Sunday, 01 November 2020 00:00

ወሌ ሾይንካ ከ50 አመታት በኋላ መጽሐፍ ሊያሳትም ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)


          ታዋቂው ናይጀሪያዊ ጸሃፌ ተውኔት፣ ገጣሚና ደራሲ ወሌ ሾይንካ፣ የረጅም ልቦለድ መጽሐፍ ለህትመት ካበቃ ከ50 አመታት በኋላ በቅርቡ አዲስ መጽሐፍ ሊያሳትም ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
የኖቤል ስነጽሑፍ ሽልማትን በማግኘት የመጀመሪያው አፍሪካዊ የሆነው የ86 አመቱ አንጋፋ ደራሲ ወሌ ሾይንካ፤ በኮሮና ቫይረስ ወቅት ከቤቱ ባለመውጣት ያገኘውን መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ የጻፈውና በቅርቡ ለህትመት ይበቃል የተባለው መጽሐፍ “ክሮኒክልስ ኦፍ ዘ ሃፒየስት ፒዩፕል ኦን አርዝ” የሚል ርዕስ እንዳለውም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ከጓደኝነት እስከ ጠላትነት፣ ከእምነት እስከ ክህደት፣ ከተስፈኝነት እስከ ጨለምተኝነት የተለያዩ ለየቅል የሆኑ የህይወት መልኮችን ይዳስሳል የተባለው አዲሱ የሾይንካ መጽሐፍ፤ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ በናይጀሪያ ታትሞ በገበያ ላይ ይውላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፣ ከወራት በኋላ ደግሞ በውጭ አገራት ታትሞ ለአለማቀፍ ገበያ እንደሚሰራጭ አስታውቋል፡፡
ሾይንካ “ዘ ኢንተርፕሬተርስ” የሚል ርዕስ ያለውን የመጀመሪያውን ተወዳጅ የልቦለድ መጽሐፉን ለአንባብያን ያቀረበው እ.ኤ.አ በ1965 እንደነበር ያወሳው ዘገባው፤ በ1973 ካሳተመው “ሲዝን ኦፍ አኖሚ” የተሰኘ ሁለተኛ ስራው በኋላ ረጅም ልቦለድ አሳትሞ እንደማያውቅም አስታውሷል፡፡
ወሌ ሾይንካ በኮሮና ሳቢያ ለወራት በነበረው የቤት ውስጥ ቆይታው ከአዲሱ የረጅም ልቦለድ መጽሐፉ በተጨማሪ አዲስ ትያትር መጻፉንም የጠቆመው ዘገባው፤ ከዚህ በፊት ለተመልካቾች ያቀረበውን “ዴዝ ኤንድ ዘ ኪንግስ ሆርስማን” የተሰኘውን ትያትሩን በታህሳስ ወር በአዲስ መልክ አዘጋጅቶ በሌጎስ ለእይታ ለማብቃት ማቀዱንም አክሎ ገልጧል፡፡


Read 2898 times