Saturday, 07 November 2020 13:44

ከዕለታት አንድ ቀን...

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

 "እናላችሁ... ሚዲያው ላይ በሉት፣ በፖለቲካው መንደር በሉት፣ በስብሰባ አዳራሽ በሉት፣ በማህበራዊ ሚዲያ በሉት፣ በዘመድ ጉባኤ በሉት...አለ አይደል... “ውሸት ለመናገር አትሻም ምላሴ፣” አይነት ‘ፕሪሚቲቭ’ ዘፈን አይሠራም፡፡ (እንደውም “ያለፈውን ናፋቂ!” በሚል ባያስከስስ ነው!)..."
           
            እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ፈጣሪ ይቺን ሀገር በቃሽ ይበላትማ!
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል... የባህርይ ችግር በሉት፣ ግዴለሽነት በሉት፣ ማን አለብኝነት በሉት...ብቻ ከተማ ውስጥ ወዲህ ወዲያ ስትሉ የሚገጥሟችሁ መአት ነገሮች ናቸው፡፡ እኔ የምለው... በዚህ ‘ሰለጠነ’ በሚባለው ዘመን...አለ አይደል... የአስራ ምናምነኛ ክፍለ ዘመን የሚባሉ አይነት ባህሪያት እያየን ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን...
መንገድ መሄጃ ነበር፡፡ መንገድ ሁሉም ሌላውን ሳይነካ፣ ዘና ብሎ የሚረማመድበት ነበር፡፡  ድንገት ደግሞ አንዱ ክው፣ ክው ሲል ድንገት ገፍተር ያደርጋችሁ የለ፣  ቆም ብሎ “ይቅርታ..” የሚል ብዙ ነበር...ከልብ የመነጨ እውነተኛ ይቅርታ፡፡ ራቅ ካለም በሆነ አካላዊ እንቅሰቃሴ ይቅርታውን አስተላልፎ ነበር መንገዱን የሚቀጥለው። መንገድ አንዱ የሌላውን መብት ሳይነካ፣ የሁሉ የጋራ መጠቀሚያ ነበር፡፡
ዛሬስ...
ዛሬ? ዛሬማ እንዴት መሰላችሁ... መጀመሪያ ነገር “መገፋፋት ማለት ምን ማለት ነው?” ብሎ ቢጠይቃችሁ፣ “ይሄን ሳያውቅ ቀርቶ ነው?” አይነት ‘ሰርፕራይዝ’ ምናምን ነገር አያስፈልግም፡፡  አሀ...ልክ ነዋ! ፈረንጅ ‘ኖርማል’ እንደሚለው አይነት ነገር ሆኗላ! እንደው አየር ለመቀበልም፣ ለምንም ወጣ ብላችሁ ትከሻችሁን ‘ገጨት’ ሳትደረጉ ቤት ከተመለሳችሁ፣ መስሏችሁ አንጂ አዲስ አበባ ውስጥ አልነበራችሁም ማለት ነው፡፡
እናላችሁ... ጨዋታም አይደል... እውነተኛው ግፊያ የሚመጣው እንደ ‘አሜሪካን ፉትቦል’ ተጫዋቾች የሰው ትከሻ ሳይሆን ከሆነ ኮርማ ላይ ‘በግፍ’ የተነጠቀ ሻኛ የተገጠመለት የሚመስል የከተማችን ‘ኩዋርተርባክ’ ሲገጥማችሁ ነው፡፡ በአጋጣሚ ሰዉ ሳሳ ያለበትና ገና የጭንቅንቁ ሰዓት ያልደረሰ ቢሆን እንኳን እንዳለ ነው መጥቶ የሚከመርባችሁ፡፡ (እባካችሁማ... ብረት የምታነሱ ጡንቻችሁ ‘ምን ያሳድራል’ አይነት የምትባሉት ሰዎች፣ ብረት ያመጣው ‘ባይሴፕ’ ምናምን ይበቃል። አሀ... ‘ኪኒናውን’ ቀንሱታ!
ደግሞላችሁ... ሌላኛው “አርባ ስምንት ቁጥር የለንም” እየተባለ የጫማ ሱቆችን ሲያስስ በሚያስውለው እግሩ፣ ሦስት አራተኛ ክብደቱን ያሳርፋባችኋል፡፡ እናማ አቃስታችሁ ካበቃችሁ በኋላ ከሰውየው “ይቅርታ፣ አላየሁም፣” ምናምን ነገር የምትጠብቁ ከሆነ፣ እንደገና በብስጭት ታቃስታላችሁ እንጂ ዘወር ብሎም አያያችሁም፡፡ እሱዬው አይደለም ሰው እግር ላይ፣ ትንኝ ላይም የቆመ አይመስለውም። ለነገሩማ... እኛም “ይቅርታ...” ከሀገር ተሰዶ የት እንደደረሰ የማይታወቅ   አሁን፣ አሁን ጭርሱን ‘ባእድ’ የሆነብንን ነገር በመጠበቃችን፣ ይቅርታ ጠያቂዎች መሆን ያለብን እኛው ሳንሆን አንቀርም፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን...
