Print this page
Saturday, 31 October 2020 12:35

የ368 ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መታሰቢያ ሐውልት - በላምፔዱሳ

Written by  ቀናው ገብረስላሴ
Rate this item
(0 votes)

  (ኦክቶብር 3፣ 2013 ባህር ውስጥ ሰምጠው የረገፉ ወገኖች)
                     
            ይህ የበርካታ ኤርትራዊያንና የጥቂት ኢትዮጵያውያንን ስሞችን እንደ ጥንግ ድርብ ለብሶ በብረትና በእንጨት የተዋቀረ፣ ከስሩ ሜድትራኒያን ባህርን እንዲወክል ሰማያዊ ግምጃ መሳይ ቅብ የተነጠፈለት ሐውልት፤ በጣሊያን የጠረፍ የባህር ዳርቻ በምትገኘው ላምፔዱሳ በምትባል ከተማ ላይ የቆመ ገመናችን ነው፡፡ ተስፋሂዎት ሀዲሽ፣ ሔለን ጊላይ፣ ሚካኤል ዘርአይ፣ ወልዳይ ፈቃዱ፣ አማን አስገደ፣ ነአምን ተክላይ፣ ዮርዳኖስ ሽሻይ፣ ካህሳይ ሀብቴ፣ መርሃዊት … … … ይርጋለም ኢትዮጵያ … … … እያለ የስም ዝርዝሩ ይወጣል ይወርዳል፡፡
ከሰባት ዓመት በፊት በያዝነው ወር ኦክቶብር 3፣ 2013 የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወይም የመንግስታቸው ግፍ አንገፍግፏቸው፣ በሌላም ምክኒያት ከሀገራቸው የተሰደዱ፣ ባህር ውስጥ ሰምጠው የረገፉ ወገኖች - 368 ስደተኞች መታሰቢያ ሐውልት፡፡ አምና በዚህ ወር 6ኛ ዓመታቸው ሲዘከር ለመታሰቢያቸው ይሆን ዘንድ የቆመ ሐውልት ነው፡፡
እነዚህ ወገኖቻችን ሲታሰቡ፣ ስም ዝርዝራቸው በጉልህ የታተመበት ሐውልት ሲመረቅ፣ እዚያው ከሜድትራኒያን ባህር በቅርብ ርቀት ቆሜአለሁ፡፡ በደረቁ ሌሊት ከሰፊውና ከጥልቁ ባህር ለመውጣት፣ ለመትረፍ ታግለው… ጓጉጠው…ተወራጭተው ይህችን ዓለም የተሰናበቱባት ሰዓት ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ስለነበር የሐውልቱ ምረቃም በዚሁ ሰዓት እንዲከወን ተደረገ፡፡ ያችን የሞት ሽረታቸውን፣ ህልፈታቸውን ለማሰብ በተሰናዳው የሌሊት ፕሮግራም ላይ ለጉድ ተገትሬ፤ ለጉድ ታድሜ በሐዘን ተኮራምቻለሁ፡፡ የባህሩን ወጀብ፣ የሌሊቱን ፅልመት፣ ስቃያቸውን ለአፍታ እንድናሰላስል ታስቦ በሐውልቱ ዙሪያ የበሩ መብራቶች ሁሉ እንዲጠፉ ተደረገ፡፡ ምንም አይነት ድምፅ እንዳይሰማ ሆነ፡፡ ቀድሞ በተበላው አንጀቴ ላይ አንጀት የሚበላ እንጉርጉሮ፣ ዋሽንት መሳይ ነገር በቀጭኑ ተለቀቀ፡፡
የህሊና ፀሎቱን ተከትሎ ያኔ በነብስ ግቢ-ነብስ ውጭ ጭንቅ ውስጥ እያሉ፣ በአሳ አስጋሪዎች እገዛ በተዓምር ተርፈው በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች ይኖሩ የነበሩ ኤርትራዊያን ወጣቶች በትግርኛ ትውስታቸውን አካፈሉ፡፡ በእንግሊዝኛና በጣሊያንኛ ተተረጎመልን፡፡ በሌሊት የነብሳችንን አድኑን ጩኽት ሰምተው፣ ደርሰው የተወሰኑ ልጆችን ከሞት የታደጉ አሳ አስጋሪዎች ታግለው ካተረፏቸው ልጆች ጋር ከስድስት ዓመታት በኋላ ተገናኝተው ተላቀሱ፣ ተመሰጋገኑ…ያኔ የነበረውን አስከፊ እውነት አወጉ፡፡
