓ ፣አሁን ባለው መንግስት የሚመራ “የሽግግር መንግስት ማቋቋም ያስፈልጋል በሚለው አቋሙ የፀናው፡፡

Read 7636 times

Follow us on twitter

Due to an error, potentially a timed-out connection to Twitter, this user's tweets are unable to be displayed.