Tuesday, 10 November 2020 00:00

ፈተና በዝቶ፣ የመስከን ፋታ ያጠራት አገር፡፡

Written by 
Rate this item
(7 votes)

 የዚህች አገር ፈተና ስፍር ቁጥር አለው? ድህነትና ስራ አጥነት፣ የኢኮኖሚ ቀውስና የኑሮ ውድነት፣ ምኑ ይነገራል? እነዚህ የምዕተ ዓመት ችግሮችና ሌላው ሁሉ ባይኖር እንኳ፣ አመጽና ሥርዓት አልበኝነት፣ ግድያና ጦርነት ሳይጨመርበትም፣
በሕዳሴ ግድብና በአባይ ወንዝ ላይ፣ ከግብጽ መንግስት የሚጋረጥብን አደጋ፣ …ለኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና ነው፡፡
አሳዛኙ ነገር፣ ከዚያ በፊትም፣ ከዚያ በኋላም፣ ኢትዮጵያ - ከፈተናዎች ትንሽ ፋታ አለማግኘቷ ነው፡፡ ፈተናዎቿ በዝተዋል፡፡ ከመብዛታቸውም መክበዳቸው፡፡
ነባር የኑሮ ችግርና የዋጋ ንረት፣ ነባር የስራ አጥነትና የውጭ እዳ .
ሳያንስ፣ የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ተጨምሮበታል፡፡ የአገር ኢኮኖሚ ተዳክሞ፣ የብዙ ዜጐች ኑሮ ተጐሳቁሏል፡፡ መንግስት፣ ከሌሎች በርካታ አገራት በተሻለ መንገድ፣ የምርትና የንግድ እንቅስቃሴዎችን ከመከርቸም ስለተቆጠበ እንጂ፣ ወረርሽኙን ለመከላከል በስክነትና በጥንቃቄ ለመስራት ስለወሰነ፣ የባሰ ጉዳት በደረሰብን ነበር፡፡
ለነገሩ፣ ካወቅንበትና በቅንነት ከተጋንበት፣ በተፈጥሮ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ማሸነፍ አያቅተንም፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው? ከውጭ በኩል ከሚሰነዘሩ አደጋዎች ይልቅ፣ በአገር ውስጥ የምንፈጥራቸው ችግሮች ይበልጣሉ። በተፈጥሮ ከሚከሰቱ እክሎች ይልቅ፣ በየጊዜው በገዛ ምርጫችን፣ የምንወልዳቸው ፈተናዎች ይብሳሉ፡፡
በአላዋቂነትም፣ በቀሽም ብልጣብልጥነትም፣ በክፋትም የተነሳ የምንፈለፍላቸው ቀውሶች፣ የምንለኩሳቸው ጥፋቶች፣ የምናዛምታቸው የፖለቲካ በሽታዎች፣ በዓይነትና በቁጥር መብዛታቸው ነው፤ አገሪቱን ፋታ የነሳት። ካሁን በፊት ያከማቸናቸውና ቀን ከሌት በገፍ የምንፈጥራቸው ችግሮች፤ ለስፍር ለቁጥር ያስቸግራሉ፡፡
እንደዚያ ባይሆን ኖሮ፣ በተፈጥሮ የሚከሰቱ ፈተናዎች፣ ያን ያህልም ባልከበዱን ነበር፡፡
የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝንም ሆነ የአንበጣ መንጋዎችን ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች በተፈጥሮ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችንም ጭምር የመከላከል ጠንካራ አቅም በስፋት ይኖረን ነበር፡፡ አደጋዎቹን የመግታት እና በቀላሉ የማሸነፍ ብቃትም ይኖረን ነበር፡፡
ለምዕተ ዓመት የተከማቹ የኢኮኖሚና የኑሮ ችግሮችን፣ የስራ አጥነትና የተስፋ ቢስነት ስደትን፣ በፍጥነት ለማቃለልም ባልከበደን ነበር፡፡
ግን፣ መች ፋታ ተገኝቶ? በእልፍ ፋይዳቢስ ጉዳይና በእልፍ የውድቀት አቅጣጫ፣ ትኩረታችንን የሚበታትኑ፣ መዓት የቀውስ ሰበቦችን ማራባት ላይ ነው ያተኮርነው፡፡
ቀልብ በሚያሳጣ የብሽሽቅና የውዝግብ እሽቅድምድም ተጠምደን ስንደናበር፣ ጥፋትን የመለኮስና የማዛመት ፉክክር ውስጥ ስንዋከብ፣ …በላይ በላዩ ፈተናዎችን ስናራባ፣ ለመፍትሔና ለስኬት የሚሆን ቀልብ ከየት ይመጣል?
ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ፣ ስንት ውዝግብና ውንጀላ፣ ምንኛ እየበዛ፣ ውዝግብን የሚያራግብ እንጂ የሚያስተካክል፣ የሚያጋግል እንጂ የሚያረግብ ሃሳብ እየጠፋ፣ ስንቱ ውዝግብ ወደለየለት ጥፋት አመራ? ስንት የፖለቲካ ቀውስና የአመጽ ጥፋት፣ ስንት የነፍስ ግድያና የንብረት ውድመት፣ ስንት የፈተናና የሀዘን መዓት እየተከታተለና እየተደራረበ አገራችንን ሲያናውጣት እንደከረመ አስታወሱ፡፡ በተፈጥሮ ከሚያጋጥም ችግር ይልቅ፣ ሰው ሰራሽ ጥፋት በዝቶ፣ ለወራት ሳያባራ እንደወረደብን አስቡት፡፡
ከኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ በተጨማሪ፣ በየክልሉ የሚፈጠሩ ፈተናዎችና ጥፋቶች አልበዙብንም? የፌደራል መንግስትና የትግራይ ክልል አስተዳደር ውዝግብ፣ “ምርጫ አካሂዳለሁ” በሚል እየተባባሰ አልቀጠለም?
ከዚያ በፊት፣ “የአገሪቱ ምርጫ መራዘም አለበት” ሲሉ ከነበሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተፈጥሮ የነበረው ውዝግብስ? በኮረና ቫይረስ ሳቢያ ምርጫው ሲራዘም፣ የቀድሞው ውዝግብ ረግቦ መፍትሔ አገኘ? ቅጥ እያጣ ባሰበት እንጂ፡፡ “ምርጫው ስለተራዘመ፣ የመንግስት የስልጣን ዘመን ያበቃለታል፡፡ የስልጣን ክፍፍል ይደረግ፣ የሽግግር መንግስት ይፈጠር” ወደሚል ውዝግብ አልተሸጋገረም?
የሕዳሴ ግድብና የአባይ ወንዝ ጉዳይም፣ እየከበደ እንጂ እየተቃለለ አልመጣም። “የግብጽ መንግስት ካልተስማማ በቀር፣ የሕዳሴ ግድብ፣ ውሃ መያዝ የለበትም” የሚል የውጭ ጫና እየበረታ የመጣው መቼ እንደሆነም አስታውሱ፡፡
ግድቡ፣ ለመነሻ የሚሆን ውሃ ከያዘ በኋላ፣ ፈተናውና ጫናው አልረገበም፡፡ የ130 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ታግዶባታል። ኢትዮጵያን ይጐዳል፡፡ በእርግጥ፣ በስክነት ይህንን የውጭ ጫናና ጉዳት መቋቋም ባልከበደን ነበር፡፡
ነገር ግን፣ ከውስጥ፣ ቀስፈው በሚይዙና በሚያሰቃዩ ብዙ የጐን ውጋቶች ሳቢያ የተወጠረች አገር፣ መች እረፍት አላት? ሲግለበለቡ የነበሩ ውዝግቦችና ዛቻዎች፣ የጥላቻና የጥቃት ቅስቀሳዎች፣ መች ጊዜ ይሰጣሉ? በየእለቱ፣ ጥፋቶችን ይለኩሳሉ እንጂ፡፡
አንዴ ከመሃል አገር፣ በማግስቱ ከዳር አገር፣ ጥዋት ላይ ከሰሜን ወይም ከምስራቅ፣ አመሻሽ ላይ ከደቡብ ወይም ከምዕራብ፣ ክፉ ጥቃትና አሳዛኝ ጥፋት ያልደረሰበት እለት ማግኘት ይከብዳል፡፡ ግን፣ ይብቃን አላልንም፡፡ ከሰኔ አጋማሽ በኋላ፣ በአርቲስት ሃጫሉ ላይ የተፈፀመው ግድያ፣ በጣም አሳዛኝ፣ በእጅጉ አደገኛ እንደሆነ ማን ይጠፋዋል?