በጤና ችግርም ሆነ በሌላ ድንገተኛ በሆነ አካላዊ ምክንያት ‘እንትፍ’ የምትባል ነገር ከገጠመችም ግለሰቡ ዘወር ብሎ አፉን በሁለት እጆቹ ሸፍኖ፣ ወይም ወደሆነ ጥግ ሄዶ ሰው ሳያይ ነበር የሚያደርገው። ምክንያቱም በአደባባይ እንደዛ ማድረጉ የባህሪይ ችግር እንደሆነ የሚወሰድ ነበርና ነው፡፡
ዛሬስ...
ዛሬማ ሌላ ነው...ዛሬማ ‘እንትፍ’ ከማለት ባለፈ ‘ሰው አለ፣ ሰው የለም’ ብሎ ነገር የለ... “ወደ ጥግ ዘወር ልበልና ሰው ሳያየኝ ላድርገው፣” ብሎ ነገር የለ፣ ምን አለፋችሁ...ጭራሽ አሎሎ ይመስል ከዳር ዳር ሲያስወነጭፉት ቀፈፍ እንኳን የማይለው መአት ነው፡፡ ሙሉ ልብሱን ግጥም አድርጎ፣ የጄምስ ቦንድን መነጽር ሰክቶ፣ ‘ጎልድ ብራስሌቱን’ አስሮ ... ነገርዬውን ከዛ ማዶ እዚህ ማዶ ይወረውረዋል፡፡
እናማ... ገብስ ገብሷን እንጫወትና እንደው ዘንድሮ ከእንጨት ወንበር ትንሽ ሻል ያለችው ላይ የተቀመጠውም፣ “አረፍ ሲሉበት ይዞ ጭልጥ ይላል” እያሉ የሚያወሩበት ወንበር ላይ ፈልሰስ ያለውም... እንደው የሆነ የሥራ ጉድለት ሲደርስ፣ መደረግ የሌለበት ነገር ሲደረግ እንደው አንዳቸው  “ተያይዞ በደረሰን ዜና...” ለመባል የሚበቃ ያህል አንኳን “ለተፈጸመው ችግር በሥራ ባልደረቦቼ ስም ይቅርታ እጠይቃለሁ፣” ቢሉን...አለ አይደል... ፀሀይ ከነገ ጀምሮ መውጣት ታቆማለች! ይቅርታ መጠየቅ እኮ ከፕሬሚየር ሊግ ወደ ጤና ቡድን መወርወር ሳይሆን በራስ የመተማመንና የሞራል ጥንካሬ ምልክት ነው፡፡ (የፈላስፎቹን መንደር አጥር መዞር ጀመርኩ እንዴ!) እኔ የምለው...ቀደም ሲል እኮ ሲከመርባችሁ...“መቼም ከወፈሩ ሰው አይፈሩ፣ ደግሞ ምን ያክላል! በትከሻህ ተሸከማት የተባለውን ወይፈን እንዳለች ሆዱ ውስጥ ከተታት እንዴ!” ምናምን ብለን ለራሳችን ሹክ እንላለን፡፡ አፍ አውጥተን ከተናገርን ከወይፈኗ ጋር ሊቀላቅለን ይችላላ!
የሚገርማችሁ የእኛ ቢጤ...አለ አይደል... በአመራረት ስህተት ቁመቷ የረዘመ የክብሪት እንጨት የሚያካክለው ሁሉ ቀላል ይጋፋል እንዴ!
ከእለታት  አንድ ቀን....
“ለወሬ የለውም ፍሬ” የሚባል ነገር ነበር፡፡ በተለይ መዋሸት አንገት የሚያስደፋ ነበር፣ በህብረተሰቡ ዘንድ መጠቋቆሚያ የሚያደርግ፣ “እሱ እኮ ጫፍ ከያዘ እንደ ጣቃ ሲተረተር ነው የሚውለው፣” የሚያሰኝ ነበር። ከተዋሸ እንኳን አይደለም በአካባቢያችን ያለን ሰው፣ ጣራና ግድግዳው ‘ያሳብቅብናል’ ብለን እየሰጋን ነበር፡፡ “እሱ እኮ የለየለት ዋሾ ነው፡፡ ተሳስቶ እንኳን ከአንደበቱ እውነት አይወጣም!”  ከመባል የባሰ ነገር አልነበረም።
ያልሆነውን ሆነ ብዬ ከማለት
እውነት ተናግሬ ይሻለኛል ሞት
እየተባለም የሚዘፈንበት ነበር፡፡ 
ዛሬስ!
ዛሬማ “እንደ ጣቃ መተርተር...” የሚሉት ነገር ‘አፕግሬድ’ መደረግ አለበት፡፡ (ስለ ሆነ ነገር “ግን በጉዳዩ ላይ ስሜት አለህ?” ሲባል “አዎ፣ ኢንተረስቲንግ ነኝ፣” የሚል  በርከት ስላለ፣ የፈረንጅ አፍ የተጠቀምነው፣ ማን ከማን ያንሳል በሚል እንደሆነ ይጣፍልንማ! የምር ግን... አንድም ሀገር እያመሰ ያለው እኮ ‘ማን ከማን ያንሳል!’ የሚሉት ጠጅ በስሙኒ ሁለት ብርሌ የነበረበት ዘመን ነገር ነው!)
ታዲያላችሁ... መዋሸት አይደለም አንገት ሊያስደፋ፣ አይደለም በሰው ምን ይለኛል ሊያሸማቅቅ፣ ከ‘አርትነት’ ወደ ‘ሳይንስነት’ እየተሸጋገረ ያለ ነው የሚመስለው... መቶ ሺህ ለመሙላቱ የሚያጠራጥረውን “ሁለት ሚሊየን በተገኘበት...” እንደሚባለው አይነት፡፡
እናላችሁ... ሚዲያው ላይ በሉት፣ በፖለቲካው መንደር በሉት፣ በስብሰባ አዳራሽ በሉት፣ በማህበራዊ ሚዲያ በሉት፣ በዘመድ ጉባኤ በሉት...አለ አይደል... “ውሸት ለመናገር አትሻም ምላሴ፣” አይነት ‘ፕሪሚቲቭ’ ዘፈን አይሠራም፡፡ (እንደውም “ያለፈውን ናፋቂ!” በሚል ባያስከስስ ነው!)  እናላችሁ... ‘ከእለታት አንድ ቀን’  መሳቀቂያ የነበረው ‘ሰብቅ መናገር’ ዘንድሮ እንደውም  በሆነ ሚዲያ የእንግድነት ክብር ሊያስገኝ ይችላል፡፡ ታማኝነት የባህሪ ጥንካሬ መሆኑ ቀረና፣ ሀቀኝነት የሚያኮራ፣ አንገትን ቀና የሚያስደርግ መሆኑ ቀረና...ሰብቅ ማሸማቀቁና አንገት ማስደፋቱ የቀረ ነው የሚመስለው፡፡ “ሰማይ ላይ ጤፍ እየተወቃ ነው ቢለው፣ እብቁ ዓይኔ ገባ አለ፣” እንደተባለው፣ ሰማይ ላይ ጤፍ ሲወቃ ‘የምናይ’ እና እብቁ ‘ዓይናችን የሚገባ’ የበዛን ነው የሚመስለው፡፡
ስሙኝማ... እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው... የስፖርት ‘ጆርናሊስቶቻችን’ ነገር አንዳንዴ ፈገግ ያሰኛል...የማንቼ ደጋፊ እስካልሆኑ ድረስ፡፡ (ቂ...ቂ....ቂ...) ለምሳሌ ይቺን ስሙኝማ... “ባለፈው እሁድ በተካሄደው ጨዋታ፣ እከሌና እከሌ የተባሉ ቡድኖች ሁለት ለሁለት አቻ ተለያይተዋል፣” እኔ የምለው... ‘ሁለት ለሁለት’ ሌላ ትርጉም ካልተሰጠው በቀር ‘አቻ’ ማለት አይደለም እንዴ! “ባዶ ለባዶ ያለ ግብ ተለያይተዋል።” እና... ባዶ ለባዶ ማለት ‘ያለ ግብ’ ማለት አይደለም እንዴ!  
ወይ ደግሞ... “እከሌ የተባለው ቡድን እከሌ የተባለውን ቡድን ሰባት ለባዶ በሆነ ሰፊ የጎል ልዩነት አሸንፏል፡፡” እናማ... በቃ ‘ሰባት ለባዶ’ ያለ ምንም ተቀጥላ ሰፊ ልዩነት መሆኑ ይታወቅ የለም እንዴ! እንዲሁ እግረ መንገድ ‘ሶሊዳሪቲያችንን’ ለመግልጽ ያህል ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1894 times