እነዚያ አገር ያላቸው፣ ቤተሰብና ወገን ያላቸው፣ ስም ያላቸው…ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን ለላምፔዱሳ ነዋሪዎች፣ ለጣሊያንና ለመላው አውሮፓ ህዝቦች ቁጥር ብቻ ነበሩ፡፡ በሞታቸው ዕለት በቁጥር ተለይተው የሆነ ታዛ ላይ የተቀበሩ ወጣት ወንዶች፣ ሴቶችና ህፃናት፤ አገር እንደሌላቸው፣ ወገን ቤተሰብ እንደሌላቸው፣ ስም እንደሌላቸው በስም የለሽ መቃብር በላምፔዱሳ ደሴት ተበታትነው አረፉ፣ ለዚያውም አስከሬናቸው ተገኝቶ ለቀብር የበቁት - የዛሬ ሰባት ዓመት በኦክቶበር 03 (በሐውልቱ ላይ ያረፈው ስማቸው በኋላ በሕይወት ከተረፉ ጓደኞቻቸው፣ ዘመድ አዝማዶቻቸው ተጠይቆ የተሰበሰበ ነው)፡፡
በእነዚህ ወገኖቻችን የሞት ሰልፍ፣ የስም ዝርዝር ግርጌ አንድ ስም ጎልቶ ይታየኛል - ‘ይርጋዓለም ኢትዮጵያ’ ይላል። ኢትዮጵያዊ፣ በፆታ ሴት ትመስለኛለች - እርግጠኛ አይደለሁም - መረጃ ጠይቄ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ በጥቅል ሁሉም ኤርትራዊያን ናቸው ያኔ ያለቁት የሚል ብቻ ነው ከብዙ ሰዎች የተነገረኝ፡፡ በሕይወት ከተረፉ፣ በዚህ በፎቶው ላይ ከሚታዩት፣ ለአጭር ጊዜ እድሉን አግኝቼ ያነጋገርኳቸው፣ ኤርትራዊያን እንዲሁም ወደ ስምንት የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንና ሁለት-ሶስት የሌላ አገር ዜጎች አብረዋቸው እንደተጓዙ፣ እንደሞቱም ነግረውኛል)፡፡
‘ይርጋለም ኢትዮጵያ’፤ ከ500 በላይ ስደተኞችን ይዛ ከሊቢያ ጠረፍ ተነስታ ወደ አውሮፓ ለመሻገር በምታዘግመው ጀልባ ውስጥ ከተጓዙት ውስጥ አንዷ ነበረች፡፡ ስደተኞቹ ከብዙ እንግልት በኋላ፣ ከስንት ሰቆቃ በኋላ ገና ከሀገራቸው ሲነሱ ያልሟት ወደ ነበረችው አውሮፓ ለመሻገር ተቃርበዋል። እኩለ ሌሊቱ አልፎ ወደ ንጋት መዳረሻ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ሆኗል። አብዛኛውን መንገዳቸውን አገባደዋል፡፡ የሰሀራ በርሃን ውጣ ውረድ፣ የሜድትራንያንን ባህር ወጀብ፣ ቅዝቃዜ፣ ጥሙንና ርሃቡን ችለው አልፈዋል፡፡ ገንዘባቸው፣ አቅማቸው፣ ትእግስታቸው ተሟጦ የጣሊያንኗን የወደብ ከተማ፣ የመጀመሪያዋን የስደተኞች መዳረሻ፣ የአውሮፓ በር  (Gate of Europe) ተብላ የምትታወቀውን ላምፔዱሳን ከቅርብ ርቀት እያይዋት ነው፡፡ ምን አልባትም በጉዟቸው ብዙ ከአገራቸው አብረዋቸው የወጡ ጓደኞቻቸውን፣ አብሮ አደጎቻቸውን፣ ምን አልባትም እህት ወንድሞቻቸውን ጨምሮ መንገድ ላይ አፈር አልብሰው፣ በህገ-ወጥ ደላሎች፣ በወንበዴዎች ተነጥቀውም ይሆናል እዚህ የደረሱት፡፡
