Saturday, 07 November 2020 13:16

ያልታሰበው ክስተት በትግራይ የቱ ይቀላል? ውይይት ወይስ ጦርነት?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

   “በጦርነት ዘላቂ ሠላም መጥቶ አያውቅም”           (ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ፤ አንጋፋ ፖለቲከኛ)

          በአገራችን ብዙዎች እንዳይከሰት ሲፈሩት የነበረው ጉዳይ ሰሞኑን እውን ሆኗል፡፡    የህወሃት ቡድን በትግራይ በሰፈረውና ህዝቡን ከ20 ዓመታት በላይ ሲጠብቅ በቆየው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ያነጋገራቸው ያስታወቁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ይህን ተከትሎም መንግስታቸው ህዝብንና አገርን ለማዳን ወደማይፈልገው ጦርነት እንዲገባ መገደዱን ገልፀዋል፡፡  ከዚህ በኋላም ከህወኃት ቡድን ጋር ውይይትና ድርድር እንደማይኖር ነው ጠ/ሚኒስትሩ ያስታወቁት፡፡ አሁንም ግን ከውጭም ከውስጥም ከሃይል ይልቅ ለውይይትና ንግግር ቅድሚያ እንዲሰጥ የሚወተውቱ ወገኖች አሉ፡፡
የአዲስ አድማሱ አለማየሁ አንበሴ ያነጋገራቸው ሁለት አንጋፋ የትግራይ ፖለቲከኞች ተጠቃሽ ናቸው ሃሳባቸውን እነሆ፡-

           ግጭትና ጦርነት ለማንንም ወገን ተጠቃሚ አያደርግም፡፡ በጦርነት የሚፈታ ችግር ውጤቱ ያማረ አይሆንም፡፡ ጦርነት በምንም መንገድ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ሆኖም አያውቅም፡፡ ችግሩ የፖለቲካ እንጂ የውጭ ሃይል ጉዳይ አይደለም፡፡ አሁንም ቢሆን በሆነ መልክ ሁኔታው መቋጨት አለበት፡፡ የትግራይም ይሁን በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ችግር በንግግርና በውይይት መፈታት አለበት ባይ ነኝ፡፡
ኢትዮጵያን በአጠቃላይ ለማረጋጋት ከተፈለገ፣ መነጋገርና መቀራረብ ነው ጠቃሚው። በሃይል የሚመጣ መረጋጋት በባህሪው ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ ውጤትም አይኖረውም። በውይይትና በመነጋገር የሚመጣ ሠላም ነው ዘላቂ ሊሆን የሚችለው፡፡ የትግራይ አስተዳደር ምን ፈልጐ ጦርነት ውስጥ እንደገባ አይገባኝም፡፡ ነገር ግን ሁለቱም አካላት አስቀድሞ መነጋገር ቢችሉ ይሄ ሁሉ ችግር ባልተፈጠረ ነበር። ህወኃቶች ጦርነቱን ለምን እንደፈለጉት ባናውቅም፣ በጣም ይወተወቱ ነበር፡፡
እንግዲህ ውጤቱን ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡ ሲነዛ የነበረው ፕሮፓጋንዳ ጦርነቱ አይቀሬ እንደነበር ነው የሚያሳየው፡፡ ያው የፈለጉት ሆኖላቸዋል፡፡ መጨረሻው ምን እንደሚሆን አይታወቅም።
በጦርነት ዲሞክራሲ መጥቶ አያውቅም። ስለዚህ በሀገሪቱ ያሉ የሲቪክ ተቋማት፣ የእምነት አባቶችና፣ የሀገር ሽማግሌዎች በትግራይ ክልላዊ መንግስትና በፌደራል መንግስት መካከልም እንዲሁም በአጠቃላይ በሀገሪቱ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች በእውነተኛ ሀገራዊ ውይይት እንዲፈታ ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡
ሁሉም ወገኖች ወደ ውይይት እንዲመጡ ጥሪ ማቅረብ እንጂ በሁለቱም ወገን “ግፋ በለው” ማለት አያዋጣም፡፡ ሁላችንም ሀገር እንዲረጋጋ ነው መጮህ ያለብን፡፡ ለሁሉም ወገን የሠላም ጥሪ ነው እንደ ዜጋ ማቅረብ የምፈልገው፡፡
ሀገር ማዳን የሚቻለው በጦርነት አይደለም፡፡ ጦርነት አዋጭ የሚሆነው የውጭ ወራሪን ለመመከት ሲሆን ነው፡፡ በፖለቲካ ልዩነት ሳቢያ የሚደረግ ጦርነት ውጤቱ የተወሳሰበ ነው፡፡ ሁላችንም ይሄን በአስተውሎት ማጤን አለብን፡፡

Read 1863 times