ለወራት ሲራገቡ የቆዩ የጥላቻና የጥቃት ቅስቀሳዎች፣ በየከተማውና በየገጠሩ፣ በየአውራ ጐዳናውና በየአደባባዩ፣ በየፋብሪካውና በየእርሻው፣ ብርቱ የጥፋት ሰደድ እሳት፣ ምንኛ በፍጥነት እንደተቀጣጠለ አይተናል፡፡ የብዙ ሰዎች ሕይወት ተቀጠፈ። አካላቸው ጐደለ፡፡ ኑሯቸው ተቃጠለ። የብዙዎች ንብረትና ኢንቨስትመንት ወድሞ፣ የእልፍ ሰዎች መተዳደሪያ ስራና የእለት ጉርስ ተዘጋ፡፡ አሳዛኝና ዘግናኝ ጥፋት መድረሱ ሳያንስ፣ እጅግ ወደባሰ የእልቂት ትርምስ ከመግባት የተረፍነው ለጥቂት ነው። ያስፈራል፡፡
እንደ ሌሎች አካባቢዎች ሁሉ፤ በደቡብ ክልልም፤ በላይ በላዩ ውዝግቦች እየጦዙ፣ በተደጋጋሚ እንዳየነው፣ ከማርገቢያ ሃሳብ ይልቅ፣ ማራገቢያና ማጋጋያ ቅስቀሳ እየገነነ፣ እንደለመድነው፣ ወደ ለየለት አመጽና ቀውስ ተሸጋግረዋል፡፡
ብዙዎችም የጥፋት ሰለባ ሆነዋል፡፡
“ክልል እመሰርታለሁ፤ አትመሰረትም” በሚል ውዝግብ፣ ህይወት ጠፋ፣ ኑሮ ፈረሰ። ይሄ ሁሉ፣ በጥቂት ወራት ብቻ የተከሰተ የመዓት ውርጅብኝ ነው፡፡ በቤኒሻንጉል፣ ከዚያም በምዕራብ ወለጋ የተከሰቱ ጥፋቶችንም አስቡ፡፡  
በትግራይ ክልልም፣ ውዝግብ ከመቀነስና ከመርገብ ይልቅ፣ የውዝግብ አይነትና ቁጥር እየበረከተ፣ እየከረረም ሲሄድ፣ መጨረሻው እንደማያምር ማወቅ ተሳነን?
እንዴት ይሳነናል? እልፍ ጊዜ አይተናልኮ። ወደ ህሊና በመመለስ፣ የብሽሽቅና የውንጀላ ውዝግቦችን ከማብረድ ይልቅ ማጋጋል እየገነነ፣ ወደለየለት ቀውስና ጥፋት እንደሚደርስ፣ ሺ ጊዜ ማየታችን አይበቃም?
“ምርጫ አካሂዳለሁ” የሚለው ውዝግብ፤ ከመርገብ ይልቅ፣ “ለፌደራል መንግስት እውቅና አልሰጥም፤ ለክልሉ አስተዳደር እውቅ አልሰጥም” ወደሚል የባሰ ቀውስ መክረር ነበረበት? እያካረሩ በማጦዝ፣ ከጥፋት ውጭ ሌላ ውጤት አይገኝ ነገር! የማርገብ ሙከራና ጥረት አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ በትግራይ ክልል የተወጠነው ምርጫ ከተገቢው መንገድ የወጣ ቢሆንም፤ የተረጋጋ አማራጭ ጠቃሚ ነው በማለት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መናገራቸው፤ ነገርን ለማብረድ የሚረዳ እድል መፍጠራቸው ነበር፡፡
ነገር ግን፤ የአገራችን የፖለቲካ ቅኝት፣ ነገርን የማብረድና ወደ ቀልብ የመመለስ ሙከራን ሳይሆን፣ ነገር የማራገብና የማጦዝ እሽቅድምድምን እንደጀግንነት የሚቆጥር ኋላቀር ቅኝት ነው፡፡
ቀልብ የመግዛት፣ ወደ ህሊና የመመለስ፣ ለእውነት የመታመን፣ ትክክለኛ ሃሳብንና የተቃና የስነምግባር መንገድን የማክበር፣…
“የእያንዳንዱን ሰው መብት (የግል ነፃነትን) ማስጠበቅ” የፖለቲካ ሁሉ አስኳል እንዲሆን የመመኘት፣…
የሕግ የበላይነትም፣ የሰላምና የፍትህ ሁሉ አስተማማኝ መሠረት እንዲሆን የማለም፣ ለዚህም መነሻ የሚሆን ሕግና ሥርዓትን የማጽናት ጥረት፣ ከሁሉም ሰው የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው፡፡
ወደ ስልጡን የፖለቲካ ባሕል የሚወስድ እንዲህ አይነት አስተሳሰብ ሲስፋፋ፣ የፈተናዎችን ብዛት ይቀንስልናል፡፡ ፈተናዎች ያለተከላካይ ሳይጦዙና ሳይፈነዱ የማብረድ፣ በሁነኛ መፍትሔም የማሸነፍ ብቃታችንን ይጨምራል፡፡  

Read 7562 times