የከተማዋን መብራቶች አሻግረው እያዩ ነው፤ ግን አሁንም ባህሩ ላይ ናቸው - ጀልባዋ ውስጥ፣ በጀልባዋ ጠርዝ ዳርና ዳር፣ ከላይም ከታችም ተደራርበዋል፡፡ ሳግ፣ እንባ፣ ደስታ…ሌላ ተስፋ… በተዘበራረቀ ስሜት ውስጥ ናቸው፡፡ ንጋቱ ናፍቋቸዋል፣ መሬቷን መርገጥ ጓጉተዋል፡፡ አውሮፓ መግባታቸውን ብቻ አለሙ እንጅ፤ ገንዘባቸውን፣ ላብ-ወዛቸውን አፈሰሱ እንጂ እዚያ የሚገጥማቸውን የስደት ሌላ ዙር ውጣ-ውረድን፣ መገፋት፣ መሸማቀቅና መዋረድን አላሰቡም፣ አላወቁም፡፡ ገንዘባቸውን አሟጠው በወሰዱባቸው ህገ-ወጥ አሸጋጋሪዎቻቸው የተነገራቸው ብቻ ይሆናል ውስጣቸው የሚመላለሰው፡፡ ምናልባትም ከእነሱ በፊት በርሃውን ማቋረጥ፣ ባህሩን መሻገር ቀንቷቸው አውሮፓ በገቡ ጓደኞቻቸው የተሰጣቸው የተፋለሰ መረጃ ብቻ ይሆናል በውስጣቸው የሚወጣ የሚወርደው፡፡  
ጀልባዋ ወደ ላምፔዱሳ የባህር ዳርቻ ለመጠጋት ትንፏቀቃለች፡፡ የጀልባዋ አሽከርካሪ ወደ ወደቡ መጠጋት አልፈለገም፣ በፍፁም በፖሊሶች መያዝ አይፈልግም፣ በህገ-ወጥ መንገድ ስደተኞችን በማመላለስ፣ ባህር ላይ ደፍቶ በማምለጥ በጣሊያን የባህር ጠባቂዎች (Coast Guards) ስሙ ተመዝግቦ የተያዘ፣ የሚፈለግ ሰው ነው። እናም የጀልባዋን መሪ ለረዳቱ ሰጥቶ፣ ከተሳፋሪ ስደተኞች መሀል ተቀላቅሎ ቁጭ አለ፡፡ ረዳቱ አሽከርካሪ አልቻለም፤ ሲደናበር የጀልባዋን የሆነ ነገር ነካ፣ የጀልባዋ ሞተር እክል ገጠመው፡፡ ጀልባዋ ባህር ላይ እየተወዛወዘች ቆመች፡፡ ግራ የገባው ረዳት፤ በዚያ ድቅድቅ ጨለማ ሊታደጓቸው የሚችሉ ሰዎች ከሩቅ እንዲያዩአቸው፤ ድረሱልን ለማለት ምልክት ሆኖ ባህሩ ላይ እንዲያበራ ጋዝ የተነከረ የፎጣ ቁራጭ አቀጣጥሎ ወደ ባህሩ ሊወረውር ሲዘጋጅ፣ የተቀጣጠለው ፎጣ፣ ፎጣውን በያዘው እጁ በኩል ወደ ልብሱ ተሸጋገረበትና በድንጋጤ ወርውሮ የጀልባዋ ወለል ላይ ጣለው፡፡ የጀልባዋ ወለል በእሳት ሲያያዝ፣ ስደተኞቹ ከእሳቱ ለማምለጥ ወደ መርከቧ አንደኛው ጎን ግር ብለው ተሰባሰቡ፤ ተደራረቡ፤ ጀልባዋ ወደ አንድ ጎን አጋድላ ከፊል አካሏ ወደ ባህሩ መውረድ ጀመረ፡፡ ሁሉም የራሱን ሕይወት ለማትረፍ ግብግብ ውስጥ ገባ፡፡ በዚያ ደረቅ ሌሊት፣ በዚያ ቆፈን አሻግረው የሚያይዋትን የ’ተስፋቸውን ምድር’ ሳይረግጡ ወደ ጥልቁ ባህር ሰረጉ፣ አለቁ (ያነጋገርኳቸው በህይወት የተረፉ ኤርትራዊያን እንደነገሩኝ)፡፡
አሻግረው ከሚያይዋት የድንበር ከተማ ለመድረስ የጓጉት፣ ተሻገርን - በቃ - አለቀ - ገባን - ብለው ለእፎይታ፣ ለእልልታ የተዘጋጁት ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን የስደት ጎደሎ ቀን እዚህም ተከትሏቸው መጣ፡፡ እልልታቸው ከአፋቸው ተነጠቀ፣ እፎይታቸው በሞታቸው ተደመደመ፡፡ 368 ስደተኞች ረገፉ፡፡ ዓለም አቀፍ ሚዲያው ይሄንን የስደት ሰቆቃ፣ ከዳር ዳር እየተቀባበለ አስተጋበው፡፡ እለቱም በስደተኞች እልቂት ታሪክ የተለየ ተደርጎ በየአመቱ በኦክቶበር 03 በጣልያንንና በሌሎች የአውሮፓ ከተሞች ይዘከራል፣ ይታሰባል፡፡ ዘንድሮም በቅርቡ የቢቢሲው የአማርኛ ዜና “ስደት፡ የኤርትራውያን ዋይታ የተሰማባት ላምፔዱሳ” በሚል ርእስ ስር እንዳተተው፣ በህይወት የተረፉ ኤርትራዊያን ወደ ላምፔዱሳና ወደ ሌሎች የጣሊያን ድንበር ከተሞች  ከተማ ብቅ ብለው ጓደኞቻቸው፣ ወገኖቻቸው ባረፉባቸው ስም በሌላቸው የመቃብር ቦታዎች ላይ አበባዎችን በማስቀመጥ አስበዋቸዋል፡፡  
