Tuesday, 03 November 2020 00:00

ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ የተጋረጠበት አደጋ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  • ፓርኩ እንኳን ለትልልቅ እንስሳት ለአይጥም አይሆንም
     • የኮሬ ማህበረሰብ ለፓርኩ ሲባል ተነስቶ ሌላ ወገን መስፈር የለበትም
     • ፓርኩ ዳግም ይካለል የሚለውን ነገር ፈፅሞ አንቀበለውም
               

           በሃገራችን ከሚገኙት 27 ፓርኮችና  በፌደራል መንግስት ከሚተዳደሩ 13 ፓርኮች አንዱ የሆነው በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን የሚገኘው ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ የዛሬ 46 ዓመት ነው የተቋቋመው 514 ስኩዌር ኪሎ.ሜትር ስፋት ያለው፤ በዓመት  ከ45 ሺህ በላይ ቱሪስቶች እንደሚጎበኙት ይነገርለታል።
ለፓርኩ የገጠመው አደጋ ምስራቃዊና ምዕራባዊ በሚል በሁለት ተከፍሎ ሊታይ እንደሚችል ይነገራል። በመሰረተ ልማትና በጥበቃ በኩል በ46 ዓመታት ጊዜ ውስጥ  የረባ ነገር አልተደረገለትም  ይላሉ፤ የፓርኩ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ሽመልስ ዘነበ ምንም ዓይነት መንገድ አልተሰራለትም፤ ያን የሚያህል ስፋት ያለው ፓርክ በ40 ስካውቶች ብቻ ነው የሚጠበቀው። የራሱ የሆነ የረባ ጽ/ቤት  እንኳን የለውም። የፓርኩን ጠባቂዎች ቁጥር አናሳነት የጋሞ ዞን ዋና አተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ ሲገልጹ“ በአንድ ስካውት አርባ ምንጭ ከተማን እንደማስጠበቅ ነው” ይላሉ።
በፓርኩ ምዕራባዊ ክፍል ከአርባ ምንጭ ከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ፣ ለከሰልና ለተለያዩ  ጉዳዮች  የደን ጭፍጨፋና መሰል ጥፋቶች ሲደርሱ መቆየታቸው ይገልፃሉ የዞኑ አስተዳዳሪ።“በዚህም ምክንያት በደኖች መድረቅና መመናመን ሳቢያ አባያ ሀይቅ በተለይም በአዞ ገበያ አካባቢ ያለው የሀይቁ ክፍል በደለል እየተሞላ፣ ውሃው ወደ ውጭ እየወጣ ነው።  በሌላ በኩል፤ በውስጡ ያሉ እንስሳት መጠለያ በማጣት እየተሰደዱና፣ ለመጥፋት እየታቃረቡ መጥተዋል ይላሉ” አቶ ብርሃኑ ዘውዴ አክለው።
በምስራቃዊ የፓርኩ ክፍል የገጠመውን ችግር በተመለከተ ሲያስረዱም፤ ከረጅም ዓመታት በፊት የምስራቅ ጉጂ ማህበረሰብ በፓርኩ ውስጥ መስፈሩና ከጊዜ ወደ ጊዜ የሰፋሪው መጠን እየበዛ መምጣት በፓርኩ ህልውና ላይ አደጋ ጋርጧል የሚሉት አስተዳዳሪው። አብዛኛው የጉጂ ማህበረሰብ  አርብቶ አደር እንደመሆኑ መጠን የበርካታ ከብቶች የግጦሽ መዋያም ይኸው ብርቅዬ ፓርክ ነው።
የፓርክ ጽ/ቤት ሀላፊው አቶ ሽመልስ በበኩላቸው፤ በተለይ በክረምት ወቅት ላይ ሳሩ በከብቶች እየተረጋገጠ፤ ፓርኩ በቁጥቋጦ እየተወረረ፣ ለሜዳ ፍየሎችና ለሌሎች እንስሳትም ምቾት እየነሳ በመሆኑ በየዓመቱ ከ2-4 ሄክታር የፓርኩን ክፍል በሰው ጉልበት እንደሚያስመነጥሩ ይናገራሉ።
 ከሰፋሪው የጊዜው ወደ ጊዜ መጨመር ጋር ተያይዞ፣ በፓርኩ መግቢያ ላይ በተመሰረተው አዲስ ገበያ ምክንያት፤ ፌስታልን ጨምሮ የተለዩ ቆሻሻዎች ወደ ፓርኩ እየተጣሉ በመሆኑ ሌላው የፓርኩ ህልውና አደጋ ሲሆን የከብቶች ግጦሽ፣የማገዶ እንጨትና የከሰል ምርትም  ልክ አየጨመረ ፓርኩን አስጊ ደረጃ አድርሶታል ይላሉ - አቶ ሽመልስ ዘነበ።
የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ እንደሚሉት፤ ለሶስትና አራት ዓመታት በአገር አቀፍ ደረጃ በተከሰተ የጸጥታና ያለመረጋጋት ችግር ምክንያት አብዛኞቹ ብሔራዊ ፓርኮቻችን በሰው ሰራሽ አደጋ ውስጥ መሆናቸውንና ከነጭ ሳር በተጨማሪ እንደ አዋሽና ቃፍታ ሽራሮ ያሉ ብሔራዊ ፓርኮችም አደጋ ላይ ናቸው።
ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 14 በጋሞ ዞን ዋና ከተማ  አርባ ምንጭ፣ ኦሞ አዳራሽ ፓርኩን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣናት ከፍተኛ አመራሮች በፓርኩ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይቶ ነበር።
በመክፈቻው ላይ ፓርኩ የገጠመውን መጠነ ሰፊ ችግር ለመግታትና ፓርኩን ከአደጋው ለመታደግ  በ2012 ዓ.ም መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ መደረጉን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር መክፈቻ ላይ ገልጸዋል። ከነዚህም መካከል በጋሞ አርባ ምንጭና በምዕራብ ጉጂ ቡሌ ሆራ ከተማ፤አባ ገዳዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የዞኑ ባለስልጣናትና የሚመለከታቸው አካላት  በተገኙበት በሁለቱም ዞኖች ሰፊ ውይይት መደረጉን በመጠቆም በፌደራል ደረጃ የሁለቱን ዞኖች ባለድርሻ አካላት በጥምር ለማወያየት ዕቅድ መያዙንነገር ግን፣በኮቪድ-19 ሳቢያ ሳይካሄድ መቅረቱን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክትሩ ጠቁመዋል- ጥምር ስብሰባው በቀጣይ እንደሚካሄድ በመግለፅ።
በመቀጠልም የጋሞ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ብርሀኑ ዘውዴ፤ ሁሌ ችግሩ ላይ ከምናለቅስ መፍትሄው ላይ በግልጽ እንነጋገር የሚል ጠቅለል ያለ ሀሳብ  የፓርኩ ፅ/ቤት ሀላፊም ፓርኩ ያለበትን ዘርፈ ብዙ ችግር አብራርተዋል ከዚያም  በፓርኩ ዙሪያ ሀሳብና ጥያቄ እንዲያቀርቡ ለተሳታፊዎች እድል ተሰጥቷል።
የመጀመሪያውበን እድል ያገኙት  የቀድሞ የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሰ መምህር የነበሩ በአሁኑ ሰዓት በጋሞ መማክርት የሀገር ሽማግሌዎች ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ሳዲቃ ስሜ በፓርኩ ጉዳይ ለበርካታ ጊዜ ስብሰባ መካፈላቸውን፣ ፓርኩ ከልጅነት እስከ እውቀት አብጠርጥረው እንደሚያውቁት ገለጹ። የእከዛሬ ስብሰባ ያመጣው ለውጥ እንደሌለ በመጠቆምም፤ በፓርኩ ዙሪያ የሚንቀሳቀሱትና የሚሰሩት ጥርስ የሌላቸው አንበሳ እንደሆኑ ተናገሩ። ቀጠሉናም “ ፓርኩ ፈጣሪ በራሱ ጊዜያት የከለለው የተፈጥሮ ፓርክ ነው፤ የውሃ፣ የየብስ፣ የተራራ፣ የዕፅዋት፣ የአጥቢና አጥቢ ያልሆኑ እንስሳት…. ሁሉንም አሟልቶ የሰጠ ነው” ይላሉአቶ ሰዲቃ “እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ፤ ከጋሞ ውጪ ከየትኛውም ክልል ጋር አይዋሰንም፤ ቀደም ሲል  የጉጂ አርብቶ አደሮች ከአካባቢው የጋሞ ሰዎች ጋር ተስማምተው ለከብቶቻቸው ሳር አብልተው፣ውሃ አጠጥተው የነጭ ሳር ሁኔታ ለግጦሽ ምቹ ሳይሆን ሲቀር ከብቶቻቸውን ነድተው ይሄዳሉ እንጂ በቋሚነት ሰፍረው አያውቁም። እርሻ ማረስ፣ ያን ሁሉ መዓት  ከብት ፓርኩ ውስጥ መልቀቅ አሁን በቅርብ የመጣ  ነው” ያሉት አቶ ስዲቃ ስሜ፤በአንድ በኩል ፓርኩን ከንክኪ ነጻ እናደርጋለን እያልን በሌላ በኩል ሰው እያሰፈርን፤ በውስጡ ት/ቤት፣ ጤና ጣቢያና የሀይማኖት ተቋም እየገነባን…. ወዴት ወዴት የሚሄድ ስብሰባ ነው?” ሲሉ ሞግተዋል።
የእርሳቸውን አስተያየት ተከትሎ የተናገሩት የዞኑ አስተዳዳሪ፤ “ከፓርኩ ማዶ የሚገኘው ገላን አባያ ወረዳ የኦሮሚያ መሆኑን መካድ አይቻልም” “ከየትኛውም  የኦሮሚያ አካባቢ ጋር ፓርኩ አይዋሰንም” አስተያየት ላይ ማስተካከያ ሰጥተዋል።
በጋሞ ዞን የአካባቢ ጥበቃ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ማዜ ሸቀኔ በበኩላቸው “ሁሌ የሚያጋጥመኝ ስብሰባ በፓርኩ ጉዳይ ዞኑን ከባለቤትነት  ገለል የሚያደርግ ነው ይህ ትክክል አይደለም፣ሲመሰረት 514 ስኩየር ኪሎ.ሜትር ስፋት የነበረውን ፓርክ፤ 50 በመቶ ሰው አስፍሮ ፓርኩ እንደገና ይካለል ማለት ተስፋ የሌለው ነገር ነው፣ አሁን ፓርኩን የጎዳው በፌደራል መተዳደሩ ነው ”ይላሉ።
“በፌደራል ከሚተዳደሩት ይልቅ በክልል የሚተዳደሩት ፓርኮች የተሻለ ህልውና አላቸው” የሚሉት ሀላፊው፤ ፌደራል መንግስት አልችልም የሚል ከሆነ ለጋሞ ዞን ይሰጥና ከዚያ በኋላ ፓርኩን እንዴት እንደምናስከብረው ለእኛ ይተውልን፤ በዚህ ፓርክ ጉዳይ የጋሞ ህዝብ  ትዕግስት እያለቀ ነው”። ሲሉ ሃላፊው አሳስበዋል።
ዶ/ር ስምኦን ሽብሩ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት እንዲሁም በስነ-ህይወት  ት/ቤት የስነምህዳር ባለሙያ ናቸው። እሳቸው እንደተናገሩት፤ የእድሜያቸውን ግማሽ የፈጁት ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ላይ በመመራመር ነው። ፓርኩ በአሁኑ ሰዓት እንኳን ለትላልቅ እንስሳት ለአይጥ መኖሪያነት  አመቺ እንዳልሆነ በጥናታቸው ማረጋገጣቸውን ይገልፃሉ። ቀደም ሲል የነበረውን ህልውናም እያጣ ስለሆነ በፓርኩ ላይ ተስፋ መቁረጣቸውን፣ ቢጮሁም ሰሚ ማጣታቸውን፣ በዚህም ስብሰባ ላይ ሳይጋበዙ በድንኳን ሰባሪነት  መገኘታቸውን  በቁጭት ገልጸዋል። አሁን ላይ ጉዳዩ የፖለቲካ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ መሆኑን የሚያስታውሱት ዶ/ር ስምኦን፤ፓርኩ ዳግም ይካለላል በሚለው ነገር ላይ ፈፅሞ እንደማይስማሙና በፌደራል ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት እልባት እንዲያገኝ ጠይቀዋል።
ፓርኩ ከውድመቱና ከጥፋቱ ባሻገር የፀጥታ ችግር ስጋት ሆኗል የሚሉት ደግሞ በጋሞ ዞን የሰላምና ፀጥታ መምሪያ ሀላፊ የሆኑት ኮማንደር  ሞናዬ ሞሴ ናቸው።የፓርኩ ምስራቃዊ ክፍል ሽጥ ሽጡን ይዞ እስከ ጥግ ድረስ የኦነግ ሸኔ መፈንጫና መፈልፈያ ሆኖ ለዞናችን የፀጥታ ስጋትን ፈጥሯል። በፓርኩ ዙሪያ እኛ የፀጥታ አካላት ደክሞናል፤ትዕግስታችን አልቋል የሕግ የበላይነት ይከበር ይላሉ።
