Monday, 02 November 2020 00:00

ከካይሮ ዋሽንግተን የገባው ዛቻ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

   "ግብጾች ዓባይ የእነሱ ሕይወት ነውና ከስሩ ከምንጩ ጀምሮ ጥበቃው በረቀቀ ዘዴ ይደረግለት ጀመር፡፡ የግብጽ ጳጳስ፤ ዓባይ ቅዱስ ውኃ ነው፤ ፈዋሽ ነው፤ ስለሆነም ጸበል ነው። ከመጠመቅና አህል ሳይበሉ ከመጠጣት በስተቀር ጠላ አይጠመቅበትም፤ ጋን አይታጠብበትም ብለው አስከለከሉ፤ ገዘቱ፡፡ ግብጽ ሲደርስ ግን ሴቶች ግብር ውኃ ይወጡበታል፡፡ መንገድ ይታጠብበታል፡፡ አሸዋ ይቦካበታል፡፡ ልብስ ይታጠብበታል፡፡ የማያደርጉት ነገር የለም፡፡  በግብጽ ሰማዩ ተለጉሟል፤ ነገር ግን ዓባይ፣ የኢትዮጵያው ቅዱስ፣ በግብጽ ሁለገብ መለቃለቂያ ሆነ፡፡ . . .የአካበቢው ሰው ነገሩ እየገረመው፣ እህል በልቶ የማይጠጡት ውኃ ካጠገቡ ተቀምጦ፣ ለምላሱ ማራሻ ቢያጣ - የዓባይን ልጅ ውኃ ጠማው አለ፡፡ ዓባይ እንዳይባክንባቸው ልብሱን እንዳያጥብበት፣ ከመንፈሳዊ ሕይወቱ ከእምነቱ ጋር አያያዙበት፡፡ ምንኛ የከፋ ተንኮል ነው?"   "ጸ ጸ ት" - በለይኩን ብርሃኑ (ዶር)
       