የላምፔዱሳውን መታሰቢያ ሐውልት የቀረፀው ጣሊያናዊው ቪቶ ፊዮሪኖ፣ ከሐውልቱ አጠገብ አንዲህ ብሎ ፅፏል፡-  “ያለ ስም በቁጥር ብቻ ተለይተው፣ በቁጥር ብቻ ተሰይመው፣ በተለያዩ የመቃብር ቦታዎች ለተቀበሩት፣ በዚያች የእልቂታቸው ምሽት በነፈግናቸው መታደግ ዘላለም ለጨለመባቸው ለእነዚህ የሰው ዘሮች፣ ወንዶች፣ ሴቶችና ህፃናት ስም መስጠት እፈልጋለሁ፡፡”
እነዚህ ኤርትራዊያንና ኢትዮጵያውያን በሚታሰቡበት በዚህ የሐውልት ምረቃ ላይ መሪዎቻችን እንደኔው ታድመው ቢሆን ኖሮ ምን ይሰማቸው ነበር? ስል እጠይቃለሁ፡፡ እነሱ ከሚመሯቸው፣ ከሚያስተዳድሯቸው አገራት የተሰደዱ ግን ሳይሳካላቸው ባህር የበላቸው የዜጎቻቸው መታሰቢያ ሐውልት ፊት ተገትረው ሲያስታውሷቸው ምን ይሉ ይሆን? ብዬ አስባለሁ…፡፡ ምናልባት ቪቶ በእልቂታቸው ምሽት ሊታደጓቸው ሲችሉ ግን ያልደረሱላቸውን የጣሊያን የባህር ጠባቂዎችን፤ የጣልያን ባለስልጣናትን… እንደወቀሰው፣ እነሱም ፊት ለነሷቸው ዜጎቻቸው አገራቸው ላይ ሰርተው በሰላም የሚኖሩበትን ሁኔታ ባለማመቻቸታቸው ይፀፀቱ ይሆን? ስል አወጣለሁ አወርዳለሁ፡፡

 --- በስደት ካለቁት ዝርዝር ‘ይርጋለም ኢትዮጵያ’ አለች---
‘ይርጋለም ኢትዮጵያ’ እራሷን ኢትዮጵያን ትመስለኛለች፤ የኢትዮጵያ ውክልና አላትና። ሁላችንም በክፉም ሆነ በበጎ፣ በውርደትም ሆነ በሽልማት፣ በስደተኛነት ተመዝግበንም ሆነ በአምባሳደርነት ተሹመን፣ በሀዘናችንም ሆነ በደስታችን…ኢትዮጵያን ለማስጠራት፣ ለማስነሳት ውክልና አለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ‘ይርጋለም ኢትዮጵያ’ አገራቸው ላይ ረግተው ለመኖር ምክንያት ያጡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የምትወክል ይመስለኛል፡፡ የዛሬ ሶስት ዓመት አካባቢ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናት ማዕከል ውስጥ  ‘አገሬ ላይ እንድቆይ ምክንያት ስጡኝ (Give me a reason to stay)’ በሚል በስደት ላይ አተኩሮ በተሰናዳ የፎቶግራፍ አውደ-ርእይ ላይ መገኘቴ ትዝ ይለኛል፡፡ ዛሬም ለብዙ አገራቸው ላይ ለመኖር ምክንያት ላጡ በሊቢያ በርሃ፣ በየመን ጠረፍ፣ በሳውዲ እስር ቤት፣ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሻገር……ፍዳ ለሚያዩ፣ በየመንገዱ ለሚረግፉ ወገኖቻችን ማሳያ ወካይ ትመስለኛለች - ይርጋለም ኢትዮጵያ…ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ይዛ የተንከራተተች ስደተኛ፣ ታሪኳ በጊዜ በሞት የተደመደመ ምስኪን፡፡
ኢትዮጵያዊው አበበ ቢቂላ የማራቶንን ድል በተቀዳጀበት በጣልያን ምድር፣ አሁንም ድረስ ስሙ በዝና በሚነሳበት ምድር፣ በስሙ ድልድይ (PONTE ABEBE BIKILA) በተሰየመባት አገር - ‘ይርጋለም’ ስም የለሽ ስደተኛ ሆና በቁጥር ተሰይማ፣ በዚያው በጣልያን ምድር ከሌሎች የሀገሯ ልጆችና ኤርትራዊያን ወገኖቿ ጋር አርፋለች፡፡ አዎ ‘ይርጋለም ኢትዮጵያ’ እራሷ ኢትዮጵያን ሀገሬን  ትመስለኛለች፣ በጀግኖቿ፣ በህዝቦቿ ክንድ ወራሪውን ጣልያንን ድል ነስታ ያባረረች፣ በዚያም የምትኮራ ሀገሬ፣ ዛሬ ለስደት የተንበረከከች፤ በስደት ባህር የበላት ኢትዮጵያን፣ የሊቢያ በርሃ፣ የሳውዲ አረቢያ እስር ቤት ያነደዳት አንጀት የምትበላ ኢትዮጵያን ትመስለኛለች፡፡