“በፓርኩ እንስሳት ሞተው ይገኛሉ፤ አንዲት ሴትም ተገድላ ተገኝታለች፤ ሰው እየሞተ ገዳዮቹ ለህግ አልቀረቡም፤ እንደ ፀጥታ ሃላፊነቴ ይሄ ነገር እንቆቅልሽ ሆኖብኛል፤ የሚመለከተው ሁሉ የማይረባና አሰልቺ ስብሰባ ማድረጉን አቁሞ አፋጣኝ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት፣የህግ የበላይነት መከበር አለበት” ሲሉ መረር ያለ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። የሚመጣውን  የከፋ ችግር  አሁን በትኩረት መፍታት ትርፋማ ነውም ብለዋል።
የአማሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ   አቶ ወገኔ ደጀኔ በበኩላቸው፤ “ለፓርኩ ህልውና ሲባል ከ1080 በላይ የኮሬ ቀበሌ ማህበረሰብ ከፓርኩ በፍቃደኝነት ተነስቷል። ፃልቄ ቀበሌ የሚባል የኮሬ ቦታ አሁን ጉጂዎች ሰፍረውበታል፤ ስሙም “ኤርጌንሳ” በሚል ተቀይሮ ሰዎች እየተስፋፉ ነው፤ ይሄ እንደ አማሮ ዞን አስተዳደሪነቴ አንገቴን የሚያስደፋኝ ነው” ይላሉ። እኔ  በማስተዳድረው፤ አማሮ ወረዳ፣ ስለ ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ የማወራበትም አንደበት የለኝም የሚሉት አቶ ወገኔ፤ በዚህ ፓርክ ዙሪያ እንዲህ አይነት  ለይስሙላ የሚደረጉ ስብሰባዎች መቆምና የማያዳግም መፍትሄ የሚያመጣ ስራ መስራት፤ በጉዳዩ ዙሪያ የምዕራብ ጉጂ ዞን አስተዳዳር አቶ ተፈሪን በስልክ ያነጋገርናቸው ሲሆን አስተዳዳሪው በሰጡት ምላሽ፤ “ችግሩ የፌደራል መንግስት ነው፤ ጥምር ስብሰባ እናድርግ፤ በችግሩ ላይ እንወያይ ብለን ብንጠይቅ ስብሰባ ማድረግ አልቻሉም። ስልክ ደውዬ  ስብሰባውን ለምን አታካሂዱም ብዬም ጠይቄያለሁ ስብሰባው ባልተካሄደበትና በችግሩ ዙሪያ በጋራ ባልተወያየንበት ሁኔታ በፓርኩ ዙሪያ የምሰጠው አስተያየት የለም። ስብሰባው በኮቪድ ምክንያት አልተካሄዱም የሚባለውን  አንቀበልም ፤ሌሎች ስራዎች ጥንቃቄ እየተደረገ እየተካሄደ ነው” ብለዋለል።
ስብሰባውንም የመሩት የኢትዮጵያ ዱር እንስሳትና ልማት ጥበቃ ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን፣ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሀኑ ዘውዴ፣ የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ም/ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ፍሬህይወት ዱባለና የፓርኩ ፅ/ቤት  ሀላፊ  በመጨረሻም በ2013 ፓርኩን ከንክኪ ነፃ ለማድረግ ቀጣይ ስራዎችና የጋራ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ፣ለ46 ዓመት መንገድ ያልነበረው ፓርኩ መንገድ ለማሰራት የዲይዛን ስራው አልቆ ጨረታ እየወጣ ስለመሆኑ ፓርኩ እስከ ዛሬ ፅ/ቤት ያልነበረው ቢሆንም፤ የፅ/ቤቱ ግንባታ ተጠናቆ ከሁለት ወር በኋላ እንደሚመረቅ፣ የስካውቶችን ቁጥር በመጨመር የተሻለ ጥበቃ እንዲደረግ እየተሰራና ለእስካውቶች በፓርኩ የተለያየ ቦታዎች ካምፕ እየተገነባ እንደሆነም፣ አብራርተዋል።
በፓርኩ ዙሪያ ሌሎች ግጭቶች እንዳይነሱም ከስሜታዊነት መውጣትና አላስፈላጊ ቃላቶች ከመጠቀም መታቀብ እንደሚገባ ይመክራሉ። ፓርኩን በምዕራብም በምስራቅም በመጠበቅ ህልውናቸውን ፓርኩ ላይ ያደረጉ ዜጎች አማራጭ ስራ የሚሰሩበትንና ፓርኩን የሚተውበትን መንገድ መፈለግ ይገባል ብለዋል።


Read 8664 times