          እኔም የእዚህ እውነት ተጋሪ ነኝ፡፡ ዓባይን በዋናተኛ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሻገርኩት  የአስራ አራት ዓመት ልጅ እያለሁ፣ ጥር 1953 ዓ.ም ነበር፡፡ ከጎጃም ወደ ወሎ ቦረና የተሻገርነው በአባራ መልካ ነው፡፡ አባራ መልካ  ከቢቸና የድኋ አልፎ በረሃው ውስጥ የሚገኝ መንደር ነው፡፡ የዓባይን ውኃ ጠበሉን ለመጠጣት በማለት ከአደርንበት ተነስተን  ጉዞ የጀመርነው እህል ሳንቀምስ ነበር፡፡ የዓባይን ውኃ ጠጥተንና በዓባይ ውኃ ገላችንን ታጥበን እህል የቀመስነው፣ እንዳይረክስ ወንዙን ከተሻገርን በኋላ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ይህ እምነት ስላለም ነው ደጀን መሻገሪያ ዓባይ ድልድይ፣ ሰዎች መኪናቸውን እያቆሙ፣  ወደ ወንዙ በመውረድ  ውኃ እየቀዱ የሚመለሱት፡፡
ኢትዮጵያ፤ ከግብጽ ብዙ እጥፍ የሚበዛ  የክርስትና እምነት ተከታይ ሕዝብም አላት። እንደ ታለፈ ሃሳብ ተቆጥሮ ፍትሐ ነገሥቱ ውስጥ በጭረት በገባ ‹‹ኢትዮጵያዊያን ከምሁራኖቻቸው የሃይማኖት አባት ጳጳሳት  አይሹሙ›› በሚል የሐሰት ድንጋጌ፤ የቤተ ክርስቲያንን መሪነት ጠፍሮ በመያዝ፣ ለ1600 ዓመታት ገዝተዋል፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ነፍስ ይማር፤ ከባርነቱ ተገላግለናል። ተክለውት በሄዱት ባህል ላይ ግን የነቃበት ሰው አለ ወይ?  እጠይቃለሁ፡፡
ኤርትራን ከእንግሊዝ የሞግዚት አስተዳደር ለማላቀቅ የዲፕሎማሲ ትግል በተጀመረበት ጊዜ፣ ግብጽ ወደ ኋላ ብትተወውም፣ በኤርትራ ላይ የይገባኛል ጥያቄ አንስታ ነበር፡፡ በኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር መዋሐድ የፈዴሬሽን ግንኙነት ሲፈርስ፣ እነ ዑስማን ሳልህ ሳቤ፣ የመሣሪያ ትግል ሲጀምሩ፣ የፖለቲካ ድጋፍ በመስጠት አልጀሪያ ገብተው ወታደራዊ ሥልጠና እንዲያገኙ የረዳቻቸው ግብጽ መሆኗን ብዙዎች ጽፈዋል፡፡ ጦርነቱ እስከተጠናቀቀበትና ኤርትራ ነጻ አገር እስከሆነችበት ጊዜ ድረስም ከጎኗ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡
ሕወሓት በበላይነት የሚመረው የኢሕአዴግ መንግሥት እየተዳከመ በሄደ ጊዜ፣ ‹‹ሕወሓት የሕዝብ መሠረቱ አነስተኛ ነው፤ ሰፊ ሕዝብ ያላቸውን ጸረ ምኒልክ የሆኑትን ኦሮሞ ተቃዋሚዎች ማገዝ አለብን.." ብለው እንደተነሱ በዚሁ ጋዜጣ ከወራት በፊት ጽፌ ነበር፡፡  ድምጻዊ  ሃጫሉ ሁንዴሳ በተገደለ ጊዜ የግብጽ መገናኛ ብዙኃን ጉዳዩን ያስተናገዱበት መንገድ ምን ተገኘ? የሚያሰኝ እንደነበርም ብዙዎች የታዘቡት ጉዳይ ነው፡፡
ግብጽና ኢትዮጵያ የጋራ ድንበር ስለሌላቸው በእግረኛ ጦር ይወሩናል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ይሁን እንጂ ከላይ በጠቀስኳቸው መንገዶች እየመጡ ተሸናፊ አድርገውናል፡፡ ይህ በር እንዴት ነው የሚዘጋው? መንግሥት መላ ሊፈልግለት ይገባል፡፡
የግብጹ ፕሬዚዳንት አልሲሲ፣ የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት የሚገልጧቸው ‹‹የሚመቸኝ አምባገነን (my favorite dictator)›› በማለት ነው፡፡ ሦስቱ አገሮች በሕዳሴ ግድብ ላይ በሚያደርጉት ድርድር፣ ግብጽ አሜሪካንን በታዛቢነት እንድትገባ ያደረገችው፤ ይህ ከውስጥ የመነጨ ፍቅር በመኖሩ ነው፡፡ የትራምፕ መንግሥት ከታዛቢነት ዘሎ ወደ ውል አርቃቂነት የተሸጋገረውም የግብጽን ፈቃድ ለመፈጸም ነው፡፡ በዚህ አይቆምም፤ አሜሪካ የመካከለኛውን ምሥራቅ ፖለቲካ ሙቀቱንም ቅዝቃዜውንም የምትለካው በግብጽ ክንድ በመሆኑ ይህን መሣሪያነት መጠበቅ የሚቻለው እንዲህ ያለውን አጋጣሚ በመሞረጃነት ለመጠቀም አገልግሎቱን በማቅረብ መሆኑን  የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይረዳሉ፡፡ ‹‹ ሌላ አማራጭ የላትም፤ ግብጽ የሕዳሴውን ግድብ ልታፈነዳው ትችላለች›› ሲሉ የተናገሩት  ለግብጽ ያላቸውን ታማኝነት  ለማረጋገጥ ነው፡፡
‹‹የዓባይ ውኃ ከተነካ በኢትዮጵያ ላይ እሳት እናዘንባለን›› የሚለው ዛቻ፣ ከግብጹ ፕሬዚዳንት ሳዳት ጀምሮ ያለማቋረጥ ሲሰማ የዘለቀ ነው፡፡ አዲሱ ነገር ዛቻው ከካይሮ ተነስቶ ዋሽንግተን መግባቱና በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አንደበት መነገሩ ነው፡፡ የኬኒያው ኬንያ እስታር  የተሰኘ  ጋዜጣ፤ ‹‹ኢትዮጵያ በአሜሪካ ተከዳች›› ሲል ነው ስለ ሁኔታው የዘገበው፡፡ ከሁለት ወር በፊት ድርድሩን ጥላ የወጣችው ግብጽ መሆኗ እየታወቀ፣ ኢትዮጵያ በአደናቃፊነት መከሰሷ፣ ቀድሞ መግለጫ ካለመስጠት የተፈጠረ ችግር ነው  ብዬ አምናለሁ፡፡ ጉዳዩ የሚመለከተው ክፍል አጥብቆ ሊያስብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
አሜሪካ ያሰናዳችውን ውል የፈረመችው ግብጽ ብቻ ናት፡፡ ሱዳን ውሉን እንዳልፈረመች ቢታወቅም፣ በትራምፕ የተከሰሰችው ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ በሶስቱ አገሮች መካከል መተማመን ለመፍጠር ስትል፣ የሕዳሴ ግድብ ሥራ እንደተጀመረ፣ ኢትዮጵያ የግድቡን ዲዛይን ጨምሮ  ስለ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሚያስረዱ 150 ልዩ ልዩ ሰነዶች ለግብጽ፣ ለሱዳንና ለዓለም አቀፍ ኤክስፐርቶች (IPOE) አድርሳለች፡፡  የኤክስፐርቶች ቡድን የቀረቡለትን ሰነዶች መርምሮ የደረሰበትን መደምደሚያ ሃሳብ፣ ኢትዮጵያ ተቀብላ እየሠራችበት መሆኑም ይታወቃል፡፡
በዓለም አቀፍ ኤክስፐርቶች ቡድን ውሳኔ  አባልነታቸው ከግብጽ ዶ/ር ሸሪፍ ሞሐመዲን አልሰይድ፣ ከሱዳን ዶ/ር አሕመድ አትያ አሕመድ በፊርማቸው ያጸደቁት ቢሆንም፣ ሱዳንና ግብጽ  በየጊዜው ወቀሳ የሚደረድሩት ምንም እንደማያውቅ ሆነው ነው፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ  የማባበል ዘመን አብቅቷል ልትላቸው ይገባል፡፡
በእኔ እምነት፤ ከካይሮ ዋሽንግተን የገባው ዛቻ፣ መልስ ሊሆን ይገባል፡፡ "በፈለግህበት መንገድ ና፤ እኛም እንጠብቅሃለን.". ነው ያሉት እትጌ ጣይቱ ብጡል? ወደ ኋላ መመለስ የለም፡፡

Read 3461 times