ትላንት በሳውዲ አረቢያ ከ16ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን፣ #የኮቪድ-19 በሽታን ታሰራጫላችሁ; በሚል በታጎሩበት አሰቃቂ እስር ቤት፣ እራሱን ሰቀሎ የገደለው የ16 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ አዳጊ ወጣት፣ የምንጠራበት ወካያችንን ነው፡፡ በዚህ ሁሉ መከራ አንገታችንን ቀና አድርገን “ከየት ነህ አትበሉኝ ይናገራል መልኬ…” ብሎ ዘፍንን (ናቲ ማን)፣ “አያውቁንም እኛን አያውቁንም…” ብሎ ሙዚቃን (አብነት አጎናፍር ) እንዴት ደፍሮ መዘመር ይቻላል? ይሄንን ባቀነቀንን ማግስት ማቁ፣ ሰቀቀኑ የሚከተለን ህዝቦች እኮ ነን፡፡

… ኤርትራዊያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን…   
ለሀገሬ ልጆች አድልቼ አብዝቼ ጮኽኩ እንጂ፣ በዚያች የላምፔዱሳ የጀልባ እልቂት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ኤርትራዊያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ነበሩ፡፡ እነ በረከት ተወልደ፣ እነ ደሊና መሃሪ (ጓል ሔለን)፣ እነ ገብሩ ፍስሃየ… እነ ፍሊሞን….እነ አማን ሀጎስ፣ እነ ሀበን ተስፉ፣ ለምለም አርአያ……ኤርትራን፤ ኤርትራዊያንን ወካይ ናቸው፡፡ በላምፔዱሳ ቆይታዬ ከሞት ተርፈው ጓዶኞቻቸውን ለማስታወስ የተገኙ ኤርትራዊያን፤ እነዚያ የሰቆቃ ጊዜያት አልፈው በዚሁ ጓደኞቻቸውን፣ ወገኖቻቸውን በተነጠቁበት ሜድትራኒያን የባህር ዳርቻ ቆመው ፎቶ ሲነሱ አየኋቸው።  የያኔውን አስጨናቂ የሰቆቃ ሌሊት፣ ከሞት ጋር የተደረገን ግብግብ እያስታወሱ…በሞት ያጧቸውን ወገኖቻቸውን እያነሱ ለመርሻ ሳይሆን ለማስታወሻ ፎቶ ይነሳሉ…በሀዘንና በተስፋ፡፡ ከአንዳንዶቹ ጋር አብሬ ፎቶ ተነሳሁ፡፡  
ትዝታው፣ ሀዘኑ የሞቱ ወገኖቻቸውን ቆጥረው፣ ስም ሳይሆን ቁጥር ሰጥተው ከቀበሯቸው ሰዎች ቢወጣ እንኳ ከእነሱ ሊወጣ አይችልም፡፡ እንባቸውን ሊያብስላቸው የሚችል አንዳች ነገር ተለውጧልን? የለም! ዛሬም የወገኖቻቸው ኤርትራዊያን ስደት፣ ሞት አለ፡፡ ዛሬም ኤርትራዊያን እናቶች በስደት ያለቁ፣ የጠፉ ልጆቻቸው ይመጣሉ እያሉ ይጠብቃሉ…፡፡ ይሄንን ያውቃሉ፡፡ ዛሬም ለስደት የተዘጋጁ፣ እንደ ኢትዮጵያና ሱዳን ባሉ የመሸጋገሪያ አገሮች የመሸጉ፣ ገና እጣ ፈንታቸውን ያላወቁ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት ኤርትራዊያን አሉ፡፡ ስንቶቹ ተሳክቶላቸው ወደ አውሮፓና አሜሪካ… ይሻገራሉ? መሻገር ብቻውን፣ መድረስ ብቻውን ስኬትስ ነውን? ሙሉ ነውን?
ተሳክቶላቸው ድንበር የተሻገሩ፣ ያልተሻገሩ የወንድምና እህቶቻቸውን ሐዘን ይዘው ይዘልቃሉ (በዚህ ፎቶ ላይ የወንድሙን ስም በሀዘን አተኩሮ የሚያየውን ወጣት ልጅ ልብ ይሏል)። በጎደሎ ስኬት፣ ባልተሟላ የስደት ኖሮ ይዘልቃል፡፡ በእያንዳንዷ የኤርትራ ጎጆ ስደት የተከለው ሐዘን አለ፡፡ ምናልባትም ከ2013 በኋላ 368ቱ በብዙ መቶዎች ተባዝተው፣ ሀዘን የብዙ ኤርትራዊያንን በር እንኳኩቶ ይሆናል። ምን አልባትም ከጎጆዎች ከፊሉ አሁንም ልጆቻችን በህይወት አሉ ብለው የሚጠብቁ እናቶች ይኖራሉ፡፡
ከዚያ ከ2013ቱ አሰቃቂ እልቂት እስከ 2019 (በፈረንጆች) ብቻ ከ18ሺ በላይ ሰዎች በሜዲትራኒያን ባህር ሰጥመው ህይወታቸው አልፏል፡፡ ይሄ ሰቆቃ አሁንም አላባራም፡፡ በዚህ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ ዓለምን በሚያስጨንቅበት ወቅት እንኳ ሊያባራ አልቻለም፡፡ በሺህ የሚቆጠሩ አፍሪካዊያን ስደተኞች ባህር አቋርጠው አውሮፓ ዘልቀዋል፡፡
እንደ አልጀዚራ ዘገባ፤ በፈረንጆች አቆጣጠር በዚህ ዓመት፣ እስከ ኦገስት 30 ድረስ ከ8ሺ በላይ ቱኒዚያውያን፣ ሜድትራኒያንን አቋርጠው ጣሊያን ደርሰዋል፡፡ በዚሁ የፈረንጆች ዓመት ኦገስት 30 ብቻ የጣልያን ፖሊሶች፤ ከ360 በላይ ስደተኞችን ላምዱፔዱሳ ባህር ዳርቻ ከሞት ታድገዋል፡፡
በስደት በተለያዩ አገራት የሚገኙት አፍሪካዊያን - በርካታ ኢትዮጵያውያን ጨምሮ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ይነገራል፡፡ በተለይ ለኮሮና ቫይረስ ስርጭት መንስኤ ትሆናላችሁ ተብለው በአሰቃቂ እስር ቤት ሰቆቃ ውስጥ ያሉ ከ16ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጉዳይ፣ በታላላቅ አለም አቀፍ ሚዲያዎች ሲዘገብ ቆይቷል…፡፡ በቅርቡ በጅቡቲ አቅራቢያ ያለቁና የገቡበት የጠፉ ኢትዮጵያውያን የትላንት ትኩስ ሐዘናችን ናቸው፡፡
የስደተኞች መነሻ አገራት ምን እያደረጉ ነው? ምን ድርሻ አላቸው? እውነት ድርሻቸውን ከአንጀት እየተወጡ ነው?  የሚለውን በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ….
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 3598 times